ክረምትና አመጋገባችን

Wednesday, 17 August 2016 12:30

ጉንፋን፣ ኢንፍሉዌንዛ ፣ ኮሌራ፣የተቅማጥ በሽታ፣ የምግብ መመረዝ እና ተመሳሳይ በሽታዎች በአብዛኛው የሚቀሰቀሱት በክረምት እና በቀዝቃዛ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ሰውነት በሽታን የመከላከል አቅሙ ዝቅተኛ ስለሚሆን ብዙዎች ለነዚህ ችግሮች የመጋለጥ እድላችን ከፍተኛ ይሆናል። ይሄንን ተጋላጭነታችንን ለመቀነስ የመጀመሪያው እርምጃ ራሳችንን ከቅዝቃዜ እና ከዝናብ መከላከል ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን ግን በቫይታሚን የበለፀጉ የምግብ አይነቶችን መመገብ አስፈላጊው ነገር እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በክረምት ወቅት ከፍተኛ ወበቅ ስለሚኖር የሰውነታችን የምግብ ልመት ስርኣት ዘገምተኛ ይሆናል። በመሆኑም ስርኣቱን ለማስተካከል አመጋገባችንንም ማስተካከል ያስፈልጋል። ከተለያዩ ምንጮች የሰበሰብናቸው መረጃዎች እንደሚጠቀሙትም ከዚሁ በታች የተዘረዘሩት የምግብ አይነቶች በክረምትና በቀዝቃዛ ወቅት ጤናማ ለመሆን እና ሰውነታችን ለበሽታ ያለውን ተጋላጭነት ለማስቀረት ይጠቅማሉ ፤ እንዲሁም ሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅሙ እንዲዳብር ያግዛል። መረጃዎቹን ያገኘናቸው ከጆን ሆፕኪነስ ዩኒቨርሲቲ ስነምግብ ኢንሰቲትዩት፣ ከላንሴት እና ሄልዝ ሜድ ድረ ገጽ ነው።

ስጋ

ማንኛውም የስጋ አይነት ለሰው ልጅ ሰውነት አስፈላጊ በሆኑ ፕሮቲኖች የበለፀገ ነው። በስጋ ውስጥ የሚገኙት ፕሮቲኖችም የሰውነት ህዋሳትን የመገንባት እና መልሶ የመጠገን አገልግሎት ይሰጣል። በተጨማሪም ፕሮቲኖች ሰውነት እንዳይመረቅዝ (infection) እንዳይፈጥር የማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። በመሆኑም በቀን ውስጥ በምንመገበው ምግብ ላይ የተወሰነ የስጋ መጠን አክለን መመገብ ከቻልን ሰውነታችን ለኢንፌክሽን ያለው ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ያስችለናል። ስጋ በፕሮቲን ብቻ ሳይሆን በቫይታሚን ቢ፣ በብረት እና ዚንክ ማዕድናት እንዲሁም በኦሜጋ 3 ነጥረ ነገሮች የበለፀገ የምግብ አይነት ስለሆነ ሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅሙ ጠንካራ እንዲሆን ያግዛል። የበሬ፣ የዶሮ አሊያም የበግ ስጋ ሁሉ በእነዚህ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ በመሆናቸው በቀዝቃዛ ወቅት ብንመገባቸው ጠቃሚዎች ናቸው።

እርጎ

       

በእርጎ እና ሌሎች የተብላሉ የምግብ አይነቶች (fermented foods) ውስጥ በርካታ ጤናማ እና ጠቃሚ የሚባሉ ባክቴሪያዎች ይገኛሉ። እነዚህ የባክቴሪያ አይነቶችም ሰውነት በሽታን የመከላከል አቅሙ እንዲዳብር የማድረግ አገልግሎት ይሰጣሉ። በተጨማሪም እነዚህ ጠቃሚ የባክቴሪያ አይነቶች በሰውነት ውስጥ በብዛት በሚኖሩበት ወቅት በሽታን የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። እርጎ የቫይታሚን ዲ ይዘቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሰውነት የጉንፋን እና የኢንፍሉዌዛ በሽታን እንዲቋቋም ያግዛል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም አንድ ሲኒ እርጎ በመጠጣት ብቻ ለጉንፋን እና ለኢንፍሉዌንዛ የመጋለጥ እድልን እስከ 25 በመቶ ዝቅ ያደርገዋል። በመሆኑም ከምግብ በፊትም ሆነ ከምግብ በኋላ የተወሰነ መጠን ያለው እርጎን መጠጣት በሰውነት ውስጥ የሚኖረውን ጠቃሚ ባክቴሪያ መጠን ለመጨመር፣ የሰውነትን በሽታ የመቋቋም አቅም ለማዳበር እንዲሁም ክረምት እና ቀዝቃዛ ወቅትን ተከትለው የሚመጡ እንደ ጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ያሉ ህመሞችን ለመከላከል ያግዛል። በተጨማሪም በክረምት ወቅት የሚኖረው ዘገምተኛ የምግብ መፈጨት ሂደት ፈጣን እንዲሆን ያግዛል።

እንጉዳይ

እንጉዳይ በምግብ ይዘቱ ከበርካታ የምግብ አይነቶች የተሻለ ነው። ይህ ተክል ጥሩ የሆነ የቫይታሚን ቢ ምንጭ ፣ እንዲሁም በኒአሲን፣ ሪቦፍላቬን እንዲሁም የፓንተቴኒክ አሲድ ምንጭ ነው። በተጨማሪም ሀይለኛ አንቲ ኦክሲአንት እና ጥሩ ሴሌኒየም የተባለ ንጥረ ነገር ምንጭ ነው። ይህ ይዘቱ ደግሞ ተክሉ ሰውነት ለመመርቀዝ (ኢንፌክሽን) ያለው ተጋላጭነት አነስተኛ እንዲሆን ያግዘዋል። በውስጡ ያለው ቫይታሚን ቢ ደግሞ ሰውነት ጥሩ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም እንዲኖረው ያደርገዋል። በተጨማሪም እንጉዳይ 177 ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ወሳኝ አሚኖ አሲዶች እና ከፍተኛ መጠን ያላቸው ፕሮቲኖች ያሉበት ተክል ነው። በመሆኑም ይህን ተክል በተለይ በክረምት ወቅት በመጠቀም ጤናማ ጊዜን ማሳለፍ ይቻላል።     

አረንጓዴ እና ባለቀለም አትክልቶች

እንደ ጥቅል ጎመን፣ አበባ ጎመን፣ ጎመን እና ቆስጣ ያሉት ቅጠላማ አትክልቶች ጥሩ የቫይታሚን ምንጮች ናቸው። በተለይ ቀለማማ በሆኑ በእነዚህ የአትክልት አይነቶች ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የቫይታሚን ኤ፣ ሲ እና ኢ ክምችት እንዲሁም ከፍተኛ የአሰር መጠን፣ አንቲ ኦክሲደንት እና ፎሌት ይገኛል። ቀለማቸው ወደ ጥቁር አረንጓዴ የሚያመሩ የአትክልት ዘሮች የሰውነት ህዋሳት ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚያግዙ አንቲኦክሲደንቶች ጥሩ ምንጭ ናቸው። የአበባ ጎመን ግሎታቲዮን በተባለ ሃይለኛ አንቲ ኦክሲደንት የበለፀገ ሲሆን፤ ጎመን ደግሞ ግሎታሚን የተባለ እና በሽታን የመቋቋም አቅምን በሚጨምር ንጥረ ነገር የበለፀገ አትክልት ነው። በአረንጓዴ እና ባለቀለም አትክልቶች ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም እንዲጠነክር ከማድረግ በተጨማሪም ለኢንፌክሽን የመገለጥ እድልን ስለሚቀንሱ የክረምት በሽታ የሚባሉትን የህመም አይነቶች ለመከላከል ያግዛሉ።

አትክልቶችን በክረምት ወቅት በምንጠቀምበት ወቅት ከሌላው ጊዜ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ነው ባለሞያዎች የሚመክሩት።ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት የአትክልቶቹ ቅጠሎች የመቆሸሽ አጋጣሚያቸው ብዙ ስለሆነ በቀላሉ ለጀርም፣ ለባክቴሪያ እና ለተለያዩ ተዋሲያን ይጋለጣል። በዚህም ሳቢያ ለተለያዩ የሆድ ኢንፌክሽኖች፣ ለተቅማጥ እና ትውከት የመዳረግ እድላቸው የሰፋ ነው። በመሆኑም እነዚህን አትክልቶች በምንመገብበት ወቅት ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ንጽኅናቸውን በመጠበቅ መሆን አለበት። በቅጠሎቻቸው ላይ የሚገኙትን ቆሻሻዎች ከማጠብ በተጨማሪም በአይን የማይታዩትን ጀርሞች፣ ባክቴሪያዎች እና ሌሎች ተዋሲያን ለመግደል በፈላ ውሃ ውስጥ መንከር ያስፈልጋል። በተቻለ አቅምም በጥሬው የሚበሉ የአትክልት ዘሮችን በዚህ በክረምት ወቅት ላለመመገብ መሞከር ያስፈልጋል።

ለውዝና ጥራጥሬዎች

ለውዝ በተፈጥሮ በቫይታሚን ኢ፣ በሪቦፍላቪን እና ኒያሲን የበለፀገ የቅባት እህል ዘር ነው። በተጨማሪም ለውዝ ለሰውነት አስፈላጊ የሆነ አንቲኦክሲደንት ያለው በመሆኑ የሰውነት ህዋሳት ጤነኛ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል። በመሆኑም በቀዝቃዛ እና በዝናባማ ወቅት ለውዝን መመገብ የሰውነት ህዋሳት ጤናማ እና በሽታን መቋቋም የሚችሉ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል። ለውዝን ከደረቁ ፍራፍሬዎች እና ከስኳር ጋር ቀላቅሎ መመገብ ደግሞ ሰውነት የሚያስፈልገውን ሃይል እንዲያገኝ ይረዳዋል።

ወደ ጥራጥሬዎች ስንመጣ ደግሞ አብዛኞቹ ጥራጥሬዎች ለሰውነት አስፈላጊ የሆነ ሃይል የመስጠት ጠቀሜታ አላቸው። በክረምት እና በቀዝቃዛ ወቅት ለሰውነታችን የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ሃይል ለማግኘት እንደ ገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ እና የመሳሰሉት የጥራጥሬ አይነቶች በምንመገበው የምግብ አይነት ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል።

ትኩስና ፈሳሽ ነገሮች

እንደሻይ እና የተለያዩ ትኩስ ነገሮችን በቀዝቃዛ ወቅት መጠጣት የብዙዎቻችን ልምድ ነው። ይሄንን ነገር በዘልማድ ብናደርገውም ባለሞያዎችም ድርጊቱ የሚደገፍ እና እንዲህ ላለው ወቅት አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ። ሻይ ስንል የተለያዩ ቀለማት ያሉት ቢሆንም፤ ሁሉም የሻይ አይነቶች ግን ለሰውነት ሙቀት ከመስጠት የዘለለ ብዙ የጤና ጠቀሜታ አላቸው። ሻይ ፐሊፊኖል እና ፍላቮቢኦድ የተባሉ ንጥረ ነገሮች እንዲሁም ኦክሲደንት አለው። እነዚህ ንጥረ ነገሮችም የሰውነት ህዋሳት ጤናማ እንዲሆኑ እንዲሁም ለበሽታ ያላቸው ተጋላጭነት ዝቅተኛ እንዲሆን ያግዛሉ። በተጨማሪም ሰውነታችን በቂ ውሃ እንዲይዝ የማድረግ አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይ አረንጓዴ እና ጥቁር ሻይ ደግሞ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም እንዲጨምር እና ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ እድል እንዲቀንስ ያግዛሉ፤ በልብ ህመም እና ተያያዥ ህመሞች የመጋለጥ እድልንም ዝቅ ያደርጋሉ። ሻይ ላይ ዝንጅብል አሊያም ማር ጨምሮ መጠጣት ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ ነው።

ከትኩስ ነገሮች በተጨማሪም ምንም እንኳን አየሩ ቀዝቃዛ ቢሆንም በክረምት ወቅት ብዙ ውሃ መጠጣት አስፈላጊ ነው። ይሄ የሚያስፈልገውም ሰውነታችን የሚያከናውናቸው ራሱን የማጽዳት ተግባራት በአግባቡ መከናወን ስለለባቸው ነው። ውሃ በምንጠጣበት ጊዜም ልክ እንደ አትክልቶች ሁሉ ለምንጠጣው ውሃ ከሌላው ጊዜ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደ የተቅማጥ በሽታ እና ተያያዥ በሽታዎች የሚከሰቱት ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃ በመጠጣት ስለሆነ በተቻለ አቅም የሚጠጣውን ውሃ በማፍላት አሊያም በክሎሪን በማከም መጠጣት ያስፈልጋል። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2081 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 122 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us