ስልጣኔ ያልገታው የሴት ልጅ ጥቃት

Wednesday, 07 December 2016 15:58

  

በዚህ በሰለጠነ ዘመን እንኳን የሴት ልጅ ጥቃት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሰሞኑን የተለያዩ አካላት ጥናቶች ይፋ እያደረጉ ነው። መረጃዎቹ እየወጡ ያሉትም በየዓመቱ በፈረንጆቹ ኖቬምበር 25 ቀን የሚከበረውን የፀረ የሴት ልጅ ጥቃት ቀን አስመልክቶ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል የዓለም ጤና ድርጅት አንዱ ሲሆን፤ እንደ ድርጅቱ የቅርብ ጊዜ መረጃ ከሆነ በዓለማችን ላይ ከሚኖሩ ሴቶች መካከል 35 በመቶዎቹ ለአካላዊ ወይም ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው። ችግሩን አሳሳቢ ያደረገው ነገር ደግሞ ጥቃቱ እየተፈፀመ ያለው በቅርብ ሰው (በባል፣ በወንድ ጓደኛ እና በዘመድ) መሆኑ ነው። በዚህ መሠረትም ከሶስት ሴቶች አንዷ ለዚህ የቅርብ ሰው ጥቃት የተጋለጠች ናት። ከወንዶች ጋር በፆታዊ ግንኙነት ውስጥ ከሚኖሩ የዓለማችን ሴቶች መካከልም 30 በመቶዎቹ በህይወት ዘመናቸው ለአካላዊ ወይም ለጾታዊ አሊያም ለሁለቱም ጥቃቶች ተጋልጠዋል ይላል በመገባደድ ላይ ባው የፈረንጆች ህዳር ወር የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ።

በሴቶች ላይ እየተፈፀሙ ያሉት ፆታዊም ሆነ አካላዊ ጥቃቶች በሴቷ ላይ በቀሪው ህይወቷ ሁሉ የሚከተሏት መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ እስከ ህይወት መጥፋት የደረሰ ዋጋም እያስከፈለ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል። ጥቃቱን የሚያደርሱት ቅርብ ወንዶች እንደመሆናቸው ሁሉ በርካታ ሴቶችም በእነዚሁ በቅርብ ወንዶች ህይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ። በዚህም መሠረት በዓለም ላይ ከሚከሰቱ የሴት ልጅ ሞት ውስጥ 38 በመቶው የሚፈፀመው በቅርብ ወንድ (ባል፣ ፍቅረኛ እና ዘመድ) ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴት ልጅ ጥቃትን በዚህ መልኩ ይገልፀዋል። “ማንኛውም ፆታዊን መሠረት አድርጎ የሚፈፀም እና በሴቷ ላይ አካላዊ፣ ፆታዊ ወይም የአእምሮ ጉዳት የሚያስከትል፤ ሴቷን የሚያሰቃይ፣ የፍራቻ ስሜትን የሚፈጥር እና በማስገደድ ወይም ያለፈቃዷ ነፃነቷን በሚገፍ መልኩ በአደባባይ ወይም በግል ህይወቷ ላይ የሚፈፀም ተግባር ነው” ይላል። በተያያዘም በቅርብ ሰው የሚፈፀም ጥቃትን (intimate partner violence) የሚለውንም በዚህ መልኩ ያብራራዋል። “በሴቷ ላይ አካላዊ፣ ፆታዊ ወይም ስነልቦናዊ ጉዳቶችን ሊያደርሰ የሚችል እንደ ጠብ ማጫር፣ ለወሲብ ማስገደድ፣ ስነልቦናዊ ጥቃት ማድረስ እና ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ ያሉ እና በቅርብ ጓደኛ ወይም የቀድሞ ጓደኛ የሚደረግ ጥቃት ነው” ሲል ያስቀምጠዋል። ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም ፆታዊ ጥቃት (sexual violence) የሚለውን ከዚህ በታች በተቀመጠው መልኩ ያብራራዋል። ፆታዊ ጥቃት ማለት “ማንኛውም ኃይልን በመጠቀም የሚደረግ ፆታዊ ድርጊት፣ ፆታዊ ድርጊት ለመፈፀም የሚደረግ ሙከራ ሆኖ ድርጊቱን የሚፈፅመው ሰው ከተጠቂዋ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ያለው ሊሆን ይችላል። በሴቷ ላይ የሚፈፀመው ፆታዊ ጥቃትም አስገድዶ መድፈር እና ማንኛውንም አይነት በግዳጅ የሚደረግ የወሲብ ግንኙነትን ያጠቃልላል”ይላል።

ይህ በተለያየ መልኩ የተገለፀ የሴት ልጅ ጥቃት በተለይም በቅርብ ሰው የሚፈፀመው ጥቃት በሀገራችን በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ እንዳለም ነው ሪፖርቱ ያስቀመጠው። እንደ መረጃው በሀገሪቱ ከሚገኙ ሴቶች መካከል ግማሾቹ አካላዊ ወይም ፆታዊ ወይም ደግሞ ሁለቱም ጥቃቶች በህይወት ዘመናቸው ያጋጥማቸዋል። በተለያየ መልኩ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ፆታዊን መሠረት ያደረገ ጥቃት በከተማ አካባቢ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ በገጠር አካባቢ በሚኖሩ ሴቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚፈፀምም ሪፖርቱ አስቀምጧል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች በተለይ የመጀመሪያውን ፆታዊ ግንኙነት የሚፈፅሙት በግዳጅ ነው።

በሴቶች ላይ የሚፈፀሙት ጥቃቶች የበለጠ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዲያደርሱ የሚያደርጋቸው ችግር ደግሞ ጥቃቱን ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ አለመቻሉ ነው ብሏል መረጃው። ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እንኳን ችግራቸውን አውጥተው ለመናገር አለመድፈራቸው ደግሞ ነገሩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል ብሏል። በዚህ ረገድ በኢትዮጵ ያለውን ሁኔታ ሲያስቀምጥም አካላዊ ጥቃት ከተፈፀመባቸው አስር ሴቶች መካከል አራቱ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው አይናገሩም ብሏል። ከአስር ሚስቶች ስምንቱ ባል ወይም ወዳጅ ቢያንስ አንድ ምክንያት ካለው ሚስቱን መደብደብ አለበት ብለው ያምናሉ፤ ይቀበሉታልም ብሏል። በጥናት ውስጥ የተካተቱ ሚስቶችም ይሄንን እውነት እንደሚቀበሉት መረጃው ጠቁሟል። ባል ሚስቱን ሊደበድብ የሚችልባቸው ምክንያቶችም ምግብ ካሳረረች፣ ከተጨቃጨቀች፣ ወይም ከተከራከረች ሳታስፈቅደው ከቤት ከወጣች፣ ህጻናትን ከዘነጋች እንዲሁም ወሲባዊ ግንኙነት ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነች የሚሉት ናቸው። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ባል ያለምንም ምክንያት ሚስቱን የመደብደብ ስልጣን አለው ተብሎ እንደሚታሰብ ነው መረጃው ያመለከተው።

ጥቃቶች በሴቶች ላይ እንዲፈፀሙ እንዲሁም ወንዶች በሴቶች ላይ ጥቃቶችን እንዲፈፅሙ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ምክንያቶችም ተለይተው ተቀምጠዋል። እነሱም የሁለቱም አካላት የትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ ጥቃት ሲፈፀም እያዩ ማደግ፣ ከመጠን በላይ የሆነ አልኮል ተጠቃሚነት፣ አለመተማመን፣ የሴቶች እኩልነት አለመቀበል፣ በጋብቻ መርካት አለመቻል፣ አለመግባባት፣ ቀደም ብሎ ለጥቃትን ተጋላጭ መሆን እንዲሁም ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ያለው ሕግ የላላ መሆን የሚሉት ይገኙበታል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ጥቃት እየተፈፀመ ያለው በታዳጊዎች እና በህፃናት ላይ ጭምር ነው ተብሏል። በዚህም መሠረት በዓለም ላይ 20 በመቶ ሴቶች እና እስከ 10 በመቶ ወንዶች በህጻንነት እድሜያቸው ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው ያለው መረጃው፤ ይህም ሌላው አለምን እየፈተናት ያለ ችግር ነው ሲል ያስቀምጣል።

የሚያስከትለው መዘዝ

በሴት ልጆች ላይ እየተፈፀመ ያለው ፆታን መሠረት ያደረገ ማንኛውም አይነት ጥቃት የሴት ልጅን ሰብዓዊ መብት ከመጣስ ባለፈም ዋናው የህብረተሰብ ጤና ችግር እየሆነ መምጣቱን ነው የዓለም ጤና ድርጅት የገለፀው። በቅርብ ሰውም ሆነ በማንኛው ሰው የሚፈፀም ፆታዊ ጥቃት በሴቷ ላይም ሆነ በቀጣይ ህይወቷ በምታፈራቸው ልጆች ላይ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ጠባሳን ጥሎባት ያልፋል ይላል። በአጠቃላይ በአካሏ፣ በአእምሮዋ፣ በወሲብ ህይወቷ እንዲሁም በስነተዋልዶ ህይወቷ ላይ ሊገመት የማይችል ችግርን እንደሚያስከትልባት በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሶ መረጃው አትቷል። ከጥቃቅን የጤና መታወክ አንስቶ በህይወት ዘመን ሁሉ የሚከተሏትን አሰቃቂ ችግሮችን ያስከትልባታል ተብሏል።

የመጀመሪያው ፆታዊ ጥቃትን ተከትሎ የሚያጋጥማት ችግር አካላዊ ጉዳት እና ተስፋ መቁረጥ ነው። በዚህም መሠረት በቅርብ ሰው ፆታዊ ጥቃት ከተፈፀባቸው ሴቶች መካከል 42 በመቶዎቹ ለተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች ይዳረጋሉ። ሌላው ፆታዊ ጥቃትን ተከትሎ የሚከሰተው ችግር ካልተፈለገ እርግዝና እና እርሱን ተከትሎ ለሚፈፀም ውርጃ መዳረግ፣ ለተለያዩ የማህጸን ችግሮች መጋለጥ እንዲሁም ለአባላዘር እና ኢንፌክሽን በሽታዎች ተጋላጭ መሆን ናቸው። ድርጅቱ የ2013 ጥናትን ዋቢ አድርጎ እንዳስቀመጠውም አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት የደረሰባት ሴት ከጥቃቷ በኋላ ለኤች አይ ቪ ኤድስ የመጋለጥ እድሏ በ1 ነጥብ 5 ጊዜ ጥቃት ላልደረሰባት ሴት የበለጠ የተጋጠች ሆና ተገኝታለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለውርጃ የመዳረግ እድሏ በሁለት እጥፍ የጨመረ ሆኗል ብሏል።

ፆታዊ ጥቃት የተፈፀመባት ሴት በቀሪ ህይወቷ ሁሉ ያ ድርጊት ከህሊናዋ የማይጠፋ ስለሚሆን ለተለያዩ የስነ-ልቦና ችግሮችም እንደምትጋለጥ ነው የድርጅቱ ማስረጃ የሚጠቁመው። እነዚህ ስነ-ልቦናዊ ችግሮችም ድብርት፣ ጭንቀት፣ የእንቅልፍ እና አመጋገብ መዛባት፣ ያለፈውን ጠባሳ ለመርሳት መቸገር እንዲሁም ራሷን ለማጥፋት ሙከራ ማድረግ ናቸው። ከላይ የተጠቀሰው ጥናት እንዳመለከተውም ለእንዲህ አይነቱ ጥቃት የተጋለጡ ሴቶች ጥቃቱ ካልደረሰባቸው ጋር ሲነፃፀሩ ለድብርት በሽታ የመጋለጥ እድላቸው በሁለት እጥፍ ይጨምራል። እንዲሁም ለተለያዩ መጠጦች ሱሰኝነት የመዳረግ እድላቸውም ሁለት እጥፍ የበለጠ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ አይነቱ ችግር ደግሞ በቅርብ ሰው ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ብቻም ሳይሆን ለማንኛውም ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችን እንደሚያጋጥም ነው መረጃው ያስቀመጠው።

ፆታዊ ጥቃቱ በማንም ይፈፀም በማንም የሚያስከትለው መዘዝ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ይልቁንም ሴቷን ለተደጋጋሚ ራስ ምታት፣ ለጀርባ ህመም፣ ለጨጓራ እና አንጀት ጋር ለተያያዙ ችግሮች፣ ለሆድ ህመም እንዲሁም ለስነ-ተዋዶ ጤና ችግሮች ያጋልጣታል። ብዙ ጊዜ ጥቃቶች የሚፈፀሙት ሴቷ መጠንቀቅ በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆና በመሆኑ ለተለያዩ ስር የሰደዱ ህመሞች ይዳርጋታል። ጥቃቱ የተፈፀመው በህፃንነት ወይም በታዳጊነት እድሜ ላይ ከሆነ ደግሞ ቀሪው ህይወቷ በሙሉ የተመሰቃቀለ እንዲሆን ከማድረግ አንስቶ የሲጋራ፣ የአደንዛዥ ዕፆች እና አልኮል ሱሰኛ እንድትሆን እንዲሁም ጥንቃቄ ለጎደለው ወሲባዊ ግንኙነት እንድትዳረግ ያደርጋታል። በዚህም ሳቢያ ለተደጋጋሚ ፆታዊ ጥቃት እንድትጋለጥ የማድረግ ችግርን ይፈጥርባታል። ጥቃቱ የተፈፀመበት ወንድ ከሆነ ደግሞ በቀጣይ ተመሳሳይ ፆታዊ ጥቃት እንዲያደርስ መነሳሳትን ይፈጥርበታል።

ጥቃት የተፈፀመባት ሴት በጤናዋ ላይ ከሚደርሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት በተጨማሪም የሚያጋጥማት ማህበራዊ ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ጥቃት ሲፈፀም ሴቷ እንደተጠቃች እና እንደተጎዳች ከማሰብ ይልቅ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጣት ከበሬታ እና ተቀባይነት እንዲቀንስ ይዳርጋል። ጥቃት ከፈፀመው ሰው ይልቅ እርሷን ጥፋተኛ ማድረግ ስለሚስተዋልም ሴቷ የተለያዩ ጉዳቶች ይደርሱባታል። ከእነዚህ መካከልም መገለል፣ ስራን በአግባቡ ሰርቶ ቤተሰብን ለማስተዳደር መቸገር፣ የራሷ የሆነ ገቢ ማጣት፣ በማህበራዊ እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በቂ ተሳትፎ ማድረግ አለመቻል እንዲሁም ለራሳቸው እና ለልጆቻቸው ጥንቃቄ እና እንክብካቤ አለማድረግ የሚያጋጥሟት ችግሮች ናቸው።

ሴት ልጅ ጥቃት ሲደርስባት ጥቃቱን ተከትሎ የሚፈጠረው መዘዝ በእርሷ ህይወት ላይ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። እንደምንም ታግላ ህይወቷን ማስቀጠል ብትችል እንኳን በቀጣይ በምትመሰርተው ቤተሰብ እና በምትወልዳቸው ልጆች ላይ የማይሽር ጠባሳን ይጥላል። የተረጋጋ ቤተሰብ መመስረት ካለመቻሏም በተጨማሪ የሚወለደው ልጅ የመወለጃው ቀን ሳይደርሰ መወለድ፣ ሞቶ መውለድ እንዲሁም የሚወለደው ልጅ ክብደት ዝቅተኛ ሆኖ መወለድ እንዲሁም ለተቅማጥ እና ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት መዳረግ ይገኙበታል። ህፃናቱ የሚያድጉት ጥቃት በሚፈፀምበት ቤተሰብ ውስጥ ከሆነም ከፍተኛ የሆነ የባህሪይ መዛባት የሚከሰትባቸው ሲሆን በቀጣይ ህይወታቸውም ጥቃት ለመፈፀም የተመቸ ይሆናል።

በአንዲት ሴት ላይ የሚፈፀም ጥቃት በመላው ቤተሰብ እና በቀጣይ ትውልድ ላይ ጭምር የማያቋርጥ ችግርን ጥሎ የሚያልፍ በመሆኑ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ችግሩን ከስሩ ማድረቅ አስፈላጊ ነው ሲል ድርጅቱ አሳስቧል። ይሄን ችግር ለመቅረፍም መላው ህብረተሰብ በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣ ሴቶችን መደገፍ እንዲሁም ጠንካራ ህግን ማውጣት እና መፈፀም እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። መንግስታትም ወደ ኋላ መለስ ብለው ፖሊሲዎቻቸውን መቃኘት እና ማሻሻል እንደሚጠበቅባቸው የጠቆመው ድርጅቱ፤ ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ግን መዘዙን ተሸክሞ ሩቅ መጓዝ እንደማይቻል አሳስቧል።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2566 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Addvvrt1.jpg
  • Adv.jpg
  • Advverttt.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1054 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us