የስራ ላይ ጉዳትና ካሳ

Wednesday, 03 June 2015 14:22

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

- በስራ ላይ የሚደርሱ የጉዳት አይነቶች ምን ምን ናቸው?

- ለየጉዳቶቹ መጠን የሚከፈሉ የካሳ ክፍያዎች፣

- በሥራ ላይ ለደረሱ ጉዳት የሞተ ሰራተኞች ክፍያ የሚያገኙ ጥገኞች እነማን ናቸው?

- አሰሪ ያለበት የጉዳት የካሳ እና የህክምና ወጪ የመሸፈን ኃላፊነቶች፣

እንዴት ናችሁ? ባለፈው ሳምንት ሰራተኞች ላይ በስራ ምክንያት ስለሚደርስ ጉዳቶች ጉዳቶቹን ለመከላከል በአሰሪውም ሆነ በሰራተኞች በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ላይ የተቀመጡ ግዴታዎችን ተመልክተዋል። የሙያ ደህንነት ጤንነትና የስራ አካባቢን ለመጠበቅ መሟላት ያለባቸውን ነገሮችም አይተናል። በስራ ላይ ጉዳቶች የሚባሉት በስራ ላይ የደረሱ አደጋዎችን እና በስራ የሚመጡ በሽታዎችም የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁ አሰሪው ያለበትን ኃላፊነትና ሰራተኛው በስራ ላይ ለደረሰ ጉዳት ካሳ የማግኘት መብቱን ሊያጣ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች አንስተናል። ዛሬስ? በይደር ያቆየነውን የጉዳት አይነቶች የሚሰጡ የካሳ ክፍያዎን ተያያዥ ጉዳዮችን እናወጋለን።

የሥራ ላይ የጉዳት ዓይነቶች

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀፅ 99 መሠረት ሰራተኛው ጉዳትን ወይም ሞትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው የአካል ጉዳት ማለት የሰራተኛውን የመስራት ችሎታ መቀነስን ወይም ማጣትን በሚያስከትል ሁኔታ በስራው ላይ የሚደርስበት ጉዳት ሲሆን ሶስት የአካል ጉዳት አይነቶች አሉ። እነሱም 

ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፣

ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት፣

ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ተብለው ይመደባሉ።

በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት በሰራተኛው ላይ የሞት ጉዳትም ሊያስከትል ስለሚችል አራተኛው የጉዳት አይነት ሆኖ ተቀምጧል።

ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፡- የሚባለው ሰራተኛው ሥራውን ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማከናወን የማያስችል የጉዳት የአካል ጉዳት አይነት ነው። ይህ የጉዳት አይነት በባህሪው በስራ ላይ በደረሰው አደጋ ወይም በስራ ምክንያት የመጣ በሽታ ሰራተኛው ላይ የሚከሰትና ጉዳቱ ለጊዜው በህክምና እስኪድን ድረስ የሰራተኛውን የመስራት አቅም የሚገድብ ነው።

ሰራተኛው ጊዜያዊ የስራ ላይ ጉዳት ሲደርስበት በአዋጅ አንቀጽ 107(1) መሰረት ጊዜያዊ የአካል ጉዳቱ እስከሚወገድ ድረስ በአሰሪው በየጊዜው የሚደረጉ ክፍያዎችን ያገኛል።

በየጊዜው የሚገኙ ክፍያዎች፡- ሰራተኛው ጊዜያዊ የአካል ጉዳት ከደረሰበት በአዋጁ አንቀጽ 108 መሰረት ከሚያገኘው ህክምና በተጨማሪ በጉዳቱ ምክንያት ሰራተኛው ስራ ባይሰራም አሰሪው ከአንድ ዓመት ለበለጠ ጊዜ የሚከፍላቸው በሰራተኛው አማካይ ደመወዝና የጉዳቱ ማገገሚያ ጊዜ ቆይታ ላይ ተመስርተው የሚሰሉ ክፍያዎች ናቸው።

የመጀመሪያው ዙር የጊዜያዊ የአካል ጉዳት ክፍያ ጉዳት ከደረሰበት እለት ጀምሮ የሚከፈል ነው። ይህ የመጀመሪያው የጊዜያዊ የአካል ጉዳት ክፍያ ለ3 ወራት የሚቆይ ሲሆን ሰራተኛው ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ያገኝ የነበረው የአንድ ዓመት አማካይ የወር ደምወዙን በሙሉ በየወሩ ሳይሰራ የሚያገኝነበት ነው። ይህ ክፍያ ጉዳቱ መወገድ በሀኪም እስካልተረጋገጠ ወይም የጉዳት ጡረታ ወይም ዳረጎት እስካገኘበት ቀን ድረስ ከጉዳቱ ከደረሰበት ቀን ጀምሮ ላሉት ቀጣይ ሰዓት ወራት አሰሪው ከሰራተኛው የሚከፍለው ክፍያ ነው።

ሁለተኛው ዙር ክፍያ የሚቀጥለው በሶስቱ ወራት ውስጥ ጊዜያዊ ጉዳቱ ካልተወገደ ወይም ሰራተኛው የጉዳት ጡረታ ወይም ዳረጎት ካላገኘ ለቀጣዮቹ ሰዓት ወራት የሚቀጥል ሲሆን መጠኑም የሰራተኛው የአመቱ አማካይ ወርሃዊ ደምወዙ 75 በመቶ ነው። ለምሳሌ ጊዜያዊ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት በነበረው ዓመት 1000 ብር በወር ያገኝ የነበረ ሰራተኛ 6ኛው ወር ላይ ደመወዙ በጭማሪ በወር 1500 ብር ቢሆን እና 12ኛው ወር ላይ ጊዜያዊ ጉዳቱ ቢደርስበት ጊዜያዊ ክፍያው የሚሰላው በሰራተኛው ከጉዳቱ ቀን በፊት በነበረው የአመቱ አማካይ የወር ደምወዝ በመሆኑ የ6 ወራቱ 1000 ሺ ብር ከደመወዙ ጭማሪው በኋላ እስከ ጉዳቱ ቀን በወር ያገኘው የነበረው 1500 ብር በ6 ተባዝቶ አንድ ላይ ሲደመሩ የአመቱን ደመወዝ ብር 15000 ይመጣል። የዓመቱን አማካይ የወር ደምወዝ ለማግኘት ከ12 ወራት ስናካፍለው 1250 ብር ይመጣል። ይህ ሰራተኛው ከጉዳቱ በፊት ያገኝ የነበረው የአመቱ አማካይ ደመወዝ በመሆኑ ጉዳቱ ከደረሰበት ቀን ለቀጣዩ 3 ወር በወር ብር 1250 ጊዜያዊ የጉዳት ክፍያ ይከፈለዋል።

በሁለተኛው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ደግሞ ለቀጣዩ 3 ወር ጊዜ አማካይ የወር ደመወዙ የ1250 ወደ 75 በመቶ ይከፈለዋል።

ጉዳቱ ከመጀመሪያውና በሁለተኛው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ካልተወገደ ደግሞ ሶስተኛውና የመጨረሻው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ለቀጣዮቹ 6 ወራት የሚቀጥል ሲሆን መጠኑም የአማካይ የወር ደምወዙ 50 በመቶ ነው።

አሰሪው ሰራተኛው በጊዜያዊ ጉዳት ምክንያት ስራ መስራት ካቀመበት እለት ጀምሮ አስራ ሁለት ወራት ከሞላው ሰራተኛው ያገኝ የነበረው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ይቋረጣል። ለጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ የሚቀበል ወይም የጠየቀ ሰራተኛ ለህክምና ምርመራ ለመቅረብ እምቢተኛ ወይም ቸልተኛ ከሆነ፣ በማናቸውም ሁኔታ ሆን ብሎ ምርመራውን ካደናቀፈ ወይም ያለበቂ ምክንያት ካንጓተተ፡-

- ጉዳቱ የሚድንበትን ጊዜ ለማዘግየት አስቦ ያልተገባ ፀባይ ካሳየ

- አግባብ ባለው ካሳስልጣን ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰራተኞች የመጣውን መመሪያ ከተላለፈ በየጊዜው የሚደረገው ጉዳት ሊታገድ ይችላል። ለእገዳው ምክንያት የሆነው ሁኔታ ሲወገድ ክፍያው እንደገና የሚቀጥል ሲሆን በእገዳው ጊዜ ያልተከፈለውን ክፍያ ግን ሰራተኛው የማግኘት መብት የለውም።

ዘላቂ የአካል ጉዳት፡- ሰራተኛው የደረሰበት ጉዳት ሙሉ ወይም ከፊል ዘላቂ የአካል ጉዳት ከሆነ የጉዳት ጡረታ ወይም የዳረጎት ወይም ካሳ እንደሚያገኝ በአዋጁ አንቀጽ 107(ለ) ይደነግጋል። ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት የሚባለው በአንቀጽ 101 (1) መሠረት ጉዳት የደረሰበትን ሠራተኛ የመስራት ችሎታ የሚቀንስ የማይድን በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው። ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ደግሞ ሠራተኛውን ማናቸውንም ደምወዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመስራት የመከላከል የማይድን በሥራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው።

ከነዚህ ጉዳቶች በተጨማሪ ከባድ የአካል ወይም የመልክ መበላሸትን ያስከተለ ጉዳት የመስራት ችሎታ ማጣትን ቢያስከትልም ለጉዳት ካሳ አከፋፈልና ሌሎች ጥቅሞች ሲባል እንደ ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት ይቆጠራል።

የዘላቂ ጉዳት መጠን ደረጃው የሚወሰነው የሰራተኛውና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያወጣው ሰንጠረዥ መሰረት ሲሆን የጉዳት መጠኑ የሚወሰነው ሥልጣን ባለው የህክምና ቦርድ ሲሆን ምርመራው ትክክል ካልሆነ ሰራተኛው ወይም አሰሪው ሲጠይቁ ድጋሚ ይደረጋል።

የጉዳት ካሳው መጠን በጡረታ ሕግ ለሚሸፈኑ ሰራተኞች በመንግስት ሰራተኞች የጡረታ ሕግ መሰረት የሚፈፀም ሲሆን፤ በጡረታ ሕጉ ለማይሸፈኑ ሰራተኞች ደግሞ

ሀ. ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት፡- በአዋጁ አንቀፅ 104 (3) መሰረት የሰራተኛው የአመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው ክፍያ ሲሆን በአንድ ጊዜ ነው የሚከፈለው፣

ለ. ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት፡- የማይድን ሆኖም የሰራተኛውን የመስራት ችሎታ የቀነሰ ክፍል የአካል ጉዳት የካሳ ክፍያው የአምስት ዓመት ደመወዙ በመቶኛ ጉዳቱ ሰራተኛው አካል ላይ ላስከተለው ጉዳት ከተሰጠው ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ ነው።

ጉዳቱ ለማጅ ሠራተኞች ላይ የደረሰ ከሆነ ደግሞ ለማጁ ልምምዱን ሲጨርስ ሊያገኝ ይችል በነበረው ደመወዙ የሚሰራ ነው።

ለጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2005 አንቀጽ 23 መሰረት ቢያስ 10 ዓት ያገለገለ ሰራተኛ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ከስራ ሲሰናበት ከቀጣዩ ወር ጀምሮ እድሜ ልኩን የጡረታ አካል ያገኛል። አገልግሎቱ አስር ዓመት ያልሞላ ሰረተኛ ደግሞ በጤና ጉድለቱ ምክንያት ከስራ ሲሰናበት አማካይ የወር ደምወዙ ከፖሊስና ከመከላከያ ውጭ ያለ ሰራተኛ 1ነጥብ 25 በመቶ ያገለገለበት ዓመት ብዛት ተባዝቶ ይከፈለዋል።

እነዚህን ክፍያዎች ሠራተኞች በሰራተኛ ማህበራቸው ከአሰሪው ጋር በሚያደረጉት ድርድር ከሕጉ የተሻለ ለሰራተኛው በሚጠቅም መልኩ ሊያሻሽሉት ይችላሉ።

የሞት ጉዳት፡- ሠራተኛው ወይም ተለማማጅ ሰራተኛው በስራ ላይ በደረሰ ጉዳት ከሞተ በአዋጅ አንቀፅ 110 መሠረት ለጥገኞች ክፍያ እና ለቀብር ማስፈፀሚያ ከሁለት ወር ደምወዝ ያላነሰ ክፍያ ይከፍላል። በጡረታ ሕግ የሚሸፈኑ ሰራተኞች የሚያገኙት የጡረታ አበል ሲሆን በጡረታ ሕጉ ለማይሸፈን ሰራተኛ ደግሞ የዓመት ደመወዙ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ነው።

የሟች ሰራተኛ ጥገኞች የሚባሉት

የሟች ሕጋዊ ባል ወይም ሚስት የጥገኞች ካሳ ክፍያውን 50 በመቶ

እድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች ለእያንዳንዳቸው 10 በመቶ

በሟች ድጋፍ ይረዱ የነበሩ የሟች ወላጆ እያንዳንዳቸው 10 በመቶ ያገኛሉ።

የክፍፍሉ መጠን ሙሉ የካሳውን መጠን እስኪሸፈን ድረስ እንደ ጥገኞቹ ቁጥር ብዛት ማነስ ወይም መብዛት እየተቀነሰ ወይም እየተጨመረ ይደለደላል።

የአሰሪ ግዴታዎች፡- በአዋጁ አንቀጽ 104 ላይ አሰሪው ላይ ሰራተኞች ላይ ከሚደርስ ጉዳት አንጻር ልዩ ግዴታዎች ተጥለዋል እነሱም የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ጉዳት ለደረሰበት ሰራተኛ ወዲያውኑ መስጠትና ተስማሚ በሆነ መጓጓዣ ወደ ህክምና ጣቢያ ማድረስና ጉዳቱን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ናቸው። ሰራተኛው ከሞተ የቀብር ወጪ መሸፈንም ልዩ የአሰሪው ግዴታ ነው። ጉዳት የደረሰበት ሰራተኛ በአሰሪው የህክምና ወጪዎችን የመሸፈን ግዴታ የተጣለበት ሲሆን ጠቅላላና ልዩ ህክምና እንዲሁም የቀዶ ህክምና ወጪ፣ የሆስፒታልና የመድሃት ወጪ፣ የማንኛውንም አስፈላጊ ጥገና ወጪዎችንም የመሸፈን ግዴታ አለበት። ሰራተኛው የሚደረግለት ህክምና የሚቋረጠውም የህክምና ቦርድ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ነው። 

  

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
8412 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1047 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us