የመኪና ሽያጭና ስም ማዛወር

Wednesday, 08 July 2015 15:22

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    የተሽከርካሪ ሽያጭ ውል በውል አዋዋይ ፊት መደረግ አለበት?

-    የስም ዝውውርን ለማድረግ የመኪና ሻጭ ያለበት ግዴታ እስከምን ድረስ ነው?

-    ተሽጦ ስሙ ያልተዛወረ ተሽከርካሪ አደጋ ቢያደርስ ሻጭ ይጠየቃል?

-    እስከ ሰበር የደረሱ የመኪና ሽያጭና የስም ዝውውር ጉዳዮች በምን ውሳኔ ተቋጩ

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? በዛሬው ጽሁፍ አንድ መኪና በሽያጭ ወይም በስጦታ ለሌላ ሰው ተላልፏል የሚባለው ምን ነገሮች ተሟልተው ሲገኙ ነው። የመኪና ባለሀብትነት ስም ዝውውር ባልተደረገበት ሁኔታ ተሽከርካሪው ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ቢያደርስ የባለቤቱ የካሳ ኃላፊነት ምን ይመስላል የሚሉትን ጉዳዮችና ተያያዥ ነጥቦች እናነሳለን።

 

 

1.ለወ/ሮ አስናቀች ማን ካሳ ይክፈል?

ወ/ሮ አስናቀች ልጃቸው በመኪና ተገጭቶ ሞተ። ልጃቸውን ምናሴ ከበደን ገጭቶ የገደለው የስ.ቁ. 3-03657 የሆነው መኪና የአቶ አለማየሁ አህመድ ነበር። አቶ አለማየሁ ይህን መኪናቸውን ለሌላ ሰው ቢሸጡም፤ ስሙ በገዢው አልተዛወረም። የግጭት አደጋው የደረሰውም ገዢው ቀጥረው ያሰሩት በነበረው ሹፌር መኪናው ሲሽከረከር ነበር። ሹፌሩ በቸልተኝነት ሰው ገጭቶ በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በእስር ተቀጣ።

ወ/ሮ አስናቀች በልጃቸው ሞት ለደረሰባቸው ጉዳት በ1ኛ ተከሳሽነት አቶ አለማየሁን መኪናው በስማቸው ስለሚገኝ፣ በ2ኛ ተከሳሽነት ገዢውን ተሽከርካሪው ገዝተው እየተጠቀሙበት ስለሚገኙ፣ በ3ኛነት አሽከርካሪውን ደግሞ ጉዳቱን ስላደረሰ በአንድነትና በነጠላ ካሳ እንዲከፍሏቸው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ መሰረቱ።

ፍ/ቤቱም የከሳሽና የ3ቱን ተከሳሾች ክርክር መርምሮ አቶ አለማየሁ መኪናውን ለ2ኛ ተከሳሽ በሽያጭ ስላስተላለፈ ሊጠየቅ አይገባም። የጉዳት ካሳ የመካስ ኃላፊነት ያለባቸው የመኪናው ገዢና ተቀጥሮ መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው ሹፌር ናቸው ሲል ወሰነ።

የወ/ሮ አስናቀች ጠበቃ ኪሩቤል ኃ/ማርያም በውሳኔው ቅር ስለተሰኘ ስም ያላዛወሩት የመኪናው የቀድሞ ባለቤት አቶ አለማየሁም ሊጠየቁ ይገባል ብሎ ይግባኝ ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ ይግባኙን ሳይቀበለው ቀረ።

የወ/ሮ አስናቀች ጠበቃ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የተሽከርካሪው የቀድሞ ባለቤት የሆነው አቶ አለማየሁ የተሽከርካሪው ስሙ ሀብት ስላልተዛወረ የካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት፣ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ይታረምልኝ ሲል ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረበ።

ሰበር የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ሕጉን በመተርጐም ውሳኔ ሰጥቷል። ከውሳኔው በፊት አንድ ክርክር እንጨምር።

2.ዳዊትና ተሻለ

አቶ ተሻለና ወ/ሮ ደብሪቱ የስ.ቁ. 3-07999 ኦሮ የሆነውን መኪና ብር 250 ሺህ ብር ከአቶ ዳዊት ላይ ይገዛሉ። ከሽያጩ ገንዘብ ውስጥ ብር 200 ሺህ ከፍለዋል። ሆኖም ገዢዎቹ አቶ ተሻለ እና ወ/ሮ ደብሪቱ የገዙት ተሽከርካሪያቸው የሽያጭ ውል ውል ክፍል ቀርቦ ባለመመዝገቡ ስሙ ሊዛወርባቸው አልቻለም። በዚህም የተነሳ መኪናወን ማስመርመርና ቦሎ ማሳደስ ባለመቻላቸው በተሽከርካሪው ሰርተው ገቢ ማግኘት አልቻሉም። ለዚህም ሰበቡ የሻጩ የአቶ ዳዊት ላይ ክስ መሰረቱ። በገዥው ምክንያት የመኪናው ስም ስላልተዛወረ ከመጋቢት 2000 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ሰርተን ልናገኝ የምንችለውን ብር 8ሺህ ስላሳጣ በተጨማሪ ብር 20ሺ ጨምሮ ይከፈለን ሲሉ ክስ አቀረቡ።

አቶ ዳዊት ቀርቦ የመኪና ሽያጭ ውሉን በአግባቡ ፈጽሜያለሁ። ይዞታውንም አስተላልፌያለሁ። የመኪናውን ባለቤትነት ለማስተላለፍ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ሁሉ ለገዥዎች አስረክቤያለሁ። ስም ማዞር የእኔ የሻጭ ኃላፊነትና ግዴታ አይደለም ሲል ተከራከረ።

ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ አቶ ዳዊት የመኪናው ባለሀብትነት ለማዛወር የሚያስፈልገውን ውል በውል አዋዋይ ፊት ለመፈፀም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ውሉ መፍረስ አለበት።

አቶ ዳዊት ለተከሳሾች ለእያንዳንዳቸው 112 ሺህ 500 ብር ይከፈል። ከሳሾችም መኪናውን ይመልሱለት ሲል ወሰነ።

አቶ ዳዊት ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ይግባኝ ጥቅምት 2001 ዓ.ም አቀረበ። ፍ/ቤቱም ይግባኙን መርምሮ ዳዊት ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ሁሉ ለገዢዎች አስረክቧል። ስም ማዛወር የሻጭ ግዴታ አይደለም። የመኪና ሽያጭ ውል በውል አዋዋይ ፊት እንዲደረግ የሚያስገድድ ሕግ የለም። ስለዚህ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም በሚል የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሻረው።

አቶ ተሻለ በውሳኔው ቅር ተሰኝተው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ አቀረቡ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ደግሞ የከፍተኛ ፍ/ቤትን ውሳኔ ሽሮ የመ/ደ/ፍ/ቤትን ውሳኔ በማፅናት የመኪና ሽያጨ ውሉ መፍረስ አለበት አለ።

አቶ ዳዊት ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የመኪና ሽያጭ ውሉን ከ3 ዓመት በፊት ፈጽሜያለሁ። የመኪናውን ባለሀብትነት ወደ ገዥዎች አላዛወርክም በሚል የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ስለዚህ ውሳኔው ታይቶ ይታረምልኝ ሲል አመለከተ።

ሰበር ሰሚው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቶበታል።

3.ሰበር ምን አለ?

ያነሳናቸው በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ትርጉም የተሰጠባቸው ሁለት ክርክሮች ሁለት መሰረታዊ ጭብጦችን አንስተዋል። አንድ የመኪና ሻጭ ወደ ገዢ ስም ለማዛወር ምን ግዴታዎች አሉበት? ግዴታዎቹን ተወጥቷል የሚባለውስ የትኞቹን ሁኔታዎች ሲያሟላ ነው የሚለው በሁለተኛው ክርክር ላይ የተነሳ ነው። በመጀመሪያ ክርክር ላይ ደግሞ በስጦታ ወይም በሽያጭ ለሌላ ሰው የተላለፈ መኪና ጋር በተያያዘ ሻጭ ወይም ስጦታ ሰጪ ተሽከርካሪው ከሚያደርሰው ጉዳት ጋር ያለበትን ኃላፊነት ይመለከታል። በመቀጠል ክርክሮቹ ላይ የተሰጡትን አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች እንመልከት።

 

 

3.1.   ስም ያላዛወረ የመኪና ሻጭ መኪናው ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊነት አለበት?

ይሄን ነጥብ ወ/ሮ አስናቀች መኪና ሽጠው ስም ባላዛወሩት በአቶ አለማየሁ ላይ ባቀረቡት የጉዳት ካሳ ላይ ነው የተነሳው። ሰበር ሰሚ ችሎቱ ቅጽ 11 ላይ ታትሞ በወጣው የሰ/መ/ቁ. 24643 ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም ውሳኔ ሰበር ለውሳኔው መሰረት ያደረገው ተሽከርካሪዎች ልዩ ከሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ባለሀብት ማስተላለፊያ መንገዶች አንፃር የሕጉን ድንጋጌዎች በማየት ነው።

በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1186 ግዙፍነት ያላቸው ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በግዢ ወይም በሌላ አኳሀን ወይም በኑዛዜ የታሰበው ሰው ንብረቱን በእጁ ባደረገ ጊዜ የተላለፈለት ይሆናል ይላል። ማለትም ተንቀሳቃሽ ንብረት ባለቤት ለመሆን ተጨማሪ ሁኔታ ማሟላት ሳያስፈልግ ንብረቱን መግዛት ወይም በስጦታ በኑዛዜ ወይም በሌላ ሁኔታ በእጅ ማድረግ በቂ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ድንጋጌ ልዩ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን እንደሚያካትት በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1186(2) ላይ ተደንግጓል።

መኪናና ባለ ሞተር ተሽከርካሪዎች የምዝገባና የባለሀብትነትን ማስተላለፊያ ስርዓትን በመከተል መሆኑን በመንገዶች ላይ ጉዞንና ማመላለሻን ለመቆጣጠርና ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 256/1960 እና በተለያዩ ጊዜዎች የተሻሻለውን ሕግ ክፍል 360/1961 መመልከት ያስፈልጋል።

የፍጥነት ወሰኑ በሰዓት ከ20 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ልዩ ተሽከርካሪ በስተቀር ማንኛውም ባለሞተር ተሽከርካሪን ማስመዝገብ ግዴታ መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 256/60 አንቀጽ 6 እና የመንገድ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር አንቀጽ 21 ያስረዳል።

በዚህም መሰረት ምዝገባ አያስፈልጋቸውም ከተባሉት ተሽከርካሪዎች ውጭ ለአገልግሎት ከተላለፈ ቀን ጀምሮ በ30 ቀን የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር እንዲሰጠው ለሚመለከተው ፍ/ቤት ማመልከት አለበት። ባለቤትነቱ የተላለፈለትን አግባብ የሚያረጋግጡ ሰነዶችን የቀድሞዋን ባለቤት የመታወቂያ ደብተር እና አስፈላጊ ሰነዶችን አያይዞ ማቅረብ አለበት።

በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት አንድ ተሽከርካሪ ከአንዱ ወደ ሌላ በሽያጭ፣ በስጦታ ወይም በሌላ መንገድ ሲተላለፍ ውል ከመዋዋል በተጨማሪ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተመዝግቦ የባለቤትነት ማስተላለፊያ አስፈላጊው ስርዓት መፈፀም አለበት። ይህም ተሽከርካሪዎች ባላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ባሻገር ሊያስከትሉ የሚችሉት የጉዳት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሀገራት ልምድም መረዳት የሚቻል ነው።

በመሆኑም የተሽከርካሪ ባለሀብትነት የሚተላለፈው ተገቢው ምዝገባ በሚመለከተው መስሪያ ቤት ተሰጥቶ የተሽከርካሪው ባለቤትነት ስም ሲዛወር ነው።

ከዚህ አንፃር የፍትሐብሔር ሕጉን ከውል ውጭ የሚደርሱ ጉዳቶችን የሚመለከተውን አንቀጽ 2081(1) ስንመለከት አንድ ባለሞተር ተሽከርካሪ ባለቤት የሆነ ሰው ተሽከርካሪው ተሰርቆ እያለ ላደረሰው አደጋ ከተጠያቂነት ነፃ ከሚሆን በስተቀር መኪናውን ለመንዳት ባልተፈቀደለት ሰው እንኳን ሲሽከረከር ጉዳት ቢያደርስ የካሳ ኃላፊነት አለበት። ይህም የኃላፊነት አይነት ካለጥፋት ኃላፊነት ከሚያስከትሉ ምድቦች ውስጥ የሚመደብ ነው።

በመሆኑም አቶ አለማየሁ መኪናውን ለ2ኛ ተከሳሽ ሸጠው ስሙ ሳይዛወር በስማቸው ስለሚገኝ ተሽከርካሪው ላደረሰው ጉዳት ከ2ኛና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት አለባቸው። ለካሳው ኃላፊ በሆኑበት መጠን ንብረቱን ገዝቶ በእጁ አድርጐ ሲገለገልበት ከነበረው ሰው ላይ ከሶ ገንዘቡን ማስመለስ ግን ይችላል በማለት ስም ያላዛወሩት አቶ አለማየሁ ነፃ ናቸው በሚል የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል።

3.2.   የመኪና ሻጭ ስም በማዛወር ግዴታ አለበት?

የአቶ ዳዊትን እና የአቶ ተሻለን ክርክር ላይ በስ/መ/ቁ. 56569 መጋቢት 23 ቀን 2003 ዓ.ም ሰበር በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቶበት በቅጽ 12 ላይ ታትሞ ወጥቷል። የውሳኔው ይዘት አቶ ዳዊት ስም ለማዛወር አስፈላጊውን ሰነዶች ለገዥዎች አስረክቧል። ተሽከርካሪው እዳ እገዳ እንደሌለበት ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ አቅርቧል። የመኪና ሽያጭ ውል በውል አዋዋይ ፊት እንዲደረግ የሚያስገድድ ሕግ የለም።

 

 

በመሆኑም አቶ ተሻለ ሊጠይቁ የሚገባቸው የተሽከርካሪ ምዝገባና ባለቤትነት ማረጋገጫ የሚሰጠውን የመንግስት አካል ነው። በመሆኑም ይህ ተከራካሪዎቹ በሌላ መዝገብ በነበራቸው ክርክር ተረጋግጦ እያለ የስር የመ/ደ/ፍ/ቤትና የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሉ ይፍረስ በሚል የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በሚል ውሉን ሽሮ የከፍተኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ በማጽናት የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ አይገባውም ሲል ወስኗል።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
8673 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 815 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us