የመብት ንድፈ ሀሳቦች

Wednesday, 05 February 2014 15:22

በኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    መብት ማለት ምን ማለት ነው?

-    በተለያየ ሕጎች ለተደነገጉ መብቶች መነሻ የሆኑ እሳቤዎች ምን ይላሉ?

-    መብት፣ ነፃነት፣ ችሎታ፣ የማይደፈር መብት ልዩነታቸውና አንድነታቸው

-    መብቶችና ግዴታዎች በምን ይገናኛሉ?

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው ዛሬ የምፅፈው ስለ መብት ነው። ከዚህ በፊት የተለያዩ ሕጎችን፣ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን እያጣቀስን የተወሰኑ መብቶችን፣ ግዴታዎችን፣ የተደነገጉትን ሕጎች መተላለፍ የሚያስከትለውን ኃላፊነት በዚህ አምዳችን ላይ አንስተናል። ወደፊትም እንቀጥልበታለን። ለዛሬ ይሄ በየሕጎቹ የተደነገገው መብት ራሱ ምንድን ነው በዓለማችን ስርዓቶች ሁሉ አልጎደለም እየተባለ በየአጋጣሚዎቹ የሚነሳው የመብት ምድንነው የሚለውን እናነሳለን። አንቱ የተባሉ ሊቃውንትስ በየእለቱ በየእንቅስቃሴዎችን በማንኛውም ጉዳያችን ውስጥ ስለሚነሱት ስለመብትና መብትን አለማስከበር መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳቦች ምን አሉ የሚለውን በአምዳች ቅርፅና መጠን ለክተን ብናነሳ ምን ይለናል? ምንም። ለማጣቀሻችን እንዲሁ በራይዋንድ ዋክ የተፃፈውና በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አሳታሚነት በፈረንጆችቹ አቆጣጠር በ2006 የታተመው (Philosophy of Law) የሕግ ፍልስፍናዎች የሚለው መፅሀፍ አለልን። ስለዚህ እንቀጥላ. . .

መብትን መጠየቅ ለምን?

በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች በያንዳንዱ ነገር ላይ ማለት ይቻላል መብታቸውን ለመጠየቅ ፈጣን ናቸው። መብታቸው መጣሱን ለማሳየትም ዘዴውንና ብልሀቱን አያጡትም። በመንግስታትና በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይም የሴቶችን፣ የአናሳ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና ባጠቃላይ የዜጎችን መብት እንዲጠብቁና እንዲያስፋፉ ጫናዎች ከያቅጣጫው እየጨመረባቸው ነው። መብቶችን የሚደነግጉ የተለያዩ ሕግጋት በየሀገራቱ መፅደቃቸውም ፍ/ቤቶች ላይ በግልፅም ሆነ በዝምታ ጥበቃ የተደረገላቸውን መብቶች እውቅና ሰጥቶ የመዳኘት አዲስ ግዴታ ጥሎባቸዋል። ታዲያ ይሄ መብት የሚባለው ነገር ምንድን ነው? በሕግ እውቅና በተሰጠው መብቴና እኔ ሊኖረኝ ግድ ነው ብዬ በማስበው መብት መካከል ልዩነት አለ? የተለያዩ ግለሰቦች የሚጠይቋቸው ሰብዓዊ መብቶች ማሻቀባቸው ያስከተላቸው ችግሮች ምንድን ናቸው? የተወሰኑ የመንግስት ወጪን የሚጠይቁ የመስራት መብትን የመማር መብትን የመሳሰሉ መብቶችን መጠየቅ አግባብ ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ መብቶቻችንን ብቻ ሳይሆን የመብቶችን ምንነት ማወቅ አለብን።

የህግ ንድፈ ሀሳቦች እነኚህን ከላይ የተነሱትን የተወሰኑ ጥያቄዎች ለመመለስ ሲሞክሩ ቀዳሚ ስራቸው የመብትን ጽንሰ ሃሳብ ትርጉሙን ማስቀመጥ፣ የመብቱን ተፈጥሮ የሚደግፉ እና የሚያብራሩ ንድፈ ሃሳቦችን ማዳበርና በዚህም እንዴት ወደረኛ የተወዳዳሪ መብቶችን አጣጥሞ ማስኬድ እንደሚቻል ማስቀመጥ ነው። በዚህ መሰረት ስለመብት ለመናገር ሁለቱን አበይት የመብት ንድፈ ሃሳቦች በማንሳት መጀመር እንችላለን።

  1.      1. የነፃ ፍቃድ የመብት ንድፈ ሃሳብ፡- ይህንድፈ ሃሳብ የሚያተኩረው በባለመብቱ ፍቃድ ወይም ፍላጎት ላይ ነው። ለምሳሌ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት እኔ አንድ ነገር ለማድረግ መብት ካለኝ በመብቱ የተጠበቀልኝ ያንን ነገር የማድረግ ወይም ያለማድረግ ምርጫዬ ነው።
 1.     2. የጥቅም የመብት ንድፈ ሃሳብ፡- ይህ ንድፈ ሃሳብ ደግሞ የመብት አላማ የግለሰቡን ምርጫ መጠበቅ ሳይሆን የተወሰነ ጥቅሙን ወይም ፍላጎቱን ማስጠበቅ ነው ይላል። በመሆኑም ዋነኛ የሚተኮርበት ነጥብ መብቱ አለኝ የሚለው ነገር ላይ ነው። ይህን ንድፈ ሃሳብ የሚደግፉ በነፃ ፈቃድ (ምርጫ) ንድፈ ሃሳብ ላይ ሁለት ትችቶችን ይሰነዘራሉ የመጀመሪያው የመብት ጠቀሜታው አንድ ሰው ግዴታውን ቀሪ ማድረግ እንዲችል ነው የሚለውን እይታ የሚያጣጥል ነው። ይህንም ሲያስረዳ አንዳንዱ ሕጉ ግዴታዬን የማስቀረት ችሎታዬን መሰረታዊ መብቴን ሳያጠፋ የሚኬድበት አጋጣሚ አለ።

ለምሳሌ እንድገደል ነፃፈቃዴን መስጠት አልችልም ወይም የአካል ክፍሌን አጉድዬ ለሌላ ሰው ለመሸጥ ውል መግባት አልችልም። በመሆኑም መብቶች ሁሉ ለባለመብቱ ምርጫ የተተወ አይደሉም ይላሉ። ሁለተኛው ትችታቸው ደግሞ በጥሬ መብት (በሕግ በተቀመጠው) እና መብቱን በማስፈፀም (በመተግበር) መብት መካከል ልዩነት አለ የሚል ነው። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት መብታቸውን አለመጠቀምን መምረጥ አይችሉም። በዚህ መነሻነት ከሄድን ግን ህጻናት መብት የላቸውም ልንል ነውና። መብት በባለመብቱ ምርጫ ላይ የተመሰረተ ነው የሚለው ንድፈ ሃሳብ ምሉእነት ያንሳዋል ይሉታል።

የዌስሊ ሆህፌልድ ትንታኔ

አብዛኛዎቹ ስለመብት የተሰጡ ትንታኔዎች መነሻቸው አሜሪካዊው የሕግ ሊቅ ዌስሊ ሆህፊልድ (1879-191) የሰጠው ታዋቂ የመብት ትንታኔ ነው። ሆህፌልድ መብትን ለማብራራት የሞከረው እንበልና አበበ እንትን የማድረግ መብት አለው ብንል የሚለውን መነሻ በማስቀመጥ ነው። የተነሳንበት ምሳሌ የሚከተሉትን አራት ሃሳቦች ማለት ሊሆን ይችላል ብሎ ሆህፌልድ የሚከተሉትን ትርጓሜዎች ሰጥቷል።

 1.       1. ከባድ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው አበበን እንትን እንዲያደርግ የመፍቀድ (ያለመከላከል) ግዴታ አለበት። ይህም ማለት አበበ ከከበደ ላይ የሚጠይቀው መብት አለው ማለት ሲሆን ሆህፌልድ ይህን ከሌለው እንዲከብርልን የምንጠይቀውን መብት ነው በቀጥታ ‘መብት’ ብሎ የሚጠራው።
 2.       2. አበበ እንትን የማድረግ ወይም ከማድረግ የመቆጠብ ነፃነት አለው። ወይም ደግሞ ከበደ (ሌላ ሰው) ለአበበ ማክበር ያሉት ግዴታ የለበትም ማለትም ሊሆን ይችላል። ይህ አንድን ነገር የማድረግ ወይም ያለማድረግ መብት የመጠቀም ነፃነት ‘Privilege’ ወይም ‘liberty’ ነፃ መሆን ተብሎ ይጠራል።
 3.       3. አበበ እንትን የማድረግ ችሎታ (የማድረግ ስልጣን) አለው ማለትም ይሆናል። ይህ ማለት አበበ ሕጋዊ መብቶችን እና ግዴታዎቹን ወይም ባጠቃላይ ሕጋዊ ግንኙነቶችን የሚለውጡ ነገሮችን ለማድረግ ነፃ ነው (ለምሳሌ ንብረቱን የመሸጥ ችሎታ አለው) ይህንን የማድረግ ችሎታውን የሚጠይቀው መብትም ወይም ነፃነት ኖረው አልኖረው መጠቀም ይችላል። ሆህፊልድ ይህን የማድረግ ችሎታ (ስልጣን) ይለዋል።
 4.      4. የመጨረሻው ደግሞ አበበ አንድነገር የማድረግመብት አለው ማለት አበበ ለከበደም (ለማንኛውም ሰው) ሰው ጋር መብቱን በመጠቀም ረገድ የሚያገናኘው ነገር ሳይኖርበት የራሱን ህጋዊ ሁኔታ የመቀየር ስልጣን (ችሎታ) አለው ማለት ሲሆን ይህንን አይነት መብት ‘immunity’ የማይደፈር መብት ይለዋል ሆህፌልድ።
 5.      5. የተነሳንበትን የአበበን ምሳሌ ይዘን በሌላ አገላለፅ ስናስቀምጠው አራቱም የመብት አይነቶች ‘ተቃራኒና’ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው የሚባሉት ‘ተመጋጋቢ’ ግዴታዎችና ውጤቶች አሏቸው ለምሳሌ አበበ ከከበደ ላይ የሚጠይቀው የይዞታ መብት አለው ካልን ከበደ ከአበበ ይዞታ ውስጥ መግባት የለበትም። የዚህመብት ተመጣጣኝ ወይም ተመጋጋቢ ከበደ በአበበ ይዞታ ውስጥ ያለመግባት ግዴታ ያለበት መሆኑ ነው። ነፃ የመሆን መብት ደግሞ የግዴታ ተቃራኒ ሲሆን ተመጋጋቢው ደግሞ ከማንም የሚጠየቅ መብት አለመኖሩ ነው። አበበ ከበደን ከይዞታው እንዲራቅ የመጠየቅ መብት ካለው አበበ እራሱ ግን ወደይዞታው ለመግባት ነፃ ነው ወይም አበበ ከይዞታው የመራቅ ግዴታ የለበትም።

በተለምዶ መብት የሚባሉት ከሌላው ላይ የሚጠየቅ መብቶች ሆህፌልድ እንደሚለው ተመጋጋቢ ከሆኑት ከሌላው እንዲመጣልን ከምንጠይቀው ግዴታ ጋር ተዛማጅ ናቸው። አበበ የሚጠይቀው የሆነ መብት አለው ስንል ከበደ (ሌላ ማንኛውም ሰው) ለአበበ አንድ የተወሰነ ግዴታ አለበት ማለታችን ነው። ሆኖም አበበ የሆነ ነፃነት አለው ስንል ከሌላ ከማንም ሰው ላይ እንዲያከብርለት የሚጠይቀው ግዴታ አለው ማለታችን አይደለም። ከበደ ባርኔጣ የማድረግ ነፃነት አለው ስንል ከበደ ለአበበ ባርኔጣ ማድረግ ያለማድረግ አንዳችም ግዴታ የለበትም። ሆኖም አበበ ባርኔጣ መልበስ የለበትም የሚልም ሌላ መብት አይኖርም። በሌላ አገላለፅ የነፃነት ተዛማጅ የሆነ መብት የለህም የሚባል ነገር የለም። በተመሳሳይ የማድረግ መቻል ተመጋጋቢው ኃላፊነት ነው። የአንድን ሕጋዊ ግንኙነት ሌላው ካለወጠበት ለዚያ ሰው ኃላፊነት ወይም ተጠያቂነት አለበት። የማይደፈር መብት ተዛማጁ ደግሞ ማድረግ አለመቻል ነው ይህም ማለት የሌላውን ሕጋዊ ግንኙነት ለመለወጥ አለመቻል ማለት ነው።

እነኚህ የሆህፊልድ ትንታኔዎች በዘመናዊው የሕግ ስርዓት ላይ ተጽእኖ የፈጠሩ ናቸው። የሚከበር (የሚጠየቅ) መብት፣ ነፃነት የማድረግ ችሎታ እና የማይደፈር መብት ተብለው ይታወቃሉ፡፤ የሚጠየቁትም ከአንድ ወይም ከብዙ ሰዎች ላይ ነው። ሆኖም ግን የተወሰኑ ትችቶችን ትንተናው ማስተናገዱ አልቀረም። የሆነ ግዴታ ሲኖርብኝ የሆነ ሰው ደግሞ ተነፃፃሪ መብት አለው ወይም እኔ መብት ካለኝ ሌላው ሰው ደግሞ ተነፃፃሪ ግዴታ አለበት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሁሌም እውነት አይደለም። አንተ ወይም ሌላ ሰው ከኔ ምጠይቀው መብት ሳይኖርህ ግዴታ ሊኖርብኝ ይችላል። ለምሳሌ የወንጀል ሕግ የትራፊክ ደንቦችን የማክበር ግዴታ ጥሎብኛል ሆኖም ግን እኔ ይህን ግዴታዬን በመወጣቴ ተመጋጋቢ መብት የሚያገኝ ተለይቶ የታወቀ ሰው የለም። ይህ የሆነው ለሌላ ለአንድ ሰው የምፈፅመው ግዴታ ሳይሆን ግዴታ ሊጣልብኝ ስለሚችል ነው። ለምሳሌ አንድ የፖሊስ ባልደረባ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ግልፅ ግዴታ (ኃላፊነት) ተጥሎበታል ሆኖም ይህን ግዴታ የገባው ለአንድ ተለይቶ ለታወቀ ሰው ባለመሆኑ ከዚህ ግዴታው ሌላው ሰው በግል የሚያገኘው መብት የለም።

አንድ ሰው ለሌላው ሰው የሆነ ነገር የማድረግ ግዴታ ቢኖርበትም እንኳን የግድ ይህ ግዴታ የተገባለት ሰው ተመጣጣኝ የሆነ መብት አለው ሊባል አይችልም። ለምሳሌ አንዲት መምህርት ለተማሪዎቿ የተወሰኑ ኃላፊነቶች (ግዴታዎች) አሉበት ሆኖም ይህ የግድ ለተማሪዎቿ ተመጣጣኝ መብት ያስገኝላቸዋል ማለት አይደለም። በተመሳሳይ ለማንኛውም ለህፃናት ለአዛውነቶች ኃላፊነት እንዳለብን ሊሰማን ይችላል። ይህ ማለት ግን እነሱም ከኛ ላይ የሚጠይቁት መብት አላቸው ማለት አይደለም። ሌላ ምሳሌ ብንመለከት የመብቶችን ንድፈ ኃሳቦች በመጠቀም እንበልና የመስራት መብቱን የሚጠይቅ ሰው የዚህ መብቴ ተመጋጋቢ ግዴታ አለው ካለ ለኔ ስራ የመስጠት የመስራት መብቴ ተመጋጋቢ የሆነው ግዴታ ያለበት ማነው የሚለውን በቅድሚያ መለየት ይጠበቅበታል።

አለም አቀፍ መብቶች

የምንኖው በመብቶች ዘመን ነው። ሰብዓዊ መብቶች፣ የእንስሳትመብቶች፣ የሞራል እና ፖለቲካዊ መብቶች፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የመወያያ ነጥቦችናቸው። ሆኖም በመብት ላይ ከተመሰረቱ ንድፈ ሃሳቦች በተጨማሪ አንዳንድ የሞራልና የሕግ ፈላስፎች በግዴታ ላይ የተመሰረቱ ወይም በአላማ ላይ የተመሰረቱ የመብት ንድፈ ሃሳቦችን ይከተላሉ። በሶስቱ ንድፈ ሃሳቦች መካከል ያለው ልዩነት ያን ያህል የስራ ባይሆንም ከሚከተለው መልኩ ሊገለፅ ይችላል።

ለምሳሌ አንተ የሰው ልችን ማሰቃየትን ምትቃወመው በሚሰቃየው ሰው ምክንያት ከሆነ ተቃውሞህ በመብቱ ላይ የተመሰረተ ነው (ማንም ሰው ከሚያሰቃይ ኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት ስላለው። ተቃውሞህ የሰው ልጅ ላይ የጭካኔና የሚያሰቃይ ድርጊት መፈፀም የሚያሰቃየውንም ሰው ሰብዓዊ ባህሪውን ከሰውነት ተራ አውጥቶ አውሬ ስለሚያደርገው በመሆኑ ከሆነ ደግሞ ተቃውሞህ በኃላፊነት (በግዴታ) ላይ የተመሰረተ ነው። ለምን ቢባል ሰው የሆነ ሁሉ ሌላውን የሰው ልጅ ላይ አካላዊ ስቃይ ያለመፈፀም ግዴታ አለበት የሚል ነው መነሻህ። ኢ-ሰብዓዊ የጭካኔ ማስቃየትን የምትቃወመው ድርጊቱ ከአሰቃይ እና ከተሰቃይ ሌላ ሌሎችን ሰዎች ፍላጎት ወይም ጥቅም ስለሚነካ ብቻ ከሆነ ደግሞ ተቃውሞህ ድርጊቱ ለሰው ልጆች ካለው ጥቅም ወይም ፋይዳ የመነጨ ነው።

የሮናልድ ዶርኬን የሕግ ንድፈ ሃሳብ ስለመብቶች ባቀረበው ጥናት የተደገፈ ነበር። መብቶችን የሕግን ጨዋታ የሚወስኑ ካርዶች ናቸው ይላቸዋል። እኩል ትኩረት ና ከበሬታ የማግኘት ጉዳዮች ለሰው ልጅ ክብርና ለፍትሀዊ ማህበረሰብ መሰረቶች ናቸው። እኩልነት ከነፃነትም የቀደመ ቦታ ተሰጥቶታል። ይህ የእኩልነት ጥያቄ በተለያዩ ማህበረሰቦችም ያለውን ፋይዳ በታሪክ ተገልጿል። የ1950ዎቹ የአሜሪካ የሲቪል መብቶች ንቅናቄ እናደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መገርሰስ ማሳያዎች ናቸው። ሕገ መንግስታዊ ለውጦች የተደረጉት በአንፃራዊነት ውስብስብ ባልሆኑት የሰዎች ልጆች እኩልነት ላይ በተመሰረቱ ጠንካራ የሕግና የሞራል መከራከሪዎች አማካኝነት ነው።

በዘመናችን የሰብዓዊ መብቶች ፅንሰ ሃሳብ ዋነኛው የፖለቲካና የህግ ክርክሮች ነጥብ ነው። በየመገናኛ ብዙሃኑ የሰብኣዊ መብት ጉዳዮች በሰፊው ይነሳሉ። ሃሳቡ የተመሰረተው እያንዳንዳችን ሰው ስለሆንን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በእድሜ በማህበራዊ ደረጃ ሳይገደብ መሰረታዊና የማይገፈፉ መብቶች አሉን። ይህ መብት ያለን የሰው ልጅ ዝርያ በመፈጠራችን ብቻ ነው። እነኚህ መብቶች በህግ እውቅና ተሰጣቸው አልተሰጣቸው የሚለው ከግምት ውስጥ ሳይገባ መብቶቹ ሊከበሩልን ይገባል። ምክንያቱም እነኚህ መብቶች በሕግ የተሰጡን ሳይሆኑ ከሁሉም ከሕጎችም ከሕገ መንግስቶችም የበላይ ከሆነው የተፈጥሮ ሕግ የመነጩ ናቸው። የተባበሩት መንግስታት በ1948 አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነድን ተቀብሏል። በ1976 ደግሞ የሲቪል እና የፖለቲካዊ መብቶችን እና ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ተቀብሎ በማጽደቁ ሀገራት በማህበራቸው አማካኝነት ሰብዓዊ መብቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።

ሰብዓዊ መብቶች በሶስት ትውልዶች ውስጥ አልፈዋል። የመጀመሪው ትውልድ በአብዛኛው የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች እንዳይጣሱ የሚከላከሉና በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመናት በእንግሊዛውያኑ የፖለቲካ ፈላስፎች በሆብስ በሎክ እና በሚል የዳበሩ ናቸው። ባጠቃላይ የባለመብቱ ነፃነት ውስጥ ጣልቃ ገብነትን የሚከላከሉ ናቸው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ተደርጎ የሚጠቀሰው ሕግ አውጭው የመናገር ነፀነትን እንዳይገድብ የከለከለው የአሜሪካ የመጀመሪያው የሕገ መንግስት ማሻሻያ ነው።

ሁለተኛው የሰብዓዊ መብቶች ትውልድ ደግሞ በዋናነት አዎንታዊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶችን የሚመለከት ሲሆን የትምህርት፣ የምግብ፣ የህክምና መብቶች ይገኙበታል።

ሶስተኛው የሰብዓዊ መብቶች ትውልድ ደግሞ በዋናነት የሚያተኩረው የቡድን መብቶች ላይ ሲሆን በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነድ አንቀጽ 28 ላይ “እያዳዱ ሰው በዚህ የቃል ኪዳን ሰነድ የተጠበቁት መብቶቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያስችል የማህበራዊና የአለማቀፋዊ ደህንነት (ሰላም) መብት አለው” በሚል ተቀምጧል። እነኚህ የጋራ መብቶች የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ እድገት መብቶችንና እንዲሁም ከምድረ እና ከጠፈር ሀብቶችን የመጠቀምና የመሳተፍ መብቶችን ሳይንሳዊና ቴክኒካል የሆኑ መረጃዎችን የማግኘት መብትን ያካትታል። (በተለይም ለሶስተኛው አለም ሀገራት ጠቃሚ ናቸው) በተጨማሪም ጤናማ የመኖሪያ አካባቢ፣ ሰላምና፣ አደጋዎች ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የማግኘት መብቶችንም ያካተቱ ናቸው።

     ስለመብቶች ምንነት ይሄን ያህል ከተባባልን መብቶቻችንን ለይተን አውቀን በሕጋዊው መንገድ ማስከበር የሌሎችን መብት ደግሞ ማክበር የኛ ፈንታ ነው። ለዛሬ በዚሁ ይብቃን።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
9425 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1043 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us