በአዲስ አበባ ከአጥንት ላይ ሥጋ ገፋፊ ሐኪሞች፤ ከዓይን ሐኪሙ ከዶክተር አብዱላዚዝ ኢስማኤል ምን ይማራሉ?

Wednesday, 14 December 2016 13:40

 

በሕክምና ባለሙያዎች የተከፈቱ እንዲሁም ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በሽርክና የተከፈቱ በርካታ የግል ሆስፒታሎች እና ክሊኒኮች በአዲስ አበባ ይገኛሉ። በዋናነት የተከፈቱት ለሕብረተሰቡ ተመጣጣኝ አገልግሎት በማቅረብ ራሳቸውን እና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋሉ በሚል ታሳቢ በማድረግ ነው። በእርግጥም ሀገሪቷ በምትከተለው የነፃ ገበያ አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት በገበያው ውስጥ ተወዳድረው የሕክምና ተቋም የመክፈት እና በገበያ የሚመራ የአገልግሎት ዋጋ ሕብረተሰቡን ማስከፈል መብታቸው ነው። መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ፈጽሞ የተገላቢጦሽ ነው።

ከተገልጋዩ ከሚነሱት መከራከሪያ ነጥቦች መካከል፣ የሕክምና ባለሙያዎቹን ማን ነው ያስተማራቸው? ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በነፃ የገበያ ስርዓት ዋጋ ተተምኖላቸው ነው፣ የተማሩት? የሕክምና ተማሪዎቹን ለሙያ ባለቤትነት ለማብቃት የመንግስት እና የሕብረተሰቡ ድርሻ እንዴት ነው የሚገለጸው? ከሕክምና ባለሙያነት በዘለለ በዜግነት የሚጠበቅባቸው ድርሻ  ይኖር ይሆን? አንድ የሕክምና ባለሙያን ለማነጋገር ከ200 እስከ 1ሺ ብር ድረስ ሕብረተሰቡ እንዲከፍል መደረጉስ እንዴት ይታያል? ከላይ ለሰፈሩት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የአንድ ጋዜጣ ጽሁፍ በቂ አይደለም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ግን ከሶማሌ ብሔረሰብ የተገኙ የዓይን ሐኪም እያከናወኗቸው ያሉት ተግባሮች በከፊልም ቢሆን የሚመልሱልን ነጥቦች አሉ።

በሶማሌ ክልላዊ መንግስት ሰር በምትገኘው አሰቦት ቀበሌ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1977 ተወለደ። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በአሰቦት ቀበሌ ትምህርት ቤት (1982-1988) ተከታትሏል። በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሰቦት ቀበሌ ውስጥ ባለመኖሩ ወደ አሰበተፈሪ (ጭሮ) በመሄድ ትምህርቱን (1989-1992) መጨረስ ችሏል።

በሀገር አቀፍ ፈተና (ማትሪክ) ውጤቱ ከፍተኛ በመሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር በሚገኘው በጥቁር አንበሳ የሕክምና ትምህርቱን ተከታትሎ በዶክትሬት ዲግሪ (ፌብሩዋሪ 28 2002) ለመመረቅ በቅቷል። ተመራቂው፣ ዶክተር አብዱላዚዝ ኢስማኤል ነው። ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ያቀናው ወደ ትውልድ ክልሉ ሲሆን የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግሏል። ከባልደረቦቹ ባገኘነው መረጃ ዶክተር አብዱላዚዝ ለክልሉ ጤና ቢሮ መሻሻል ከፍተኛ ድርሻ ነበረው።

ዶክተር አብዱላዚዝ የሕክምና ሙያውን ወደ ስፔሻላይዜሽን ከፍ ለማድረግ በዓይን ሕክምና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ በመከታተል ተመርቋል። ወደ ክልሉ ሲመለስ ወደ ጤና ቢሮ አልገባም። በተማረበት የሕክምና ሙያ በጅግጅጋ ከተማ በግሉ ክሊኒክ በመክፈት ሥራ ይጀምራል። ለሕብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአካባቢው ካሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች የዓይን ታማሚ የሆኑት አብዛኞቹ ብርሃን ማየት ቢፈልጉም፣ አቅመ ደካማ በመሆናቸው አገልግሎቱን ማግኘት አልቻሉም ነበር። ይህንን ሁኔታ የተረዳው ዶክተር አብዱላዚዝ፣ አቅም ያላቸውን በክፍያ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በእኩሌታ እንዲሁም ምንም አቅም የሌላቸው ብርሐን ያጡትን ሙሉ በሙሉ በነፃ አገልግሎት አቀረበ። በዚህ በዶክተሩ እቅድ በርካቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።

የዶክተር አብዱላዚዝ መልካም ሥራዎቹን የተመለከቱት የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ሥራዎቹን ወደጎን አላደረጉትም። አይቶ እንዳላ አላለፉትም። መልካም ሥራዎቹን በጋራ ለቀሪው የሶማሌ ሕብረተሰብ እንዴት ማዳረስ እንደሚቻል አብረውት መክረዋል። በተለይ ከሶማሌ ክልል አካባቢዎች ወደ ጅግጅጋ ከተማ መምጣት የማይችሉትን የሕብረተሰብ ክፍሎች የመጀመሪያ ኢላማቸው አድርገው ለመንቀሳቀስ የወሰኑት። በዚህ ጊዜ ነበር የዶክተር አብዱላዚዝ ማንነት ጎልቶ የወጣው። ይኽውም፣ በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ ብርሃን ያጡ ዜጎች በነፃ ገበያ ስም ተሰማርተው በሚበዘብዙ ሐኪሞች አስተሳሰቦች አንፃር ስንመለከተው፣ ታማሚዎቹ ለዶክተር አብዱላዚዝ የገንዘብ ምንጮቹ መሆናቸው አጠያያቂ ባይሆኑም፣ ዶክተሩ ግን የሶማሌ ክልል መንግስት ባቀረበው በጋራ የመስራት እቅድን ተቀብለው አጋር ባለሙያዎቹን ሰብስበው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁነቱን አረጋግጠዋል።

ይህም በመሆኑ በሶማሌ ክልል ተንቀሳቃሽ የአይን ሕክምና ማዕከል ተመሰረተ። በዚህ ተንቀሳቃሽ የዓይን ሕክምና ማዕከል አጋዥነት በ20 ወረዳዎች ውስጥ በመንቀሳቀስ፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ6ሺ በላይ የቀዶ ሕክምና ለታማሚዎች በዶክተር አብዱላዚዝ መሪነት ተከናውኗል። አብዛኞቹ ከጨለማ ወደ ብርሐን ተቀላቅለዋል። ተመልካች የለንም ብለው ተስፋ ቆርጠው በበረሃ የወደቁ የመሰላቸው ዜጎች፣ እጁ ወርቅ የሆነ ልጅ መውለዳቸውን በአይናቸው አይተው አረጋግጠዋል። ሕብረተሰቡ ለሕክምና ባለሙያው ዶክተር አብዱላዚዝ እንዲማር የከፈለውን ግብሩን፣ በብርሃን ተከፍሎታል።

ብዙ ስግብግብ የሕክምና ባለሙያዎች የማይገነዘቡት ፍሬነገር፣ የገንዘብ ትርጉምን ነው። የገንዘብ ጉልበተኛነት፣ ገንዘብን ከያዙት በኋላ ያበቃል። ምንም ነገር የራስ ካደረጉት በኋላ፣ ስሜቱ ቀዝቃዛ ነው። ወይም ከመገኘቱ በፊት የነበረን ስሜት ያህል አይሆንም። በአንፃሩ፣ የመልካም ስብዕና ግንባታ ወይም ማሕበራዊ ቅቡልነት እርካታው ወደርየለሽ ነው። ይህንን ማግኘት የቻለ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ አብሮ የሚዘልቅ የደስታ ምንጭ ያገኛል። ማሕበራዊ እውቅናውም፣ ወደ ተሻለ ኃላፊነቶች የሚያበቃ መሰላል ይሆንለታል።       

የዶክተር አብዱላዚዝ ምርጫን፣ ገንዘብ ከሚያሳድዱ ራስ ወዳድ ሐኪሞች የተለየ ቦታ የሰጠነው ለዚህም ነው። በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከልጆቻቸው በላይ ማን ደራሽ አላቸው? በሕብረተሰቡ ግብር የተማረ ባለሙያ እንዴት ከሕብረተሰቡ አጥንት ላይ ሥጋ ሊገፍ ይሰናዳል? በአዲስ አበባ ያሉት ደግሞ የተለዩ፣ በላኤሰብትል (ሰውን የሚመገቡ ምስጦች) ሐኪሞች ናቸው። መንግስትም በተደጋጋሚ እነዚህን ከአጥንት ላይ ሥጋ የሚገፉ ሐኪሞችን መስመር የሚያሲዝ ሕግ አወጣለሁ ሲል በተደጋጋሚ ይደመጣል። እስካሁን ግን አላየንም።

ከሶማሌ ክልል ባገኘነው መረጃ፣ በ2009 ዓ.ም የክልሉ መንግስት በቀሩት ከ50 በላይ ወረዳዎች 10 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ “ዘመቻ ዳግም ብርሃንን” ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል።

የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዲ ማሐመድ ዑመር፣ የዶክተር አብዱል አዚዝን መልካም የሙያ ሥነምግባር እና አስተዋፅኦ እንዲሁም የትምህርት ዝግጅታቸውን ከግምት በማስገባት ለቦርዱ አቅርበው፣ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት አድርገው ሾመዋቸዋል።

እኛም የኝህ ሰው ትምህርት ተገልጦና አስተዋኝነት በእያንዳንዳችን ልቦና ውስጥ ይስፈን እንላለን።

ሀርትሼክ ላይ የተሰጠ እርዳታ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1782 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Addvvrt1.jpg
  • Adv.jpg
  • Advverttt.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1057 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us