ስለመኖሪያ ቦታ እና አድራሻ ሕጋችን ምን ይላል?

Wednesday, 12 March 2014 12:22

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-         ለመሆኑ በሕግ የመኖሪያ ቦታችን እንደሆነ ተደርጎ የሚታወቀው ሥፍራ የቱ ነው?

-         አንድ ሰው በአንድ ቦታ ነዋሪ ነው ለመባል ምን ማሟላት አለበት?

-     የተለያዩ ሕጋዊ ተግባራትን ከመፈፀምና ከማሥፈፃም አንፃር የመኖሪያ ቦታችን

ምን ሚና አለው?

ሰላም እንዴት ናችሁ? ዛሬ የምናወራው ስለመኖሪያ ቦታና ስለአድራሻ ነው። ለመሆኑ አድራሻዎት የት ነው? ማንኛችንም ከስማችን ቀጥሎ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ አድራሻችንም አብሮ ይነሳል። ይህም የሚያሳየው ከኛነታችን ቀጥሎ መገኘትን የሚገልጽበት ቦታ ምንያህል ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ ነው።

የመኖሪያ ቦታ አንደ ሰው የሚገኝበትን ስፍራ መጠቆሚያ ማለት ነው። ለምሳሌ በዓለም ካርታ ሀገሮችን “በዚህ ዲግሪ ምእራብ፣ በዚህ ዲግሪ ሰሜን፣ በነዚህ አገሮች አዋሳኝነታቸው ወዘተ . . .” ብለን መገኛቸውን እንደምንገልጸው ሰዎችን ደግሞ በመኖሪያ ቦታቸው አድራሻ እንገልፃቸዋለን። ሰዎች መንቀሳቀስ የምንችል ተዘዋዋሪ ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን መገኛችን የመኖሪያ ቦታችን ሊሆን ከቦታው አንጻር ብቻ ሳይሆን የህይወታችን ማዕከል እንደሆን ይቆጠራል። የምናሳልፋቸው ዋና ዋና የማህበራዊ ህይወታችን ሒደቶችም ከመኖሪያ ቦታችን ጋር የተሳሰሩ ስለሆነ መኖሪያ ቦታችን በማህበረሰቡ ውስጥ የምንገኝበትን አቅጣጫ ይጠቁማል። በመሆኑም በዘመናዊው አለም ሰዎች በግለሰብ ደረጃም ሆነ ከአጠቃላዩ ማህበረሰብ ጋር በምናደረገው ግንኘነት ላይ የሚኖሩንን ባህሪያት ለመቆጣጠር የምናወጣቸው ዘመናዊ ህጎች የመኖሪያ ቦታንም ምንነት በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ የሚኖረውን ውጤት ይደነግጋሉ።

ወደሀገራችን ህጎች ስንመለስ በ1952 የወጣው የፍታብሔር ህጋችን ከአንቀፅ 174-191 ድረስ የመኖሪያ ቦታን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን በዝርዝር አስቀምጧል። መኖሪያ ቦታና መደበኛ ቦታ በሚል በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈሉ ቢሆኑም የህጎቹ ዋነኛ አላማ ግን ግለሰቦች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸውን አድራሻና ያላቸውን ውጤቶች በመግለፅ ላይ ያተኮረ ነው። ሶስት መሰረታዊ የሆኑትን ጉዳዮች በጥያቄ መልክ ያነሳል እንመልከታቸው።

ለመሆኑ የመኖሪያ ቦታ ምንድን ነው?

በፍታብሔር ህጋችን መሰረት በሁለት ክፍሎች ተቀምጧል። የመጀመሪያው የመኖሪያ ቦታን የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ክፍል መደበኛ ቦታን የተመለከተ ነው።

የመኖሪያ ቦታ፡- በፍ/ብ/ሕ/ቁ 174 መሰረት የአንድ ሰው የመኖሪያ ቦታ የሚባለው ለጊዜው የሚኖርበት ስፍራ ነው የሚል ትርጓሜ ተሰጥቷል። ሆኖም ግን ግለሰቡ የቆየበት ወይም የሰነበተበት ስፍራ ሁሉ መኖሪያ ቦታው ነው እንዳይባል ህጉ ገደብ አስቀምጧል። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 175 መሰረት ሰውዬው በቦታው መሰንበቱን የሚቀጥል ከሆነና ከሶስት ወር በላይ በቦታው ላይ ከቆየ ነው ያ ስፍራ ስንቀሳቀስ የምንቆይባቸው ቦታዎች ሁሉ መኖሪያ ቦታችን ሊባሉ አይችሉም።

ለምሳሌ ወደ አንድ ቀበሌ ሄዶ ለሁለት ወራት የቆየ ሰው እንደ ቀበሌው ነዋሪ ሊቆጠርና የነዋሪነት መታወቂያ ሊጠይቅ አይገባም። ነዋሪ ነው ለመባል በቀጣይነት ለመኖር ማሰብ ወይም ከሶስት ወር በላይ መቆየት አለበት።

መደበኛ ቦታ፡- የሚባለው ደግሞ አንድ ሰው ለመኖር በማሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቹን የመሰረተበት ቦታ ነው። አንቀፅ 183

ለምሳሌ፡- ቤተሰብ ገቢ የሚያስገኝበት መተዳደሪያ ስራና የመሳሰሉት ጥቅሞች።

አንድ ሰው የመኖሪያ ቦታ ከሌለውስ?

ከተለያየ የህይወት አጋጣሚዎች በተለያየ ምክንያት የመኖሪያ ቦታን መስፈርት ለሟሟላት ያህል እንኳን አንድ ቦታ የማይቀመጡ ወይም አድራሻ የላቸውም የምንላቸው ሰዎች አሉ፡፤ ለምሳሌ አንድ ሰው በአንድ ቦታ ከሶስት ወር በላይ የሚቆይ ከሆነና የመቆየት አዝማሚያ ከሌለው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 174 መሰረት የመኖሪያ ቦታ አለው ሊል አይችልም። በዚህ ጊዜ ሌላ የመኖሪያ ቦታ እንዳለው የሚያስረዳ ማስረጃ ካልቀረበ በቀር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 176 መሰረት የሚገኝበት ቦታ እንደመኖሪያ ቦታ ይቆጠርለታል።

ከአንድ በላይ መኖሪያ ቦታ ይፈቀዳል? አዎ አንድ ሰው ብዙ የመኖሪያ ቦታዎች ሊኖሩት ይችላሉ። በዚህ ጊዜ አንድ የመኖሪያ ቦታው ደንበኛ የመኖርያ ቦታው ሊባል ሌሎቹ ደግሞ ተጨማሪ የመኖሪየ ቦታዎች ሊባሉ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- አዲስ አበባም አዳማም ሁለት መኖሪያ ቤቶ ያሉት ሰውና በሁለቱም ውስጥ በዓመት ለስድስት ወር የሚኖር ሰው ሁለቱም መኖሪያ ቦታዎቹ ሆነው መደበኛ ተጨማሪ ሊባሉ ይችላሉ። (የፍ/ብ/ሕ/አንቀጽ 177 ያመለክታል) መደበኛ መኖሪያ ቦታን በተመለከተ ግን አንድ ሰው ከአንድ በላይ መደበኛ የመኖሪያ ቦታ ሊኖረው አይችልም።

የመኖሪያ ቦታን የሚወስኑ ሌሎች ሁኔታዎችስ ምንምን ናቸው?

ጋብቻ አንዱ ሊሆን በቀድሞው ዘመን ስራ ላይ በነበረው የፍ/ብ/ሕ/አ 189 መሰረት ያገባች ሴት የባሏ መደበኛ ቦታ የመደበኛ መኖሪያ ቦታዋ ነበር። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 54 መሰረት ተጋቢዎች የመኖሪያ ስፍራቸውን በጋራ ይወስናሉ፡፤ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት መደበኛ የመኖሪያ ቦታቸው የወላጆቻቸው ወይም የህጋዊ ሞግዚቶቻቸው መኖሪያ ቦታ ሲሆን ከዚህ የመኖሪያ ቦታ ውጭ ካለ ከወላጆቻቸው ፍቃድ ሊኖሩ አይችሉም። የመኖሪያ ስፍራቸውን ትተው ከሄዱም ሞግዚታቸው አልያም ወላጆቻቸው አስገድደው ሊመልሷቸው እንደሚችሉ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 254 ላይ ተደንግጓል።

የመንግስት ሰራተኞችን በተመለከተ የሚሰሩበት ስፍራ እንደመኖሪያ ቦታቸው ይቆጠራል። በፍ/ብ/ሕ/አ 179 መሠረት ነጋዴዎች ደግሞ የንግድ ስራቸውን የሚያከናውኑበት ቦታ እንደ አንደኛው መኖሪያ ቦታቸው እንደሚቆጠር አንቀፅ 180 ይደነግጋል። በተጨማሪም ተዋዋዮቹ በውል በተወሰነ ቦታን እንደ መኖሪ ቦታቸው እንዲቆጠሩ መስማማት ይችላሉ። እነኚህ ሁኔታዎች አንድ ሰው ከአንድ በላይ የመኖሪያ ስፍራ እንዲኖረው ያስችላሉ።

መደበኛ መኖሪያ ቦታ የሌለው ሰው በቋሚነት ለመኖር ንብረትና ሌሎች ማህበራዊ ጥቅሞቹን ያልመሰረተ ሰው መደበኛ መኖያ ቦታው ወይም ተጨማሪ የመኖሪያ ቦታ እንደ መደበኛ ቦታው ይቆጠራል።

መደበኛ የመኖሪያ ቦታው የግለሰቡ የስራ፣ የኢኮኖሚና የቤተዘመድ ጥቅሞቹን ወይም ግንኙነቱን ማእከል ያደረገ ሲሆን የግለሰቡ ማህበራዊ ኑሮና የሙያ ስራ የተለያዩ ቦታዎች ከተመሰረተ ማህበራዊ ኑሮው ያለበት ቦታ እንደመደበኛ ቦታ ይቆጠራል።

እንደ ምሳሌ ብንመለከት አቶ ከበደ በአዋሳ ከተማ ውስጥ አሳ ማስገሪያና መሸጫ አላቸው። የሚሰሩት እዛው ሲሆን እየተመላለሱ የሚኖሩት ደግሞ አዲስ አበባ ከሚኖሩት ቤተሰቦቻቸውጋር ነው። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 185 መሰረት መደበኛ መኖሪያ ቦታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚኖሩበት አዲስ አበባ ውስጥ ነው። አሁን ደግሞ መኖሪያ ቦታን የሚመለከቱትን ድንጋጌዎች ይህን ያህል ከቃኘን ከሕግ አንጻር የመኖሪያ ቦታ ተለይቶ መታወቅ ያለውን ጠቀሜታ እንመልከት።

የሰው ልጅ ተንቀሳቃሽ ፍጡር እንደመሆኑ የተለያዩ ግዴታዎችንና መብቶችን የሚፈጥር ህጋዊ ግንኙነቶችን ለመመስረት የመኖሪያ ቦታው ያለው ሚና በፍ/ብሔር ህግን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ላይ ተደንግጓል።

ለምሳሌ አንድ ሰው በመራጭነት ለመዘገብ የሚችለው ከስድስት ወር በላይ ነዋሪ በሆነበት የምርጫ ጣቢያ ነው። ነዋሪ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ ለመወሰን የመኖሪያ ቦታው የት እንደሆነ በሕጉ አግባብ መወሰን አለበት። በሌላ በኩል ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ለመፈፀም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 22 መሰረት ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ከወላጆቻቸው ወይም ለቅርብ ዘመዶቻቸው አንዱ ከስድስት ወራት በላይ ሳያቋርጥ በኖርበት ቦታ በሚገኘው የክብር መዝገብ ሹም ፊት መፈፀም አለበት።

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 826 መሰረት ደግሞ የሟች ውርስ የሚከፈተው የሟቹ ደምበኛ መኖሪያ በሆነው ቦታ ነው።

ለምሳሌ ሟች ከስድስት ወራት በላይ የኖረው በድሬደዋ ከተማ ቢሆንና ለስራ ወደ ባህር ዳር ሄዶ ለአራት ወራት ቆይቶ ቢሞት እንደ መደበኛ መኖርያ ስፋራው ተቆጥሮ ውርሱ የሚከፈተው በድሬደዋ ነው።

ውርስን በተመለከተ ደግሞ ተዋዋዮች ስራዋን በተመለከተ ውሉ ላይ ካልተስማሙ ከፍያው ሊፈፀም የሚገባው ውሉ በሚደረግበት ጊዜ ባለዕዳው ይኖርበት በነበረው መደበኛ ቦታው ላይ መሆኑን የው/በ/ሕ/ቀ 1755 (2) ይደነግጋል። በተለያዩ ጉዳዮች ተከራካሪ ወገኖች የፍ/ቤት መኖሪያ በሚያደርሱበት ጊዜ መኖሪያ የተላከለት ወገን መኖያው እንደደርሰው የሚቆጠረው መጥሪያው በደንበኛ መኖር ቦታው ላይ የተሰጠው እንደሆነ የፍ/ብ/ሥ/ሕ/ቁ 106 ይደነግጋል።

የመኖሪያ ቦታ የዳኝነት ሥልጣንንም ለመወሰን እንደሚጠቅም ከፍ/በ/መ/መ/ሕ ድንጋጌዎች መረዳት ይችላል። በአንቀፀ 19 መሠረት የፍ/ቤቶች በግዛት ክልል የሚወሰን የዳኝነት ሥልጣን አላቸው በመሆኑም በሕግ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር ማንኛውም ከስ መቅረብ የሚገባው ተከሳሽ በሚኖርበት የግል ጥቅሙን ስር በሚያከናውንበት ከልል በሚያስችለው ፍ/ቤት ነው።

ተከሳሽ ኢትዮጵያዊ ከሆነና የሚኖረው ወይም የግል ጥቅሙን ሥራ የሚያካሂደው ከኢትዮጵያ ውጭ ከሆነ ደግሞ ከሳሹ በማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት በሚገኝ የሥራ ነገር ሥልጣን ባለው ፍ/ቤት ጉዳዩን ማቅረብ የሚችል ሲሆን የክሱ መነሻ የማይንቀሳቀስ ንብረት ስሆን ክሱ መቅረብ ያለበት ንብረቱ በሚገኝበት ቦታ በሚያስችለው ፍ/ቤት መሆን እንዳለበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 20 ላይ ተደንግጓል።

ተከሳሹ የውጭ ሀገር ዜጋ በሚሆንበት ጊዜና የሚኖረውና ቋሚ ስራውን የሚሰራው በኢትዮጵያ ውስጥ ከሆነ ክሱ እዚሁ መቅረብ ሲችል ነገር ግን መኖሪያውና ስራው በውጭ ሀገር ከሆነ ከሱ እዚሐ ሊቀርብ የሚችለው የሚንቀሳቀስ ወይም የማየንቀሳቀስ ንብረቱ ባለበት ሥፍራ ነው።    

መንግስት ተከሳሽ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ከሳሹ ክሱን ማቅረብ የሚችለው ራሱ በሚኖርበት ወይም ቋሚ ስራውን በሚሰራበት ቦታ ላይ የስራ ነገር የመዳኘት ስልጣኑ ላለው ፍ/ቤት ወይም ሊከራከሩ መነሻ የሆነው ውል በተፈረመበት ወይም ውሉ ሊፈፀም በታቀደበት ክፍል ላስቻለው ፍ/ቤት ሲሆን የክሱ መነሻ የሆነው ጉዳይ ኃላፊነትን ያስከተለ ተግባር ተፈፅሞ ከሆነ ድርጊቱ በተፈፀመበት ቦታ በሚያስችለው ፍ/ቤት ክሱ ይቀርባል።

የንግድ ድርጅቶችን በሚመለከት ደግሞ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ወይም ቅርንጫፍ በሚገኝበት ቦታ ክሱ እንደሚቀርብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 22(1) ላይ ተደንግጓል።

                        ለዛሬ በዚህ ይብቃን

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
9065 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 947 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us