ከውርስ መነቀል

Wednesday, 10 June 2015 12:00

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-         ተናዛዥ ሕጋዊ ወራሾቹን ከውርስ ሊከለክል የሚችልበት ሁኔታና ገደቦቹ፣

-         ከውርስ መነቀልና አይነቶቹ፣

-         በልጅና በሟች የእህት ልጅ ልጅ መካከል የተደረገው ከውርስ የመነቀል ክርክር በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ የምናወጋው አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ሀብቱን በኑዛዜ ሲያወርስ በሕግ ወራሾቹ ሊሆኑ የሚችሉ ልጆቹን ሀብቱን እንዳይወርስ ማድረግ ይቻላል? በሕግ ወራሽ የሟችን ሀብት እንዳይወርስ ማድረግ የማይችሉት የትኞቹ ምክንያቶች ናቸው። በኑዛዜ የወራሽነት መብቱን እንዲያጣ የተደረገ ወራሽስ ምን መከራከሪያዎችን ማንሳት ይችላል? የሚሉትን እና ሌሎችንም ተያያዥ ነጥቦች እናነሳለን።

1.የወ/ሮ በላይነሽ ኑዛዜ፡-

ወ/ሮ በላይነሽ ሚያዝያ 1996 ተናዘዙ። ከተናዘዙ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ኑዛዜው ተከፍቶ ታየ። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን ቤቴን ለእህቴ ልጅ ልጅ ለኤርምያስ አውርሼዋለሁ። ለልጄ ለፍቃዱ ደግሞ አንድ አንድ መቶ ብር ብቻ ስጡልኝ የሚል ነበር። ፈቃዱ እናቱ ያለውን አንድ ቤት ለአክስቱ የልጅ ልጅ ለኤርሚያስ ብቻ ሰጥተው እሱን ልጃቸውን በአንድ መቶ ብር ማሰናበታቸው አስከፋው።

ፍቃዱ ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ኑዛዜውን አቅርቦ የወ/ሮ በላይነሽ የኑዛዜ ወራሽ መሆኑን አረጋግጦ መጣ። በዚህ ውሳኔ መሰረት የእናቱ ብቸኛ ቤት ለአክስቱ የልጅ ልጅ ሊሰጥበት በመሆኑ ፍቃዱ በሌለሁበት የተሰጠው ውሳኔ መብቴን ይነካል ልጅ እንደመሆኑ በሕግ አገኝ የነበረውን የውርስ ድርሻ በማሳጣት በ100 ብር ብቻ ስለተሰጠኝ አላግባብ ከኑዛዜ ተነቅያለሁ። ስለዚህ ኤርምያስ የኑዛዜ ወራሽ መሆኑን የሚያረጋግጠው ውሳኔ ይሻርልኝ ሲል አመለከተ።

ፍ/ቤቱም የኤርሚያስና የአያቱ የህግ ልጅ የሆነው የፍቃዱን ክርክር መርምሮ ኑዛዜው በሕግ የተቀመጡትን መስፈርቶች ስለሚያሟላና ሟች ለፍቃዱ አንድ መቶ ብር በማውረሳቸው ነቅለውታል። (በውርስ ሀብታቸውን እንዳያገኝ) አድርገዋል ሊባል የሚችል ባለመሆኑ የሰጠሁት የኑዛዜ ወራሽነት ውሳኔ ሊሽር አይገባም ብሎ ወሰነ።

አቶ ፍቃዱ ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ቅር ስለተሰኙ ለከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት እና ለሰበር ችሎቱ አቤቱታ ቢያቀርብም ተቀባይነት ሳያገኝ ስለቀረ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ስለተፈፀመ ውሳኔው ይሻርልኝ ሲል ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት ሰበር አቤቱታ አቀረበ። ሰበር ሰሚው ችሎት የፍቃዱንና የኤርሚያስን ክርክር እና የወ/ሮ በላይነሽን ኑዛዜ መርምሮ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ውሳኔውን ከማየታችን በፊት ለክርክሩ መነሻ የሆኑትን የሕግ አንቀፆች ምን እንደሚሉ እንጥቀስ።

2.ከውርስ መነቀል

አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ አብረውት የማይሞቱ ቀሪ መብቶቹና ግዴታዎቹን ለወራሾቹ ይተላለፋሉ። ይህ የውርስ መተላለፍ በሁለት መንገዶች የሚደረግ ነው። አንደኛው የሚፀና ኑዛዜ ሳያስቀር የሞተ ሰውን ውርስ የሚመለከት ሲሆን በሕግ መሰረት ከሟች ልጆች፣ እነሱ ከሌለ ወላጆች እያለ በቅደም ተከተል የወራሽነት መብታቸውንና ከውርሱ የሚደርሳቸውን ድርሻ በፍ/ብሔር ሕጉ የሕግ የወራሽነት መብት ድንጋጌዎች መሰረት ወራሾች መብታቸውን የሚያገኙበት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ሟች በሕግ ፊት ተቀባይነት ያለው የፀና ኑዛዜ ትቶ ሲያልፍ በኑዛዜው መሰረት ኑዛዜው ሟች የሚፈልገውን ሃሳብ ይዟል ተብሎ ስለሚገመት ከሞተ በኋላ በሚቀረው ኑዛዜ መሰረት የኑዛዜ ወራሾች እና የኑዛዜ ተጠቃሚዎች እና ከሟች ሀብት የሚደርሳቸው የውርስ ድርሻ የሚለይበት ነው። በተጨማሪ ሞግዚትነትን እንዲሁም ደግሞ ከንብረቱ ላይ ስጦታ፣ ቀለብ ወይም መጦሪያ ማግኘት ያለባቸውንም ሰዎች ሊጠቀስም ይችላል።

ኑዛዜ ሟች ከሞተ በኋላ በሕግ ተፈፃሚነቱ የሚያገኝ ሰነድ በመሆኑ ኑዛዜው ባይኖር በሕግ ከሟች የውርስ ሀብት ላይ ድርሻ ያላቸውን አንድ ወይም ብዙ ወራሾቹን ከውርስ መብታቸው መንቀል (መከልከልም) ይቻላል። በሕጉ አግባብ የተደረገ ኑዛዜ የሚፀና ውጤትን የሚያስከትል በመሆኑ የሟች ስለ ውርስ ሀብቱ በህይወት እያለ የነበረው ሃሳብ ከሞተ በኋላ ተፈፃሚ የሚሆንበት ሰነድ በመሆኑ በሕግ ተቀባይነት ያለው ከውርስ መነቀልም እንዲሁ በሕግ ከተቀመጠው የወራሽነት መብት በላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል። ሟች በኑዛዜ በሁለት መንገድ ወራሾቹን ከውርስ ሊነቀል ይችላል።

2.1     በግልጽ ከውርስ መንቀል፡- ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ ያለ ኑዛዜ ሊወርሱት የሚችሉትን ወራሾቹን በሙሉ ወይም አንደኛቸውን በግልፅ በስም ወይም በዝምድና ደረጃቸው በመጥቀስ የወራሽነት መብት እንዳይኖራቸው መከልከል (መንቀል) እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 937(1) ሆኖም ተናዛዡ በግልፅ ወራሾቹን ከኑዛዜ በሚነቅልበት ጊዜ ሁለተኛና ከዚያ በላይ ያሉ የሕግ የወራሽነት ደረጃ ያላቸው ወራሾችን (የሟች እናት አባት፣ አያቶች፣ እህት ወንድም፣ አክስት ፣ አጎት) የመሳሰሉትን የውርስ ሀብቱን ማግኘት እንደሌለባች ብቻ በግልጽ በመጥቀስ ማስቀመጥ ብቻ ከውርስ መነቀሉን በሕግ ፊት የፀና የሚያደርገው ሲሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 937 (1) መሠረት እነኚህ በግልጽ የተነቀሉ ወራሾች ከተናዛዡ በፊት እንደሞቱ ይቆጠራል፡ (በሕግም እራሳቸው የመውረስ መብቱን ሳያገኙ የሞቱ ተተኪዎች (ልጆች ካላቸው) መውረስ የሚችሉበት የምትክነት ሕግ አለ) በመሆኑም የተነቀሉት የሟች ዘመዶች ለመውረስ የሚያስፈልገው ሟች በሚሞትበት ጊዜ በሕይወት የመኖር መስፈርትን እናዳላሟሉ ይዘለሉና መብቱ ለሌሎች የሕግ ወራሾች ወይም በኑዛዜ ልዩ ወይም ጠቅላላ ስጦታ ለተደረገላቸው ሰዎች ይተላለፋል።

ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆችን (የሟች ልጅ፣ የልጅ ልጅ) በግልፅ ኑዛዜ ከውርስ ለመንቀል ግን በፍ/ብ/ሕ/ቁ938 (1) መሠረት ተናዛዡ ከውርስ ለመንቀል የደረሰበትን ምክንያት መግለፅ አለበት። ምክንያቱ ሳይገልፅ ልጁን ወይም የልጅ ልጁን ከውርስ ከነቀለ ኑዛዜው በሕግ ፊት አይፀናም።

የሚሞት ሰው ትክክለኛውን ይናገራል በሚል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 938(2) ከውርስ የመንቀያ ምክንያት ትክክል (እውነት) አድርገው መቁጠር እንዳለባቸውና እውነት ነው አይደለም የሚለውን የመመርመር ስልጣን እንደሌላቸው ይደነግጋል። ሆኖም ግን ዳኞቹ ተናዛዥ ለወሰደው እርምጃ አደረሰብኝ ብሎ የጠቀሰው ምክንያት በቂ ነው ወይም የሚለውን ይመረምራሉ። ምክንያቱ በቂና በምክንያታዊ አስተሳሰብ ከውርስ ለመንቀል የሚያበቃ ሆኖ ካገኙት ከውርስ መነቀሉ በሕግ ፊት ውጤት የሚያስከትል ይሆናል።

2.2     በዝምታ ከውርስ መንቀል፡- ተናዛዡ ከ2ኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ያላቸው ዘመዶቹን (ከወላጆች እስከ ቅድመ አያት) ያሉትን በዝምታ መንቀሉን ወይም እንዳይወርሱ መከልከሉን ሳይገልጽ ለአንደኛው ያለኑዛዜ ወራሽ ወይም ለሌላ ሰው ሀብቱን ጠቅላላ በመናዘዝ በዝምታ ከውርስ መንቀል እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 939 (3) ይደነግጋል።

ሟች ልጆቹን ወይም የልጅ ልጆቹንም በዝምታ ማለፍ የሚችል ሲሆን ይህ የሚያስከትለው ግን ከውርስ መነቀልን ሳይሆን የኑዛዜ ጠቅላላ ስጦታ የተደረገለትን ሰው ከሟች የህግ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች (ልጆች) እንደ አንዱ ተቆጥሮ እኩል የወርሱ ድርሻ ተካፋይ እንዲሆን ማድረግን ነው እንጂ የተነቀለውን ወራሽ ሙሉ በሙሉ የውርስ መብት ወይም ድርሻ ማሳጣት አለበት።

በዝምታ በሚደረግ የውርስ መነቀል ውስጥ ሟች ካለው ጠቅላላ ሀብት እጅግ አነስተኛ የሆነውን ሰጥቶ ብቻ ካለፈውና ይህ ተራ የኑዛዜ ክፍያ እንጂ እንደኑዛዜ ስጦታ እንደማይቆጠር ይደነግጋል። ወራሹ የተደረገለት ስጦታ በሕግ ከሚያገኘው የውርስ ድርሻ መጠን ከአንድ አራተኛ እጅ በላይ የሚያሰጠው ከሆነ ከውርስ እንደመነቀል እንደሚቆጠርና ኑዛዜና ቀሪ እንዲሆን መጠየቅ እንደሚችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1123 ላይ ተደንግጓል።

ሰበር ምን አለ?

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 54 ጥር 27 ቀን 2003 በዋለው ችሎት ፍቃዱ ሟች እናታቸው ወ/ሮ በላይነሽ በኑዛዜ ለሱ መቶ ብር ለእህታቸው የልጅ ልጅ ለኤርሚያስ ብቸኛ ሐብታቸው የሆነውን ቤታቸውን በማውረሳቸው ከሕግ አግባብ ውጭ በኑዛዜ ተነቅያለሁ በሚል ያቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።

    በውሳኔውም ሟች ለልጃቸው ለአቶ ፍቃዱ 100 ብር ብቻ እንዲሰጠው ተናዘው ቤታቸውን ለእህታቸው የልጅ ልጅ በማውረሳቸው በተዘዋዋሪ አቶ ፍቃዱን ከውርስ ነቅለዋል። ሆኖም በሕግ የተቀመጠ በቂ የሚባል ያስቀመጡት ምክንያት ባለመኖሩ ፍቃዱ የተዘዋዋሪ በዝምታ ከውርስ ነቅለውታል። በመሆኑም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 939(3) መሰረት ኑዛዜውን ሙሉ በሙሉ ወራሽ ባይሆንም ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ የተደረገበት የሟች የእህት ልጅ ልጅ እንደ ሕጋዊ ወራሽ ተቆጥሮ የውርስ ሀብቱን የሚካፈል በመሆኑ ኑዛዜው ተሻሽሎ አቶ ፍቃዱና ኤርሚያስ የሟችን ሀብት እኩል መካፈል አለባቸው በሚል የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ አሻሽሎታል።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
8213 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 868 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us