መተቃቀፍ - ከሠላምታም ያለፈው ፈውስ

Wednesday, 31 August 2016 12:26

 

በማንኛውም ምክንያት ቢሆን እርስ በእርስ መተቃቀፍ ስሜትን ከመግለፅ ባለፈም ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ነው ጥናቶች የሚጠቁሙት። ብዙዎቻችን የደስታ ስሜታችንን ለመግለፅ አሊያም በጣም የምንወደውን ሰው ስናገኝ ናፍቆታችንን ለመግለፅ እና ፍቅራችንን ለመጋራት በማሰብ ነው የምንተቃቀፈው። ነገር ግን መተቃቀፍ በሁለቱም ወገን የሚኖረው ጠቀሜታ ከምንገምተው በላይ ነው ባይ ናቸው የዘርፉ ባለሞያዎች። ሳይንስ ኦፍ ዶምሽን በሚል ርዕስ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ፋደህ ባሺር የተባሉ ባለሞያም መተቃቀፍ ስሜትን ከመግለፅ በዘለለ በራስ መተማመን እንዲኖር እና የተፈላጊነት ስሜትን ለማዳበር ያለው ጠቀሜታ የትየለሌ እንደሆነ አስቀምጠዋል።

ሰዎች በሚተቃቀፉበት ወቅት ሰውነታቸው በፒቱታሪ እጢ አማካይነት ኦክሲቶሲን የተባለውን ሆርሞን በብዛት እንዲያመነጭ ያደርገዋል። ይሄ ሆርሞን ደግሞ አእምሯችን የመገለል፣ የብቸኝነት እና የብስጭት ስሜቶች እንዳይሰሙን እንዲያደርግ ያግዘዋል። በተቃራኒው ደግሞ የመፈለግ እና የቆራጥነት ስሜት እንዲሰማን በማድረግ ከሰዎች (ከአቃፊዎቹ) ጋር የሚኖረው ግንኙነት የበለጠ እንዲዳብር ያደርገዋል። በዚሁ ጊዜ የደህንነት ስሜት እንዲሰማ እና የታማኝነት ስሜትም እንዲዳብር ያደርጋል ይላሉ ዶ/ር ፋዳህ። ይህ ኦክሲቶሲን የተባለው ሆርሞን ኮርቲሶል የተባለው እና ለጭንቀት፣ ለልብ ህመም እና ለከፍተኛ የደም ግፊት መፈጠር መንስኤ የሚሆነው ሆርሞን የመመንጨት ፍጥነትም እንዲቀንስ ያደርገዋል ይላል ጥናቱ።

ሌላው ሰዎች በሚተቃቀፉበት ወቅት ሰውነት የሚያመነጨው ሆርሞን ኢንዶርፊን የተባለው ሆርሞን ነው። ኢንዶርፊን ሆርሞን ደግሞ አእምሯችን ውስጥ የሚገኙ የህመም ስሜት መስመሮችን በመዝጋት ህመሙ ስሜት በሰውነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖረው የማድረግ አገልግሎት ይኖረዋል። እግረመንገዱንም የስስ ህዋሳትና (Soft tissues) ዝውውርን በማላላት የህመም ስሜት እንዳይሰማ ያደርጋል። ለዚህም ነው ሰዎች በሚተቃቀፉበት ጊዜ የመደሰት እና ከጭንቀት የመላቀቅ ስሜት የሚሰማቸው ይላሉ ባለሞያው።

ሌላው በመተቃቀፍ ወቅት አእምሯችን በብዛት የሚያመነጨው ዲፓሚን የተባለው ሆርሞን ነው። ይሄ ሆርሞን የደስታ ሆርሞን (pleasure hormone) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ይሄ ሆርሞን በሰውነት ውስጥ በመመንጨት የደስታ ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል ይላሉ ጥናቶች።

እንደ ፊዚዮቲራፒስቱ ቪርጂን ሳተር ጥናት ገለፃ አንድ ሰው ጤናማ ህይወት ለመኖር በቀን አራት ጊዜ፣ ከደረሰበት ስሜት ለመላቀቅ በቀን ስምንት ጊዜ እንዲሁም የበለጠ ለማደግ እና ለመዳበር በቀን 12 ጊዜ መተቃቀፍ አለበት። ጥናቶች እንዳመለከቱትም መተቃቀፍ የልብ ምት ፍጥነትን ለማስተካከል፣ የደም ግፊትን ለመቀነስና ከህመም የመዳኛ ጊዜን ለመቀነስ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በተለይ 20 ሰኮንድ እና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የሚቆይ መተቃቀፍ እና የእጅ መጨባበጥ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትን የመከላከል ጠቀሜታ አለው። በዚህም ከጭንቀት ጋር ተያይዞ የሚከሰትን ከፍተኛ የደም ግፊት ለመቀነስ እንዲሁም የልብ ምት ፍጥነትን ለማስተካከል መተቃቀፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይሄ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት ደግሞ በጭንቀት ወቅት የሚመነጨው ኮርቲሶል መጠን በመተቃቀፍ ወቅት ስለሚቀንስ ነው።

የሰው ልጅ ቆዳ የእንቁላል ቅርፅ ያላቸው ቀጫጭን የግፊት  ማዕከል የሆኑ እና ፓሲኒያን የተባሉ ድሮች (network) አሉት የሚሉት ፊዚየቴራፒስቱ ቫርጂን ሳተር፣ እነዚህ ድሮችም በመተቃቀፍ ወቅት የሚፈጠረውን ንክኪ ወደ አእምሮ የማድረስ አገልግሎት እንደሚሰጡ አስረድተዋል። በዚህ ጊዜም አእምሯችን መልእክቱን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በማድረስ ሰውነታችን የምቾት፣ የደስተኝነት ስሜት እንዲሰማው እንዲሁም ከድብርት የመላቀቅ ስሜት ውስጥ እንዲገባ ያግዛል። በተጨማሪም መተቃቀፍ በሽታ የመከልከል አቅምን የማዳበር፣ ኢንፌክሽኖችን የመከላከል እንዲሁም ድብርትና ተያያዥ ችግሮችን የማስወገድ አገልግሎት ይኖረናል ይላሉ ፊዚዮቴራፒስቱ።

መተቃቀፍ የሰው ልጅ የደስተኝነት ስሜት እንዲያሻቅብ የማድረግ አገልግሎትም አለው። ይሄም የሚሆነው ስንተቃቀፍ አእምሯችን ሶሮይኒን የሚባለውን ሆርሞን በብዛት ማመንጨት ስለሚጀምር ነው። ይህ ሆርሞን ስለራሳችን ያለን አመለካከት ቀና እንዲሆን፤ ደስተኛ እንድንሆን፤ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማን እና ጭንቀት ካለብንም እንዲለቀን የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በተጨማሪም በመተቃቀፍ ወቅት አንጎላችን ኢንዶርፊን የተባለውን ንጥረ ነገር በማመንጨት እና ንጥረ ነገርን ወደ ደም ስር በማስገባት የደስተኝት ስሜት እንዲፈጠር እና የሃዘን ስሜት ደግሞ በአንፃሩ እየቀነሰ እንዲመጣ የማድረግ ጠቀሜታ አለው የሚለው በኤምኔ ዩኒቨርስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ የተካሄደ ጥናት ነው፡፡ በዚህ ጥናት እንደተረጋገጠውም የኮርቲሶል ሆርሞን መጠን መቀነስ ለስኳር ህመም እና በደም ውስጥ ለሚፈጠር ከፍተኛ የስኳር ክምችት መጋለጥን ይከላከላል።

በደቡብ ካሮሊና ቻፕል ሂል ዩኒቨርስቲ የተደረገ አንድ ጥናት ይፋ እንዳደረገው ደግሞ መተቃቀፍ የልብ ምት ፍጥነትን ይቀንሳል። በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ምንም አይነት የመተቃቀፍ ባህል የሌላቸው ተሳታፊዎች የመተቃቀፍ ልምዱ እና አጋጣሚው ካላቸው ጋር ሲነፃፀሩ የልብ ምታቸው በደቂቃ አስር ጊዜ ሆኖ ተገኝቷል። የመተቃቀፍ እድል ያላቸው ግን ልባቸው የሚመታው በደቂቃ አምስት ጊዜ ብቻ ሆኖ ነው የተገኘው። የልብ ምት ፍጥነት መቀነስ ደግሞ የደም ግፊት ዝቅተኛ እንዲሆን እና የልብ ጤንነትም የተጠበቀ እንዲሆን ያደርገዋል ሲል ጥናቱ አስቀምጦቷል። ሌላው በጥናቱ የተካተተው የመተቃቀፉ ጠቀሜታ መተቃቀፍ በሽታን የመከላከል አቅምን እንደሚያዳብር ነው። በመተቃቀፍ ወቅት ስሜታዊ የሆኑ ክስተቶች የነጭ ደም ሴልን የሚያመጣጥነው እጢ ንቁ እንዲሆን ያደርጉታል። በዚህም በቂ እና ለሰውነት አስፈላጊ የሆነ ነጭ የደም ሴል በሰውነት ውስጥ በመመንጨት ሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅሙ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ከዚህ ውጪ መተቃቀፍ የሰውነት ጡንቻዎች የመፍታታት እና የመዝናናት ስሜት እንዲፈጠርላቸው የማድረግ ጠቀሜታ አለው። መተቃቀፍ አንድ ሰው መስጠትና መቀበልን የሚማርበት ዋናው መንገድ እንደሆነም ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት፡፡ በተጨማሪም በመተቃቀፍ ወቅት በሚተቃቀፉ ሰዎች መካከል እኩል የሆነ የደስተኝነት ስሜትንና ፍቅርን በመካፈል በሁለቱ ወገን ያለውን ስሜት ለማዳመጥ ያግዛል። ሰዎች ሲተቃቀፉ በህይወት ውስጥ ያሉ ነገሮችን የመጋራት ስሜትን ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ፣ ከህይወት የእለት ተእለት ሽክርክሪት ውስጥ ወጥተን ለተወሰነ ጊዜ በሌሎች ዘንድ ስላለን ተፈላጊነት እና ተደማጭነት እንድናስብ ያደርገናል ሲል በቻፕል ሂል የተደረገው ጥናት ያመለክታል።

መተቃቀፍ በአዋቂነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች ብቻም ሳይሆን በህፃናት ላይ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ሆኖ ነው የተገኘው። ገና ከህጻንነታቸው ጀምሮ በወላጆቻቸው በበቂ ሁኔታ የመታቀፍ እና የመተሻሸት እድል ያገኙ ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን፤ ወደ ስራ አለም በገቡበት ወቅት በተሰማሩበት ስራ ላይ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ሆነው ተገኝተዋል። መተቃቀፍ በማንኛውም እድሜና ፆታ ዘንድ ለበርካታ ችግሮች መፍትሔና ለብዙ ህመሞችም ፈውስ እንደሚሰጥ ነው ባለሞያዎቹ ያረጋገጡት።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
2113 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 120 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us