ጥንቃቄን የሚጠይቁት ሲቲ ስካን እና ኤም አር አይ

Wednesday, 07 September 2016 13:48

 

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በየዓመቱ መጨረሻ “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መርህ ነፃ የኤም አር አይ፣ የሲቲ ስካን፣ የአልትራሳውንድ፣ የዲጂታል ኤክስሬይ እና ኢኬጂ ምርመራዎች ሲያደርግ ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል። ምርመራዎቹ በየዓመቱ የሚሰጡት ምርመራውን ከፍለው የማድረግ አቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲሆን፤ የምርመራው ተጠቃሚዎችም ከመንግስት ሆስፒታሎች እነዚህን ምርመራዎች እንዲያደርጉ የታዘዘላቸው ናቸው። ማዕከሉ እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው ነፃ የምርመራ አገልግሎቶች ከ15 ሺህ በላይ ዜጐች ተጠቃሚ ሆነዋል። ዘንድሮም ከጳጉሜ 1 እስከ 5 ቀን 2008 ዓ.ም የሚካሄደውን የምርመራ ዝግጅት አስመልክቶ ባለፈው ሐሙስ በሸራተን ሆቴል የጋዜጣዊ መግለጫ እና የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በእለቱ በመድረኩ ላይ ሲቲ ስካን እና ኤም አይ አር የምርመራ አይነትን አስመልክቶ በባለሙያ ገለፃ አድርገው ነበር። ባለሙያው ዶ/ር ተስፋዬ ከበደ ሲሆኑ፤ ዶ/ር ተስፋዬ የኢትዮጵያ ራዲዮሎጂ ማኅበር ፕሬዝደንት ናቸው። ባለሙያው የምርመራዎቹን ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም አስፈላጊነት አስመልክቶ ያቀረቡት እውነታ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።

 

የሲቲ ስካን እና ኤም አር አይ ምርመራ በሀገራችን መተግበር ከጀመረ ከአምስት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። በአሁኑ ወቅትም በሆስፒታሎች እና በክሊኒኮች በከፍተኛ ሁኔታ ለአገልግሎት እየዋሉ ይገኛሉ። እነዚህ ምርመራዎች የተፈጠረውን የጤና እክል ለማወቅ እና ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም፤ ከጠቀሜታዎቻቸው ጐን ለጐን ደግሞ የሚያስከትሏቸው ችግሮችም እንዳሉ ባለሙያው ገልፀዋል። በመሆኑም የምርመራው ተጠቃሚዎችም ሆኑ ምርመራው እንዲደረግ የሚያዘው ባለሙያ ስለምርመራዎቹ ጠቀሜታ እና ስለሚያስከትሏቸው ችግሮች በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ ዶ/ር ተስፋዬ ገልፀዋል። ዶ/ር ተስፋዬ የሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ የሚከተለው ነው፡-

 

ድሮ ሲቲ ስካን በሌለበት ጊዜ አንድ ሰው ወድቆ ወይም ለስትሮክ ተጋልጦ ወደ ህክምና ሲመጣ የሚታከመው ጉዳቱን በዓይን በማየት እና ቀደም ብሎ ካለው የህክምና ታሪክ (Medical History) በመነሳት ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ማንም ባለሙያ ያለ ሲቲ ስካን ወይም ያለ ኤም አር አይ ምርመራ የሰውን ጭንቅላት መክፈት አይችልም። ስለዚህ ቴክኖሎጂው እየመጣ ሲሄድ የመጠቀም ፍላጐቱ እያሻቀበ፣ ኅብረተሰቡም ለመጠቀም ጥያቄ የማቅረብ ሁኔታው እያደገ እንዲሁም ባለሙያዎችም ይሄን ምርመራ የማዘዝ ሁኔታ እየጨመረ ይመጣል። ሁኔታው እየተለመደ ሲመጣም ከእነዚህ ምርመራዎች ጠቀሜታ ተጓዳኝ የሆኑ ችግሮችን ወደመርሳት ይመጣል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በዘመቻ መልክ ከፍለው ምርመራውን ማድረግ ለማይችሉ ሰዎች ነፃ የምርመራ አገለግሎት ለመስጠት በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ ምርመራዎቹ ለጠቅላላ ምርመራ ያገለግላሉ ከሚል የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ሰዎች ለራሳቸው ምርመራውን ሲያዙ ይታያሉ።

 

ሲቲ ስካን (Computed Tomography) በጨረር የሚሰራ መሣሪያ ነው። ይህ መሣሪያ በሰውነት ውስጥ ያሉ የሰውነት ክፍሎችን ሁኔታ ጥርት ባለ መልኩ የሚያሳይ ነው። መሣሪያው በሰው ልጅ እና በእንስሳት የሰውነት የውስጠኛው ክፍል ላይ ያሉትን ትክክለኛ እና ትክክለኛ ያልሆኑ ቅርጾች ለመለየት ያግዛል። የሲቲ ስካን ምርመራ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ምርመራ ለማድረግ የሚያገለግል የምርመራ አይነት ነው። ይሄን አይነቱን ምርመራ የሰውነት የውስጥ አካላትን፣ የአጥንት፣ የለስላሳ የሰውነት ህዋሳትን እንዲሁም የደምስሮችን ሁኔታ በመመርመር ጥልቅ መረጃ ለመስጠት የሚያገለግል የምርመራ አይነት ነው። በተለይ ስስ የሆኑ የሰውነት ህዋሳትን እና የደምስሮችን በተመለከተ ከራጅ ምርመራ የተሻለ መረጃ በመስጠት ረገድ ቀዳሚው ነው። የሲቲ ስካን ምርመራ ከራጅ ምርመራ ጋር ሲነፃፀርም በፍጥነት ውጤቱን ለማወቅ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ የሚያስገኘው ውጤት እርግጠኛ የሆነ ውጤት ነው።

 

የሲቲ ስካን (Computed Tomography) በባህሪው ጨረርን በመጠቀም የሚሰራ መሣሪያ ነው። ጨረር ደግሞ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሲውል የሚያስከትላቸው ችግሮች አሉ። የሲቲ ስካን ምርመራ ሲደረግም በሰውነት ውስጥ ጨረር እንዲያልፍ ነው የሚደረገው። ይሄ የሲቲ ስካን ምርመራ የሚጠቀመው ጨረር ደግሞ የራጅ ምርመራ ከሚጠቀመው የጨረር መጠን የላቀ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው አንድ የሆድ ሲቲ ስካን (Abdominal Ct) ቢነሳ ሰውነቱ አምስት ሚሊ ሲቨርት የሆነ ጨረር ይቀበላል። ይሄ ማለት ደግሞ የአንድ መቶ ራጅ ምርመራ ከሚያመነጨው የጨረር መጠን ጋር እኩል ነው። ሰዎች በተደጋጋሚ የሲቲ ስካን ምርመራ በሚያደርጉበት ጊዜ ለጨረር የመጋለጥ እድላቸውም ያንኑ ያህል እየጨመረ ይመጣል። አንድ ሰው አንዴ፣ ሁለቴ፣ ሦስቴ የሲቲ ስካን ምርመራ ማድረግ ይችላል። ነገር ግን ምርመራውን ባደረገ ቁጥር ለጨረር ይጋለጣል። በእያንዳንዱ የሲቲ ስካን ምርመራ ጊዜ የሰውነት ለጨረር የመጋለጥ እድል እየጨመረ በመሄድ ብዙ ጊዜ ለጨረር እየተጋለጠ በሄደ ቁጥር ከአስር ወይም ከሃያ ዓመት በኋላ ለካንሰር ህመም ያለ ተጋላጭነት ይጨምረዋል። አንድ ሰው ከሃያ በላይ የሆድ ሲቲ ስካን ቢነሳ ከአስር ወይም ከሃያ ዓመት በኋላ ለካንሰር የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ይሆናል። ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ደግሞ ረጅም እድሜ የመኖር እድሉ የቀነሰ ይሆናል።

 

ጨረር በባህሪው የሚያጠቃው ቶሎ ቶሎ የሚያድጉ የሰውነት ክፍሎችን ነው። ከዚህ ሳቢያ ከሲቲ ስካን የሚመነጨው ጨረር የበለጠ የሚያጠቃቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ ህፃናት፣ ነፍሰጡር ሴቶች፣ ከወንዶች ይልቅ ሴቶችም ለዚህ ጨረር የበለጠሪ ተጋላጮች ናቸው። እድሜያቸው ትልቅ የሆኑ ሰዎች ለዚህ የሲቲ ስካን ጨረር የሚጋለጡትም ቶሎ ቶሎ የሚያድጉ የሰውነት ክፍሎቻቸው በጨረር ስለሚጠቁ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን የጉዳቱ ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታይ ባይሆንም፤ ምርመራው እየተደጋገመ በሄደ ቁጥር ከጊዜ በኋላ ለችግር የሚያጋልጥ ስለሆነ ለምርመራው ከመጣደፍ በፊት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

 

በህክምና ዘርፍ ከትንሿ ፓራስታሞል ጀምሮ ሁሉም ከጥቅማቸው ጐን ለጐን ጉዳት አላቸው። ነገር ግን የሚያስገኙት ጥቅም እና የሚያስከትሉት ጉዳት ተመዛዝኖ ነው አገልግሎት ላይ የሚውሉት። ልክ እንደዚህ ሁሉ ሲቲ ስካንም ጥቅሙ እና ጉዳቱ ተመዝኖ ስራ ላይ መዋል አለበት። የመጀመሪያው ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ ወደዚህ ምርመራ ከመግባት በፊት ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ነው። ቀጥታ ወደ ሲቲ ስካን ከመሄድ ይልቅ ሌሎች ጨረር አመንጪ ያልሆኑ መሣሪያዎችን የሚጠቀሙ ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። በእነዚህ መሣሪያዎች በመጠቀም በሚደረጉ ምርመራዎች መዳን ከተቻለ ለጨረር የሚኖረውን ተጋላጭነት ያስቀረዋል ማለት ነው።

 

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ባለሙያው ምርመራዎችን ሲያዝ መጠንቀቅ አለበት። ባለሙያው የሲቲ ስካን ምርመራ ከማዘዙ በፊት ምርመራው በትክክል አስፈላጊ ነው ወይ? በሌላ የምርመራ መሣሪያዎች ተጠቅሞ ምርመራ ማድረግ አይቻልም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። ለምሳሌ አልትራሳውንድ አለ፣ ክሊኒካል ኢቫዩዌሽን አለ፣ ላብራቶሪ ኢንቨስቲጌሽን አለ። ስለዚህ ሲቲ ስካን ለማዘዝ ከመወሰን በፊት ሁሉንም በየደረጃው መገምገም ያስፈልጋል። በጣም አስፈላጊ ከሆነ መሰራት አለበት። ካልሆነ ግን መሰረዝ ነው ያለበት።

 

ሌላው ለተመሳሳይ ምርመራ የሚያገለግለው የምርመራ አይነት ኤም አር አይ (Magnetic Resonance Imaging) ነው። ይሄንኛው የምርመራ አይነት ከሲቲ ስካን ለየት የሚያደርገው ጨረር አለመጠቀሙ ነው። ኤም አር አይ ማግኔት እና ማግኔቲክ ፊልድ የሚጠቀም ምርመራ ነው። ይሄንኛው የምርመራ አይነት የሬዲዮ ሞገድን እና ማግኔትን ተጠቅሞ የሚደረግ የምርመራ አይነት ነው። ስለዚህ ይሄንኛው የምርመራ መሣሪያ መቶ በመቶ ከጨረር ነፃ የሆነ መሣሪያ ነው። ምናልባት ምርመራው የሚደረገው ጠበብ ባለ ክፍል ውስጥ ስለሆነ ለእንደዚህ አይነት ነገር ፍርሃት (Phobia) ላለባቸው ሰዎች ምቾትን ላይሰጥ ይችላል እንጂ የሚያመጣው ችግር ከሲቲ ስካን ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው።

 

የኤም አር አይ ምርመራ በሚደረግበት ወቅትም ሆነ ባለሙያው በሚያዝበት ወቅት አስቀድሞ መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች አሉ። ኤም አር አይ ስካነር የሚፈጠሩት ጠንካራ የማግኔት ፊልዶች ብረት ነክ የሆኑ ቁሳችን በከፍተኛ ጉልበት የመሳብ ባህሪይ አላቸው። ስለዚህ አንድ ሰው ወደ ምርመራ ማሽኑ ከመግባቱ በፊት በሰውነቱ ላይ እና በሰውነቱ ውስጥ ከማግኔት ጋር ሊቃወሙ የሚችሉ ብረት ነክ ነገሮች አለመኖራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በልብ ውስጥ የሚቀበሩ፣ ስቴንት እንዲሁም በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ብረት ነክ የሆኑ ነገሮች አለመኖራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ኤም አር አይ ማግኔት እንደመሆኑ ማግኔቲክ የሆኑ ነገሮች በሙሉ በማግኔቱ ዙሪያ ሊሳቡ አሊያም ሊወረወሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የፀጉር ማስያዣ ሽቦዎች፣ የሒጃብ ሽቦዎች ተወርውረው በመምጣት በሰው ላይ ወይም በማሽኑ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። ስለዚህ በምርመራ ወቅት ብረት ነክ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ከአካባቢው መወገድ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት ያለበት ምርመራውን የሚያዘው ባለሙያ፣ የምርመራው ተጠቃሚ እና በየደረጃው ያሉ አካላት ሁሉ ናቸው።

 

በአጠቃላይ በተለይ የሲቲ ስካን ምረመራ ከመታዘዙ በፊት አስፈላጊነቱ መረጋገጥ አለበት። ባለሙያው ስለጥቅም እና ጉዳቱ ለማኅበረሰቡ በቂ መረጀ መስጠት አለት። ራዲዮሎጂስቶችም በተለይ ጨረር በሰውነት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ለባለሙያውም ሆነ ለታካሚው በቂ ማብራሪያ መስጠት አለበት። አንድን ሰው ከጨረር ነፃ ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ምርመራውን አለማዘዝ ነው። ነገር ግን ያ ሰው የጨረር ምርመራ ሳይደረግለት መታከም ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የጨረር ህክምናው የሚኖረው ጥቅም ከጉዳቱ ጋር ተነፃፅሮ መወሰን ያስፈልጋል።¾   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1954 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 121 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us