ጥናቶች ተስፋ እየፈነጠቁ ይገኛሉ

Wednesday, 10 August 2016 13:47

 

·        አትክልትን መመገብ ዋናው የካንሰር መከላከያ ነው

 

ለሰውን ልጅ ጤናማ አኗኗር ለመፍጠር እና በምድር የሚኖርበት ጊዜ የተሻለ ይሆን ዘንድ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል። በየጊዜው የሚከሰቱ በሽታዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና የሰው ልጆችን ለመታደግ የዘርፉ ባለሞያዎች በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ረጅም ዓመታትን አስቆጥረዋል። የሰው ልጅ የምርምር እና የጥናት ውጤት በሆኑ ስራዎችም እስከዛሬ በርካታ የሰው ዘርን መታደግ ተችሏል። አሁንም ድረስ ያላቆመው የባለሞያዎች ምርምር በየጊዜው አዳዲስ ግኝቶችን እየያዘ እየመጣ ነው። በአሁኑ ጊዜ እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ህመሞችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያግዙ በርካታ ጥናቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። የጥናት ውጤቶቹ በመገምገም እና ውታማነታቸውን በማረጋገጥ ለህዝብ እንዲደርሱ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት የአለም ጤና ድርጅትም በተለያዩ አትሞች የጥናቶቹን ውጤቶች ሪፖርት ይፋ ያደርጋል። ሪፖርቶቹን ይፋ የሚያደርገውም ሰዎች በተለይ በሽታ በመከላከል ረገድ የየራሳቸውን እርምጃ እንዲወስዱ እና አለማችንም ከስቃይ የፀዳች እንድትሆን በማሰብ ነው። ከሰሞኑ የወጡ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱትም በተለይ የካንሰር በሽታ እና የስኳር ህመምን አስመልክቶ ባለሞያዎች ጥናት አድረገዋል። እኛም የካንሰር በሽታን ለመከላከል እንዲሁም የስኳር ህመምን ለማከም በሚያግዙ ሁኔታዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶችን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

ለተለያዩ የካንሰር አይነቶች ከሚያጋልጡ እና በሽታውንም ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ የአኗኗር እና የአመጋገብ ስርዓታችን የተስተካከለ አለመሆኑ ነው ሲሉ ጥናቶች በተደጋጋሚ ያስቀምጣሉ። የአመጋገብ መስተካከል ለካንሰር ያለውን ተጋላጭነት ከመቀነስም አልፎ ችግሩን ለማስወገድ ጠቃሚ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጥናት ሲደረግ የቆየ ሲሆን፤ በቅርቡ የተደረገው ጥናት እንዳረጋገጠውም በተለይ አትክልት በልነት (Vegetarianism) ካንሰርን ለመከላከል ከፍተኛ አቅም አለው። አሁንም ድረስ ሰዎች ከእንስሳት ውጤቶች ይልቅ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አዘውትረው እንዲመገቡ እየተመከረ ይገኛል።

ጥናቱ እንዳመለከተው ከሆነ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚመገቡ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ለካንሰር የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ከሁለቱም ወገኖች(የእንስሳት ተዋፅኦ አዘውትረው ከሚመገቡ እና አትክልትና ፍራፍሬ ሚመገቡ ሰዎች) በተወሰደ የደም ናሙና ማረጋገጥ የተቻለውም በአትክልት ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች በስጋ ውስጥ ከሚገኙት በስምንት እጥፍ የካንሰር ህዋሳትን የመግደል አቅም አላቸው። ጥናቱ ለአንድ ዓመት ያህል የተደረገ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች በሁለት ተከፍለው አንደኛው ቡድን የእንስሳት ውጤቶችን እንዲሁም ሁለተኛው ክፍል አትክልቶችን እንዲመገቡ በማድረግ ነበር። አትክልት ተመጋቢዎች በዚህ የጥናት ጊዜ ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ሃይል ሰጪ የሆኑ ጥራጥሬዎችን እየተመገቡ በሳምንት ለስድስት ቀናትም ለ30 ደቂቃ ያህል የእግር ጉዞ እንዲያደርጉ በማድርግ ነበር ጥናቱ የተካሄደው። ተሳታፊዎቹ የአኗኗር ዘይቤያቸውም ከጭንቀት የተላቀቀ እና በተወሰነ ደረጃ ዘና የሚያደርግ እንዲሆን ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል።

ለጥናቱ የተቀመጠው ጊዜ ሲጠናቀቅ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተውም በዚህ መልኩ የአትክልት ውጤቶችን ብቻ ከተመገቡ የጥናቱ ተሳታፊዎች የተወሰደው የደም ናሙና ያመለከተው እነዚህ ሰዎች የካንሰር ህዋሳት እድገትን የመግታት አቅሙ ስምንት እጥፍ ሆኖ ተገኝቷል። የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተውም እነዚህ አትክልት በል (Vegetarians) ከሌሎቹ በብዙ እጥፍ በተሻለ መልኩ በተለይ በሽንት ፊኛ አካባቢ የሚኖረውን የካንሰር ህዋሳት እድገት የመግታት አቅም ኖሯቸው ተገኝተዋል።

በዚህ ረገድ የተደረጉ ተከታታይ ጥናቶች እንዲመለከቱት ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትሮ መመገብ የጡት ካንሰርን ለመከላከል ያለው አቅም በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል። አስገራሚው የጥናቱ መልክ ደግሞ ጥናቱ ያመጣው ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘ መሆኑ ነው። የጡት ካንሰር ያለባቸው ሴቶች ለ14 ቀናት ያህል አትክልትና ፍራፍሬ እንዲመገቡ እንዲሁም በየእለቱ ከ30 እስከ 60 ደቂቃ የሚደርስ የእግር ጉዞ እንዲያደርጉ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም አስደናቂ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል። ሴቶቹ ከሁለት ሳምንታት በኋላ (ከ14 ቀናት በኋላ) በድጋሚ ደማቸው ተወስዶ ጥናት ሲደረግም ደማቸው የካንሰር ህዋሳትን እድገት የመግታት እንዲሁም ህዋሳቱን የመግደል አቅማቸው ከቀድሞው በጣም የተሻሻለ ሆኖ ተገኝቷል።

ከላይ የተጠቀሱት የጥናት ውጤቶች የተመዘገቡት አትክልት በልነት እና የሰውነት እንቅስቃሴ ተደማምረው ያመጡት ውጤት ነው። በመሆኑም ሳይንቲስቶቹ የአትክልት በልነት ለብቻው የካንሰር ህዋሳትን እድገት በመግታት እና በመግደል ረገድ የሚያመጣውን ለውጥ ለማየት ተደጋጋሚ ጥናት አድርገዋል። በዚህም የተመዘገበው ውጤት አስደሳች ሆኖ ተገኝቷል። በዚህ ጥናት መሰረትም አትክልት እና የአትክልት ውጤት የሆኑ ምግቦችን እያዘወተሩ ነገር ግን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያላደረጉ ሰዎች የካንሰር ህዋሳትን እድገት የመግታት እና የመግደል አቅማቸው ከሌላው ጋር ሲነፃፀር ሁለት የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ጥናቱ በግልፅ ያስቀመጠውም በአጠቃላይ የአመጋገብ እና የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል በሰው ልጅ ጤናማ ህይወት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ከእነዚህ ጠቀሜታዎች መካከልም የካንሰር ህዋሳት እንዳያድጉ የሚከላከል ደም ባለቤት መሆኑ ዋንኛው መሆኑን ጥናቱ ገልጿል። የካንሰር በሽታን አስቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ከበሽታው ጋር አብሮ ለመኖር የአኗኗር ዘይቤ የሚኖረው ጠቀሜታውም በጥናቱ ጎልቶ ወጥቷል።

 

 

ለስኳር ህሙማን ተስፋ ሰጪው ክትባት

ቀደም ባለው ጊዜ በሲለስ ካልሜት ጉሪን የተባለው ክትባት የሳንባ በሽታን ለማከም የሚያግዝ የክትባት አይነት ነበር። ይህ ክትባት ለሳንባ መሽታ ህክምና ላለፉት መቶ አመታት እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ጊዜያት ያገለገለ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ክትባቱ የፊኛ  ካንሰርን ለማከምም እንደሚያገለግል ተገልጿል። ከሰሞኑ ደግሞ የወጣ አንድ ጥናት ያመለከተው ይህ ክትባት በተለይ አይነት አንድ (type 1) የተባለውን የስኳር ህመም ለማከም እንደሚያገለግል ነው። የምርምር ጥናቱም ለብዙዎች ተስፋ ሰጥቷል።

በአሜሪካ ስኳር ህመም ማህበር ጥናት ተደርጎበት ከሳምንት በፊት ይፋ የሆነ የጥናት ውጤት እንዳመለከተው ክትባቱ በሳንባ በሽታ እና በፊኛ ካንሰር ላይ ካመጣው ለውጥ ባልተናነሰ መልኩ በአይነት አንድ የስኳር ህመም ላይም አመርቂ ውጤት አምጥቷል። የአይነት አንድ የስኳር ህመምተኞች ዋናው የህመማቸው መንስኤ በሰውነት ውስጥ ኢንሱሊን የሚያመርቱ ህዋሳት ተግባራቸውን ማከናወን አለመቻል ነው። በዚህም ሳቢያ ሰውነት የሚያስፈልገውን ኢንሱሊን እንዳያገኝ ያደርገዋል። በዚህ ክትባት ማድረግ የሚቻለውም ሰውነት ኢንሱሊኑን ማምረት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ይህ ክትባት በዚህ አይነቱ የስኳር ህመም በተያዙ ሰዎች ላይ የተሞከረ ሲሆን፤ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎችም በሰውነታቸው ውስጥ ያሉት እጢዎች ቁጥር የጨመረ ሲሆን፤ ኢንሱሊን እንዳይመረት የሚያደርጉ ህዋሳት እንዲጠፉም አግዟል። ይህ ክትባት ቀደም ብሎ የተሰጣቸው ሰዎች ከክትባቱ በኋላ ሰውነታቸው በራሱ ኢንሱሊን የማምረት ደረጃ ላይ እንደደረሰም ጥናቱ አስቀምጧል።

በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ባለሞያዎች መካከል አንዷ የሆኑት ዶ/ር ዴኒስ ፋኤትማን እንደገለፁትም በጥናቱ የተገኘው ውጤት አስደሳች እና ተስፋ ፈንጣቂ ነው። እንደ ዶክተሯ ገለፃ አሁን የተደረገው ጥናት በመጀመሪያ ደረጃ የተደረገ በመሆኑ በቀጣይ ሰፊ ጥናት በማድረግ ክትባቱ የረጅም ጊዜ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችልበትን ሁኔታ እያፈላለጉ ይገኛሉ። ክትባቱ እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ ከመሆኑ የተነሳም ሌሎች ውስብስብ ህመሞችን ማከም በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተጨማሪ ጥናት ለማድረግ እቅድ መኖሩን ዶ/ር ዴኒስ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም አዳዲስ ምርምሮች እየተደረጉ ሲሆን፤ ምርምሮቹ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ይቀጥላሉ ተብሏል። በምርምሩ ላይ የሚሳተፉ የአይነት አንድ ስኳር ህመምተኞም እድሜያቸው ለ18 አመት ከሆኑ ወጣቶች እስከ 60 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ያሉት ናቸው። እነዚህ ህመምተኞች በአንድ ወር ውስጥ ሁለት ጊዜ ክትባት ይሰጣቸዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት አራት አመታት ውስጥም በየአመቱ አንዳንድ ጊዜ ክትባቱን በመውሰድ የክትባቱን ውጤታማነት ለማወቅ ምርምር ይደረጋል። እንደ ባለሞያዎቹ ገለፃ የዚህ ጥናት ውጤት በጥቂቱም ቢሆን በስኳር ህመምተኞች ላይ ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀ የጥናት ውጤት ነው። ነገር ግን ብዙ ምርምር የሚጠይቅ እንደሆነ ባለሞያዎች እየገለፁ ይገኛሉ። ጥናቱ እያሳየ ባለው ለውጥ ልክ ከሄደ ምናልባትም በጥቂት አመታት ውስጥ አይነት አንድ የተባለውን የስኳር ህመም ማከም የሚቻልበት ደረጃ ላይ ሊደረስ ይችል ይሆናል።  

     

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2007 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 122 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us