ወንዶች ለጡንቻ አለመታዘዝ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው

Wednesday, 24 August 2016 14:05

የጡንቻ አለመታዘዝ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ችግር ነው። ችግሩ የሚከሰተውም በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ እንደመሆኑ የሚያመጣው ጉዳትም የተለያየ ነው። እድሜያቸው የገፉ ወንዶች ደግሞ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ባለሞያ አነጋግረናል። ባለሞያዋ ዶ/ር ሜሮን አውራሪስ ሲሆኑ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በነርቭ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር እና የነርቭ ህክምና ስፔሻሊስት ናቸው።

ሰንደቅ፡- የጡንቻ አለመታዘዝ (weakness) ሲባል ምን ማለት ነው? በስንት ይከፈላል?

ዶ/ር ሜሮን፡- የጡንቻ አለመታዘዝ የሚባለው የአንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ጡንቻዎች እንደልብ አለመታዘዝ ማለት  ነው። የጡንቻ አለመታዘዝ በአንድ የሰውነት ክፍል ላይ ወይም በብዙ የሰውነት ክፍሎች ላይ ሊከሰት ይችላል። የጡንቻ አለመታዘዝን በሶስት አይነት ከፍለን ማየት ይቻላል። እነዚህም እውነተኛ (true) የጡንቻ አለመታዘዝ፣ ፋቲግ (fatigue) የጡንቻ አለመታዘዝ እንዲሁም አስቴኒያ (asthenia) የጡንቻ አለመታዘዝ ናቸው። እውነተኛ የምንለው የጡንቻ ወይም የነርቭ በሽታ ሲኖር የሚከሰት ነው። አስቴኒያ የሚባለው የጡንቻ አለመታዘዝ ግን የጡንቻ መድከም ነው እንጂ አለመታዘዝ አይደለም፡፤ ይሄ ማለት ድሮ የምናደርጋቸውን ነገሮች በሚፈለገው ፍጥነት ማድረግ አለመቻል ነው። ነገር ግን ሃይል አሰባስቦ ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ ካንሰር እና የኩላሊት በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንዲሁ አይነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ለምሳሌ አንድ ዕቃ ለማንሳት እምቢ ማለት ሳይሆን እንደምንም ብለው ለማንሳት ኃይል ማሰባሰብ ያስፈልጋቸዋል። እንደበፊቱ ቀልጠፍ ብለው ማከናወን አይቻሉ እንጂ አልታዘዘም አይላቸውም። ፊቲግ የሚባለው የጡንቻ መድከም አይነት ደግሞ ጠዋት ላይ ደህና ተሆኖ ከሰዓት በኋላ አለመታዘዝ ሊከሰት ነው። ጠዋት ላይ የነበራቸውን ኃይል ከሰዓት በኋላ በማሟጠጥ ከሰዓት በኋላ ጡንቻቸው ይደክማል። ለምሳሌ ፅሁፍ ሲያነቡ ፅሁፉ ጥርት ብሎ አለመታየት እና አንዱ ፊደል ሁለት ሆኖ መታየት ሊኖር ይችላል። ጠዋት ላይ ጮክ ብለው ያወሩ ከነበሩ ከሰዓት በኋላ ቀስ እያለ መናገር ጠዋት ታክሲ ላይ ደህና ወጥተው ወደ ማታ ታክሲ ላይ ለመውጣት መቸገር ይከሰታል። ብዙ ጊዜ የሚቸገሩትም እቃ ለመስቀል እና ለማውረድ አሊያም እጃቸውን ጭንቅላታቸው ላይ አድርገው ለረጅም ጊዜ ለመቆየት መቸገር ናቸው። መድከሙ የሚከሰተውም ከክርናቸው እስከ ትከሻቸው እና ከጉልበታቸው እስከ ወገባቸው ባሉት ጡንቻዎቻቸው ላይ ነው። ስለዚህ ታክሲ ላይ ለመውጣት እና መሬት ላይ ያሉ መፀዳጃ ቤቶችን ቁጢጥ ብሎ ለመጠቀም ይቸገራሉ። ጠዋት ላይ ተገልጦ የነበረው አይናቸውም ከሰዓት በኋላ ይከደናል። ከተከደነም ለመግለጥ አስቸጋሪ ይሆናል።

ሰንደቅ፡- ይሄ የጡንቻ አለመታዘዝ በተለየ መልኩ ሊከሰትባቸው የሚችሉ የሰውነት ክፍሎች ይኖሩ ይሆን?

ዶ/ር ሜሮን፡- የጡንቻ አለመታዘዝ የመንስኤ ቦታዎች በሁለት ይከፈላሉ። ይኸውም ማዕከላዊ (central) እና ፔሪፈራል (peripheral) ተብለው ይከፈላሉ። ማዕከላዊ የምንለው አንጎል እና ሀብለሰረሰር ላይ ጉዳት ሲደርስ የሚከሰት ነው። ፔሪፈራል የምንለው ደግሞ በነርቭ ላይ ወይም በጡንቻ ላይ አሊያም በጡንቻና ነርቭ መገናኛ ላይ ጉዳት ሲደርስ የሚከሰት ነው። ፋቲግ የተባለው የጡንቻ አለመታዘዝ የሚከሰተው እዚህ ጋር ነው። ይህ የጡንቻ መዛል የሚከሰተውም ከነርቭ ወደ ጡንቻ መልክት ሊተላለፍ ሲል በትክክል የሚቀበለው ሳይኖር ሲቀር የሚከሰት ነው።

ፔሪፈራል ላይ የሚከሰተው የጡንቻ አለመታዘዝ ሁለት ቦታዎች ላይ ሊከሰት ይችላል። የመጀመሪያው ፕሮክሲማል የሚባለው ሲሆን ይሄን አይነት መዛል የሚከሰተው ከክርን በላይ እና ከጉልበት እስከ ወገብ ባለው የሰውነት ክፍል ላይ የሚከሰት የመዛል ችግር ነው። ይሄ የሚከሰተውም በኢንፌክሽን ምክንያት ሊሆን ይችላል። በዚህኛው አይነት ችግር ጉዳቱ የሚኖረው በጡንቻው ወይም በጡንቻና ነርቭ መጋጠሚያ ላይ ችግር ሊኖር ይችላል። ሁለተኛው ደግሞ ዲልታል የተባለው ነው። ይኼንኛው በነርቭ ላይ ችግር ኖሮ በእግር ከቁርጭምጭሚት በታች እና በእጅ አንጓ (wlist) በታች ያለው የሰውነተ ክፍል አልታዘዝ ሲል የሚከሰት ነው።

ሰንደቅ፡- ለጡንቻ አለመታዘዝ የተለያዩ የበሽታ አይነቶች እንደምክንያት የሚቀመጡ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ምክንያቶቹ ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ሜሮን፡- ለጡንቻ አለመታዘዝ እጢ እና ስትሮድ መንስኤ ናቸው። በተጨማሪም የተለያዩ ኢንፌክሽኖች፣ ጭንቅላት በዱላ መመታት፣ በሽታን የመቋቋም ኃይል መዳከም፣ ካንሰር፣ ኢንፍላሜሽን፣ ከወሊድ ጋር የተያያዘ ችግር፣ የስኳር ህመም፣ የሚጥል በሽታ እንዲሁም ከአስተዳደግ ጋር የተያያዙ ችግሮች ምክንያት ሊሆኑ ይችላል። በአስተዳደግ ወቅት ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በበቂ ሆኔታ አለማግኘት ሊዘህ ችግር ሊያጋልጥ ይችላል። በአጠቃላይ ግን ለእንቅስቃሴ የሚያገለግለው የአንጎላችን ክፍል ጉዳት ከተደረሰበት ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው። ስትሮክን የመሳሰሉ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ወይም የደም ቧንቧ መዘጋት መንስኤ ሊሆን ይችላል።

ሰንደቅ፡- የጡንቻ አለመታዘዝ ችግር የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት ይታወቃል። እነዚህ ደረጃዎች ምን ምን  ናቸው? በደረጃ የሚቀመጡትስ በምን መነሻ ነው?

ዶ/ር ሜሮን፡- ህመምተኞች በሚሰጡት መረጃ ላይ ተመስርቶ ለዚህ ችግር ደረጃዎች አሉት። ዋናው የደረጃዎቹ መስፈርት ችግሩ የቆየበት ጊዜ ነው። በዚህ መሠረት ችግሮቹን በሶስት ደረጃ ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው አጣዳፊ (acute) ሲሆን ሁለተኛው መካከለኛ (sub acute) እንዲሁም ሶስተኛው ስር የሰደደ (chronic) ናቸው። አጣዳፊ የሚባለው ከመቅፅበት የሚከሰት እንደ ስትሮክ ያለ ነው። ጡንቻ ወዲያው በደቂቃ ወይም በሰከንድም ውስጥ አልታዘዝ ቢል ይሄ አጣዳፊ ነው። መካከለኛ የሚባለው ደግሞ ችግሩ ጀምሮ በቀናት ወይም በወራት ውስጥ እየተባባሰ ሲሄድ የሚፈጠር ነው። ለዚህ አይነቱ ችግር መንስኤው ብዙ ጊዜ ኢንፌክሽኖች ናቸው። ስር የሰደደ የሚባለው ግን ችግሩ የተከሰተው በአመታት እድሜ ውስጥ ሲሆን ነው። ለዚህኛው ችግር መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉት ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከውልደት ጀምሮ ለጡንቻ ህመም የሚያጋልጥ ጂን ይዞ ከተወለደ ሰው ለዚህ ችግር ሊጋለጥ ይችላል። ለምሳሌ ዶቼኒ የተባለው የጡንቻ አለመታዘዝ አይነት በወንዶች ላይ ብቻ በስድስት ዓመታት ዕድሜያቸው አካባቢ የሚጀምራቸው እና ቁጭ ብለው ለመነሳት እንዲቸገሩ የሚያደርጋቸው ነው። ችግሩ እየባሰ በመሄድ ዌልቸር ላይ እንዲውሉ የሚያደርጋቸው ሲሆን፤ በህይወት መቆየት የሚችሉትም ቢበዛ እስከ 20 አመት ብቻ ነው። በደንብ ለመተንፈስ እና ለመዋጥ ስለሚቸገሩ ለኢንፌክሽን ተጋልጠው ህይወታቸው ያልፋል።

ሰንደቅ፡- የጡንቻ አለመታዘዝ በምን መልኩ ነው ሊከሰት የሚችለው? አንዳንድ ጊዜ በአንደኛው የሰውነት ክፍል  ላይ ብቻ የመዛል ከስተት የሚስተዋለው ከምን የተነሳ ነው?

ዶ/ር ሜሮን፡- አንዳንዴ ሁለቱም እግር ብቻ፣ ወይም ሁለቱም እጅ ብቻ አሊያም አራቱም ሊሰንፉ ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ ግማሽ የሰውነት ክፍል ሊሰንፍ ይችላል። ብዙ ጊዜ ግማሽ ሰውነትን ከፍሎ የሚከሰተው ችግር ከአንጎል ችግር ጋር የተገናኘ ነው። ምግብ በምንመገብበት ወይም ውሃ በምንጠጣበት ወቅት የመዝረክረክ ችግር ካለው በጭንቅላት ላይ ችግር አለ ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፊት ደህና ሆኖ እጅና እግር የሚሰንፍ ሲሆን ህብለሰረሰር ላይ ችግር ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ ግን እንደተጎዳው የአንጎልና የህብለሰረሰር አይነት የጡንቻ መዛል ችግሩ የሚከሰትበት የሰውነት ክፍሎች ላይ የጡንቻ አለመታዘዝ ይከሰታል።

ሰንደቅ፡- አንድ ሰው የጡንቻ አለመታዘዝ እንዳለበት ለመለየት የሚያሳያቸው ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ሜሮን፡- የሚያሳያቸው ምልክቶች እንደየተጎዳው የሰውነት ክፍል ይለያያል። የመጀመሪያው የሰውነት አለመታዘዝ ነው። ችግሩ ያለው ከክርን እስከ ትከሻ እና ከጉልበት እስከ ወገብ ባለው ጡንቻ ላይ ከሆነ እጅን ወደ ላይ ዘርግቶ መቆየት አለመቻል፣ እጅን ራስ ላይ አድርጎ አለመቆየት ሊከሰት ይችላል። ችግሩ ያለው ከእጅ አንጓ በታች ባለው የሰውነት ክፍል እና ከቁርጭምጭሚት በታች ባለው የእግር ክፍል ላይ ከሆነ ለመጻፍ መቸገር፣ በር ለመቆለፍ እና ለመክፈት መቸገር፣ የልብስን ቁልፍ ለመዝጋት እና ለመክፈት መቸገር ይስተዋላል። በአጠቃላይ ቁጭ ብሎ ለመነሳት መቸገር፣ ምግብ ሲያላምጡ ምግቡ መዝረክረክ፣፣ አለመጨበጥ እና ድንዝዝ የማለት ችግር ይስተዋላል። ስትሮክ ከሆነም በድንገት ለመታዘዝ አለመቻል ይከሰታል። ስትሮክ የተከሰተው በህብለሰረሰር ላይ ከሆነ ሽንትን እና ሰገራን መቆጣጠር አለመቻል ችግር ሊከሰት ይችላል። የተጎዳው ንግግርን የሚቆጣጠረው የግራ አእምሮ ክፍል ከሆነ አንደበትን የመዝጋት ሁኔታ ይስተዋላል። የማንቀጥቀጥ እና የማንዘፍዘፍ ሁኔታ በአንዱ ሰውነት ክፍል ላይ ሊከሰት ይችላል።    

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
2245 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 121 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us