መድሐኒቶቹ እፅዋቶች

Wednesday, 03 August 2016 14:37

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የእህል ዘሮች እየተጨመቁ በዘይት መልክ ለምግብነት ሲውሉ ይስተዋላል። ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ ከጥንት ጀምሮ ከምግብነት ይልቅ የመድሐኒትነት ባህሪያቸው የላቀ የእፅዋት ዘይቶች አሉ። የእነዚህ እፅዋት ዘይቶች ገና ሳይንስ ሳይደርስባቸው በልማድ ብቻ በመድሐኒትነት ሲያገለግሉ የቆዩም ናቸው። ከእነዚህ ዘይቶች ዋና ዋናዎቹ የወይራ ዘይት (Olive Oil) እና የዘንባባ ፍሬ ዘይት (Coconut) ዘይት ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ የእፅዋት ዘይቶች ካላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

 

የወይራ ዘይት (olive oil)

በሜዲትራኒያን አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በአብዛኛው የሚታወቁት ባላቸው ረጅም እድሜ ነው። ለዚህ በምድር ላይ ለረጅም ዓመት የመኖር ምስጢሮቻቸው በርካታ ቢሆኑም ዋንኛው ግን የወይራ ዘይት ተጠቃሚነታቸው ነው ይላሉ የዘርፉ ተመራማሪዎች። እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምድር ላይ ለረጅም ጊዜ ከመቆየት በዘለለም ለልብ ህመም፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም ለስትሮክ ያላቸው ተጋላጭነት በጣም አነስተኛ ነው። የወይራ ዘይት ለጤንነታችን ያሉትን ጠቀሜታዎች ለማጥናት ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ የፈጀ ጊዜን ወስዷል። የጥናቶቹ ውጥቶችም የሚከተሉጥ ናቸው።

 

ለከፍተኛ የደም ግፊት እና ለልብ ህመም

የወይራ ዘይት ዋንኛው የጤናማ ስብ ምንጭ ነው። ይህ ንጥረነገር ደግሞ የልብ እና ከልብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማስወገድ ጠቃሚው ነገር ነው። በሪሴርካ ባዮሜዲካ ዲ ባርሴሎና የምርምር ተቋም ተደርጐ በፋርማኮሎጂካል ሪሰርች መፅሔት ታትሞ የወጣው ጥናት ይፋ ያደረገውም ይሄንኑ እውነታ ነው። የጥናቱ መሪ ማሪያ ኢሳቤል ኮቫስ እንደገለፁትም፤ የወይራ ዘይትን በተከታታይ (በመደበኛነት) የሚጠቀሙ ሰዎች ለልብ ህመምና ተያያዥ ችግሮች፣ ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለስትሮክ እንዲሁም ለከፍተኛ የደም ኮሌስትሮል የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ከዚህ በተጨማሪም የወይራ ዘይት የሰውነትን መቆጣት (Inflammation)፣ የደም ስሮችን ችግር፣ በልብ ውስጥ በሚገኙ ደም ስሮች ውስጥ የሚከሰትን የደም መርጋት ለመከላከል እና ለካርቦሃይድሬት ሜታቦሊዝም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በማድሪድ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዶ በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል የታተመ ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተውም በወይራ ዘይት የተዘጋጁ ምግቦችን በመደበኛነት የሚመገቡ ሰዎች ለልብ ህመም እና ያለ እድሜ ለመሞት ያላቸው ተጋላጭነት አነስተኛ ነው።

 

ለድብርት፣ ለስትሮክ እና ለአልዛይመርስ

ጠቃሚ ባልሆኑ ስቦች የበለፀጉ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለድብርት የተጋለጡ ናቸው የሚለው በስፔን ላስ ፓልማስ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት፤ ለዚህ ችግር እንደመፍትሄ የሚያስቀምጠው የወይራ ዘይትን ነው። በ12ሺህ ፍቃደኞች ላይ በደተረገ ጥናት ማረጋገጥ የተቻለውም በየእለቱ የወይራ ዘይትን በምግባቸው ውስጥ የሚያካትቱት የጥነናቱ አካላት በየዕለቱ ከማያካትቱት በ48 በመቶ ለድብርት ተግላጭ ሆነው ተገኝተዋል።

ስትሮክ በተለይ እድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ በብዛት በመከሰት የሚታወቅ ችግር ነው። በፈረንሳይ ብሔራዊ የጤና ምርምር ኢንስቲቲዩት የተደረገ ምርምር ይፋ እንዳደረገውም፤ የወይራ ዘይትን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች ለስትሮክ የመጋለጥ እድላቸውን 41 በመቶ መቀነስ ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የወይራ ዘይት እርጅናን ተከትሎ የሚመጣውን የአልዛይመርስ በሽታ የመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። የወይራ ዘይት ኦሊኦካንታል የተባለ ንጥረ ነገር ያለው ሲሆን፣ ይሄ ንጥረ ነገርም መደበኛ ያልሆኑ የአልዛይመርስ በሽታ ፕሮቲኖች ከአእምሮ ውስጥ እንዲወገዱ ያደርጋል። ይህ ንጥረ ነገር የእድሜን መግፋት ተከትሎ የሚመጡ የአእምሮ መሳት ችግሮችን ይከላከላል።

 

በሳዑዲ ዓረቢያ እና ቱኒዚያ ዩኒቨርሲቲዎች የተካሄዱ ጥናቶች እንዳመለከቱት የወይራ ዘይት የጉበት ጤንነትን ለመጠበቅ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በወይራ ዘይት ውስጥ የሚገኙት ንጥረነገሮች የጉበትን ህዋሳት በበሽታ ከመጠቃት የመታደግ ጠቀሜታ አላቸው። ይሄ የሚሆነውም በጉበት ውስጥ በሚፈጠር የኬሚካሎች ግጭት የሚጐዱ ሴሎችን በመታደግ ነው።

 

ለጡት ካንሰር

ከሌሎች የአትክልት ዘይቶች በተለየ መልኩ የወይራ ዘይት የጡት ካንሰርን በመከላከል ረገድ ወደር ያልተገኘለት ነው። የወይራ ዘይት የዘረመል (DNA) መጠቃትን የመከላከል፣ እጢዎች በፍጥነት እንዲሞቱ የማድረግ እንዲሁም የካንሰር ሴሎች እንዳይስፋፉ የማድረግ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡ የጡት ዕጢዎች በፍጥነት እንዲሞቱ በማድረግ ሰዎች ለጡት ካንሰር እንዳይጋለጡ፣ የጡት ዕጢዎችም እንዳይባባሱ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በስፔን ባርሴሎና ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ጥናት አረጋግጧል።

የወይራ ዘይትን በጥሬው ከመመገብ ይልቅ ለምግብ መጥበሻነት ማዋሉ ደግሞ ጠቀሜታውን የጐላ ያደርገዋል ተብሏል። የወይራ ዘይት በተፈጥሮው በተለያዩ የቫይታሚን አይነቶች የበለፀገ ነው። ከ100 ግራም የወይራ ዘየት ውስጥም 885 ኪሎ ካሎሪ ኃይል፣ ከ3 ነጥብ 5 እስከ 21 ግራም ኦሜጋ6፣ 14 ሚሊ ግራም (በቀን ከሚያስፈልገው 93 በመቶ) ቫይታሚን “ኢ” እንዲሁም በቀን ከሚያስፈልገው ቫይታሚን “ኬ” 59 በመቶውን እናገኛለን።

 

የዘንባባ ፍሬ ዘይት

ልክ እንደ ወይራ ዘይት ሁሉ የዘንባባ ፍሬ ዘይት ለሰው ልጅ ያለውን ጠቀሜታ በግልፅ ለማስቀመጥ ከ1ሺህ 500 በላይ ጥናቶች እንደተደረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በእነዚህ ሁሉ ጥናቶች ማረጋገጥ የተቻለውም የዘንባባ ፍሬ ዘይት ያለው ጠቀሜታ ተዘርዝሮ የማያልቅ መሆኑ ነው። የዘንባባ ዘይት 62 በመቶው ካፕርይሊክ አሲድ፣ ላውሪክ አሲድ እና ካፕሪክ አሲድ ከተባሉ ፋቲ አሲዶች የተሰራ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በዚህ ፍሬ ውስጥ የሚገኘው 91 በመቶው አሲድ ጤናማ አሲድ ነው። በዘንባባ ፍሬ ዘይት ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች ለመፈጨት ቀላል የሆኑ፣ በስብ መልክ የማይከማቹ፣ ፀረ-ባክቴሪያ እና ፀረ-ፈንገስ የሆኑ፣ በፍጥነት ወደ ኃይል ለመቀየር አመቺ የሆኑ እና መጠናቸውም ትንንሽ የሆኑ ናቸው። በመሆኑም የዘንባባ ፍሬ ዘይት በዚህ መልኩ በተፈጥሮ ተከሽኖ የተዘጋጀ በመሆኑ ለሰው ልጅ የሚሰጣቸው ጠቀሜታዎችም በርካታ ናቸው።

 

ለማስታወስ እና ለአንጐል ስራ

በዘንባባ ፍሬ ዘይት ውስጥ የሚገኘው ጤናማ ስብ በእድሜ መግፋት እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ የማስታስ ችሎታ መቀነስ እና የእንጐል ስራ መዳከምን እንደሚቀንሱ በስፔን የተደረገ ጥናት አመልክቷል። በዚህ ዘይት ውስጥ የሚገኙ ጤናማ አሲዶች በቀላሉ የሚፈጩ እና ከደም ጋር የሚቀላቀሉ በመሆናቸው ወደ አንጐል ሴሎችም በቀላሉ ይደርሳሉ። ያለ ኢንሱሊንስ እርዳታ ግሉኮስ ወደ ኃይል እንዲለወጥ የማድረግ አቅም ስላለው አንጐል ስራዎቹን ለመስራት የሚያግዘውን ጉልበት (ኃይል) በቀላሉ እንዲያገኝ ያግዘዋል። በዚህም ሳቢያ አንጐል የበለጠ ፈጣን እና ቀልጣፋ እንዲሆን ያግዘዋል።

 

      በዘንባባ ፍሬ ዘይት ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች በቀላሉ በጨጓራ የሚፈጩ በመሆናቸው አንጐል በቀላሉ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ እና ኬቶን የተባሉ ንጥረ ነገሮች እንዲፈጠሩ ያግዛል። እነዚህ ንጥረ ነገሮችም አንጐል ግሉኮስን ወደ ኃይል ለመቀየር እንዲቀለው ያደርጋል። በእነዚህ ንጥረ ነገሮች እርዳታ አንስሊንን ሳይጠቀም አንጐል ኃይል እንዲያገኝ ያግዘዋል። አንጐል ህዋሳቱ ስራቸውን እንዲሰሩ እንዲሁም ግሉኮስን ወደ ኃይል ለመቀየር ያግዘው ዘንድ አንሰሊንን ያመነጫል። የአልዛይመርስ ችግር ያለበት አንጐል ግን ይህን አንሱሊን የማመንጨት እቅም አይኖረውም። በመሆኑም የዘንባባ ፍሬ ዘይትን በሚመገቡበት ወቅት ኬቶን የተባለው ንጥረ ነገር ይሄንን ስራ ተክቶ በመስራት አንጐልን ያግዘዋል።

 

ለውስጥ ደዌ

በዘንባባ ፍሬ ዘይት ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ከሽንት ማጣራት እና ከኩላሊት ኢንፌክሽን ጋር ተያያዥነት ያሉትን ችግሮች በማከም ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ይህ ዘይት በተፈጥሮ ፀረ-ባክቴሪያ ስለሆነ በኩላሊት ላይ ኢንፌክሽን ሊፈጥሩ የሚችሉ ባክቴሪያዎች እንዳይራቡ በማድረግ እና እንዲሞቱ በማድረግ ኩላሊትን ከኢንፌክሽን የመታደግ አገልግሎት አለው። ከዚህ በተጨማሪም የዘንባባ ውሃ ኩላሊትን የማፅዳት እና የኩላሊት ጠጠርን የማስወገድ አገልግሎትም አለው። የዘንባባ ዘይት ኢንፌክሽንን ብቻም ሳይሆን የህዋሳት መቆጣትን (Inflammation) የማስወገድ ጠቀሜታም አለው።

ከፕርይሊክ እና ላውሪክ የተባሉት በዚህ ዘይት ውስጥ የሚገኙ ፋቲ አሲዶች የሰውነት መቆጣትን ከሰውነት የውጭኛው እና የውስጠኛው ክፍል የመከላከል አቅም ስላላቸው የቆዳ ጤናማነትን ለመጠበቅም ያግዛል። የቆዳን ጥራት ለመጠበቅ፣ እርጥበት እንዳያጣ ለማድረግ እንዲሁም ከፀሐይ ጨረር ለመከላከል እና የተለያዩ ችግሮችንም ለማከም ያግዛል።

 

የዘንባባ ፍሬ ዘይት የምግብ ልመትን በማፋጠን በቀላሉ ሊሟሙ የሚችሉ ቫይታሚኖች፣ ካልሲየም እና ማግኒዚየም ወደ ደም እንዲገቡ ያደርጋል። አግረመንገዱንም መጥፎ ባክቴሪያዎችን እና ፈንገስ አምጪ ተዋሲያንን በመግደል የጨጓራ አሲድ እንዲቀንስ ያደርጋል። በዘንባባ ፍሬ ዘይት ውስጥ የሚገኙት ጤናማ ስቦች በህዋሳት ውስጥ ያለው የኢንሱሊን እንቅስቃሴ የተመጣጠነ እንዲሆን ያደርጋል። ኬቶን የተባለው ንጥረ ነገር እንዲመነጭ ስለሚያደርግም ሴሎች በግሉኮስ ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ ኃይል የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ሰውነት በቂ እና ቀጣይነት ያለው ኃይል አንዲያገኝ ያደርጋል። በዚህም በተለይ አይነት ሁለት የተባለውን የስኳር ህመም ለመቋቋም ያግዛል። በተጨማሪም በዘንባባ ፍሬ ውስጥ የሚገኘው ጤናማ ስብ ከሰውነት ውስጥ የሚኖረው ሆርሞን የተመጣጠነ እንዲሆን ያግዘዋል።

 

በዚህ ዘይት ውስጥ የሚገኙት ጤናማ ስቦች ለመሰባበር የጣፊያ ኢንዛይም ስለሚያስፈልጋቸው በጣፊያ ላይ የሚኖረው ጫና እንዲቀንስ ያደርጋል። በዚህም ከሀሞት ከረጢት እና ከጣፊያ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል ያግዛል።

የዘንባባ ፍሬ በተፈጥሮው በጤናማ ስቦች የበለፀገ ነው። እነዚህ ጤናማ ስቦች ደግሞ በደም ውስጥ የሚገኘው ጤናማ ኮሌስትሮል በመጠኑ እንዲጨምር እግረመንገዱንም ጤናማ ያልሆነው ኮሌስትሮል መጠኑ እንዲቀንስ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። ይሄንን በማድረጉም ለልብ ህመም እና ተያያዥ ለሆኑ ችግሮች የመጋለጥ እድልን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።

 

ካንሰርን ለመከላከል እና ለማከም

በዘንባባ ፍሬ ዘይት ውስጥ የሚገኙ ነጥረ ነገሮች በሁለት መልኩ የካንሰር በሽታን የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። የዘንባባ ዘይት ኬቶን እንዲመረት የሚያደርግ በመሆኑ የካንሰር ዕጢዎች ደግሞ ኃይል ከኬሮቲን መውሰድ አይችሉም። ስለዚህ ኃይል (ምግብ) ማግኘት የሚችሉት ከግሉኮስ ብቻ ነው። በመሆኑም የካንሰር ታማሚዎች ይሄንን ዘይት በመጠቀም በሽታውን ለመቋቋም ያግዛቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በዘይቱ ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች ባክቴሪያን የመግደል ባህሪይ ስላላቸው በተለይ የሆድ እቃ ካንሰር ሊያመጡ የሚችሉ ባክቴሪያዎችን በመግደል ለችግሩ ያለውን ተጋላጭነት ይቀንሰዋል። የካንሰር ሴሎችም እንዳይሰራጩ እና እንዳይበዙ የማድረግ ጠቀሜታ አለው።

 

የአጥንት መሳሳትን ይከላከላል

የዘንባባ ፍሬ ዘይት ከፍተኛ የሆነ የአንቲኦክሱደንት ይዘት ስላለው ፍሪ ራዲካልስ የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ለመቋቋም ያግዛል። በዚህም ሳቢያ የአጥንት መሳሳትን ለማከም ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም የዘንባባ ፍሬ ዘይት አንጀት ካልሲየም ማዕድንን የመምጠጥ አቅሙ እንዲጨምር ያግዘዋል። በዚህም አጥንት በቂ የሆነ የካልሲየም ማዕድን እንዲያገኝ በማድረግ የአጥንት መጠኑ እንዲጨምር እና እንዲጠነክር ያደርገዋል። ከዚህ ጐን ለጐንም አጥንት እንዳይሳሳ እና መጠኑም እየቀነሰ እንዳይመጣ ያግዘዋል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2271 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 121 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us