ቅጣትን የሚያስቀሩ ወይም የሚቀንሱ ዕድሎች

Wednesday, 26 February 2014 12:47

ኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ወንጀለኞች ለምን ይቀጣሉ?

ለበቀል፣ ከወንጀል ለመከላከል፣ ለማረም፣ የወንጀል ሕጋችን የትኛውን ዓላማ ይከተላል

-    የወንጀል ቅጣቶችን የሚያስቀሩ ሕጋዊ አማራጭ

 1. ይቅርታ እንዴትና በማን ይሰጣል?
 2. ምህረት ከይቅርታ በምን ይለያል?
 3. ቅጣትን መገደብ የሚቻለው ለየትኞቹ ጥፋቶች ነው?
 4. አመክሮ መቼና እንዴት?
 5. በወንጀል የታጣ ስምን የሚያስመልሰው መሰየም በምን ሁኔታና እንዴት ይገኛል?

አስገራሚው በማሰር ሳይሆን በማሳፈር መቅጣት

የወንጀል ቅጣት የተለያዩ ዓላማዎች አሉት። ዓላማዎቹን ማሳካት መቻሉ ብቻ ሳይሆን ቅጣቱን ለማስፈፀም የሚያስከትለው ወጪም መታሰብ አለበት። የእስር ቅጣት ከወጪ አንፃር ውድ ነው። ወጪ ቆጣቢ ከሚባሉት ቅጣቶች መሀከል (እንዲያውም ገቢ የሚያስገኘው) የገንዘብ መቀጮና የማሳፈር ቅጣት ይጠቀሳሉ። የማሳፈር ቅጣት ጥፋተኛው የሰራውን የሚያሳፍር ቅጣት በመጥቀስ በሚሰማው የእፍረት ስሜት እራሱም ሆነ ሌላ ሰው ያንን ጥፋት እንዳይደግሙ ማስተማሪያ ነው። በአሜሪካን ውስጥ የማሳፈር ቅጣቶች በዚህ መልኩ ይፈፀማሉ።

-    የሱቅ እቃ የሚሰርቁ ቀበኞች ከመደብሩ በር ላይ እቃ ሳነሳ የተያዝኩኝ ሌባ ነኝ የሚል መልዕክት ያለው ልብስ ለብሰው እንዲቆሙ በማድረግ ተቀጥተዋል።

-    ቦርሳ ነጥቀው የሚሮጡ መንታፊዎች ደግሞ እየተንቋቋ የሚረብሽ ጫማ አድርገው በአደባባይ እንዲዘዋወሩ በማድረግ ተቀጥተዋል።

-    ሰክረው ሲያሽከረክሩ የተያዙ አሽከርካሪዎች ደግሞ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ መያዛቸውን የሚገልፅ ልዩ የተሽከርካሪ ታርጋ በመቀጮነት ለጥፈው እንዲያሽከክሩ ተደርገዋል።

-    በወሲባዊ ጥቃት ወንጀል የተፈረደባቸው ጥፋተኞች ደግሞ ለጥፋታቸው መቀጣጫነት ፊት ለፊት ደረታቸው ላይ ከህፃናት እንዲርቁ (ህፃናት በማይደርሱበት ቦታ ይቀመጡ) የሚል ማስጠንቀቂያ እንዲለጥፍ ፍ/ቤቱ አዟቸዋል።

-    ደረጃውን ንፅህናውን ያልጠበቀ ቤት የሚያከራይ የቤት ባለቤት ደግሞ ለጥፋቱ በአይጥ መንጋ ከተወረሩ ተልካሻ ቤቶቹ በአንዱ ውስጥ እንዲኖር ተፈርዶበታል።

-    በ1980ዎቹ ጉዳት ሳያደርሱ ቤት ዘራፊዎች በጥፋታቸው ሲፈረድባቸው ቅጣቱን እንዲመርጡ እድል ይሰጣቸዋል። ምርጫው በማፈር ወይ በመታሰር መቀጣት ነው። ከእስሩ ማፈሩ ይሻለኛል ያለ ሰው በአካባቢው በሚሰራጨው ጋዜጣ ላይ ሙሉ ገፅ የማስታወቂያ ወጪውን ሸፍኖ ምስሉ፣ የፈፀመው ወንጀል እና ማኅበረሰቡን የጠየቀው ይቅርታ ታትሞ እንዲገለፅ ይደረጋል። በወቅቱ ይህ የቅጣት አማራጭ የቀረበላቸው አብዛኞቹ ጥፋተኞች ከማፈር ይልቅ መታሰርን ይመርጡ ነበር።

ይህን የቅጣት አማራጭ በተለይም ደገሞ በሀብታሞችና ከፍተኛ የስራና የኃላፊነት መደብ ላይ ለሚገኙ ጥፋተኞች ፍቱን እንደሆነ The Economics of Crime በሚል እርእስ በሀሮልድ ዊንተር በተባሉት ፀሐፊ ተፅፎ በ2000 ዓ.ም በታተመው መፅሐፍ ላይ ተጠቅሷል።

በሀገራችን ሕግ ይህ በማሳፈር ጥፋተኞችን የመቅጣት ዘዴ የለም። ስለሌለም ነው ገርሞኝ እንደማዋዣ ያነሳሁት። ዛሬ የምንዳስሰው የወንጀል የእስር ቅጣት ጋር በተያያዘ የቅጣቱን መጠን የሚቀንሱ ወይም ቅጣቱን የሚያስቀሩ በሕጐቻችን የተፈቀዱ ሁኔታዎችን ነው። አመክሮ፣ ቅጣትን መገደብ፣ ምህረት፣ ይቅርታ፣ መሰየም የሚባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው እንዴትስ ሊፈቀዱ ይችላሉ የሚለውን እናያለን። በቅድሚያ የወንጀል ቅጣትን ዓላማ እንመልከት።

ወንጀለኞች ለምን ይቀጣሉ?

ማንኛውንም ማኅበረሰብ ከሚገጥሙት ዋነኛ ፈተናዎች አንዱ የኅብረተሰቡን ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅ ሰዎች በስራ ላይ ያሉትን ሕጐች ማክበራቸውን ማረጋገጥ ነው። ይህ በከፊል ስኬታማ የሚሆነው ቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ መምህራን፣ የመገናኛ ብዙሀን የሃይማኖት ተቋማት በሚያሳድሩት አዎንታዊ ተፅዕኖ ነው። ሌላው ደግሞ እጅግ ውጤታማ የሆነው ሰዎች ሕጐችን እንዲያከብሩ የማድረጊያው መንገድ በወንጀለ ቅጣቶች ሕግ መጣስ የሚያስከትለውን ኃላፊነት በማሳየት ማስጠንቀቅ መሆኑን በወንጀል ሕግ ዙሪያ ተፃፈው ድርሳናት ያሰምሩበታል።

በርግጥ ሕጐችን መጣስ ሁሉ ወንጀል አይደለም። ወንጀል ናቸው ተብለው በወንጀል ሕግ ወይም በሌሎች ሕጐች የተደነገጉ ካልሆኑ የተጣሱት ሕጐች የሚያስከትሉት የፍትሐብሔር ኃላፊነት ነው። በመሆኑም በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 2 ላይ እንደተደነገገው አንድ ድርጊት ወንጀል ለመባል በሕጉ ላይ ወንጀልነቱ እና የሚያስከትለው ቅጣት መደንገግ አለበት። ፍ/ቤቶችም የወንጀል ቅጣት ሊያስተላልፉ የሚችሉት በሕጉ ላይ ወንጀል ተብሎ በግልፅ በተደነገገ ድርጊት ላይ ብቻ ነው። ይህን የወንጀል ድርጊት ተከትሎ በፍ/ቤት የሚጠራው ቅጣትም የተለያዩ ዓላማዎች አሉት። እነኚህ ዓላማዎችን ለማሳካት ሁለት ዓይነት አበይት አካሄዶችን የየሀገራቱ የሕግ ስርዓቶች ይከተላሉ።

የመጀመሪያው አካሄድ የቅጣት አላማው ጥፋተኛውን በመርዳት ከጥፋቱ እንዲመለስና ጤናማ ህይወት እንዲመራ ማስቻል የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው አካሄድ ደግሞ ወንጀለኞችን ከማኅበረሰቡ መሀል በማስወገድ የኅብረተሰቡን ደህንነት ማስጠበቅ ነው።

ከዚህ አንፃር የተለያዩ የወንጀል ቅጣት ንድፈ ሀሳቦች የወንጀል ቅጣት ዓላማን በተመለከተ ለዘመናት በዓለማችን የሕግ ስርዓቶች ላይ ሲንፀባረቁ ከርመዋል። ወንጀለኞች ለምን ይቀጣሉ ስንል የተለያዩ የየዘመናቱ ሊቃወንት የሚደግፏቸውን ወይም የሚቃወሟቸውን ንድፈ ሀሳቦች የያዙ እነኚህን ምክንያቶች እናገኛለን።

1. የአፀፋ ብቀላ (Retribution)

የወንጀል ቅጣት ዓላማው አጥፊውን በመበቀል የእጅን እንዲያገኝ ማድረግ መሆን አለበት ይላሉ። የዚህ ዓላማ ደጋፊዎች ወንጀለኞች እንደየ ወንጀላቸው ከባድነት የሚገባቸውን ተገቢ ቅጣት ማግኘት አለባቸው። የዚህ የብቀላ ፍልስፍና መነሻው የሃይማኖት መፅሐፍት ዓይን ያጠፋ አይኑን ጥርስ ያወለቀ ጥርሱን ብለው የሚያስቀምጡት ጥንታዊ የቅጣት ወርሆች ናቸው። የብቀላ ንድፈ ሀሳብ የሚነሳው አጥፊዎች የሚያደርጉት ነገር ትክክል ወይም ስህተት መሆኑን ለይተው ስለሚያውቁ የሚያስከትለውን ኃላፊነትም መቀበል አለባቸው ከሚል እሳቤ ነው። በዘመናዊው የሕግ ስርዓትም ይሄን እሳቤ የሚከተሉ ቢኖሩም፤ ጥፋተኛው ያደረገውን ማድረግ በሚለው ግን አይስማሙም እንዲህ ከሆነ አስገድዶ የደፈረ ምን ሊደረግ ነው። ስለዚህ ቅጣቱ ከጥፋቱ ጋር ተመሳሳይ ባይሆንም፤ በዘመናዊ የእስር እና የገንዘብ ቅጣቶች ተመጣጣኝ ሊሆን በሚችል መልኩ መፈፀም አለበት ይላሉ። በነገራችን ላይ የእኛ የወንጀል ሕግ ይህን የብቀላ ንድፈ ሀሳብ አይከተልም።

2. ወንጀል ከመፈፀም እንዲርቁ ማድረግ (Deterrence)

በማራቅ ወይም በመከልከል ንድፈ ሀሳቦች ሁለት ዓይነት ዓላማ አላቸው። የመጀመሪያው ዓላማ መከልከል ወይም ማራቅ ሲሆን ይህም ወንጀለኛው ላይ በሚጣለው ቅጣት ለወደፊቱ ሌላ ወንጀል እንዳይፈፀም ማድረግ ነው። ተቺዎች ተደጋጋሚ ወንጀለኞች ቁጥር መኖር የወንጀል ቅጣት አጥፊዎች ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ የማድረግ አቅሙ እምብዛም መሆኑን ያሳያል ሲሉ ያሰምሩበታል። ሌላው ችግር ደግሞ ይህን ግለሰቦች ወደ ወንጀል ህይወት አንዳይመለሱ ማድረግ የሚያስችለውን የቅጣት መጠን ምን ያህል ነው የሚለው በቁርጥ ማወቅ አለመቻሉ ነው። ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ አጠቃላይ መከልከያ ወይም ማራቂያ ሲሆን፤ አንድ ወንጀለኛ ሲቀጣ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል እሱን ምሳሌ በማድረግ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠብ ማድረግ ነው። የዚህ ንድፈ ሀሳብ ተቺዎች ኅብረተሰቡ ሌሎች ላይ ስለሚጣለው ቅጣት ትኩረት አይሰጥም ወይም እውቀቱ የለውም በመሆኑም ከፍተኛ ቅጣቶች እንኳን አጠቃላዩ ኅብረተሰብ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስተላልፉት ትምህርት አነስተኛ ነው ይላሉ። ደጋፊዎች ደግሞ ፈጣንና እርግጠኛ የሆነ የወንጀል ቅጣት ትልቅ መልዕክት በማስተላለፍ ሌሎች ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ የማድረግ አቅም አለው ብለው ይሟገታሉ። ኅብረተሰቡን ለማስተማር ሲባል ግለሰቦች ላይ ከወንጀሉ ጋር የማይመጣጠን አስከፊ ቅጣት እንዳይጣልም ትኩረት መስጠት አለበት የሚል መከራከሪያም ይነሳል። የእኛ የወንጀል ሕግ በመግቢያው ላይ ካስቀመጣቸው ይህን ንድፈ ሀሳብ እንደሚከተል “ስለ ወንጀሎችና ቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ….” ከሚሉት ሀረጋት መረዳት ይቻላል።

3. ወንጀለኛው እንዲመለስ መርዳት (Rehabilitation)

ይህ ንድፈ ሀሳብ ሀሳባዊ በሆነው ሰዎች በመሠረቱ መልካሞች በመሆናቸው ከተበረታቱና ድጋፍ ከተሰጣቸው ህይወታቸውን ወደ ትክክለኛው ጐዳና መመለስ ይችላሉ በሚለው እሳቤ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ በአሜሪካን ሀገርም በቀደመው ጊዜ የወንጀል ቅጣት አላማው አጥፊው እንዲሻሻልና እንዲመለስ ከማድረግ ሕግ አክባሪና አምራች የኅብረተሰቡ አባል እንዲሆን ማድረግ እንደነበር ማቴው ሊፕማን Contemporary Criminal Law በሚለው የወቅቱን የአሜሪካንን የወንጀል ሕግ በሚተነትን መፅሐፋቸው ላይ ገልፀዋል። ሆኖም ግን በሀገሪቱ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚሰጡ የትምህርትና የሙያ ትምህርት መርሀ ግብሮች አጥፊዎችን የመመለስ አቅማቸው አጠራጣሪ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በአግባቡ ስላልተተገበረ እንጂ አጥፊዎች ተገቢውን ምክር ከትትልና ትምህርት ካገኙ ይመለሳሉ ይላሉ።

4. ወንጀል መፈፀም እንዳይችል ማድረግ (Incapacitation)

ይህ ንድፈ ሀሳብ ወንጀለኞችን ከማኅበረሰቡ በማስወገድ ሌሎችን የሚያወክ ተግባር እንዳይፈፅሙ በማገድ ላይ ያተኰረ ነው። ንድፈ ሀሳቡ የወንጀል ዝንባሌ ያላቸውና ሊታረሙ ወይም ከቅጣታቸው ሊማሩ የማይችሉ ወንጀለኞች አሉ የሚለውን ድምዳሜ ይቀበላል። የዚህ ድምዳሜ ችግሩ ግለሰቦች በርግጥም በቀጣይነት ለማኅበረሰቡ አደገኛ መሆኑን ወይም ታርሞ የሚመለስ መሆኑን አስረግጦ መናገር የሚቻልበት ዘዴ አለመኖሩ ነው። በዚህም የተነሳ አንድን ግለሰብ ወንጀል እንዳይፈፅም ለማድረግ በሚል የተሳሳተ ግምት ላይ በመመስረት ወደፊት ያደርጋል ወይም ሊያደርግ ይችላል የሚለውን ለመገመት ያለፈው ጥፋቱ በመነሻነት ሊወሰድ ይችላል። መርጦ መገደብ የሚባለው ደግሞ የተለዩ ወንጀሎችን የፈፀሙ አጥፊዎችን በመለየት የተራዘመ የእስር ቅጣት እንዲፈፀምበት ማድረግ ነው። በበርካታ የአሜሪካን ግዛቶች በአደንዛዥ ዕፅ ወይም በሁለተኛ ደረጃ ከባድ ወንጀል ሦስት ጊዜ የተቀጣ ሰው በሦስተኛው ሕግ ሊያርመው ስላልቻለ እረጅም ዘመን ወይም የእድሜ ልክ እስር ቅጣት ይፈረድበታል። ይህ አይነት ቅጣት መጣል ያለበት ለየትኞቹ የወንጀል አየነቶች ነው የሚለው ግን አከራካሪ መሆኑን ማቲው ሊፕማን ጠቅሰዋል።

በሀገራችንም የወንጀል ሕጉ አላማና ግብ በተቀመጠበት አንቀፅ አንድ ላይ ወንጀለኛውም ሆነ ኅብረተሰቡ ከቅጣቱ እንዲማር ከማድረግ በተጨማሪ “… ወንጀለኞች ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እርምጃዎች እንዲወስዱባቸው በማድረግ ነው” በማለት ይህን በቅጣት ወንጀለኛው ሌላ ጥፋት መፈፀም እንዳይችል የማድረግን ንድፈ ሀሳብም እንደሚከተል አስቀምጦታል። በሀገራችን የወንጀል ሕግ ላይ በተወሰኑ አደገኛ ወንጀሎች ላይ የሚጣሉ እረጅም የእስር ቅጣት፣ የእድሜ ልክ የአስር ቅጣትና የሞት ቅጣትም ይህንን የቅጣት ንድፈ ሀሳብ መሰረት ያደረጉ ናቸው።

5. ያጠፉትን መካስ (Restoration)

ይህ ንድፈ ሀሳብ በዳዮች ተበዳዮች ላይ የደረሰውን ጉዳት የመካስም የበደሉትን ማኅበረሰብ እንዲያገለግሉ መደረግ አለባቸው በሚለው ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ የመካስ ፍትህን የመስጠት አቀራረብ በወንጀል የፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ተበዳዮች ይዘረጋሉ። በመሆኑም አጥፊዎች ለጥፋታቸው ግላዊ ኃላፊነት እንዲሰማቸውና አባል ለሆኑበት ማኅበረሰብ ኃላፊነት እንዲኖራቸው ለማድረግ መካስ አለባቸው ይላል። ይህ ንድፈ ሀሳብ በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 101 እና 102 ላይ ወንጀለኛው ተበዳዩ ላይ ላደረሰው ጉዳት እንዲክስ ሊወሰን የሚችልባቸውን አማራጮች በማስቀመጡ ተቀብሎታል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም በእስር በሚቀጣበት ጊዜ በወንጀለ ሕግ አንቀጽ 104 ላይ የግዴታ ስራ እንዲሰራ እና ከሚያገኘው ገቢ የተወሰነው እጅ ለመንግስት ተቀንሶ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ የጐዳውን ማኅበረተሰብ እንዲክስ የሚደረግበት አማራጭ ተቀምጧል።

እንግዲህ የወንጀል ቅጣቶች አላማቸው ከላይ በዘረዘርኳቸው ንድፈ ሀሳቦች ሲሆኑ ከብቀላ በስተቀር ሌሎቹ የቅጣት አላማዎች በሀገራችን የወንጀል ሕግም ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። እነኚህን ዓላማ በማድረግ የሚጣሉ ቅጣቶች ሊቀነሱ ወይም ቀሪ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን መንገዶች ደግሞ በቀጣይነት እንመለከታለን።

ሀ. ይቅርታ

ይቅርታ በሕጋችን እውቅና የተሰጠውና በፍርድ የተወሰነ ቅጣትን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊያስቀር ወይም አይነቱ አነስተኛ በሆነ ቅጣት እንዲለወጥ ሊያደርግ የሚችል አሰራር ነው። በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 229 ይቅርታ ሊሰጥ የሚችልበት አግባብና ገደብ በሕግ እንደሚወሰን የደነገገ ሲሆን፤ በአዋጅ ቁጥር 395/96 ደግሞ የይቅርታ ስነስርዓት አዋጅ ወጥቷል። በሕገመንግስታችን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀልና ኢሰብአዊ የሆነ ሰዎችን የማሰቃየት ተግባር በይቅርታ ወይም በምህረት እንደማይታለፍ ተደንግጓል። የይቅርታ አላማው በአዋጁ አንቀፅ 11 ላይ የሕዝብን ደህንነትና ጥቅም ማስከበር መሆኑ ተደንግጓል። በመሆኑም የይቅርታ ጥያቄው ተቀባይነት የሚያገኘው የሕዝብን ደህንነትና ጥቅም የማይጐዳ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው።

የይቅርታ ጥያቄ አንድ ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን የቅጣቱ አፈፃፀምና አየነት በቀላል ሁኔታ እንዲፈፀም የሚቀርብ ሲሆን፤ በተቀጪው በባለቤቱ በቅርብ ዘመዶች በወኪሉ ወይም በጠበቃው አማካኝነት ወይም ደግሞ በማረሚያ ቤቶች ኰሚሽን በኩል ሊቀርብ ይችላል። ይቅርታውን የጠየቀው ማረሚያ ቤት ኰሚሽን ከሆነ ተቀጪው በ15 ቀን ውስጥ ይቅርታውን የማይፈልግ ከሆነ በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት። ከአቅም በላይ ችግር ካላጋጠመው በስተቀር ዝም ማለቱ ይቅርታውን እንደተቀበለ ያስቆጥረዋል።

በአዋጁ የተቋቋመው የይቅርታ ቦርድ የይቅርታ ጥያቄዎችን መርምሮ ይቅርታው በቅድመ ሁኔታ ወይም ያለ ቅድመ ሁኔታ ቅጣቱ በሙሉ በከፊል ወይም በቀላል መንገድ መፈፀም እንዳለበት ለፕሬዝዳንቱ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል። በአዋጅ አንቀፅ 10 የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በቦርዱ የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ወይም በራሱ ምክንያት ይቅርታ መስጠት ወይም የመከልከል ስልጣን ያለው ሲሆን፤ በቅድመ ሁኔታ ይቅርታ ተደርጐላቸው ቅድመ ሁኔታውን ያላሟሉትን ደግሞ በቦርዱ የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ይቅርታውን የመሰረዝ ስልጣን አለው።

ለ. ምህረት

በወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 230 መሠረት በሕግ ምህረት እንደማይሰጥባቸው ካልተደነገጉ በስተቀር በጅምላ ለአንድ ዓይነት ወንጀሎች ወይም በተመሳሳይ ደረጃ ለሚገኙ ወንጀሎች በገደብ ወይም ያለምንም ገደብ አግባብ ባለው አካል ጠቅላላ ምህረት ሊሰጥ ይችላል። ይቅርታ ግለሰባዊና ከቅጣት ውሳኔ በኋላ በተቀጪው ፍላጐትና ፍቃድ የሚጠየቅ ሲሆን፤ ምህረት በጥያቄ የሚሰጥ ካለመሆኑም በተጨማሪ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በአጠቃላይ የሚሰጥ ነው። በተጨማሪም ከነጭራሹ የወንጀል ክስ እንዳይጀመር የተጀመረውም እንዳይቀጥል ቅጣት ተወስኖ ከሆነም ቅጣቱ የሚያስከትለው የወንጀል ውጤት እንዳልነበረ ተቆጥሮ ከወንጀለኞች መዝገብ ላይ እንዲሰረዝ ያደርጋል። ይቅርታ ግን ቅጣትን ሊያስቀር ሊያስቀንስ ወይም በአነስተኛ መልኩ ሊለወጥ የሚችል ቢሆንም፤ ከምህረት በተቃራኒ በወ/ሕ/አንቀጽ 229(2) ላይ በተቀጪው ላይ የተወሰነው ፍርድና ውጤቱ በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ የሚኖር ነው። ይቅርታና ምህረት ለተበዳዩ በፍትሐብሔር ሊከፈል የሚችለውን ካሳ የማያስቀሩ ሲሆኑ፤ ተቃራኒ ትዕዛዝ ካልተሰጠ በስተቀር ለመንግስት የሚከፈል ኪሳራ በይቅርታ ወይም በምህረት ቀሪ ይሆናል።

ሐ. ቅጣትን መገደብ

በወንጀል ሕግ አንቀፅ 190 ፍ/ቤቶች ለጥፋቱ መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች የተወሰነውን ቅጣት መገደቡ ወንጀለኛውን ፀባዩን ለማረምና ወደ መደበኛ ኑሮው ለመመለስ ጠቃሚ መሆኑን ካረጋገጡ ቅጣቶችን በሁለት መልኩ ሊገድቡ ይችላሉ። የመጀመሪያው በመቀጮ፣ በግዴታ ስራ ወይም ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ለሚያስቀጡ ጥፋቶች ፍ/ቤቱ የወንጀለኛውን ጥፋተኝነት ካረጋገጠ በኋላ ወደፊት ሊታረም የሚችል እምነት ሊጣልበት የሚችል ሆኖ ሲያገኘው ቅጣት ከመወሰኑ በፊት የተወሰነ የመፈተኛ ጊዜ ይሰጠዋል። ፈተናው ፍ/ቤቱ እንደገመተው መልካም ውጤት ካስገኘ በወ/ሕ/አ 191 መሠረት ፍርዱ እንዳልነበረ ይቆጠራል።

ሁለተኛው የገደብ አየነት ደግሞ በወ/ሕ/አ 192 መሠረት ፍ/ቤቱ ቅጣቱን ከወሰነ በኋላ ለወንጀለኛው ፀባይ መሻሻል አንድ ፅኑ ማስጠንቀቂያ ብቻ በቂ መሆኑን ሲያምንበት ቅጣቱን ከመፈፀም ለተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ ማዘዝ ይችላል። የተወሰነው የፈተና ጊዜ ውጤታማ ከሆነ የተወሰነው ቅጣት አይፈፀምም ሆኖም ፍርዱና ውጤቱ በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ይኖራል።

ሆኖም ግን ሁሉም ወንጀለኞች ቅጣት ሊገደብላቸው አይችልም። በወ/ሕ/አ 194 ተደጋጋሚ ወንጀለኞች አስቀድሞ በፅኑ እስራት ወይም ከሦስት ዓመት በሚበልጥ ቀላል እስራቸው ከተቀጡና አሁን በተከሰሱበትም ከእነዚህ ቅጣቶች አንዱ የሚወስንባቸው ከሆነ ቅጣቱ ሊገደብ አይችልም። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ባይቀጡም በተከሰሱበት ወንጀል ከአምስት ዓመት የበለጠ ፅኑ እስራት የሚያስፈርድበት ከሆነ ቅጣቱ አይታገድም። ቅጣቱ ከመታገዱ በፊት ሌላ ከላይ የተጠቀሰውን ቅጣት የሚያስከትል ወንጀል መፈፀሙ ከተደረሰበት፣ ከታገደለትም በኋላ አስቦ አንድ ወንጀል ከፈፀመ፣ ፍ/ቤቱ የሰጠው የፈተና ጊዜ መልካም ውጤት እንደማያስገኝ ፍ/ቤቱ ከተረዳው ቅጣቱን አያግድም። ከሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች በተጨማሪ ቅጣት ተገድቦ የሚሰጠው የፈተና ጊዜ ከሁለት ዓመት ያነሰ ወይም ከአምስት ዓመት የበለጠ መሆን የለበትም።

መ. በአመክሮ መፈታት

በአመክሮ መፈታት ማለት ተቀጪው የተወሰነበትን ቅጣት ቢያንስ ሦስት ሁለተኛውን ካጠናቀቀ በኋላ የተቀጩውን ፀባይ ማሻሻያና ወደ መደበኛ ኑሮው መመለሻ ይሆነዋል ተብሎ ሲታሰብ የተወሰነበትን የእስር ዘመን በሙሉ ሳያጠናቅቅ ሊፈታበት የሚችልበት አሰራር ነው።

የአመክሮ ጥያቄ የእድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው ሃያ ዓመት ከታሰረ በኋላ ነው ሊያቀርበው የሚችለው። ጥያቄውን እራሱ ተቀጪው ወይም የሚመለከተው አካል ሊያቀርበው ይችላል። ጥያቄው የቀረበለት ፍ/ቤትም በወ/ሕ/አ 202 መሠረት በእስር ላይ እያለ የተረጋገጠ የጠባይ መሻሻል ማሳየቱን፣ ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን ካሳ መክፈሉን ሲያረጋግጥ አመሉና ፀባዩ በአመክሮ ሲፈታ መልካም ውጤት ያስገኛል ብሎ ሲያምን እስረኛው በአመክሮ እንዲፈታ ይወስናል። ጥፋተኞች ሲታሰሩ የአመክሮ እድል ተጠቃሚ የሚያገኙት ምን ሁኔታዎችን ሲያሟሉ እንደሆነ የሚታሰሩበት ተቋመ የማሳወቅ ግዴታ በወ/ሕ/አ 203 ላይ ተጥሎበታል። አመክሮውም መፈታት የፈተና ጊዜ ነው ቀሪውን የእስራት ዘመኑን ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ጊዜ የእድሜ ልክ እስር ሲሆን ደግሞ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት እስረኛው ከእስር ተለቆ ይፈተናል። የተወሰነለትን የጠባይ ደንብ ከጣሰ ወይመ አዲስ ወንጀል ከፈፀመ በተሰጠው የሙከራ እድል መጠቀም ባለመቻሉ በወ/ሕ/አ 206 መሠረት አመክሮው ተሽሮ ቀሪ ቅጣቱን ይፈፅማል። አዲስ ወንጀል የፈፀመ በአመክሮ ላይ ያለ ሰው የደጋጋሚነት ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በአመክሮ የተቀነሰለት ቅጣትና የአዲሱ ወንጀል ቅጣት ተደርቦ ይፈፀምበታል።

ሠ. መሠየም

መሠየም ማለት የተወሰነበትን ቅጣት የፈፀመ ቅጣቱ በይርጋ በይቅርታ የቀረለት፣ በአመክሮ ወይም በገደብ የታገደለት ማንኛውም ሰው በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ከቅጣቱ በፊት የነበረው ስም እንዲመለስና ፍርዱ አንዲሰረዝለት በወ/ሕ/አ 232 መሠረት የሚጠይቅበት ስርዓት ነው። ሕጉ መሠየም የሚገኘው በመልካም ስራ እንጂ እንደ መብት ይገባኛል የሚባል አለመሆኑን ደንግጓል። ተቀጪው ከሞተ ወይም ችሎታ ካጣ የቅርብ ዘመዶቹ ወይም ወኪሉ ጥያቄውን ሊያቀርብ ይችላል።

መሰየም የሚፈቀደው ቅጣቱ ካለቀበት ወይም ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ አምስት ዓመት ወይም በሌላ ቀላል ሁኔታዎች የሁለት ዓመት ጊዜ ካለፈ በኋላ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ፀባዩ መልካም ከሆነና ወንጀል ካልፈፀመ እንዲሁም አቅሙና ሁኔታው በሚፈቅድለት መልኩ በፍርድ የተወሰነበትን ወይም ሊከፈል ይገባዋል ተብሎ የሚገመትበትን ካሳ፣ የዳኝነትና ማናቸውንም ኪሳራ ከከፈለ ቅጣቱ በይርጋ የታገደለት ሰው ደግሞ ቅጣቱ ቢፈፀም ከሚጠናቀቅበት ጊዜ በፊት ልዩ ወይም የሚያስመሰግን ወታደራዊ ወይም ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ካላበረከተ በቀር መሰየም ሊፈቀድለት አይችልም።

መሠየም በቅጣት የቀረ የመብት፣ የማዕረግ ወይም ችሎታ ማጣት ቀሪ ሆኖ ህዝባዊና የቤተሰብ የማስተዳደር የሙያ ስራ የመስራት መብቱን እንደገና እንዲያገኝ እንደሚያደርገው በወ/ሕ/አ 235 ላይ ተደንግጓል። በተጨማሪም ፍርዱ ከወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተሰርዞ ወደፊትም እንዳልተፈረደበት የሚቆጠር ሲሆን በጠላትነት ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ያለፈውን ጥፋት አንስቶ መወቀስ ወቃሹን በስም ማጥፋት በወንጀል ያስቀጣል። ለህዝብ ጥቅም የተደረገ ነው ብሎ መከራከሪያ ማቅረብም አይቻልም።

    ጥያቄው የሚቀርበው ፍ/ቤት ሲሆን፤ ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ካልተቀበለው ከሁለት ዓመት በፊት ድጋሚ የመሰየም ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም። በወ/ሕ/አ 237 መሠረት መሰየም ከተፈቀደ በአምስት ዓመት ጊዜ እንደገና በሞት ወይም በፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል የሰራና የተፈረደበት ሰው መሰየሙ ይሰርዝበታል። ዳግመኛም የመሰየም ጥያቄ ማቅረብ አይችልም።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
9093 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1006 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us