የእንቅልፍ ፀር ምግቦች

Wednesday, 21 December 2016 14:48

 

ልክ እንደ ምግብ ሁሉ እንቅልፍም ለሰው ልጅ ጤናማነት የራሱን ድርሻ ይወጣል። በቀን ውስጥ በቂ የሆነ እንቅልፍ መተኛት ደግሞ የተስተካከለ አስተሳሰብ እንዲኖረን፣ ስራችን እና በእንቅስቃሴያችን የተነቃቃን እንድንሆን እንዲሁም ጥሩ የሆነ ስሜት እንዲኖረን በማድረግ በህይወታችን ጤናማ አኗኗርን እንድንመራ ያደርገናል። እንቅልፍ ያለው ጠቀሜታ በርካታ ሆኖ ሳለ አንዳንድ እንቅልፍን የሚያዛቡ እና እንቅልፍ የሚያሳጡ ነገሮች ሲገጥሙን ደግሞ አኗኗራችን ያልተስተካከለ እንዲሆን ያደርገዋል። እንቅልፍን በተገቢው መልኩ እንዳንተኛ ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል ደግሞ ለሰውነታችን ይጠቅማሉ ብለን የምንመገባቸው የምግብ አይነቶች ይገኛሉ። እነዚህን ምግቦች የመኝታ ሰዓት በተቃረበ ጊዜ መመገቡ ሌሊቱን ያለ እንቅልፍ እንድናሳልፍ የማድረግ ባህሪይ ይፈጥርብናል። በዚህም ሳቢያ አዋዋላችን ያልተስተካከለ እንዲሆን ያደርገናል። እኛም በዛሬው ፅሁፋችን የትኞቹ የምግብ አይነቶች የእንቅልፍ ሁኔታን እንደሚያዛቡ ከነምክንያታቸው እንቃኛለን።

የወይን ፍሬ

የመጀመሪያው እንቅልፍን የሚያዛባው እና በእንቅልፍ ሰዓት መመገብ የሌለብን የወይን ፍሬ ነው። የወይን ፍሬ በተፈጥሮው በቂ የሆነ የምግብ ዘይት ያለው እና በቫይታሚኖች የበለፀገ ነው። ነገር ግን ከዚህ ይዘቱ በተጨማሪም የአሲድ ይዘቱ ቀላል የሚባል አይደለም። ወደመኝታችን በምናመራበት ወቅት ይሄንን ፍሬ የምንመገብ ከሆነም ይሄ የአሲድ ይዘቱ የማቃጠል ስሜት ይፈጥርብናል። አሲዱ ወደ ላይ ወደ ጉሮሮአችን እና ወደ ልባችን በመምጣትም የቃር ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል ሲሉ የሚገልፁት የቦስተን ህክምና ማዕከል የስነ ምግብ እና ክብደት ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር ካሮሊን አፖቪያን፣ ይህን ፍራፍሬ መመገብ ካስፈለገ ቁርስ ላይ መመገብ የተሻለ ነው ሲሉ ምክራቸውን አስቀምጠዋል።

ቲማቲም

ቲማቲም በታይራሚን እና አሚኖ አሲዶች የበለፀገ የአትክልት ዘር ነው። በዚህ ቲማቲም ውስጥ የሚገኘው አሲድም አንጎል ኖርኔፍሪን የተባለ ንጥረ ነገርን እንዲያመነጭ ያደርገዋል። ይሄ ንጥረ ነገርም የአንጎልን እንቅስቃሴ እና መነቃቃት የሚጨምር እና እንቅልፍ እንዲዘገይ የማድረግ ባህሪይ አለው። በዚህም ሳቢያ ቲማቲም ወደ መኝታ በምንሄድበት ወቅት ከተመገብነው እንቅልፍ አልባ ሌሊትን እንድናሳልፍ ያደርገናል። ልክ እንደ ቲማቲም ሁሉ በኖርፒኔፍሪን ንጥረ ነገር የበለፀጉት እንደ ቀይ ወይን እና የቆየ አይብ በመኝታ ወቅት አገልግሎት ላይ ከዋሉ እንቅልፍ የመንሳት ችግር አለባቸው።

አልኮል

ብዙ ጊዜ አልኮልን ወደመኝታ በምናመራበት ወቅት መጎንጨት የድካም ስሜት እንዲሰማ እና እንቅልፍ እንዲጥለን ያደርጋል። ነገር ግን ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይሄ በአልኮል ምክንያት የሚገኝ እንቅልፍ ጥልቅ እንቅልፍ ባለመሆኑ ለረጅም ጊዜ የመቆየት እድሉ አነስተኛ ነው። በመሆኑም ሌሊት ላይ ከእንቅልፍ በመቀስቀስ የእንቅልፍ ስርዓትን ያዛባል። በዚህም ሳቢያ በቀጣዩ ቀን ሃሳብን በአንድ ነገር ላይ አሰባስቦ ለማሰብ፣ ለማስታወስ እንዲሁም ነገሮችን አቀናጅቶ ለማከናወን ያስቸግራል። በመሆኑም አልኮል መጎንጨት የግድ ከሆነ ወደ መኝታ ከመሄድ ሁለት ሰዓታት በፊት መጠጣት ይመከራል።

አበባ ጎመን እና ባቄላ

አበባ ጎመን የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ካላቸው የምግብ አይነቶች መካከል ተጠቃሽ ነው። ይሄ የምግብ አይነት ታዲያ ከተመገብነው በኋላ ለመፈጨት እና ከደም ጋር ለመዋሃድ ረጅም ጊዜ ይወስድበታል። በዚህም ምክንያት ወደ መኝታችን በምናመራበት ወቅት  ከተመገብነው ሰውነታችን ሌሊቱን ሙሉ ይሄንን ምግብ በማላም ስራ ተወጥሮ እንዲቆይ ያደርገዋል። በዚህም ሳቢያ ሌሊት ላይ እንቅልፍ አንተኛም። ከዚህ በተጨማሪም አበባ ጎመን እና ዝርያዎቹ ከፍተኛ የሆነ ጋዝ የማምረት አቅም ያለው ቶሎ የማይፈጭ የስኳር አይነት ስላላቸው ጋዙ ሆድን በመንፋት እንቅልፍ ያሳጣናል። ልክ እንደ አበባ ጎመን ሁሉ ባቄላም በሰውነት ውስጥ ለመፈጨት ረጅም ጊዜ ከሚጠይቁ የጥራጥሬ አይነቶች አንዱ ነው። በመኝታ ሰዓት ይሄን ባቄላ መመገብም ሰውነታችን ሌሊቱን ሙሉ ምግብ በመፍጨት ስራ ተወጥሮ እንዲያደር ያደርገዋል ይላሉ በቱፍትስ ዩኒቨርስቲ የስነ ምግብ ተመራማሪዋ ሐለን ራስሙስን። እንደተመራማሪዋ ገለፃ ባቄላ ከፍተኛ የሆነ ጋዝ የማመንጨት ባህሪይ ስላለው ይሄ ጋዝ በሰውነት ውስጥ በመዘዋወር እና ሆድ የህመም ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ሌሊታችን ከእንቅልፍ የምንርቅበት እንዲሆን ስለሚያደርግ ባቄላን በምሳ ሰዓት ላይ ብንመገብ መልካም እንደሆነ ይመከራል። በተመሳሳይ የአበባ ጎመንንም በምሳ ሰዓት በመመገብ ጥሩ እንቅልፍ የሚገኝበትን ሌሊት ማሳለፍ ይቻላል።

ለስላሳ መጠጦች እና ጥቁር ቸኮሌት

በካርቦሃይድሬት የበለፀጉ ለስላሳ መጠጦች ውስጥ የሚገኘው ካፌይን እንቅልፍን የመንሳት ባህሪይ አለው። የሎሚ ይዘት ባላቸው እና በአንዳንድ የቢራ አይነቶች ውስጥ የሚገኘው ካፌይን በመኝታ ሰዓት ሲጠጣ እንቅልፍ ይነሳል። በተለይ ያልቀዘቀዘ ኮካ ኮላ እና ትኩስ ሻይ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ካፌይን በቡና፣ በሻይ እና በቸኮሌት ውስጥ በከፍተኛ መጠን ይገኛል። በመሆኑም እነዚህን ነገሮች መጠጣት እንቅልፍ እንዲዛባ ያደርጋል።

ቸኮሌትን በተመለከተ በተለይ ጥቁር ቸኮሌትን በመኝታ ወቅት መመገብ አይመከርም። ምክንያቱም በዚህ ጥቁር ቸኮሌት ውስጥ ከፍተኛ የካፌይን ይዘት ስላለ ነው። ትንሽ ቁራሽ እንኳን ጥቁር ቸኮሌትን በእንቅልፍ ሰዓት ላይ መመገብ ሌሊቱን ያለ እንቅልፍ እንድናሳልፍ ያደርገናል። በመሆኑም እነዚህን እና ሌሎች መሰል የካፌይን ይዘት ያላቸው ነገሮች ወደመኝታችን ከመሄዳችን ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ቀደም ብለን መጠቀም ይኖርብናል።

ድንች ጥብስ እና ስጋ ጥብስ

በዘይት የሚጠበሱ እንደ ድንች ጥብስ ያሉ ምግቦች በሰውነት ውስጥ ልመው የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት ፈጣን አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪም የዘይት ይዘታቸው እና የምግቦቹ ተፈጥሮ ተደማምሮ ለቃር የማጋለጥ ባህሪይ አላቸው። የሚጠበሱበት ዘይት በከፍተኛ ሙቀት የሚፈላ በመሆኑም ለጨጓራ ከባድ እንዲሆኑ በማድረግ ሰላማዊ ሌሊትን እንዳናሳልፍ ያደርጉናል። በተመሳሳይም የተጠበሰ ስጋ ለመፈጨት ረጅም ጊዜ ስለሚወስድበት ሰውነታችን ሌሊቱን ሙሉ በስራ ተጠምዶ እንዲያድር ያደርጉታል። በእነዚህ በተጠበሱ ምግቦች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስብ ይዘት ስላለ ሌሊታችን የምናርፍበት ሳይሆን በጭንቀት የምናሳልፈው ይሆናል ይላሉ ተመራማሪ ሄለን። በመሆኑም እንደስቴክ ያሉ ምግቦችን እና የተጠበሱ ስጋዎችን ወደመኝታ ከመሄዳችን ሶስት ሰዓታት አስቀድሞ መመገብ ያስፈልጋል።

ሀባብ እና ዝርያዎቹ

ከሀባብ ውስጥ 92 በመቶ ይዘቱ ውሃ ነው። የዚህ ሀባብ ዝርያ የሆኑት እንደ ዱባ እና ሌሎችም የውሃ ይዘታቸው ከፍተኛ ነው። ምንም እንኳን እነዚህ ፍራፍሬዎች በቀላሉ በሰውነት የመፈጨት ባህሪይ ቢኖራቸውም የሚያመነጩት ውሃ ከፍተኛ መጠን ያለው ሽንት እንዲመረት ያደርጋል። በመሆኑም ሌሊት ላይ ሽንት ከእንቅልፋችን እንዲቀሰቅሰን ያደርጋል። በወቅቱ ሽንትን ማስወገድ ካልተቻለም፣ ፊኛ ሽንትን ለመቋጠር እንዲገደድ ያደርገዋል። በመሆኑም እንዲህ አይነት ዝርያ ያላቸው የምግብ አይነቶችን ወደመኝታችን ከመሄዳችን 90 ደቂቃ ቀደም ብሎ መመገብ ይመከራል።

ከረሜላ እና ሌሎች ጣፋጮች

የጣፋጭነት ባህሪይ ያላቸው እንደ ከረሜላ ያሉ ነገሮችን በምንመገብበት ወቅት የሰውነታችን የስኳር መጠን እንዲጨምር ያደርገዋል። ይሄንን ክስተት ለመቋቋም ያግዘው ዘንድ ሰውነታችን ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንሱሊን ሲያመነጭም የስኳር መጠኑ በፍጥነት ይቀንሳል። ይህ ክስተት ሰውነት በፍጥነት እንቅልፍ እንዲጥለው ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን በዚህ መልኩ የሚከሰተው እንቅልፍ ዘላቂነት የሌለው ስለሚሆን በሰውነት ላይ መናጋትን ይፈጥራል። በዚህም ሳቢያ ሌሊቱን ሙሉ ባልተስተካከለ እና ምቾት በማይሰጥ ሁኔታ ውስጥ ለማሳለፍ እንገደዳለን የሚሉት የዘርፉ ባለሞያዎች፣ ይህንን ችግር ለማስወገድም ወደመኝታችን ከመሄዳችን ከሁለት እስከ ሶስት ሰዓት በፊት ብንመገባቸው መልካም ነው ይላሉ።   

ከሞላ ጎደል ከላይ የተጠቀሱት የምግብ አይነቶች ወደመንታ በምንሄድበት ወቅት ብንጠቀማቸው እንቅልፍ የሚነሱን ናቸው። እንቅልፍ ማጣት እና መዛባት ደግሞ በየዕለት እንቅስቃሴያችን ላይ ከሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ በተጨማሪ ዘላቂ ለሆነ የአእምሮ ጤና ችግር እንደሚዳርግ ባለሞያዎች ይገልጻሉ። በመሆኑም የተረጋጋ ሌሊትን ለማሳለፍ እና በቂ እንቅልፍ ለማግኘት በአመጋገባችን ላይ ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። የእንቅልፍ ሰዓት ከመድረሱ ቀደም ብሎ መመገብ፣ ቆይቶ መመገብ ካስፈለገም የምንመገበውን ምግብ መጠን መቀነስ እንዳለብን ባለሞያዎች ይመክራሉ። ከዚህ በተጨማሪም በእንቅልፍ ሰዓት የምንመገባቸው ምግቦች የጥራጥሬ ተዋፅዖ፣ ፓስታ፣ ሩዝ እና ጥሩ እና በቂ የሆነ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው ምግቦች፣ ቅጠላቅተሎች፣ አቮካዶ፣ ወተት እና ሌሎች በቀላሉ ሊፈጪ የሚችሉ የምግብ አይነቶችን ያሟሉ ቢሆኑ ለጤናማ እንቅልፍ ይረዳል።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
2636 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Addvvrt1.jpg
  • Adv.jpg
  • Advverttt.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1051 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us