የኤሌክትሪክ አደጋ እና ካሳ

Wednesday, 01 July 2015 14:22

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    በኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት የሚደርስ ጉዳቶችን የመካስ ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?

-    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኤሌክትሪክ አደጋ ኃላፊ የሚሆነው በምን ሁኔታዎች ነው?

-    እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የደረሱ ኢ.ኤ.ኃ.ኮ ተከሳሽ የሆነባቸው ሶስት የኤሌክትሪክ ጉዳት ክርክሮች በምን ውሳኔ ተቋጩ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የኤሌክትሪክ ኃይል የዓለማችንን የስልጣኔ ግስጋሴ ፍጥነት የቀየረ ለማንኛውም የዕለት ተዕለት ህይወታችን የደም ስር ያህል ወሳኝ የሆነ የኃይል ምንጭ ነው። ነገር ግን አንዳንዴ የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት መንስኤም ይሆናል። ለመሆኑ በኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት ንብረትና፣ ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ሲደርስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለጉዳቱ ኃላፊ የሚሆነው በምን አይነት ሁኔታዎች ነው? የሚለውን ነጥብ አግባብነት ያላቸውን ሕጎች እና እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱ በመብራት ኃይልና በተጎጂዎች መካከል የተደረጉ ክርክሮችን እናያለን።

 

 

1. የጎረቤት አንቴና. . .

 

ጉዳዩ የተከሰተው በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ውስጥ ነው። ወልደሚካኤል ሻንቆ ጎረቤት ከአቶ ማቴያስ ባህር ዛፍ ላይ ሰቅለውት የነበረው የቴሌቭዥን አንቴና በነበረው ኃይለኛ ንፋስ ተገፍትሮ ከሌሊቱ 9፡45 ላይ በአጠገቡ በሚያልፈው የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ይወድቃል። ይሄኔ የአቶ ማቲያስ ቴሌቭዥን ከፍተኛ ድምፅ አሰምቶ ቤታቸውን በኃይለኛ ብርሃን ሞላው ከእንቅልፋቸው ደንግጠው ሲነሱ ኡኡ ድረሱልን ተቃጠልን የሚል ጩኸት አሰሙ። መምህር ወልደሚካኤልም ጩኸቱን ሰምተው ከእንቅልፋቸው ባነው በመውጣት ወዲያውኑ በመጣላቸው አደጋውን የማስወገድ ሃሳብ በእሳት የተያያዘውን የኤሌክትሪክ መስመሩን ለማላቀቅ ሲሞክሩ ጉዳት ደረሰባቸውና የቀኝ ቀለበት ጣትና ትንሽ ጣታቸው ተቆረጠ። ሌሎች ጣቶቻቸውም ደርቀው የቀኝ እግራቸው 5ኛ ጣትም ተቆረጠ። ከፍተኛ ስቃይና የአካል ጉዳትም ደረሰባቸው።

መምህር ወልደሚካኤልም ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን በዘረጋው መስመር ምክንያት ከፍተኛ የአካል ጉዳት ስለደረሰብኝ ካሳ ይከፈለኝ ሲሉ ከሰሱት። ክሱ የቀረበለት የሃዲያ ዞን ከ/ፍ/ቤት የከሳሹንና የተከሳሽን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ መምህር ወልደሚካኤል ላይ 63 በመቶ ቋሚ የአካል ጉዳት ስለደረሰ ይሰሩ የነበሩትን የመምህርነት ስራ መስራት ስለማይችሉ የሞራል ካሳን ጨምሮ ብር 139ሺህ 228 ብር ከ26 እንዲከፈላቸው መብራት ኃይል ላይ ፈረደ።

መብራት ኃይል በውሳኔው ቅር በመሰኘት ይግባኝ ቢጠይቅም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ውሳኔውን አፀናበት። ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መምህር ወልደሚካኤል ጉዳት የደረሰባቸው በተነሳው አደጋ የኤሌክትሪክ መስመሩን ሊያላቅቁ ሲሞክሩ በመሆኑ ብቻ መብራት ኃይል ለጉዳቱ ኃላፊ ነው መባሉ ሕጉን ያላገናዘበ ነው ስለዚህ ይታረምልኝ ሲሉ አመለከቱ። ሰበር ግራ ቀኙን አከራክሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን እና እናቆየውና ሌላ ክርክር እንመልከት።

2. ዮድ አቢሲኒያ ላይ የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመድ

 

ሚያዝያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ተከራይቶ በሚሰራበት ቤት ላይ አቅራቢያ ያለ የኤሌክትሪክ መስመር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ ተበጥሶ ይወድቅና የእሳት ቃጠሎ ይነሳል። በቃጠሎው የምግብ አዳራሹ አንደ ሚሊዮን ሃያ አራት ሺህ አምስት መቶ ስልሳ ሶስት ብር የሚገመት ንብረት ወደመ።

አቶ ትዕዛዝ ኮሬ የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኤሌክትሪክ መስመሩ መበጠስ ምክንያት በደረሰው ቃጠሎ ለደረሰው ውድመት የንብረቱን ግምት ካሳ እንዲከፍላቸው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቀረቡ።

መብራት ኃይል ለክሱ በሰጠው መልስ የእሳት አደጋው ደርሶ ንብረቱን ከማውደሙ በፊት የተበጠሰ የኤሌክትሪክ መስመር የለም። የቃጠሎው ምክንያት ኤሌክትሪክ ስለመሆኑ የቀረበው ማስረጃ ተቀባይነት የለውም። መስመሩ ሲዘረጋም የከሳሽ ድርጅት አልነበረም። ስለዚህ ክሱ ውድቅ ይደረግ ሲል መልስ ሰጠ።

ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ቃጠሎው የደረሰው በኤሌክትሪክ መስመሩ መውደቅ መሆኑን ከሳሽ ቢያስረዱም ቃጠሎው የደረሰው መብራት ኃይል ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት በፈፀመው ተግባር መሆኑን ስለሚያስረዱ መብራት ኃይል ለጉዳቱ ኃላፊነት የለበትም ሲል ወሰነ።

የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት ይግባኝ ቢጠይቁም የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ስላፀናው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። የኤሌክትሪክ መስመሮቹ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ነው። አደጋው ከመድረሱ በፊት ሪፖርት አድርጌ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ያደረገው ጥገና አስተማማኝ ስላልነበር አደጋው እንደደረሰ አስረድቻለሁ። ይህም ቸልተኝነቱን የሚያረጋግጥ ሆኖ እያለ የስር ፍ/ቤቶች ለጉዳቱ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኃላፊነት የለበትም በማለት በመወሰናቸው የህግ ስህተት ፈፅመዋል፤ ስለዚህ ይታረምልኝ ሲሉ ጠየቁ።

መብራት ኃይል በበኩሉ የእሳት ቃጠሎ የተነሳው ከኤሌክትሪክ መስመሩ ሳይሆን ከምግብ አዳራሽ ወጥ ቤት በተነሳ እሳት ምክንያት መሆኑን ማስረጃ ስላቀረብኩ የሰበር አቤቱታው ውድቅ ይደረግ ሲል መልስ ሰጠ። ሰበር የሰጠው ውሳኔ ይቆየንና አንድ ሌላ ክርክር እንድገም።

 

3. ፌሮ ብረቱ ኤሌክትሪኩን፣ ከሳሽ ደግሞ ፌሮውን ነኩና

 

አቶ ወልዱ ግንበኛ ናቸው። አቶ ሳህለ ቀጥረዋቸው የአቶ ታከለን ባለሁለት ፎቅ ህንፃ በመስራት ላይ እያሉ ነበር አደጋው የደረሰባቸው። አደጋው የደረሰው የሚሰሩበት ፎቅ ቁመቱ እየጨመረ ሲሄድ አቶ ወልዱ በስራ ላይ እያሉ በያዙት ፌሮ ብረት ከፍተኛ ኃይል ተሸክሞ የሚያልፈውን የኤሌክትሪክ መስመር በመንካታቸው ሲሆን በዚህም አደጋ ሁለት እጆቻቸው በመቆረጣቸው ሙሉ በሙሉ አቶ ወልዴ የመስራት ችሎታቸውን ማጣታቸው በህክምና ቦርድ ተረጋገጠ።

አቶ ወልዱ በፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት መብራት ኃይል፣ አሰሪያቸውን እና የህንፃውን ባለቤት ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ እንዲከፍሏቸው ከሰሱ። ፍ/ቤቱ ከሳሽና ተከሳሾችን አከራክሮ ካሳ መክፈል ያለበት አሰሪውና የቤቱ ባለቤት ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን  ነው ብሎ የአቶ ወልዴን የቀን ገቢ ብር ሃምሳ ለቀሪ የስራ እድሜያቸው በማስላት 91ሺ ብር እንዲከፍል ወሰነ።

በውሳው ላይ መብራት ኃይልም አቶ ወልዴም ይግባኝ ስላቀረቡ ከፍተኛ ፍ/ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮ መብራት ኃይልና የአቶ ወልዴ አሰሪ አቶ ሳህሌ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ ስለሆኑ በጋራ 113ሺህ 500 ብር ለአቶ ወልዴ እንዲከፍሉ ወሰነ።

መብራት ኃይል ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ አቀረበ። የህንፃው ቁመት ወደ ኤሌክትሪክ መስመሩ ሲጠጋ መስመሩ እስኪነሳ ስራው ማቆም የነበረባቸው የአቶ ወልዴ አሰሪ ናቸው ለጉዳቱ ኃላፊ መሆን ያለባቸውም እሳቸው ሆነው ኃላፊ መባሌ አላግባብ ነው አሉ።

አቶ ወልዱ ከማናቸውም መንገድ ህዝብ በብዛት በሚገኝበት ስፍራ የሚዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመር የአደጋ መከለያ ሊኖረው እንደሚገባ የኤሌክትሪክ ደንብ ቁጥር 49/91 ይደነግጋል። መብራት ኃይል ግን ይህን ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ አደጋው ስለደረሰ ኃላፊነት አለበት ሲሉ መልስ ሰጡ። ሰበር የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ውሳኔ ሰጠ። ውሳኔዎቹን ከማየታችን በፊት ለካሳ ኃላፊነት መስረት የሚሆኑትን የሕጉን ድንጋጌዎች በአጭሩ እንያቸው።

 

 

4. የካሳ ኃላፊነት

 

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2026 ከውል ውጭ የሆኑ የኃላፊነት ምንጮችን ደንግጓል። የመጀመሪያው ማንኛውም ሰው የውል ግዴታ ባይኖርበትም በፈፀመው ጥፋት በሌላ ሰው ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት። ይህ መርህ በጥፋት ላይ የተመሰረተ የካሳ ኃላፊነት ነው። ጥፋት ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት የሚደረግ አንድን ነገር የማድረግ ወይም ማድረግ ያለበትን ባለማድረግ ሊከሰት ይችላል።

ሌላው የካሳ ኃላፊነት ደግሞ ማንም ሰው ጥፋት ኖረባቸውም አልኖረባቸውም በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚችል ስራ ከሰራ ወይም በእጁ የያዘው ነገር ንብረቱ የሚጠቀምበት እቃ ወይም የሚሰራው ስራ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ኃላፊ ይሆናል። ለሁለቱም ሁኔታዎች ጉዳቱን ያደረሰው ሌላ ሰው ቢሆንም በሕግ ኃላፊነት ያለበት ሰው (የንብረት ባለቤት፣ አሰሪ፣ ሞግዚት) ኃላፊነት አለባቸው።

በፍ/ብ/ሕ/ቁ/ 2066 አንድ ሰው ጥፋት ባይኖርበትም በራሱ ላይ ፣ በንብረት ወይም በሌላ ሰው ንብረት ላይ ሊደርስ የሚችል እርግጠኛ አደጋን ለመከላከል በሌላ ሰው ላይ ሆን ብሎ ጉዳት ካደረሰ የመካስ ኃላፊነት አለበት። ሆኖም ጉዳቱ የደረሰው በተጎጂው ጥፋትና ምክንያት ከሆነ ጉዳት አድራሹ አይጠየቅም። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2069 ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋትን ጨምሮ የሚፈነዳ መርዝና ነገሮችን በማከማቸት የመሬትን ቅርፅ ወይም መልክ በመለወጥ አደገኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ስራ በማካሄድ ሌላ ሰው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሥራውን የሚሰራው ሰው ኃላፊ ሲሆን ጉዳቱን ያደረሰው መንግስት ወይም ስራውን እንዲሰራ የተፈቀደለት ተቋም ቢሆንም በኃላፊነት ለሚሰራው ስራ ላደረሰው ጉዳት አጠፋም፣ አላጠፋም ኃላፊ ነው። ሆኖም አሰሪው ጥፋት ካልፈጸመ የዋናው ተጎጂ ጎረቤት በሆኑ ንብረቶች ላይ በደረሰው አደጋ ምክንያት የደረሰ መበላሸትን የመካስ ኃላፊነት እንደሌለበት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2070 ላይ ተደንግጓል። ያነሳነው ጉዳይ መሰረታዊ የካሳ ኃላፊነቶችን የሚደነግጉት እነዚህ አንቀፆች ናቸው፡

5. ሰበር ምን አለ

 

የአቶ ወልደሚካኤል ጉዳይ ሰበር በሰ/መ/ቁ 63231 ግንቦት 6 ቀን 2004 በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል። አቶ ወልደሚካኤል ላይ የደረሰው ጉዳት አንቴናው ኤሌክትሪክ መስመሩ ላይ በመውደቁ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጥፋት ሳይኖርበት ተጠያቂ የሚያደርገውን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለማድረጉን ሳያጣሩ የስር ፍ/ቤቶች ካሳ እንዲከፍል መወሰናቸው አግባብ አይደለም። በመሆኑም የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍቤት የተነሱትን ነጥቦች አጣርቶ ተገቢውን ውሳኔ ይስጥ ብሎ ጉዳዩን መልሶለታል።

በሰ/መ/ቁ 65395 የካቲት 26 ቀን 2004 በዋለው ችሎት የዮድ አቢሲኒያን እና የመብራት ኃይልን ክርክር ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንና የአካባቢ ጥበቃን የሚመለከቱ የተለያዩ አዋጆችንና ደንቦችን በመጥቀስ በነዚያ ደምቦች መሰረት ዮድ አቢሲኒያ ላይ ጉዳት ያደረሰው የኤሌክትሪክ መስመር ሲወድቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ወይስ አልተወጣም፣ መስመሩ የኤሌክትሪክ ኤጀንሲ ያወጣውን የጥፋት ደረጃ ያሟላ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ካስፈለገ ሙያዊ ማብራሪያ ኤጀንሲው እንዲያቀርብ አድርጎ እንዲወስን የተሰጠውን የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ሽሮ ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍቤት መልሶታል። ሁለቱም ውሳኔዎች ቅጽ 13 ላይ ታትመው ወጥተዋል።

በአቶ ወልዱና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መካከል የነበረው ክርክር በሰ/ወ/ቁ 57 904 ታህሳስ 15ቀን 2003 ውሳኔ አግኝቶ በቅጽ 11 ላይ ታትሞ ወጥቷል። ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጉዳቱ የደረሰው በአቶ ወልዱ ጥፋት ምክንያት መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ ባለማቅረቡ መስመሩ በአደጋ መካላከያ ፕላስቲክ ተሸፍኖ የነበረ ባለመሆኑ በአቶ ወልዱ ከፍተኛ ፍ/ቤቱ የወሰነውን 113 ሺህ 500 ብር ካስ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና አሰሪው እንዲከፍሉ ሲል ውሳኔውን አፅንቷል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
7780 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 856 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us