የሥራ ላይ ጉዳቶች

Wednesday, 27 May 2015 17:45

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    አሰሪዎችም ሰራተኞውም የሙያ ደህንነትን የሰራተኞን ጤንነት ለማስጠበቅ ማክበር ያለባቸው ግዱታዎች፣

-    በስራ ላይ የደረሱ ጉዳቶች የሚሉት የትኞቹ የጉዳት አይነቶች ናቸው፣

-    በአሰሪዎች ኃላፊነት ምንድነው?

-    በስራ ላይ ጉዳቶች አሰሪው በኃላፊነት እንዳይጠየቅ የሚያደርጉ የሰራተኛው ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ስራ እንዴት ነው? የዛሬው ወጋችን ከስራ ጋር በተያያዘ ሰራተኞች አካልና ህይወት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በሚመለከት አሰሪዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው? የሰራተኞስ መብትና ግዴታ ምን ይመስላል የሚሉትን ነጥቦች እናነሳለን።

1.ቅድሚያ ደህንነት

“ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚል የስራው ብሂል አለ። እያወራን ያለነው ሰራተኞች በስራ ላይ እያሉ የሚደርስባቸው ጉዳት የሚያስከትለውን ኃላፊነት ነው። የግልና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የአሰሪዎች እና የሰራተኞች የስራ ግንኙነት የሚገባው አዋጅ ቁጥር 377/96 ሰራተኞች ላይ ጉዳት ሲደርስ አሰሪው ያለበትን ኃላፊነት ከማስቀመጥ በፊት ለአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ቅድሚያ ለአሰሪውም ከሰራተኛውም ሆነ በአሰሪው መወሰድ ያለባቸውን የመከላከያ እርምጃዎች ነው። ምክንያቱም በዚህ ሆነ በሌሎ ሕጎች ጉዳት ያደረሰው ሰው ጉዳት የደረሰበትን ሰው የመካስ ግዴታ አለበት። ይህን ግዴታ ለመወጣት አሰሪው ያለበትን ኃላፊነት ለሰራተኞች የመድህን ዋስትና ሽፋን በመግባት ወይም በራሱ ኃላፊነት በመውሰድ ሊወጣው ይችላል። ከዚያ በፊት ግን መቅደም ያበት ለስጋት ተጋላጭነት (Risk) በማስወገድ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ነው። ለዚህም ነው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 92 ስር አሰሪው የሠራተኞችን ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ እርምጃዎን የመውሰድ ኃላፊነት የተጣለበት

የአሰሪ ግዴታዎች፡-

የመጀመሪያው ግዴታው ሰራተኞች የሚሰሩት ስራ ሊያስከትልባቸው ስለሚችለው አደጋና የጤንነት ጉዳት ለማስወገድ ስለሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች ተገቢውን ስልጠና መስጠት ነው። ሁለተኛው ግዴታ ደግሞ ሰራተኞችን የአደጋ ማስወገጃ ስልጠና ብቻውን በቂ አይደለም። አንድ ሰራተኛ ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ ስላወቀ ብቻ ሙሉ በሙሉ አደጋ አይደርስም ማለት ስለማይቻል አሰሪው የአደጋ ተከላካይ ሠራተኛ የመመደብ ግዴታ አለበት። ይህ በውስጣዊ አደረጃጀቱና በራሱ ወጪ አደጋዎች ቢከሰቱ ለመከላከል እንዲያስችል የተጣለበት ግዴታ ነው። በተጨማሪ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ተከታታይ ኮሚቴዎች የማቋቋም ግዴታ አለበት።

ሌላውና ዋነኛው ደግሞ እንደ ስራው ባህሪ የአደጋ መከላከያ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማቅረብ ሲሆን፤ ስለአጠቃቀሙም ለሰራተኞቹ በማሳወቁ ተገቢውን የአጠቃቀም መመሪያ መስጠት አለበት። ከዚህ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ የሥራ ቦታ እና ግቢ በሰራተኞች ደህንነትና ጤንነት ላይ አደጋ የማያስከትል መሆኑን በማረጋገጥ ምቹ እና ለደህንነት አስተማማኝ የስራ ቦታ የማቅረብ ግዴታ አለበት። ከተለያዩ የስራው ሂደቶች ጋር በተያያዘ ቁሳዊ፣ ኬሚካላዊ፣ ስነህይወታዊ፣ ከስራው ግብአቶች ንድፍ እና ስነልቦናዊ ምንጮች በሰራተኛና ደህንነት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።

አዲስ የሚቀጠሩ ሰራተኞችን እንደየስራው ባህሪ የጤና ምርመራ ማድረግ እና በአደገኛ ስራ ላይ የሚመደቡ ሰራተኞችም እንደየአስፈላጊነቱ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግም አለበት። በአዋጁ የተቀመጡትን የሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤናማነት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዲሁም በሚመለከተው የመንግስት አካል የሚሰጡ ትዕዛዞችን ማክበርም የአሰሪው ግዴታ ነው። ጥንቃቄው ከሁለቱም ወገኖች ከአሰሪውም ከሰራተኛውም የሚፈለግ ነውና ሰራተኞችም ግዴታዎች ተጥለውባቸዋል።

የሠራተኛው ግዴታዎች፡-

በስራ ላይ ደህንነትን እና ጤንነትን ለማስጠበቅ ማንኛውም ሰራተኛ ለዚሁ ዓላማ የሚወጡትን የሥራ ደንቦች በማዘጋጀት መተባበር እንዲሁም ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለበት። በድርጅቱ ወይም በመሳሪዎች ላይ የሠራተኛውን ደህንነትና ጤንነት የሚጎዳ ጉድለት ሲያገኝ እና ጉድለቱ ሊያደርሰው የሚችለውን አደጋ ወዲያውኑ ለአሰሪው የማሳወቅ ግዴታ አለበት። አይቶ እንዳላየ ማለፍ አይቻልም።

ሰራተኛው አደጋ ሊያደርስ ይችላል ብሎ ለማመን ምክንያት ያለው ሁኔታ ሲያጋጥመው በቅድሚያ በራሱ ሊያስወግደው የሚችለው ከሆነ ማስወገድ አለበት። ሊያስወግደው የማይችለው ከሆነ ደግሞ ለአሰሪው ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት። በተጨማሪ ከስራ ጋር ግንኑነት ባለው ሁኔታ በጤንነት የደረሰ ጉዳት እራሱም ላይ ሆነ ሌላ ሰራተኛ ላይ ካለም ለአሰሪው ማሳወቅ የሰራተኛው ግዴታ ነው። ምክንያቱም አደጋዎችና ጉዳቶች ሳይባባሱ አሰሪው ያለውን ክፍተት በመሙላት ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት መረጃ ስለሚያስፈልገው ነው።

የአደጋ መከላከያዎች ወይም የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን አሰሪው የማሟላት ግዴታ አለበት። ውጤታማ የሚሆኑት ግን ሰራተኛው በትክክል ሲጠቀምባቸው በመሆኑ እነዚህን የመከላከያ መሳሪያዎና ሌሎች መሳሪያዎችን በትክክል ጥቅም ላይ የማዋል ግዴታ አለበት። አሰሪው ወይም ኃላፊነት የተሰጠው አካል የሚያመጣቸውን የደህንነትና የጤንነት መጠበቂያ መመሪዎም ማክበር አለበት።

በአዋጁ አንቀጽ 94 ላይ ማንኛውም ሰራተኛ ለራሱ ወይም ለሌሎች ደህንነት ሲባል የተቀመጡ የደህንነት መጠበቂያ እቃዎች ወይም ሌሎች መሳሪያዎችን መነካካት ማንሳት ያለቦታቸው ማስቀመጥ፣ ማበላሸት ወይም ማጥፋት በስራ ላይ የሚደርስ አደጋን ለመቀነስ ሲባል የሚሰራበትን ማንኛውንም ዘዴ ወይም አሰራር ማሰናከል የተከለከለና በወንጀልም ጭምር ሊያስጠይቅ የሚችል ተግባር ነው።

የሥራ ላይ ጉዳቶች

የስጋት ተጋላጭነትን ለመቀነስ በአሰሪውና በሰራተኛው ላይ በአዋጅ የተጣሉ ግዴታዎን ተመልክተናል። ዋና አላቸውም ሰራተኞች በስራ ላይ በሚደርስባቸው ጉዳት የሚታጣውን ምርታማነት፣ የሰው ሃይል፣ ገቢ እንዲሁም አሰሪው የሚደርስበትን ኃላፊነት በመቀነስ ጉዳቶ የሚያስከትሉትን አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ መቀነስ ነው። ሆኖም አደጋን መቀነስ እንጂ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ስለማይቻል በስራ ላይ የሚመጡ ጉዳቶች የትኞቹ እንደሆኑ ተቀምጠዋል። በአንቀፅ 95 መሰረት በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት የሚባለው በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ ወይም በስራ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። እስቲ ሁለቱን የሥራ ላይ የጉዳት አይነቶች እንመልከት፡-

በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ፡- በአዋጅ አንቀጽ 97 መሰረት ማንኛውም ሰራተኛ ስራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከስራው ጋር ግንኙነት ባው ሁኔታ ከሰራተኛው ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም ስራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት በአካሉ ወይም በማንኛውም የአካል ክፍሉ ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ ላይ በድንገት የደረሰበት ጉዳት ሲሆን የሚከተሉትን የጉዳት አይነቶችም ያካትታል፣

-    በስራ ቦታው ወይም ከመደበኛ የስራ ሰዓትው የአሰሪውን ትዕዛዝ ሲተሰገብር በነበረ ጊዜ የደረሰበት ጉዳት፣

-    ከስራው ጋር በተያያዘ ግዴታ ከስራው በፊት ለጊዜው ስራው በተቋረጠበት ወይም ለስራው በኋላ (ከመደበኛ የስራ ሰዓት) በስራው ቦታ ወይም በድርጅቱ ግቢ ውስጥ እያለ የደረሰበት ማንኛውም ጉዳት፣

-    ወደስራ ወይም ከስራ ቦታ ድርጅቱ ለሰራተኞች አገልግሎት እንዲሰጥ በመደበው መጓጓዣ ወይም ለዚሁ ተግባር በተከራየውና በግልፅ ከሰራተኞች መጓጓዣ አገልግሎት ለመደበው መጓጓዣ ሲጓዝ እያለ የደረሰበት አደጋ፤ እዚህ ጋር በግል መጓጓዣ ወይም በህዝብ ማመላለሻ ወይም በሌሎች አማራጭ ወደ ስራ ቦታ ወይም ከስራ ቦታ የሚጓጓዙ ሰራተኞች በጉዞ ላይ የሚደርስባቸው አደጋ እንደ ስራ ላይ አደጋ እንደማይታይ ልብ ሊባል ይገባል።

-    ሰራተኛው ስራውን በማከናወን ላይ እያለ በአሰሪው ወይም ከሰራተኛ ወገን ድርጊት የደረሰበት ጉዳት በአዋጁ መሠረት በስራ ላይ የደረሱ አደጋዎች ናቸው።

በሥራምክንያትሚመጣ በሽታ፡- በአዋጅ አንቀፅ 98 መሠረት ሠራተኛው ከሚሰራው የስራ አይነት ወይም ከሚያከናውነው ሥራ አካባቢ ከበሽታው መከሰት በፊት በነበረው የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በቁሳዊ፣ ኬሚካላዊ ወይም ስነህይወታዊ ነገሮች አማካኝነት በሰራተኛው ላይ የሚደርስ የጤና መታወክ ነው።

በስራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች ስራው በሚሰራበት አካባቢ የሚዛመቱና የሚይዙ ነባር ተላላፊ በሽታዎች የሚያካትቱ ሲሆን እነኚህ ነባር ተላላፊ በሽታዎች እንደ ስራ በሽታ የሚቆጠሩት ስራቸው በሽታውን ማጣራት ለሆኑ ባለሙያዎች ብቻ ነው።

እነዚህ በስራ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችና በስራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች በስራ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ሲሆኑ አሰሪው ለነዚህ ጉዳቶች ካሳ የመክፈልና የህክምና ወጪ የመሸፈን ኃላፊነት አለበት።

የአሰሪው ኃላፊነት፡- በአዋጁ አንቀጽ 96 መሰረት በስራ ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች አሰሪው የፈፀመው ጥፋት ባይኖርም አሰሪ በመሆኑ ብቻ ኃላፊነት አለበት። ይሄ በአሰሪና ሰራተኛ ሕጉ የተደነገገ የአሰሪዎች ኃላፊነት ሲሆን አሰሪው ለጉዳቱ መንስኤ የሆነውን ጥፋትም ሲፈፀም እንደተጠበቀ ነው። ሆኖም አሰሪው ተጠያቂ የማይሆንባቸው የተወሰኑ ሁኔታዎች አሉ እነሱም፡-

-    ሆን ብሎ ሰራተኛው በራሱ ላይ ለደረሰው ማንኛውም ጉዳት ምክንያቱም ማንም ሰው ከጥፋቱ ተጠቃሚ መሆን የለበትም፡-

-    አሰሪው አስቀድሞ በግል የተሰጡትን የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች በመጣስ ወይም የመከላከያ ደንቦችን በመተላለፍ ወይም

-    አካሉን ወይም አእምሮውን በሚገባ ለመቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ እፅ ሰክሮ ስራ ላይ በመገኘቱ ሰራተኛው የሚደርስበትን ጉዳት ሆን ብሎ በራሱ ላይ እንደደርሰው ይቆጠራል።

ከላይ ያነሳናቸው የሥራ ላይ አደጋን የማስወገጃ አስገዳጅ የመከላከል ግዴታዎችና የስራ ላይ ጉዳቶች አሰሪው ላይ የሚያስከትሉትን የኃላፊነት አይነቶች እንዲሁም የጉዳቶቹን አይነቶ ደግሞ በቀጣዩ ሳምንት ልመለስበት።

                                                                                  መልካም ስራ

ይምረጡ
(23 ሰዎች መርጠዋል)
8867 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 946 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us