በአንድ ጥይት ሁለት ልብ

Wednesday, 12 February 2014 11:52

አሳዛኝና እውነተኛ የወንጀል ታሪክ አንተ ብትሆን ምን ትወስን ነበር?

በኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ የምተርክላችሁ እውነተኛ የወንጀል ታሪክ ነው። ወንጀሉ የተፈፀመውም የፍርድ ውሳኔ ያገኘውም በአሜሪካን ሀገር ነው። የተፈፀመውን ወንጀል የቀረበውን ክስ፣ የተደረገውን ክርክርና የቀረቡትን ምስክሮች ቃል መዝነህ ውሳኔ የምትሰጠው ግን አንተ ነህ (አንተ የሚለውን አንቺ እንደ አንቺ፣ እርስዎ ደግሞ እንደ እርስዎ አድርጋችሁ አንብቡልኝ) እና ለዛሬ በዚህ እውነተኛ የወንጀል ታሪክ ላይ ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው አይደለም የሚለውን የምትወስነው አንተ ነህና በጥሞና ተከታተለኝ። በነገራችን ላይ አሜሪካኖቹ ለሚከተሉት የሕግ ስርዓት ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ነው አይደለም የሚለውን የሚወስኑት የኛ ቢጤ ከተራው ህዝብ ተመርጠው ለፍርድ የሚቀመጡ 11 ሰዎች ናቸው። “Jury” ብለው ይጠሯቸዋል። የዳኛው ስራ የፍርድ ክርክሩን ሂደት በመምራት ጁሪዎቹ ማስረጃዎችን መዝነው ተከሳሽ ጥፋተኛ ነው አይደለም ብለው የሚወስኑበትን መሠረታዊ መመሪያ መስጠትና በመጨረሻም በውሳኔያቸው መሠረት ተከሳሹን ነፃ መልቀቅ ወይም ተከሳሽ ጥፋተኛነቱ በጁሪዎቹ ለተወሰነበት ወንጀል የተቀመጠውን ተገቢ ቅጣት መፍረድ ነው። እናም ለዛሬ ኅብረተሰቡን ወክለህ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማስተላለፍ ቦታህን በችሎቱ ይዘሀል። ጉዳዩን እነሆ…

የነገሩ መነሻ

ሮይ ካርትራይት የ52 ዓመት እድሜ ጐልማሳ ነው። የ25 ዓመት ታናሹ ከሆነችው ከማርሊን ራንሰም ጋር የፍቀር ግንኙነት ነበራቸው። በየዕለቱ ማለት ይቻላል ሮይ ማርሊንን አነስተኛ ቤቷ ድረስ በመሄድ ይጐበኛታል። አብረው እየተጨዋወቱ ሲጋራ ያጨሳሉ ውስኪ ይጐነጫሉ፣ ቴሌቪዥን ይመለከታሉ። አንዳንዴም ፍቅር ይሰራሉ። ሮይ ማርሊንን እንድታገባው ቢጠይቃትም ከተጣላችው ባሏ ጋር ገና ፍቺ ስላልፈፀመ የመጋባት እቅዳቸውን ማቆየት ነበረባቸው። ማርቲን ሆጋን ደግሞ የ33 ዓመት ጐልማሳ ሲሆን የሮይ የቅርብ ጓደኛ ነበር። ችግሩ የተጀመረው ሮይ ማርቲንን ከማርሊን ጋር ያስተዋወቀው ጊዜ ነበር። ማርቲን እና ማርሊን እርስ በርስ መፈላለግ ጀመሩ። ማርቲንም ሹልክ እያለ ማርሊንን መጐብኘቱን ተያያዘው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ አንድ ቀን ሮይ ባለ 7 ሚሊ ሜትር ጠመንጃ ገዛ። ምንም እንኳን ህይወቱን ሙሉ አጋዘን አድኖ የማያውቅ ቢሆንም፤ ገና አጋዘኖች ወደ አካባቢው ብቅ የሚሉበት ወቅት ሦስት ወራቶች የሚቀሩት ቢሆንም ሮይ እንደሚለው ጠመንጃውን የገዛው አጋዘን ለማደኛ ነበር። ሮይ ጠመንጃውን በገዛ በአምስተኛው ቀን ፍቅረኛውን ማርሊንን ለመጐብኘት ቤቷ ጐራ ብሎ እየተጨዋወቱ እያለ ድንገት ማርቲንም ማርሊንን ለመጐብኘት ከች አለ። ማርቲንና ማርሊን በማውራት ላይ እያሉ ሮይ አዲሱን ጠመንጃዬን ላሳያችሁ እፈልጋለሁ አለና ወደ መኪናው በማምራት ከመኪናው ዕቃ ማስቀመጫ ውሰጥ ጠመንጃውን ይዞ ተመለሰና ወደ ፍቅረኛውና ጓደኛው ወዳሉበት ቤት ውስጥ ገባ። ማርቲንና ማርሊን በክፍሉ በሌላኛው ጥግ እርስ በርስ በጣም ተጠጋግተው ቆመው ነበር።

ሮይ ጠመንጃው የተጠቀለለበትን ወረቀት በመፍታት ላይ ሳለ ጠመንጃው ባረቀበት። ጥይቷ በማርሊን ልብ ገባችና በጀርባዋ በመውጣት በማርቲንም ልብ በርቅሳ በጀርባው አልፋ ግርግዳውን በስታ ወጣች። ማርሊንና ማርቲን ወዲያውኑ በአንድ ጥይት ተገደሉ። ጥይቷ ገብታ ከወጣችበት ቀዳዳዎችና አስክሬናቸው ከተገኘበት ሁኔታ አንፃር ጠመንጃው ሲተኰስ ማርሊን ከማርቲን ፊት ለፊት ቆማ እንደነበር ግልፅ ሆነ።

ሮይ ወዲያውኑ ወደ መኖሪያ ቤቱ በማምራት እራሱን እንደገደለና በተፈጠረው ነገር ማዘኑን የሚገለፅ ማስታወሻ ጽፎ የጠመንጃውን አፈሙዝ ጐርሶ ቃታውን ሳበው። ጥይቷ ግን በላይኛው መንጋጋው በኩል ታጥፋ የጉንጩን ስጋ ቦርድሳ ወጣች። ሮይም ከሞት ተርፎ በሁለት የግድያ ወንጀሎች ክስ ተመሰረተበት። ሮይ የቀረበበትን ክስ በመካድ ሁለት ምረጥ ጓደኞቹን ለመግደል እንዳላሰበና ጠመንጃውን ወደ ላይ ይዞ እያለ በድንገት ተተኩሶ እንደመታቸው ተናገረ። ግድያው ድንገተኛ አጋጣሚ ነው ወይስ ሆን ተብሎ ታስቦበት የተደረገ ነበር? ሆን ተብሎ ታስቦበት የተፈፀመ ከሆነ ሮይ ለመግደል ያሰበው ማንን ነበር? ማርቲንን? ማርሊንን? ወይስ ሁለቱንም? ውሳኔው ያንተ ነው።

ክሱ ተጀመረ

ዐቃቤ ሕጉ አላን ዌክስታይን ይባላል። የክስ መክፈቻ ንግግሩን የጀመረው እኔ በስራ ዘመኔ እንዲህ ዓይነት እንግዳ የሆነ ክርክር አጋጥሞኝ አያውቅም በማለት፤ የበለጠ ክርክሩ ጉጉት እንዲያጭርብህ በማድረግ ነበር።

“አንድ ጥይት” አለና ዐቃቤ ሕጉ ንግግሩን ቆም አድርጐ ትንሽ መርማሪ ዓይኖቹን በአንተና በሌሎቹ አስር ወሳኝ ሰዎች ላይ ተከላቸው። “አንድ ጥይት ናት የሁለት ንፁሀንን ልብ የማርሊን ራንሶምንና የማርቲን ሆጋንን ልብ በስታ የገደለቻቸው፤ ይህ ሮይ ካርትራይት የተባለ ሰው ተኩሶ እንደገደላቸውና ድርጊቱን የፈፀመው ሆን ብሎ አስቦበት ሁለቱንም ለመግደል አስቦ መሆኑን እናረጋግጣለን” አለና፤ በመግቢያ ንግግሩ በቂ ትኩረት በመሳቡ መድረኩን ለወጣቷ አጠር ብሎ ሞላ ያለ ሰውነት ላለው ለተከሳሽ ተከላካይ ጠበቃ ለዶናልድ ራይደር ለቀቀ።

ራይደር በዐቃቤ ሕጉ ንግግር እንደተቆጣ ያስታወቅ ነበር፤ ስለዚህ ቆጣ ብሎ “ሮይ ካርትራይት ማንም ላይ ጉዳት ለማድረስ ሀሳብ አልነበረውም። ይህ ድርጊት የተከሰተ አጋጣሚ ነው። ተከሳሹ ጨዋ ሕግ አክባሪ ሰው ከመሆኑም በተጨማሪ የሰው ልጅ ሊያጋጥመው ከሚችለው በላይ በደረሰው አደጋ ተሰቃይቷል። የሮይ መከራ ቀሪ ህይወቱን ሙሉ እንደቀንበር ተጭኖት ይኖራል” አለ።

ተከሳሹን ተመለከትከው ያለ ምንም እንቅስቃሴ በተቀመጠበት ፊት ለፊት ዓይኖቹን ተክሏል። አጠር ያለ ፀጉሩ ገባ ገባ ማለት የጀመረና ፊቱ ቅጭም ያለ በሀምሳዎቹ ውስጥ የሚገኝ ሰው ነው።

“ታዲያ አደጋውን አሳዛኝ ያደረገው ምንድን ነው?” ተከላካይ ጠበቃው ራይደር ቀጠለ “ያቺ ጥይት የሮይን ሁለት የቅርብ ጓደኞች በመግደሏ ምክንያት ነው። ዳኛው በድንገተኛ አጋጣሚ ተኩሶ መግደል ወንጀል አለመሆኑን ይነግሯችኋል…..”

“ተቃውሞ” አለና ዐቃቤ ሕጉ ከተቀመጠበት ዘሎ በመነሳት “ለጁሪዎቹ መመሪያ እየሰጠ ነው። ይህ ግን የክቡር ዳኛው ስራ ነው” አለ።

“ተቃውሞውን ተቀብያለሁ” አለና ዳኛው ወደ ጁሪዎቹ በመነፅራቸው አሻግረው እየተመለከቱ “ክቡራትና ክቡራን የጁሪው አባላት ዐቃቤ ሕጉና ተከላካይ ጠበቃው በመክፈቻቸው ውስጥ የተናገሩት ማስረጃ የሚገኘው ከምስክሮችና ተከራካሪዎቹ ከሚጠይቁት ወይም ከሚያቀርቡት ማስረጃ ነው። ስለዚህ ማንም ሌላ ሰው ማስረጃ እንዳያቀርብ በሕጉ መሠረት አዝዣለሁ። ዐቃቤ ሕግ ቀጥል” አሉ።

ምስክሮች ምን አሉ?

የመጀመሪያው የዐቃቤ ሕግ ምስክር ፊቱ በጭንቀት የሚያለቅስ የሚመስል እድሜው በሰባዎቹ ውስጥ የሚገኝ ፈራንክ ኬርሴ የተባለ ሰው ነው። ስራው ሃያ አነስተኛ ቤቶች በሚገኙበት የቤተሰብ ይዞታ ውስጥ ጠባቂ መሆኑንና ሟች ማርሊን ራንሰም ላለፉት ሰባት ዓመታት እዚያ ስትኖር እንደሚያውቃት አስረዳ። ሐምሌ 30 ቀን 1997 ዓ.ም ጠዋት ላይ በቤቶቹ በመዘዋወር ላይ ሳለ ድው የሚል ከፍተኛ ድምፅ መስማቱንና ራቅ ብሎ ወዳለው ቁጥር ዘጠኝ ቤት ሲያመራ የሚፈስ ውሃ ድምፅ ሰማ። ድምፁ ወደተሰማበት ቦታ ሲሄድ ከዘጠኝ ቁጥር ክፍለ ጀርባ ያለው አራት ጫማ ከፍታ ላይ የሚገኘው ቧንቧ ፈንድቶ ውሀው እየፈሰሰ እንዳለ ተመለከተ። ከዚያም ከቤቱ የጀርባ ግድግዳ ላይ ቧንቧው በሚገኝበት ትይዩ ቀዳዳ ተመለከተ። ከጐጆው ውስጥ የሰማ የመሰለው ዝቅተኛ የማጓራት ድምጽ ነበር።

“ከዚያስ ነገሩን አጣራህ” ዐቃቤ ሕጉ ጠየቀ

1ኛ ምስክር፡- የሆነ ነገር እንዳለ ገብቶኛል ማርሊን ውስጥ መሆኗን አውቃለሁ ምክንያቱም መኪናዋ እዚያው ነው። ስለዚህ ዞሬ በፊት በኩል ሄድኩ

ዐቃቤ ሕግ፡- ያየኸውን ለጁሪው አስረዳ

1ኛ ምስክር፡- በሩ ገርበብ ብሏል። ማርሊንን ተጣራሁ መልስ አላገኘሁም ወደ ውስጥ ስመለከት …. የአምላክ ያለህ….

ዐቃቤ ሕግ፡- ተረጋግተህ ያየኸውን ንገረን።

1ኛ ምስክር፡- በጣም ይዘገንናል። መርሊንና ሰውዬው በአንድ ላይ ወለሉ ላይ ወድቀው ወለሉ በደም ተበክሏል። በአንዴ መሞታቸውን አመንኩ። ከዛ ወጥቼ ለፖሊስ ደወልኩ።

ዐቃቤ ሕግ፡- ተከሳሽ ሮይ ካትራይትን ታውቀዋለህ?

1ኛ ምስክር፡- እንዴታ ብዙ ጊዜ ከዚያ አይጠፋም።

ዐቃቤ ሕግ፡- የዛን እለት ጠዋትስ እዛው ነበር?

1ኛ ምስክር፡- ቀደም ብሎ መኪናው ስትወጣ አይቻለሁ። ሆኖም እኔ ያሰብኩት …።

ዐቃቤ ሕግ፡- ጨርሻለሁ አመሰግናለሁ።

ተከላካይ ጠበቃው መስቀለኛ ጥያቄውን ጀመረ። ለስለስ ብሎ “ሮይ ማርሊንን ገድሏል ብለህ እንድታስብ የሚያደርግ ምክንያት አለህ?”

1ኛ ምስክር፡- ማ! እሱ! አያደርገውም! በጣም ነው የሚያፈቅራት። በጣም ከልቡ ነበር የሚያፈቅራት። ስለዚህ እንዲህ ያለ ነገር አያደርግም። ድንገተኛ አደጋ ካልሆነ በቀር።

ተከላካይ ጠበቃ፡- ብዙ ጊዜ እነሱ ሲገናኙ ክፍላቸው አካባቢ ትሆን ነበር?

1ኛ ምስክር፡- አዎ በርካታ ጊዜ።

ተከላካይ ጠበቃ፡- ሲጨቃጨቁ ሰምተህ ታውቃለህ?

1ኛ ምስክር፡- ኧረ በፍፁም።

ተከላካይ ጠበቃ፡- ሮይ ለሌላ ሰው የጥላቻ ስሜት ሲያሳይ አይተህስ ታውቃለህ?

1ኛ ምስክር፡-      ኧረ በፍፁም።

ቀጣዩ ምስክር ደግሞ ቦታው ላይ መጀመሪያ ደረሰው ፖሊሱ ጋይ ሮብ ነበር። መጀመሪያ ያደረገው ነገር የልብ ምታቸውን መስማት ሲሆን ሁለቱም ማርቲንም ማርሊንም ሞተው እንዳገኛቸው መሰከረ። ደማቸው ከደረታቸው ገና እየፈሰሰ ነበር። ማስረጃ ፍለጋ ቤቱን ዞር ዞር ብሎ ሲቃኝ ከወለሉ 49 ኢንች ከፍታ ላይ ቀዳዳ በመመልከቱ ጥይቷ በዛ መውጣቷን አወቀ። በክፍሉ ውስጥ የተተኮሰ ቀለሀ ቢፈልግም አላገኘም የፊት ለፊቱ በር አጠገብ ያለ አልጋ ላይ መሳሪያ መሸጫዎች የሚሰጡት የጠመንጃ መጠቅለያ አገኘ። ፖሊሱ ግድግዳ በስታ የወጣችውን ጥይት ማፈላለጉንና የውሃ ቧንቧው ላይ እና በተመሳሳይ ከፍታ ጐረቤት ግድግዳ መበሳቱንና ከዚህ ቤት ከኩሽናው ወለለ ላይ የተተኳሹን ጫፍ የሚመስል ነገር ማግኘቱን መሰከረ።

ሦስተኛው የዐቃቤ ሕግ ምስክር ኢሚሊ ማስተርሰን ነበረች። ሰላሳ ዓመት የሚሆናት ደንጋጣ ሴት ስትሆን፤ ለመማል እጇን ስታነሳ ለመመስከር አለመፈለጓን በቀላሉ ትታዘባለህ። ወደ ምስክር መቆሚያው በመምጣት ላይ እያለች ቆም አለችና “ክቡር ዳኛ፤ እኔ ግን የግድ መመስከር አለብኝ?”

ዳኛ፡- እኛ የምንፈልገው እውነቱን ብቻ ነው።

ኢሚሊ፡- “እርስዎ ካላዘዙኝ በስተቀር እኔ መመስከር አልፈልግም”

ዳኛ፡- እንግዲያውስ እንድትመሰክሪ አዝዣለሁ።

ኢሚሊ፡- የሮይ ከቀድሞ ትዳሩ የተገኘች ብቸኛ ልጁ መሆኗን መሰከረች። ሮይ ከሷና ከልጇ (ከልጅ ልጁ) ጋር ተኩሱ በተከሰተበት ጊዜ አብሮ ይኖር ነበር። ከማርሊን ጋር የነበረውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ ደጋግማ እንደነገረችው፤ ምክንያቱም ማርሊን ታማኝ አልነበረችም። እሱ ግን ፍቅሯ ሰለፀናበት ካላገቧኋት ይል እንደነበር ተናገረች። የዚያን ዕለት ጠዋት እሷ ከማርሊን ቤት ሃያ ማይል ርቀት ላይ በሚገኘው የቤታቸው ኩሽና ውስጥ እያለች ከፍተኛ የተኩስ ድምፅና የማቃሰት ድምፅ ከአባቷ ክፍል መስማቷን፣ ሮጣ ስትሄድ አልጋው ላይ ጠመንጃውን እንደያዘ ተንጋሎ ማግኘቷን፣ ፊቱ በአንድ በኩል በደም መበከሉን መናገር ባይችልም እራሱን ለመግደል መሞከሩን ማወቋን ገለፀች። ከዚያም አምቡላንስ ጠርታ ወደ ሆስፒታል እንደወሰዱትና ለህይወቱ እንደማያሰጋው አረጋግጣ ወደ ቤት ስትመለስ አልጋው ላይ ማስታወሻ ማግኘቷን ስትናገር፤ ዐቃቤ ሕጉ ቁራጭ ወረቀት አወጣና “ማስታወሻው ይህ ነው?” አላት።

ኢሚሊ፡- አዎ።

ዐቃቤ ሕግ፡- የእጅ ጽሁፉን ታውቂዋለሽ?

ኢሚሊ፡- አዎ የአባባ ነው።

ዐቃቤ ሕግ፡- እባክሽ ለጁሪዎቹ አንብቢላቸው።

ኢሚሊ፡- እምባ እየተናነቃት “ማርሊን ሞታለች የእኔንም አስክሬን አደራ” ብላ አነበበችው።

ዐቃቤ ሕጉ ጠመንጃውን ሲያሳያት አባቷ ላይ ያገኘችው ጠመንጃ ራሱ መሆኑን አረጋገጠች።

ተከላካይ ጠበቃውም ጥቂት ጥያቄዎችን ጠየቃት “አባትሽን ከማንም በላይ ታውቂዋለሽ፤ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ከበሬታ እንዴት ነበር?”

ዐቃቤ ሕጉ ተስፈንጥሮ ቆመና “ተቃውሞ ክቡር ዳኛ ጥያቄው የሚያሻማ ነው ከበሬታ ከምን አንፃር?”

ዳኛ፡- መቃወሚያውን ተቀብያለሁ። ተከላካይ ጠበቃው፤ እሺ አስተካክላለሁ ክቡር ዳኛ፤ ኢሚሊ አባትሽ ሕግ አክባሪ ዜጋ ከመሆን አንፃር ያለው ስም ምን ነበር?

ኢሚሊ፡- ህይወቱን ሙሉ ከማንም ጋር ተጋጭቶ አያውቅም። ሕግ አክባሪ ነው። በሁሉም መልኩ የሰከነ ሰው በመሆኑ ይታወቅል።

ተከላካይ ጠበቃ፡- ሰላማዊ ፀብ የማይፈልግ ከመሆንስ አንፃር

ኢሚሊ፡- ማንንም ሰው ጐድቶ አያውቅም።

የምስክር መቆሚያውን ለቃ ልትሄድ ስትል ዐቃቤ ሕጉ የሆነ ነገር አስታወሰና ወደ እሷ ጠጋ ብሎ የታሸገ ፖስታ ከፊቷ አስቀመጠና “እባክሽ ክፈቺው?” ሲል ጠየቃት።

የሆነ ትንሽዬ ብረት ነገር ከፍታ አወጣች። ዐቃቤ ሕጉ ምን እንደሆነ አወቅሽው? ሲል ጠየቀ። ኢሚሊ እራሷን በአዎንታ በመነቅነቅ “አዎ አባቴ እራሱን ተኩሶ ከመታ በኋላ ከኪሱ ውስጥ ያገኘሁት ነገር ይመስላል። ዐቃቤ ሕጉ ሁሉም እንዲያየው ከፍ አድርጐ ያዘና “ባዶ የጥይት ቀለሀ ይመስላል አይደል?” ኢማሊ፡- አዎ ይመስላል። ዐቃቤ ሕግ ጨርሻለሁ አመሰግናለሁ።

አራተኛው ምስክር መሳሪያ ሻጩ ጃስን ዊልኪስ ሲሆን ሐምሌ 25 ቀን 1998 ዓ.ም ማወሰር ባለ 7 ሚሊ ሜትር ጠመንጃውን በ156.22 ዶላር እንደሸጠና ተከሳሹ መሳሪያውን የገዛው ሰው መሆኑን ባያስታውስም፤ እንደሚመሳሰሉ፤ ገዢው ስለመሳሪያ ብዙ የማያውቅ መሆኑንና እንዴት ጥይቅ እንደሚጐርስ በአንድ ጥይት እንዳሳየው ፖሊሱ በቦታው ያገኘው የመጠቅለያ ወረቀቱም እሱ መሳሪያውን ሲሸጥለት ጠቅልሎ የሰጠበት መሆኑን መሰከረ።

የመጨረሻው የዐቃቤ ሕግ ምስክር ዶ/ር ዴቪድ ፋዘርማን የተባለው የአስክሬን መርማሪ ሲሆን፤ አስክሬኖቹን መመርመሩንና ሁለቱንም ለሞት ያበቃው ደረታቸውና ልባቸው በጥይት በመቁሰሉ መሆኑን ተናገረ።

“በአንድ ጥይት ነው?” ዐቃቤ ሕግ ጠየቀ

“ተቃውሞ ይህ ጉዳይ ከእሱ ሙያ በላይ ነው” “ተከላካይ ጠበቃው ተቃውሞህን ተቀብለናል እሱን የሚወስኑት ጁሪዎቹ ናቸው” አሉ ዳኛው። ሆኖም ዳኛው ጥይቷ የገባችበትንና የወጣችበትን ቁስለቱ ላይ ባደረገው ምርመራ ተንተርሶ እንዲገልፅ ፈቀዱ። ዶ/ሩ ማርሊንን የገደለችው ጥይት የመጣችው ከአካሏ ትይዩ በቀጠታ ወደ አካሏ የገባችውም ፊት ለፊት በቀጥታ መሆኑን እና የገባችበት ቦታ ከእግሯ ሲለካ 48 ኢንች ከፍታ እንዳለው መሰከረ። ጥይቷ በጀርባዋ በስታ የወጣችው በመጠኑ ከፍ ብላ ሲሆን አረሯ ከጀርባዋ ስትወጣ አቅጣጫውን የቀየረችው መሰናክል ስላጋጠማት ትንሽ ከፍ ብላና ወደ ጐን ዘመም ብላ መውጣቷን ገለፀ። ወደ ማርቲን ሰውነት ስትገባ ደግሞ ልክ ከማርሊን አካል በወጣችበት ፍጥነትና አካሄድ መሆኑንና ይህም ማርሊን አካል ውስጥ ከመግባቷ በፊት ሌላ አካል ውስጥ ገብታ እንደነበር እንደሚያሳይና ስትገባና ስትወጣ የፈጠረችው ቀዳዳ ተመሳሳይ መሆኑንና ከፍታው አርባ ዘጠኝ ኢንች አካባቢ እንደነበር ተናገረ።

ዐቃቤ ሕጉ ዶ/ሩ ጥይቱ ሲተኮስ የአካላቸው ሁኔታ እንዴት ነበር ምን ያህልስ ተጠጋግተው ነበር? ዶክተሩ በደምብ መገመት እችላለሁ። ተከላካይ ጠበቃው ተቃውሞ! ክቡር ዳኛ ሲል አመለከተ።

ዳኛ፡- ተቃውሞህን ተቀብለናል እዚህ ግምት አይፈቀድም

ዐቃቤ ሕግ፡- እንግዲያውስ ዶ/ር ቢያንስ ጥይቱ ሲተኮስ ተቀምጠው ቆመው ወይም ተኝተው እንደነበር ልትነግረን ትችላለህ።

ተከላካይ ጠበቃ ተቃውሞ! ምስክሩ በቦታው አልነበሩም።

ዳኛው፡- ተቃውሞውን ተቀብያለሁ አሉ።

ዐቃቤ ሕጉ ተቀመጠ። በዳኛው ትዕዛዝ የተከፋ ይመስላል። ጥያቄዎችህን ማቅረብ ትችላለህ አለው ለተከላካይ ጠበቃው ለራይደር ለአፍታ ፀጥ ካለ በኋላ ራይደር መቀለኛ ጥያቄውን ጀመረ።

“በሙያህና በልምድህ ዶ/ር ተኩሱ ሆን ተብሎ ነው ወይስ በአጋጣሚ ነው የሚለውን መናገር ትችላለህ?” ዶ/ሩ ያን እንኳን መናገር አልችልም። ተ/ጠበቃ፡- የመታገል ምልክት አይተሀል? ዶ/ሩ፡- ምንም ያየሁት ነገር የለም። ሲል መለሰ። ዶ/ሩ ወደ ቦታው ሲመለስ ዐቃቤ ሕጉ ሌላ ምስክር እንደሌለው አሳወቀና ችሎቱ ለእረፍት ተቋረጠ።

ተከላካይ ጠበቃው ክሱን የሚከላከሉለትና ተከሳሹ ፀብ የኃይል ተግባር የማይወድ ሕግ አክባሪ ሰላማዊ ሰው መሆኑን የሚያሳዩለት ምስክሮች ሲሆኑ፤ አንዱ ማርቲን በሚሰራበት ሬስቶራንት የሚሰራ አስተናጋጅ ሲሆን ማርቲንና ሮይ ጥሩ ጓደኞች መሆናቸውንና ተጣልተው እንደማያውቁ አስረዳ። ሌላ ምስክር በአካባቢው ቤተክርስቲያን የሚያገለግሉ ካህን ሲሆኑ ተከሳሽ በምዕመናን ዘንድ እጅግ ጥሩ ስም ያለው መሆኑን መሰከሩ። ሦስተኛዋ የመከላከያ ምስክር የተከሳሹ የልጅ ልጅ የ14 ዓመቷ ታዳጊ ልጃገረድ ሜሊሳ ስትሆን፤ እሷም በተመሳሳይ የሮይን ጥሩነተና ማንም ሰው በማርቲንም ሆነ ማርሊን ላይ ክፉ ቃል ሲናገር ሰምቶት እንደማያውቅ አስረዳች።

ተከላካይ ጠበቃው ቀጣዩ ምስክሩ ተከሳሹ ሮይ ካርትሬይ መሆኑን አስታወቀ። ተከሳሹ በዝግታ መጥቶ መመስከሪያው ላይ ቆመ። ትከሻው ጐብጧል። የችሎቱ ሰራተኛ እንደሚምል ሲጠይቀው ጮክ ብሎ እምላለሁ ሲል አረጋገጠ። በአየር ኃየል ውስጥ በቺፍ ማሽኒስትነት ለ24 ዓመት መስራቱን ከዛም ከቀድሞው ሚስቱ ተፋቶ ብዙ ከቆየ በኋላ ከማርሊን ጋር ተዋውቆ በፍቅር እንደተያዘ። አንድ ቀን ወደእሷ ቤት ቀረብ እንዲል ስትነግረው በደስታ እንደተቀበላት፣ ከዛ ከባሏ ጋር ሲጣሉ እሱ ጋር መጥታ እንደምትከርም። ባሏ ትቷት ሲሄድ እንድታገባው ቢጠይቃትም ፍቺው እስኪወሰን እንዲቆዩ እንደነገረችው ተናገረ። ስለሚፋቀሩ ከሌላ ወጣት ጋር የፍቅር ግንኙነት ይኖራታል ብሎ እንደማያውቅና ፍቺው ሲያልቅ እንደሚጋቡ ያምን እንደነበር ገለፀ። የዛን ቀን የተኰሰችለትን ልብስ ለመቀበል ወደቤቷ መሄዱን መሳሪያውንም የገዛው አጋዘን ለማደን መሆኑን ውስኪ አምጥቶ አንዳንድ ፉት ብለው እያወሩ እያለ ስልኩ መጮኹን ገለፀ። ተከላካይ ጠበቃው ቀጥተኛ ጥያቄውን ቀጠለና፤ ሮይ የደወለው ማርቲን መሆኑን ስልኩ ከተዘጋ በኋላ እንዳወቀና ከ15 ከሃያ ደቂቃ በኋላ መምጣቱን ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ማርሊን መጠጥ ስትጋብዘው አልጠጣም ማለቱን፤ ከዚያም በመስኰት አሻግሮ የሚገኘው የማርቲን ቤት ጥሩ መሆኑንና በቅርቡ አብረው እዚያ እንዳመሹ እያመራች ማርቲንን በመስኰት አጠገብ መጥቶ በመስኮት እንዲያዩ እንደጠራችው ተጠጋግተው እስኪነካኩ መቀራረባቸውንና የገዛሁትን መሳሪያ ላሳያችሁ ብሎ እንደወጣ ተናገረ። ተከላካይ ጠበቃው ማርሊን ምን አለች። ተከሳሽ እሺ ጥሩ ነው አለች። ከዛም መሳሪያውን ከመኪናው አውጥቶ አመጣና በሩ ላይ ቆሞ ከመጠቅለያው ሲያወጣው ድንገት መባረቁን ገለፀ። ከዚያ በፊት የተናገረው ይኸው መሳሪያው የሚል ቃል ብቻ ነበር። የባረቀው መሳሪያ ጥይት ማርሊንና ማርቲንን መታቸው። ከዚያም ለቅጽበት ባለበት እንደቆመና በወደቁበት እንደተመለከታቸው ቀጥሎ ወደመኪናው መሳሪያውን ይዞ እንደሄደና ተመልሶ መጥቶ እንዳያቸው ምን ማድረግ እንዳለበት እንዳላወቀና በመኪናው ውስጥ እየነዳ ወደ ሴት ልጁ ቤት እንደሄደ እራሱን እንዳጠፋ ማስታወሻ ጽፎ እራሱን ለመግደል መሞከሩን ገለፀ። እምባ በዓይኑ ተሞልቶ ማርሊንን እንደሚያፈቅራት ማርቲንም የቅርብ ጓደኛው መሆኑን ማናቸውንም ለመጉዳት አለማሰቡን ገለፀ።

ይሄኔ ዐቃቤ ሕጉ ድምፁን አሰማ። ዳኛው ዐቃቤ ሕግ መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ ትችላለህ አሉት። ከጥቁር ቦርሳው ውስጥ ትንሽዬ ብረት መሳይ ነገር አወጣና ከዚያ ቀን በፊት መሳሪያ ተኩሰህ ታውቃለህ ሲል ጠየቀው። በአየር ኃይል እያለሁ ያኔ 19 ዓመቴ ነበር። አሁን 55 ዓመትህ ነው ከሰላሳ ስድስት ዓመት በፊት መሆኑ ነው ሲል ጠየቀው ዐቃቤ፤ ሕጉ። የተከሳሽ ምስክሩ አዎ ሲል መለሰ። እነሱ ላይ ከመተኮሰህ በፊት አልተኰስክም ዐቃቤ ሕጉ ነበር የጠየቀው። ተከላካይ ጠበቃው ተቃውሞ! ተኰስኩባቸው አላለም አለ። ዳኛው ተቀበሉት። የተከሳሽ ምስክሩ እኔ አልተኰስኩትም ባጋጣሚ ጠመንጃው ባረቀ። እኔ ምንም ያደረኩት ነገር የለም። ጠመንጃውን በእጄ ከመያዝ በስተቀር። መሳሪያው እንደጐረሰ ታውቅ ነበር? ጠየቀ ዐቃቤ ሕጉ። አይ ዘንግቼ ነበር። ታዲያ ቃታውን ማን ሳበው? አላውቅም። ሌላሰው አልነበረም ታዲያ ማን ሳበው? ዐቃቤ ሕጉ ጠየቀ። ሮይ ይመስለኛል እጄ ሳይነካው አይቀርም። እጅህ ቃታው ላይ ነበር? አላውቅም። የአጋዘን አደን ጊዜ መቼ ነው? ሮይ እ… እሱማ ..

ዐቃቤ ሕጉ አጋዘን ለማደን ነው የገዛሁት ብለሀል? ሮይ፡- አዎ። ዐቃቤ ሕግ፡- ታዲያ መቼ ነው የአደጉ ወቅት ሮይ፡- አላውቅም ጌታዬ ዐቃቤ ሕግ፡- አታውቅም ሮይ፡- እጠይቃለሁ ብዬ ነበር። የአጋዘን አደን ወቅት ገና ሦስት ወር እንደሚቀረው አታውቅም? ሮይ፡- አላውቅም። ገና እጠይቃለሁ ብዬ ነበር ዐቃቤ ሕግ፡- ተከሳሹ ወረዶ መሳሪያው ሲተኰስ እንዴት ይዞት እንደነበር እንዱያሳየው ጠየቀ። ተከላካይ ጠበቃው መቃወሚያ የቢያቀርብም ዳኛው ስላልተቀበሉት መሳሪያው አለመጉረሱ ተፈትሾ እንዲያሳይ ተፈቀደ። በመካከላቸው የነበረው እርቀትም አስር ጫማ ያህል ነበር። ከዚያም በማሳየት ላይ እያለ ዐቃቤ ሕጉ የደበቀውን የመለኪያ ሜትር አውጥቶ ለማሳያ የቆመችው ሴት ደረት ድረስ ዘርግቶ ለካው። ሮይ መሳሪያውን በትከሻው ትይዩ ፊት ለፊት ሲይዘው ማርሊን በተመታችበት አቅጣጫ ፊት ለፊት እንደሚመጣ ዐቃቤ ሕጉ ገለፀ።

በመጨረሻ ሮይ የተከሳሽ ቦታውን ሲይዝ ዐቃቤ ሕጉ ይህ መሳሪያ ሲተኰስ ቀለሀው ከጐን ነው፤ ሆኖም ግን እንዴት ኪስህ በኋላ ሊገኝ ቻለ? ሮይ አንሰቼ ከተቼው ይሆናል ሲል መለሰ። ዐቃቤ ሕግ ሁለት የቅርብ ጓደኞችህ ከፊት ለፊትህ አስክሬናቸው ተጋድሞ አንተ ቀለሀ እንኳን የምታነሳበትን ቀልብህን አልዘነጋህም? ሮይ መልስ አልሰጠም። በዝምታ የተከሳሽ መቆሚያውን ለቆ ወጣና ችሎቱ ለእረፍት ተነሳ።

ሮይ ማርቲንና ማርሊንን በመግደሉ ጥፋተኛ ነው አይደለም ውሳኔው ያንተ ነው።

እውነተኛው ዳኝነት ይህን እውነተኛ የወንጀል ክስ የሰሙት ጁሪዎቹ ሮይ በሁለቱም ግድያዎች በሁለተኛ ደረጃ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ ነው ሲል ወሰነ። የተወሰኑት የጁሪው አባላት ተከሳሹ በመጀመሪያ ደረጃ የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ እንዲሆን ተሟግተው የነበረ ቢሆንም በሁለተኛ ደረጃ ጥፋተኛ ይሁን በሚለው ተስማምተዋል። በመጨረሻም ለሁለቱም ግድያ ተከሳሹ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል።

ምንጭ፤ ዳኛው አንተ ብትሆን 20 እውነተኛ የወንጀል የክስ ሂደቶች በሚል እርዕስ በዳኛ ኖርበት አህንፋረንድ በ2000 ዓ.ም የታተመው መፅሐፉ ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
9051 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1090 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us