ሄፒታይተስ ቀዳሚው ገዳይ በሽታ ሆኗል

Wednesday, 20 July 2016 14:13

በተለምዶ የጉበት በሽታ እየተባለ የሚጠራው ሔፒታይተስ በሽታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዳይ ከሚባሉ በሽታዎች ተርታ እየተመደ ይገኛል። በሽታው የሚያሳያቸው ምልክቶች ወዲያው የማይታወቁ መሆናቸው ደግሞ በሽታው ስር እንዲሰድ የሚያደርገው ዋናው ምክንያት ነው። ሔፒታይተስ በሽታ በአሁኑ ወቅት በአለም ሀገራት ያለው ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከሰሞኑ የወጣ አንድ ጥናት አመልክቷል።

በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ እና በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በጋራ የተደረገውን ጥናት ውጤት ይፋ ያደረገው ላንሴት በሐምሌ ወር እትሙ ላይ ነው። ጥናቱ ከ1990 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ የሔፒታይተስ በሽታ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለበትን ሁኔታ የሚያመለክት ጥናት ሲሆን፤ የተካሄደውም ከ183 የአለም ሀገራት ነው። ጥናቱ እንዳመለከተውም በአሁኑ ወቅት ሔፒታይተስ ቢ በአለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች ግንባር ቀደም ሆኗል። በዚሁ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ብቻ በሔፒታይተስ በሽታ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ63 በመቶ ጫማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ይሄም ቁጥር በወባ፣ በቲቢ እና በኤች አይ ቪ ሳቢያ ከሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጋር ቁጥሩ ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በእነዚህ አመታት ውስጥ ከተከሰቱ የሞት አደጋዎች መካከል 96 በመቶዎቹ ከሔፒታይተስ ቢ እና ሲ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ሌላው የጥናቱ ውጤት ይፋ ያደረገው ነገር ቢኖር የሔፒታይተስ በሽታ ከአኗኗር ዘይቤ መሻሻል ጋር ተያይዞ መቀነስ አለመቻሉ ነው። በጥናቱ የተረጋገጠውም በዚህ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ዘንድ ነው።  ምንም እንኳን የሞት ክስተቱ በታዳጊ ሀገራትም ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም ከፍተኛው ጭማሪ የተስተዋለው ግን ጥሩ ገቢ ያላቸው ዜጎች ባሉባቸው ሀገራት ነው።

በ23 ዓመታት ውስጥ ብቻ በሔፒታይተስ በሽታ ምክንያት የተከሰተው የሞት ክስተት 63 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ጥናቱ በንፅፅር አስቀምጧል።በ1990 በቫይረስ በሚከሰት የሔፒታይተስ በሽታ የተመዘገበው ሞት 890ሺህ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በ2013 ወደ 1 ነጥብ 45 ሚሊዮን ከፍ ብሎ ተገኝቷል። ይህ ቁጥር በኤች አይ ቪ፣ በወባ እና በቲቢ ሳቢያ ከተከሰተው ሞት ጋር ሲነፃፀርም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በ2013 ብቻ 1ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በኤች አይ ቪ ኤድስ፣ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በቲቢ እንዲሁም 855ሺህ በወባ ምክንያት እንደተከሰቱም ጥናቱ አመልክቷል። በእያንዳንዷ ቀንም በዓለም አቀፍ ደረጃ 4ሺህ ሰዎች በዚህ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጣሉ። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ በሀገራችን ወደ አስር ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከሔፒታይተስ በሽታ ጋር የሚኖሩ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎችም እየተመዘገቡ ይገኛሉ።

የሔፒታይተስ በሽታ በቫይረስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። በሽታው በቫይረስ ኢንፌክሽን የሚፈጠር የጉበት ማበጥ ወይም መቆጣት (inflammation) ሲሆን፤ ድምፅ አልባ ገዳይ በሽታም ነው። የሔፒታይተስ በሽታ በጣም ከባድ በሽታ ሲሆን፤ ኢንፌክሽኑም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ግፋ ሲልም እስከ እድሜ ልክ ሊቆይ ይችላል። በኢንፌክሽኑም የመጣው የሔፒታይተስ በሽታም ጉበትን ለካንሰር የማጋለጥ እንዲሁም ጉበት ስራውን መስራት እንዲያቆም የማድረግ አደጋ አለው።

ለሔፒታይተስ ቫይረስ የሚያጋልጡ ነገሮች በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ማድረግና የመሳሰሉት ናቸው። በዚህ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ አካላትም ስለታማ ነገሮችን በጋራ የሚጠቀሙ፣ በመርፌ የሚወሰድ አደንዛዥ እፅ የሚጠቀሙ፣ ቫይረስ ካለበት እናት የሚወለዱ ህጻናት፣ ቫይረሱ ካለበት ሰው የደም ልገሳ የተደረገላቸው ሰዎች፣ የኩላሊት እና የስኳር ህመምተኞች እንዲሁም የጤና ባለሞያዎች ናቸው። በቫረሱ አማካይነት የሚከሰተው ሔፒታይተስ ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ ተብሎ የሚከፈል ነው። እነዚህ የሔፒታይተስ አይነቶችም በከፍተኛ ደረጃ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው። ሔፒታይተስ ቢ፣ ሲ፣ እና ዲ ከአንድ ሰው ወደ ሌላው የሚተላለፉት ከበሽተኛው ከሚወጡ ፈሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ሳቢያ ነው። ከበሽተኛው አፍንጫ፣ አፍ እና ሌሎች አካላት ከሚወጡ ፈሳሾች ጋር ንክኪ ያለው ሰው ለቫይረሱ የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሔፒታይተስ ኤ እና ኢ የተባሉት የሔፒታይተስ አይነቶች የሚከሰቱት እና የሚተላለፉት የተበከለ ምግብን በመመገብ እንዲሁም ንጽህናው ባልተጠበቀ ውሃን በመጠጣት እና ንጽህናው ይልተጠበቀ እቃ መመገብ ናቸው።

የሔፒታይተስ በሽታ ምልክቶቹ ቀደም ብለው መታየት ባለመቻላቸው የሚያደርሰው አደጋ እጅግ የከፋ ነው። በሽታው ያለባቸው ሰዎችም በበሽታው መያዛቸውን በጊዜ ስለማያውቁት ወደ ህክምና የሚሄዱትም በሽታው ከፀናባቸው እና ለመዳን አስቸጋሪ በሆነበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው። በአብዛኛው በዚህ በሽታ የተያዘ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶችም የሚከተሉት ናቸው። መድከም፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በተጨማሪም የሆድ ህመም፣ የሆድ መነፋት ወይም ማበጥ፣ የሰውነት ማሳከክና ሽፍ ማለት፣ የእግርና የቁርጭምጨሚት ማበጥ እንዲሁም የሰውነት መበለዝ እና የአይን ቆዳ ቢጫ መሆን የሔፒታይተስ በሽታ ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው።

የሔፒታይተስ በሽታ ከባድ በሽታ እና የሚያደርሰው ጉዳትም ከፍተኛ ቢሆንም፣ አስቀድሞ በመከላከል ለበሽታው ያለውን ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላል። ከጥንቃቄ መንገዶቹ ዋናዋናዎቹ ቫይረስ ያለበትን ሰው በምናስታምምበት ወቅት የእጅ መሸፈኛ (ጓንት) መጠቀም፣ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት አለማድረግ፣ እንደ ምላጭ፣ የጥርስ ብሩሽ እና የመሳሰሉትን ስለታማ ነገሮች በጋራ አለመጠቀም ሲሆኑ፤ በተጨማሪም ህጻናት እንደተወለዱ እና ሌሎች ሰዎችም በተገቢው ጊዜ ክትባት እንዲከተቡ በማድረግ መከላከል ይቻላል።

የሔፒታይተስ በሽታ ክትባት በተለይ ለሔፒታይተስ ኤ እና ሲ በአለም አቀፍ ደረጃ መሰጠት ከጀመረ በርካታ አመታት ተቆጥሯል። ለሔፒታይተስ ቢ ክትባት ባይኖርም በሽታውን አክሞ ለማዳን የሚያግዙ ዘመናዊ መሳሪያዎች እንዳሉ የገለፀው ጥናቱ፤ ነገር ግን የመድሐኒቱ ዋጋ ለሀብታሞችም ሆነ ለደሃዎች የሚቀመስ ባለመሆኑ በርካቶች እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ አስቀምጧል። የሔፒታይተስ ኤ እና ቢ ክትባቶች ግን በሁሉም ሀገራት እየተሰጡ የሚገኙ የክትባት አይነቶች ናቸው። ነገር ግን አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች ክትባቱን ሳይከተቡ እንደሚገኙ ጥናቱ አመልክቷል።

የሔፒታይተስ ክትባት በቫይረስ ላልተጠቃ ማንኛውም ሰው የሚሰጥ ክትባት ነው። ከዚህ ውጪ ግን ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የግድ መስጠት አለበት። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችም አዲስ የተወለዱ ህጻናትና እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች፣ የጤና ባለሞያዎች፣ በቤታቸው ውስጥ የሔፒታይተስ በሽታ ተጠቂ ያለ ወይም አስታማሚዎች፣ የኩላሊት እና የስኳር በሽተኞች እንዲሁም ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ ያላቸው አሊያም ጓደኞቸው ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጮች ስለሆኑ ክትባቱን መውሰድ ግዴታ ነው። ክትባቱም በተለያዩ ሶስት ጊዜያት የሚሰጥ ይሆናል። አንድ ሰው በማንኛውም ጊዜ ክትባቱን መከተብ የሚችል ሲሆን፤ በቀጣይም የመጀመሪያውን ከትባት በወሰደ በአንደኛው ወር ሁለተኛውን ክትባት ይወስዳሉ። ሶስተኛውን ክትባትም ሁለተኛው ክትባት ከተወለደ በ5ኛው ወር ለመጨረሻ ጊዜ ይወስዳሉ።

በተለይ የሔፒታይተስ ኤ እና ቢ ክትባት በሀገራችንም በተለያዩ የጤና ተቋማት በመሰጠት ላይ ይገኛል። ከክትባቱ ጎን ለጎንም ማህበረሰቡ ስለ በሽታው እና ክትባቱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ እየተገለፀ ይገኛል። ጥናቱ እንዳመለከተውም ምንም እንኳን ውጤታማ የሆኑ ክትባቶች እና ህክምናዎች ቢኖሩም ለችግሩ ከተሰጠው ግምት አናሳነት የተነሳ ችግሩን በአጭሩ መቅጨት አልተቻለም። በሽታው እያደረሰ ያለው ችግር ከፍተኛ ሆኖ ሳለ በችግሩ ላይ ለመስራት የሚመደብለት ገንዘብ ሳይቀር ለኤች አይ ቪ፣ ሳንባ እና ወባ ከሚመደበው ገንዘብ ያነሰ ነው ሲል ያለውን ዘርፈ ብዙ ፈተና ጥናቱ አስቀምጧል።   

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2310 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 120 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us