ስለ ማስታወቂያ

Wednesday, 19 March 2014 14:05

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-         ማስታወቂያዎቻችንና የማስታወቂያ አዋጅ

-         በሕጋችን እንደማስታወቂያ የሚቆጠሩ የማስታወቂያ አይነቶች

-             በማስታወቂያ ውስጥ የሚሳተፉ አካላትና ኃላፊነታቸው

-         በማስታወቂያ ስራ የመሰማራት መብት

-         ማስታወቂያዎቻችን ሊያሟሏቸው የሚገደዱባቸው ይዘቶችና አቀራረቦች

የማስታወቂያዎቻችን ሙዶች

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ዛሬ ወደ ዋናው ነጥቤ ከመግባቴ በፊት አንድ የምስራች ልንገራችሁ “እንዳያመልጣችሁ! ኋላ ላለመቆጨት ቀድሞ ነው መገኘት! “ለማህበራዊ፣ ለፖለቲካዊ ለኢኮኖሚያዊ ህይወትም ፍቱን የቀኝ እጅ የሆነ፣ ጠበቃ ለምኔ የሚለው ከሰው የሚረቱበት፣ ተከሰው የሚያሸንፉበት ሕግ ትምህርት ቤት ሳይገቡ ከሕግ ሊቃውንት ተርታ የሚመደቡበት የምር ሳምንታዊ የሕግ አምድ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ እሮብ እሮብ ይጠብቁ። ብዙዎች የህግ አምዳችንን አንብበው ተለውጠዋል። እርሶስ? አሁኑኑ ቋሚ ደንበኛችን ይሁኑ።”

አንድ ልጨምር ይህ ደግሞ በሬዲዮ ከለመድናቸው ድምፆች በአንዱ የሚሰማ ነው።

“ውድ የሰንደቅ ጋዜጣ የህግ አምድ አንባቢያን የሕግ አምዳችን በአንባቢዎቻችን ዘንድ ያለውን ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተነባቢነት በመረዳት በአቋራጭ ለመክበር ያሰቡ አንዳንድ ግለሰቦች የአምዱ ያልሆኑ ፅሁፎችን የአምዱ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ ላይ መሆናቸው ደርሰንበታል። በመሆኑም ጉዳዩን በሕግ እየተከታተልነው እንደምንገኝ እየገለፅን አንባቢዎቻችን ተመሳስለው ከተፃፈ የሕግ ፅሁፎች እንዲጠነቀቁ እንጠቁማለን።”

በየመገናኛ ብዙሃኑ የምንሰማቸው ማስታወቂያዎች የሚቀርቡባቸውን አቀራረቦች ለማስተዋወቅ ያህል ነው። ከላይ ያነሳኋቸውን ሁለት ሃሳባዊ የማስታወቂያ ምሳሌዎች ያነሳሁት እንጂ የህግ አምዱን ለማስተዋወቅ አይደለም። ምክንያቱም ጥሩ እቃ ማስታወቂያ አያስፈልገውም፤ ወይ ጉድ ይሄም ለካ ማስታወቂያ ነው።

ማስታወቂያዎቻችን ከሕጉ አንጻር

ማስታወቂያ አምራች ወይም አገልግሎት ሰጪው አቅርቦቱን ለተጠቃሚው ለማድረስ ተጠቃሚውም ያለውን አማራጭ ለማነፃፀር ትልቅ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም መተላለፍ የሚፈልገውን ማንኛውንም መልዕክት ከሚፈልጋቸው አካል ዘንድ ለማድረስም አስፈላጊ ነው። በሀገራችንም ከንግድ እንቅስቃሴና ከገበያ ውድድር ጋር በተያያዘ ከዘርፉ እድገት እና ከቴክኖሎጂው መስፋፋት ጋር አብረው እያደጉ ማስታወቂያዎቻችን አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የማስታወቂያ ባለሙያ እንዳለመሆኔ በዚህ ዙሪያ ብዙ የምለው የለኝም። የምለው ያለኝ ማስታወቂያንና የማስታወቂያ ተዋናዮችን የሚገዛው ሕጋችን ምን ይላል የሚለው ላይ ነው።

እራሱን የቻለ ማስታወቂያን የሚመለከት አዋጅ ነሐሴ 21 ቀን 2004 ዓ.ም ወጥቶ በስራ ላይ ይገኛል። ይህ አዋጅ ቁጥር 759/2004 ሲሆን ስለማስታወቂያ የወጣ አዋጅ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

የአዋጁ ዓላማ በመግቢው ላይ እንደተገለፀው ማስታወቂያ በምርት ግብዓት ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ለሀገራችን ሁሉን አቀፍ እድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ በምንከተለው ገበያ መር ስርዓት ውስጥ ጤናማ የገበያ ውድድር እንዲኖር አስተዋፅኦው የጎላ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ በሥርዓት ላልተመራ ህብረተሰቡንና የሀገርን ገፅታ ሊጎዳ ስለሚችል የሚመራበት ሕግ አስፈላጊ መሆኑን ሕግ አውጪው ስላመነበት ይህን አዋጅ አውጥቷል።

በተጨማሪ ማስታወቂያ ያለ ተዋንያኖቹ ሊኖርና በአግባቡ ሊካሄድ ስለማይችል የማስታወቂያ ወኪሎችን፣ አሰራጮች እና አስነጋሪዎችን መብትና ግዴታ በግልፅ ለመወሰንም በማስፈለጉ ነው። ዛሬ እያነሳነው ያለነው የማስታወቂያ ሕግ የወጣው።

ሀ. የማስታወቂያ አይነቶች

የማስታወቂያ አዋጁ በአንቀፅ 2(1) ላይ የምርት ወይም የአገልግሎት ሽያጭን ስም፣ አርማ፣ የንግድ ምልክት ወይም አላማ እንዲተዋወቅ በማስታወቂያ ማሰራጫ በኩል የሚተላፍ መልእክት ነው በሚል ትርጓሜ ይሰጠዋል። አያይዞም ሶስት የማስታወቂያ አይነቶችን ይዘረዝራል።

 1. የንግድ ማስታወቂያ ከላይ የጠቀስነው ለንግድ አላማ የሚሰራጭ ነው።
 2. የሕዝብ አገልግሎት ማስታወቂያ በአንቀጽ 2(3) መሰረት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጭ መልዕክት ነው።
 3. የግል ማስታወቂያ፡- በአዋጅ አንቀጽ 2(4) በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ አማካኝነት የሚሰራጭ የአፋልጉኝ ፣ የሀዘን መግለጫ እና ሌላ መሰል ማስታወቂያን የሚያካትት ነው።

በአጠቃላይ ማስታወቂያ የምንለው ከላይ ከጠቀስናቸው የንግድ፣ የሕዝብ አገልግሎት ወይም የግል ማስታወቂያዎች በአንዱ ውስጥ የሚወድቅና እንደየማስታወቂያው አይነት ያለመላትን መልእክት ለማስተላለፍ ማስታወቂያ አስነጋሪው በራሱ ወይም በማስታወቂያ ወኪል በኩል የተዘጋጀውን ማስታወቂያ በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶች አሰራጩ የሚያሰራቻወው መልእክት ነው።

ለ. የማስታወቂያ ተዋንያን

ማስታወቂያዎች ይዘት ምን መሆን አለበት። ከሚሰራጩባቸው መንገዶችስ አንጻር እንዴት ይታያሉ የሚለውን ከመመልከታችን በፊት በማስታወቂያ ውስጥ የሚሳተፉትን ተዋንያን እንመልከት። ሶስት ናቸው፡-

1. የማስታወቂያ አስነጋሪ፡- በአዋጁ አንቀፅ 2(8) ማስታወቂያውን የሚያስነግረው ወይም ማስታወቂያው የሚተዋወቅለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ ሰውነት የተሰጠው ተቋም ነው። ይህ ማስታወቂያ አስነጋሪ የራሱን ማስታወቂያ አዘጋጅቶ ማሰራጨት የሚችል መሆኑንና በማስታወቂያው ላይ ማንነቱንና አድራሻውን በግልፅ መጥቀስ እንዳለበት በአንቀፅ 5(4) ላይ ተደንግጓል። ማስታወቂያ አስነጋሪው ለሚያስተላልፈው መልእክት እና መረጃ ትክክለኛነቱን የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት ሲሆን ይህን ግዴታውን ካልተወጣ የማስታወቂያ ወኪሉ ወይም አሰራጩ ከአስነጋሪው ጋር የገቡትን ውል በመሰረዝ ለደረሰባቸው ኪሳራ ካሳ ሊጠይቁት እንደሚችሉ በአንቀፅ 27 ላይ ተጠቅሷል።

በማስታወቂያው ምክንያት የሚነሱ አከራካሪ ጉዳዮችን ለመወሰን እንዲቻል ማስታወቂያ አስነጋሪውም ሆነ ወኪሉ ወይም አሰራጩ በአዋጅ አንቀጽ28 ላይ የተሰራጨውን ማስታወቂያ ቢያንስ ለስድስት ወራት ቅጂውን የመያዝ ግዴታ አለባቸው። በብሮድካስት ባለስልጣን ወይም አግባብ ባለው አካል ሲጠየቁም የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ይህ ድንጋጌ በማስታወቂያ አማካኝነት የሚፈፀሙ ጥራቶችን ለማሟላትና ኃላፊነቱን ለመወሰን ማስረጃዎች እንዳይጠና ለማድረግ ያለመ ነው።

በአንቀጽ 30 ላይ ይህን አዋጅ ለመተላለፍ ለተሰራጩ ማስታወቂያ አስነጋሪው ወኪሉ እና አሰራጩ በፍቃዳቸው እንዳሰራጩት ተቆጥሮ እንደ ጥፋታቸው መጠን በአንድነት ወይም ደግሞ በየግል ተጠያቂ እንደሚሆኑ የተደነገገ ሲሆን ጥፋተኛ አለመሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ካቀረቡ ግን ኃላፊነቱን የሚወስደው ጥፋቱን የፈፀመው ሰው ብቻ ነው።

2. የማስታወቂያ ወኪል፡- በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል ላይ የማስታወቂያ ወኪል ማለት የማስታወቂያ ማዘጋጀቱን ወይም የማስታወቂያውን ስራ የሚሰራ በሕግ እውቅና የተሰጠው የንግድ ማህበር ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 4 ላይ ደግሞ የማስታወቂያ ወኪሎች ስራ በሆነው የማስታወቂያ ስራ ላይ ለመሰማራት የሚችለው ግለሰብ ወይም ደግሞ በሀገራችን ሕግ መሰረት ለሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች የተቋቋመ የንግድ ማህበር መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። የማስታወቂያ ወኪል ሆኖ ለመሰማራት የተቋቋመ ድርጅት ካፒታሉ የውጭ ሀገር ዜጋ ድርሻ ያለበት መሆን አይችልም። ሆኖም የውጭ ሀገር ዜጋው ትውልደ ኢትዮጵያወ ከሆነ በማስታወቂያ ስራ ላይ ለመሰማራት ተፈቅዶለታል።

በማስታወቂያ ወኪልነት ለመሰማት ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ማውጣት አለበት። ማስታወቂያ አሰራጮችም በማስታወቂያ ወኪልነት ለመሰማራት በአዋጁ የተፈቀደላቸው ሲሆን ሆኖም ቅድሚያ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ የማግኘትና ከሚሰሩት የመገናኛ ብዙሃን ስራ በተለየ መልኩ ማከናወን አለባቸው።

የማስታወቂያ ወኪሎች በማስታወቂያ ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ የማስታወቂያ ስራ የሚባለው ደግሞ ማስታወቂያ ማዘጋጀትና ማሰራጨትን፣ የፕሮሞሽን አገልግሎትን እና ከማስታወቂያ ጋር ተያያዥነት ያለውን ሌላ ስራ የሚያካትት እንደሆነ አዋጁ ለሰጠው ትርጓሜ መረዳት ይቻላል። በውጭ ሀገር የተዘጋጅተው ወደ ሀገር የሚገቡ ማስታወቂያዎች እንዲሰራቹ የ ሚደረገው በወኪሉ በኩል ነው።

 1.      3. የማስታወቂያ አሰራጭ፡- ይህ ሶስተኛው የማስታወቂያ ተሳታፊ አካል ደግሞ ማስታወቂያው ለተላለፈላቸው አካላት እንዲደርስ የሚያደርገው ቁልፍ አካል ሲሆን የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶችን በመጠቀም በአየር ጊዜ ፣ በሕትመት ሽፋን ወይም መሰል አገልግሎት በመስጠት ማስታወቂያውን ያሰራጫል። ማስታወቂያ አሰራጩ የተለያዩ የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶችን የሚጠቀም ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 2(2) መሰረት የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶች ማለት የመገናኛ ብዙሃን የህትመትና የብሮድካስት የውጭ ማስታወቂያ፣ ቴሌኮም የፖስታን፣ የኢንተርኔት ድረ ገፅን እና የፋክስ አገልግሎችን፣ ሲኒማን፣ ፊልምን፣ ቢዲዮን እና መሰል ማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶችን ይጨምራል።

ሐ. አስገዳጅ የማስታወቂያ ይዘትና አቀራረብ መርሆች

የማስታወቂያ አዋጅ ማንኛውም ማስታወቂያ ሊያከብራቸው የሚገቡ መሰረታዊ መርሆችን በአስገዳጅነት በአንቀጽ 6 ላይ ከይዘትና ከአቀራረብ አንፃር አስቀምጧል።

በመጀመሪያ ደረጃ ማስታወቂያዎች ይዘታቸውም ሆነ አቀራረባቸው በሕግ የተጠበቁ መብቶችን የሚጥሉ ወይም ሕገወጥ ድርጊቶችን የሚያበረታቱ መሆን የለባቸውም። በተጨማሪም የህብረተሰቡን የመልካም ስነምግባር እሴቶች የሚያንቋሽሹና በሃይማኖቱ፣ በባህሉ፣ በአመለካከቱ እንዲጠበቁለት የሚፈልጋቸውን ሥነምግባሮችም መጣስ የለባቸውም።

የሚተዋወቀውን ነገር እውተኛ ባህሪ ጥቅምጥራትና መሰል መረጃዎች በትክልል መግለፅ ያለባቸው ሲሆን አሳሳች ወይም ተገቢ ያልሆኑ አገላለጾችን ከመጠቀም መቆጠብ አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ የሌሎችን ሰዎች ምርት ወይም አገልግሎት የሚያንቋሽሹ መሆን እንደሌለባቸው በግልፅ ተደንግጓል።

ማስታወቂያዎች ሸማቾችን ትክክለኛ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ የሚያግዙ መሆን ስላለባቸው የሸማቹን ጥቅም የሚጎዱ እንዲሆኑ ሕጉ አይፈቅድም። ከግለሰብም ሆነ ከሕብረተሰብ ባሻገር የአገርን ክብርና ጥቅም የሚጠብቁና አገልግሎቱ ወይም ምርቱን የሚመለከተውንም ሙያ ሆነ የማስታወቂያ ሙያ፤ ሙያዊ ስነምግባሮችን የሚያከብሩ መሆን አለባቸው።

ከአቀራረብ ጋር በተያያዘ ማስታወቂያ ከሌሎች ፕሮግራሞች የተለየ መሆኑ በግልጽ እንዲታወቅ ሆኖ መቅረብ አለበት። በህትመት ውጤቶችም ላይ ሆነ በብሮድካስት ስርጭቶች ላይ የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች ከሌሎቹ ፅሁፎች ወይም ፕሮግራሞች መለየት ያለበት ተቀላቅሎ ሌሎቹ ፕሮግራሞች ወይም ፅሁፎች ላይ የራሱን ተፅእኖ እንዳያሳድር ነው። በሌላ በኩል ማስታወቂያዎች በዜና መልክ መዘጋጀትና መቅረብ የሌለባቸው ሲሆን ይህም ዜና በመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች ላይ ዋነኛው አካል በመሆኑ አስነጋሪው ወይም ስፖንሰሩ በሚፈፅመው ክፍያ የተነሳ ከፍላጎታቸው አንፃር የዜናን ቅርጽና እውነተኛ ባህሪ እንዳያሰራጩትና ዜጋው ማስታወቂያ ማስታወቂያው ዜና ሆኖ ነገሮች እንዳይበለሻሹ ነው።

ሌላው ደግሞ በመገናኛ ብዙሃኖቻችን ላይ ብዙ ጊዜ የምንታዘበውን ክስተት ለማስወገድ የተቀመጠው በምስል ከሚያቀርበው ተዋናይን የሚመለከት ነው። አንዳንዴ አንዱ ማስታወቂያ አንባቢ እከሌ ሳሙና ብሎ የሚነገረንን ሰምተን ቀጥሎ ደግሞ በዚያው ድምፁ ስለ እንደኔ ሳሙና ጥሩነት ይነግረናል። ይሄን ግራ እንጋባለን። እውነት እንዲህ የሚያስወራቸው የእቃው ወይም የአገልግሎቱ ጥሩነት ሳይሆን በቃ ስለተከፈላቸው ብቻ ነውን ብለን እንድንል ያደርገናል።

ከዚህ በተጨማሪ ባንኩንም፣ ቢራውንም፣ ሆቴሉንም፣ ቆርቆሮውንም ሆስፒታሉንም፣ ፍራሹንም፣ የገቢ ማሰባሰቢያውንም በአንድ ወይም በሁለት ሰው ድምፅና ምስል ወይም አቀራረብ ብቻ መስማታችን አሰልቺ እንዲሆንና በማስታወቂያ የሚነገሩ ነገሮችን እንዳናምን ያደርገናል። አይ . . . ይሄ ማስታወቂያ ደግሞ እንድንል ያደርገናል። ይሄን ለመከላከል የማስታወቂያ አዋጁ በአንቀጽ 6(4) ላይ ማስታወቂያ ወኪሉ የአንድን ሰው ምርት፣ አገልግሎት ወይም ሌላ መልእክት የሚያስተዋውቅ የንግድ ማስታወቂያ አዘጋጅቶ ባሰራጨ በሶስት ወራት ውስጥ የሌላ ሰውን ተመሳሳይ ምርት፣ አገልግሎት ወይም ሌላ መልእክት ተመሳሳይ የማስታወቂያ ተዋናይ መስል ወይም ድምፅ አዘጋጅቶ እንዳያሰራጭ ከልክሏል።

በተጨማሪም አዋጁ ለማስታወቂያ ጥቅም በሚሉበት ጊዜ የቅጅና ተዛማች መብቶች፣ የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራና የኢንዱስትሪ ንድፈ ውጤቶች መብትን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበትም ይደነግጋል። ዛሬ በዚሁ እናሳርግና ሳምንት ስለ ስፖንሰርሺፕና ማስታወቂያ እናነሳለን።  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
10867 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 981 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us