“የሆድ ድርቀት እንደምልክት የሚታይ ነገር ነው”

Wednesday, 27 July 2016 14:06

 

ዶ/ር ፋሲል ተስፋዬ

የሆድ ድርቀት እምብዛም ትኩረት የማንሰጠው ነገር ግን ብዙዎች በየቤታቸው የሚቸገሩበት ህመም ነው። ይህ ችግር በአመዛኙ እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን፤ ቶሎ መታከም ካልቻለም እስከ ህልፈተ ህይወት የሚያደርስ በሽታ ነው።ይህ ችግር ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን የሌሎች በሽታዎች ጠቋሚ መሆኑን በጉዳዩ ላይ ካነጋገርናቸው ባለሞያ መረዳት ችለናል። ከባለሙያው ያገኘነውን መረጃ በዚህ መልኩ ያቀረብነው ሲሆን፤ ባለሞያውም ዶ/ር ፋሲል ተስፋዬ ይባላል። ዶ/ር ፋሲል በሞያቸው አጠቃላይ ሀኪምና እና የማህበረሰብ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊስት ሲሆኑ፣ በአሁኑ ሰዓት የአይ ሲ ኤም ሲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው።

ሰንደቅ፡- የሆድ ድርቀት ችግር ምንድን ነው? መገለጫዎቹስ ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ፋሲል፡- የሆድ ድርቀትን ህመምተኞች በተለያዩ መንገዶች ይገልፁታል። ለመጀመር ያክል ሰገራዬ ይደርቅብኛል፣ ሆዴ የመወጠር ባህሪይ ያሳያል፣ ሰገራ ስወጣ ከመድረቁ የተነሳ የመውጫውን አካል (ፊንጢጣ) አካባቢን የመሰንጠቅ ሁኔታ ይፈጥርብኛል፣ ኪንታሮት ያመጣብኛል በሚሉት ይገልፁታል። አገላለፃቸው ከሞላ ጎደል ትክክል ነው። በአጠቃላይ ግን የሰገራ አወጋገድ ከአንዱ ሰው የሌላው ይለያያል። አንዳንድ ሰዎች በቀን አንድ ጊዜ ሊወጡ ይችላሉ። ሌሎች በሁለት ቀን ሊወጡ ይችላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ወደ ሶስት ቀን ሊሄድባቸው ይችላል። እንደ አገላለፃቸው በአንድ ቀን፣ በሁለት ቀን ወይም በቀን ሁለቴ የሚወጡትን እንደ መደበኛ (Normal) ልንወስደው እንችለዋለን።

በህክምናው ሆድ ድርቀት (constipation) የሚገለፀው በሳምንት ጊዜ ውስጥ ከሶስት ጊዜ በታች የሚኖር የሰገራ አወጋገድ ኖሮ ደረቅ ያለ ሰገራ የሚወጣበት እንዲሁም በዚህ ወቅት እስከ አስር ደቂቃ ማማጥን ሲያስከትል ነው። የሰገራ አወጋገዱም ከህመም ጋር የተያያዘ ነው። የተመገብነው ምግብ በጨጓራ እና በትንሽ አንጀት አማካይነት ከተፈጨ በኋላ ተረፈ ምርቱ ለመወገድ ወደ ትልቁ አንጀት ይሄዳል። በዚህ ስርዓተ ሂደት ውስጥ የማይፈጩ አንዳንድ ምግቦች እና አብዛኛው የወሰድነው ውሃ አብሮ ወደ ትልቁ አንጀት ይገባል። የትልቁ አንጀት ዋንኛ ተግባርም ተፈጭቶ መመጠጥ ያልቻለውን ተረፈ ምርት እና ውሃውን መምጠጥ ነው። ከዚያም ውሃው ተመጦ ደረቅ ያለው አካል ወደመወገዱ ይሄዳል። ስለዚህ አብዛኛው የሆድ ድርቀት ችግር ከትልቁ አንጀት ጋር የተያያዘ ይሆናል ማለት ነው። በመሆኑም በዚህ በትልቁ አንጀት ላይ ከሚከሰቱ ሶስት አይነት ክስተቶች ሳቢያ የሚገልፅ ይሆናል።

የመጀመሪያው የትልቁ አንጀት የአሰራር (function) ሂደት መወዛገብ ነው። ይህ ማለት ትልቁ አንጀት ጤነኛ ሆኖ ካለው አሰራር ችግር የተነሳ በበቂ ሁኔታ ሰገራው ወደታች ተላልፎ መውጣት ሳይችል እና እዚያው አንጀት ውስጥ ሲቆይ የሚከሰት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ትልቁ አንጀት ራሱ ችግር ሲፈጠርበት የሚከሰት ነው። ይሄንኛው አይነት ትልቁ አንጀት ሰገራን በተገቢው ፍጥነት እየጨመቀ እንዲያወጣ የሚያዙት ነርቮች ስርጭት ችግር ሲገጥማቸው ወይም ስርጭቱ ሲያንስ ነው። ይሄ ችግር ትልቁ አንጀት ሰገራን በተገቢው ፍጥነት ወደ ታች እንዳይገፋ ያደርገዋል። ሶስተኛው ደግሞ በሰገራ መውጫው አካባቢ ያሉ የሰውነት ክፍሎች ሰገራ የመምጣት ስሜትን አለማወቅ ችግር ወይም ስሜቱ ዘግይቶ መምጣት ችግር ነው። በዚህም አመጣጡን ተግባራዊ አድርገው ሰገራውን የማስወገድ ችግር ይፈጠራል። እነዚህ ሶስቱም አይነቶች የየራሳቸው ችግሮች እና የአመጣጥ ሂደቶች አሏቸው።

ሰንደቅ፡- የሆድ ድርቀት እንደዋና መንስኤ የሚጠቀሰው በቂ የሆነ ፈሳሽ አለመውሰድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በህክምናው የሚጠቀሱት መንስኤዎች ምን ምንናቸው?

ዶ/ር ፋሲል፡- ለሆድ ድርቀት ቀዳሚው እና አንደኛው ምክንያት የሰውነት በቂ የሆነ ፋይበር (አሳር) እጥረት ነው። እነዚህ የምግብ አይነቶች በጨጓራም ሆነ በአንጀት መፈጨት ስለማይችሉ ቀጥታ ወደ ትልቁ አንጀት የመግባት ባህሪይ አላቸው። እነዚህን የምግብ አይነቶች ሳንመገብ ስንቀር ሰገራ በቀላሉ ተመጦ ወደ ትልቁ አንጀት የሚውረድ በቂ ምግብ እንዳይኖር ያደርጋል። በቂ የሚወጣ ተረፈ ምርት ባለመኖሩ ለመውጣት ስለሚያስቸግር አንጀት ለረጅም ሰዓት ያለ እንቅስቃሴ የመቀመጥ ሀኔታ ይፈጠራል። ሌላው መንስኤ ደግሞ ሰገራን የማስወገድ ስሜትን ማዘግየት ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰገራ ይመጣና በተለያዩ ምክንያቶች የማዘግየት ሁኔታ ይፈጠራል። ይሄም ጥሩ የመጣውን የትልቁን አንጀት እንቅስቃሴ ይገድበውና የአወጋገድ ስርዓቱ እዚያ ጋር እንዲያቆም ያደርጋል። የተለያዩ የትልቁ አንጀት በሽታዎችም ለዚህ የሆድ ድርቀት ችግር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የትልቁ አንጀት መቆጣት (inflammation)፣ እጢ እና ካንሰር በትልቁ አንጀት ውስጥ መገኘት ለሰገራ መድረቅ ምክንያት ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም በሚያሰቃዩ ህመሞች መያዝ እና እርግዝና የሆድ ድርቀት መንስኤ ሊሆን ይችላል። በህመም የተያዙ ሰዎች በአንድ ቦታ የሚቀመጡ እና እንቅስቃሴ የማያደርጉ ስለሆኑ ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው። የአንጀት እንቅስቃሴ ከሰውነት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ይሄ ችግር በአጠቃላይ የአካል እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሰዎችን ያጋጥማል። ከዚህ ውጪም የሆድ ድርቀት ህመምን ሊያመጡ የሚችሉ ለጨጓራ ህመም የሚወሰዱ አሉሚኒየም አይድፒይድ የሚባሉ፤ አይረን ስለት ኪኒኖች፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለአእምሮ ህመም የሚሰጡ የማደንዘዝ ሃይል ያላቸው መድሐኒቶች የሰገራ ድርቀትን ያስከትላሉ።

ሌላው በአብዛኛው በአእምሮ ህመምተኞች ላይ የሚከሰተው ድብርት በአጠቃላይ በሰገራ መውጣት እንቅስቃሴ ላይ ችግር አለው። የሰውነታችንን የሜታቦሊዝም እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠሩ ታሮይድ ሆርሞኖች ማነስም ለዚህ ችግር ሊዳርግ ይችላል።

ሰንደቅ፡- የሆድ ድርቀት ሲነሳ በዋናነት የሚጠቀሰው ምልክት የሰገራ መድረቅ ነው። ሌሎች ይሄንን ችግር ለመለየት የሚያግዙ ምልክቶች ምን ምን ናቸው? ሌሎች የህመም ስሜቶችስ ይኖሩ ይሆን?

ዶ/ር ፋሲል፡- የሆድ ድርቀት ሲከሰት ሰገራው የመወፈር እና የመድረቅ ባህሪይ ስላለው ሲወጣ የታችኛውን የፊንጢጣ ክፍል የመሰንጠቅ ሁኔታ ስለሚፈጠር የመድማት ባህሪይ ይታያል። በመሆኑም ሰገራው ሲወጣ የማመም ስሜት ሊኖር ይችላል። ስለዚህ እንደ ምልክት የምንወስደው የሰገራው ደም መያዝ እና የፊንጢጣ መድማት፣ ከፍተኛ የሆነ የፊንጢጣ ህመም፣ ሰገራውን ለማስወጣት ቢያንስ ከአስር ደቂቃ በላይ ማማጥ እንዲሁም የሆድ መወጠር (መነፋት) አየር ሰይወጣ እስከሚችልበት ደረጃ ድረስ ሊኖር ይችላል። ከምንተነፍሰው አየር በተጨማሪ ከምግብ የምናገኘው አየር መውጫ በማጣት ሆድ ሊወጠር ይችላል። የሆድ መወጠር ሳይኖርም አንዳንድ ጊዜ በተለይ ቀጭን ሰዎች ላይ ጎርበጥበጥ ያሉ ነገሮች በሆድ አካባቢ ሊታዩ እና አንጀትን ሊይዙት ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ሰገራ ሙሉለሙሉ ያልወጣ የሚመስል ስሜት ይሰማል።

ሰንደቅ፡- በአብዛኛው የሆድ ድርቀትን እንደከባድ ችግር ያለማየት እና በቤት ውስጥ ለማከም ሙከራ የማድረግ ሁኔታዎች ይታያሉ። ይህ ችግር አሳሳቢ የሚሆነው እና የግድ ወደ ህክምና መሄድ የሚያስፈልገው በየትኛው ጊዜ ነው?

ዶ/ር ፋሲል፡- የሆድ ድርቀት ተከሰተ የሚባለው አንድ ሰው በሳምንት ውስጥ ከሶስት ጊዜ በታች ሰገራ ሲወጣ ነው ያልነው የእናት ጡት ወተት ብቻ ለሚጠቡ ህጻናት አይሰራም። እነዚህ ህጻናት በአምስት እና አራት ቀናት ሊሆን ይችላል ሰገራ የሚያወጡት። ነገር ግን ተጨማሪ ምግብ ከሚመገብ ህጻን ጀምሮ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ሲፈጠር የሆድ ድርቀት ችግር አለ እንለዋን። በዋናነት የተወሰኑ ሁኔታዎች እና ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ አሰፈላጊ ነው። ድንገተኛ የሆድ ድርቀት ከሆድ ህመም  (ቁርጠት) ጋር ሲመጣ እና አይነ ምድሩን ማውጣት ሲያቅት አደገኛ ደረጃ ነው። በተጨማሪም በሰገራ ላይ ደም ከታየ ደረጃው ከፍ እያለ ስለሆነ በአፋጣኝ መታከም አለበት። ምክንያቱም የትልቁ አንጀት ችግር የሆኑት እንደ እጢ እና ካንሰር ያሉ ችግሮች ሊሆን ይችላል። ድርቀት ከተቅማጥ ጋር እየተፈራረቀ የሚመጣ ከሆነም የአንጀቱ የስርዓት ሂደት የተዘገባ ስለሚሆን ቶሎ መታከም ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ ሰገራው ሲወጣ በጣም ቀጭን እና እንደ እርሳስ ሆኖ ከወጣ የአንጀት መጥበብ እና የእጢ መያዝ የመጀመሪያ ምልክት ሊሆን ስለሚችል በአስቸኳይ መታከም ያስፈልጋል። ምክንያቱ ያልታወቀ የሰውነት መክሳት ከሆድ ድርቀት ጋር ሲመጣ ችግሩን ስለሚያጎላው አፋጣኝ ህክምና ያስፈልገዋል።

የሆድ ድርቀት በአብዛኛው እንደ ምልክት የሚታይ ነው። ሆድ ድርቀት በሽታ ሳይሆን በትልቁ አንጀት ጋር ያሉትን ችግሮች ደረጃ ጠቋሚ ምልክት ነው። ድርቀትን ራሱን እንደቻለ በሽታ ከምንወስደው ይልቅ የበሽታዎችን ደረጃ ጠቋሚ ምልክት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ድርቀት ሲኖር አንድ ችግር አለ ማለት ነው። ችግሩ የራሱ የአንጀት ችግር፣ የአሰራር ችግር ወይም የአመጋገብ ችግር ሊሆን ይችላል። የሆድ ድርቀት ብዙም የከፋ ሳይሆን ሲቀር እና አመጋገብን በማስተካከል እና በሀኪም የሚታዘዙ የሰገራ ማለስለሻዎችን በመውሰድ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ መታከም ያስፈልጋል። በጊዜ ወደ ህክምና ከተመጣም መፍትሄ ማግኘት ይቻላል።

ችግሩን በህክምና መፍትሄ መስጠት ካልተቻለ ግን ሊያመጣቸው የሚችላቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ሆድ ድርቀት የህመም ምልክት እንደመሆኑ መንስኤው የሚታወቀው በምርመራ ነው። ምክንያቱ ካልታወቀም እስከ ህይወት ማለፍ የደረሰ ችግር ሊያመጣ ይችላል። መንስኤውም እጢ ወይም ካንሰር ከሆነ በሰውነት ውስጥ በመሰራጨት ህይወትን የማሳለፍ አደጋ ሊያደርስ ይችላል። መንስኤው የአንጀት ቁስለት ከሆነም ቁስለቱ ካልታከመ ራሱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያሸጋግር ይችላል። ስለዚህ የሆድ ድርቀቱን መንስኤ ዝም ብለን ብንተወው ችግሩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ፈቀድንለት ማለት ነው። ለተወሰነ ጊዜ ከሆድ ድርቀት ጋር ከተኖረ በኋላ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር እንፈቅድለታለን ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ህክምናው ምን ይመስላል? ከችግሩ ጋር አብሮ የመኖር እድሉስ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ፋሲል፡- ህክምናው አጠቃላይ የሰውነት ምርመራንም ያካተተ ነው። የፊንጢጣ ምርመራ እና የላብራቶሪ ምርመራ ይደረጋል። አጠቃላይ የደም ምርመራ እና የሴሎች ቆጠራ ምርመራ ይደረጋል። በተጨማሪም የታይሮድ እና የኤሌክትሮላይት ምርመራ ይደረጋል። ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረነገሮች እጥረት እና ብዛት መኖር አለመኖሩም ምርመራ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪም ኖራ በመስጠት የሆድ አካባቢዎችን ራጅ በማንሳት እና እንደ አስፈላጊነቱ ፕሮክቶሲግሞንሲንዶስ ከፒ የተባለ ምርመራ ይደረጋል። ከዚህ ምርመራ በኋላ ህመምተኛው ማደረግ ያለበት ነገሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሀኪም ምክር ይሰጠዋል።

ችግሩ የመጣው ትልቁ አንጀት ጤነኛ ሆኖ በአሰራር ችግሮች ብቻ ከሆነ ችግሩን ሊያሻሽሉት የሚችሉ መፍትሄዎችን እየወሰደ አብሮ መኖር ይቻላል። አንዴ እያስቀመጠ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚደርቅ ከሆነ በሚደርቅበት ወቅት የማማጥ ሁኔታ ስለሚኖር ኪንታሮቶችን እያመጣ እና ኢንፌክሽን እየፈጠረ የሚመጣ ከሆነ በየጊዜው እያከሙ የማዳን ሂደት ውስጥ ይገባል። እንደ ህክምና ባለሞያ የሚመከረውም ድርቀት ከመጣ የድርቀቱን መንስኤ ማከም ነው። ያም ሆኖ ግን የአንጀት የአሰራር ሂደት ችግር ከሆነ ከሁኔታው ጋር እያመቻቸ መኖር ይቻላል። ነገር ግን በአንጀቱ ውስጥ እያጠበበው የሚሄድ እጢ አሊያም ካንሰር ካለ የመሰራጨት ባህሪይ ስላለው ወደ ሰውነት በመሰራጨት በሌሎች ወሳኝ የሰውነት ክፍሎች በመሰራጨት ለሞት ይዳርጋል።

ሰንደቅ፡- የሆድ ድርቀት ችግር በአብዛኛው እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት ይነገራል። ይሄ ነገር ምን ያህል እውነት ነው?እውነት ከሆነስ ምክንያቱ ምንድ ነው?

ዶ/ር ፋሲል፡- የሆድ ድርቀት ተጠቂ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ይሄ የሚያያዘው ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ነው። እድሜያቸው የገፉ ሰዎች የሚኖራቸው እንቅስቃሴ የተገደበ ነው። የአንጀት እንቅስቃሴም ከሰውነት እንቅስቃሴ ጋር የተያዘ ስለሆነ በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ችግሩ ጎልቶ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች እድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ የአመጋገብ ዘይቤያቸው እየተቀየረ ይሄዳል። በአብዛኛው የሚመገቡት በቀላሉ ሊጠጡ እና ሊመጠጡ የሚችሉ ምግቦችን ነው። ጥርሳቸውም ደረቅ ምግቦችን ለማኘክ አቅም ስለማይኖረው ለስላሳ ምግቦችን በብዛት የመመገብ ሁኔታ ይኖራል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የምግብ ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ስለሚሆን ትንሽ ነገር ተመግበው በቃን ይላሉ። ስለዚህ ወደ ትልቁ አንጀት የሚገባው ነገር መጠኑ ስለሚያንስ ችግሩ እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የከፋ ይሆናል።

ሰንደቅ፡- የሆድ ድርቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በቤት ውስጥ ማስተካከል የሚቻልበት ሁኔታ ይኖር ይሆን?

ዶ/ር ፋሲል፡- ወደ ህክምና ሲሄዱ የደም፣ የታይሮይድ፣ የስኳር እና ሌሎች የላብራቶሪ ምርመራዎች ይደረጋሉ። ከዚህ ውጪ ግን በቤት ውስጥ ህመምተኛው በራሱ የሚያደርጋቸው ህክምናዎች ይኖራሉ። አንደኛው በቂ የሆነ አሰር ያላቸው ምግቦችን እንዲመገቡ እንመክራለን። እነዚህ አሰሮች በአትክልት፣ በቅጠላ ቅጠሎች ፣ በፍራፍሬዎች፣ ባልተፈተጉ ስንዴ እና የስንዴ ውጤት በሆኑ ምግቦች ውስጥ የሚገኙ እና የሰገራ አወጋገድ ስርዓቱን የሚያፈጥኑ ናቸው። እነዚህ አሰሮች በባህሪያቸው ውሃን መጠው የመያዝ አቅም ስላላቸው ሰገራ በቀላሉ እንዲለሰልስ ያደርጋሉ። ከዚህ ውጪ በቂ የሆነ ውሃን መጠጣትም ያስፈልጋል። ማንኛውም ሰው በቀን ቢያንስ ስምንት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት አለበት።

ሌላው በሳምንት ሁለት ጊዜም ሆነ ሶስት ጊዜ ተከታታይ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም ሰገራ በመጣበት ጊዜ ወዲያው ማስወገድ ያስፈልጋል። ሰገራ በመጣበት ሰዓት አንጀት ሰገራን እየገፋ ወደታች የሚያመጣበት እንቅስቃሴ እያለ ማስወገድ ያስፈልጋል። በእነዚህ መንገዶች መቆጣጠር ካልተቻለ ግን መድሃኒቶችን መጠቀም ያስፈልጋል። እነዚህ መድሀኒቶችም ሰገራን ለማለስለስ የሚያግዙ፣ በሰገራው ላይ የሚደረገውን ግፊት የሚጨምሩ ማለስለሻዎች ወይም የማይፈጩ አብዛኞቹ ነገሮች ወደታች እንዲገፉ የሚያደርጉ (የሰገራ መጠንን የሚጨምሩ) እንዲሁም የነርቮች እና የአንጀትን እንቅስቃሴዎች የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ።

   

ይምረጡ
(20 ሰዎች መርጠዋል)
6804 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 944 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us