አርቴፊሻል ጥርሶች ከውበት ያለፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው

Wednesday, 28 December 2016 14:08

ጥርስ ሲነሳ ምግብን አልሞ ለመዋጥ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ውበትን የመጠበቅ አገልግሎትም ይሰጣል። የተፈጥሮ ጥርስ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈጥሯዊ አገልግሎት መስጠት ሲያቅተው የተለያዩ ሰው ሰራሽ አማራጮችን ለመጠቀም ያስገድዳሉ። ከእነዚህ አማራጮች መካከልም ሰው ሰራሽ (አርቴፊሻል) ጥርሶች ተጠቃሽ ናቸው። ምንም እንኳን የተፈጥሮ ጥርስን ሊተኩልን ባይችሉም እነዚህ አርቴፊሻል ቁሶች ጥርስ መስጠት የሚገባውን አገልግሎት ይሰጣሉ። እኛም ከዚህ ከአርቴፊሻል ጥርስ ጋር በተያያዘ ባለሞያ አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል። ባለሞያው ዶ/ር ሽመልስ ተኮላ ይባላሉ። ዶ/ር ሽመልስ በሞያቸው በቃል ስፔሻሊቲ የጥርስ ህክምና ክሊኒክ የጥርስ ቀዶ ህክምና ባለሞያ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ጥርስ ባለሞያዎች ማህበር ስራ አስፈፃሚም ናቸው።

ሰንደቅ፡- አርቴፊሻል (ሰው ስራሽ) ጥርስ የተለያየ አይነት አላቸው። እነዚህ አይነቶች ምን ምን ናቸው? ጥርሶቹ የሚሰሩባቸው ንጥረ ነገሮችስ ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ሽመልስ፡- አርቴፊሻል ጥርሶችን በተለያየ መስፈርት የተለያየ ምድብ ልንሰጣቸው እንችላለን። በዚህ መስፈርት አርቴፊሻል ጥርሶችን ወጪ ገቢ እና ቋሚ ወይም (Removable and fixed) ተብለው ይከፈላሉ። ወጪ እና ገቢ የሚባለው አርቴፊሻል ጥርስ ላይ ብዙም ክፍፍል የለውም። ብዙ ክፍፍል ያለው ግን ቋሚ በሚባለው አርቴፊሻል ጥርስ ላይ ነው። ቋሚ አርቴፊሻል ጥርሶች የሚባለው ታካሚው በፈለገው ጊዜ ሊያወጣው እና ሊያስገባው የማይችለው አርቴፊሻል ጥርስ ነው። ይህ ጥርስ ካልተሰበረ ወይም ማጣበቂያው ለቆ ካልወጣ በስተቀር ታካሚው ሊያስወጣውና ሊያስገባው አይችልም። ወጪ ገቢ የሚባለው ግን ታካሚው በፈለገው ሰዓት ማታ ወይም ለማጽዳት ሲፈልግ ራሱ የሚያወጣው እና ለመጠቀም ሲፈልግ ደግሞ መልሶ የሚያስገባው ማለት ነው።

ወጪ እና ገቢ አርቴፊሻል ጥርስን በተመለከተ ሙሉ እና ክፊል (Full and Partial Denture) ተብለው ይከፈላሉ። ሙሉ የሚባለው ታካሚው በአፍ ውስጥ ምንም አይነት ጥርስ ሳይኖረው ሲቀር የሚሰራ አርቴፊሻል ጥርስ ነው። ሙሉ በሙሉ ጥርሱ (28ቱም ጥርሶች) ወጪ ገቢ ሆነው ሲሰሩ ሙሉ ዴንቸር ይባላል። ነገር ግን አንድ እና ከዚያ በላይ ጥርሶች ላሉት ታካሚ የሚሰራው ወጪ ገቢ ጥርስ ከፊል (Partial) ዴንቸር ይባላል። ቋሚ የሚባለው አርቴፊሻል ጥርስ ላይ ግን ጥርሶቹ ከሚሰራባቸው ነገሮች አንጻር በሶስት ይከፈላሉ። ይኸውም አሳነባሪ (ኦክሌሪክ)፣ ለከለር ተብሎ የተለበጠበት (ክሮሞ ኮባልት) እንዲሁም ሶስተኛው ሴራሚክ ነው። በጥራት ደረጃ ሴራሚክ የሚባለው የበለጠ ተመራጭ ነው። በዚህ በቋሚ አርቴፊሻል ጥርስ ላይ ሌላው ክፍፍል ካሪጅ እና ኢምፕላንት ተብሎ ይከፈላል። ብሪጅ የሚባለው ግራና ቀኝ ሁለት ተሸካሚ ጥርሶች ተሞርደው እነሱ ላይ ጥርሶቹ ሲገጠሙ ማለት ነው። መካከል ላይ ጥርስ የተነቀለበት ክፍት ቦታ ኖሮ ግራና ቀኝ ግን ሁለት ተሸካሚ ጥርሶች ይኖራሉ ማለት ነው። ኢንፕላንት የሚባለው ግን ግራና ቀኝ ያለው ጥርስ ሳይነካ ጥርሱ በተነቀለበት ቦታ ብቻ ሲተከል ነው። ይሄ የሚደረገው እንደስር ኢምፕላንት ቁሶችን በመጠቀም እና በቀዶ ህክምና ወደ አጥንት ውስጥ በማስገባት ከዚያም ጥርሱን በማልበስ የሚሰራ ነው።

ሰንደቅ፡- ማንኛውም ሰው የዚህ የአርቴፊሻል ጥርስ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው? በተለየ ምክንያት ተጠቃሚ መሆን የማይችሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆን?

ዶ/ር ሽመልስ፡- በእርግጥ የሚወሰነው በባለሞያው ነው። እንደየታካሚው ታይቶ የሚወሰን እንጂ ይሄ ለዚህ ይሆናል፣ ያንኛው አይሆንም ማለት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ሁሉም ሰው ደግሞ ተጠቃሚ ይሆናል ማለትም አይቻልም። ሆኖም ግን ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል። ድዳቸው በጣም የተጎዱ ሰዎች፣ የስኳር ህሙማን እና ሌሎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ጥርሱ በሚገጠምበት ወቅት የአሰራር ችግር ተፈጥሮ ድድን የሚያቆስል፣ ለኢንፌክሽን የሚያጋልጥ እና የሚያስቆጣ ነገር እንዳይፈጠር የትኛው ነው የተሻለው የሚለውን ሀኪሙ ይመርጣል። ኢምፕላንትም ቢሆን ለቀዶ ህክምና ብቁ የሆነ ማንኛውም ሰው ሊሰራለት ይችላል። ነገር ግን ኢምፕላንት ከመሰራቱ በፊት በቂ አጥንት መኖሩ፣ የሚሰራው የፊት ጥርስ ከሆነም ከሳይንስ አንስቶ ያለው ርቀት ምን ያህል ነው? ኢምፕላንቱን ለመስራት የሚሆን በቂ ቦታ አለው ወይም የሚለው በምርመራ መረጋገጥ አለበት። እነዚህ ነገሮች በሙሉ ምርመራ ታይቶ ሲረጋገጥ እንጂ ሁሉም ሰው ተነስቶ ልሰራ ቢል ላይሆን ይችላል።

ሰንደቅ፡- ህፃናትን በተመለከተ የሚሰጠው አገልግሎት ከአዋቂዎች ለየት ያለ ነው። በእድሜ ረገድ ስናየው ከስንት ዓመት ጀምሮ ነው ህክምናው የሚሰጠው? ለህፃናት የማይሰጥ አገልግሎትስ ይኖራል?

ዶ/ር ሽመልስ፡- ለህፃናት ቋሚ አርቴፊሻል ጥርስ አይገጠምም። ምክንያቱም ህጻናቱ የወተት ጥርስ እና ቋሚ ጥርስ ድብልቅ ሊኖራቸው ይችላል። በአጋጣሚ ወይም በአደጋ ምክንያት ቋሚ ጥርስ ወልቆ ሊሆን ይችላል። ይሄ ማለት ግን ጥርስ አይተከልላቸውም ማለት አይደለም። ወጪ ገቢ ጥርሶችን በዚህ እድሜ ላይ መትከል ይቻላል። እድሜያቸው ሲደርስ (ከ16 ዓመት በላይ ሲሆኑ) ግን ቋሚ ጥርስ መትከል ይቻላል። ከዚያ በፊት ግን ወጪ ገቢ ጥርሶች መተከላቸው ግዴታ ይሆናል። ምክንያቱም በጥርሶቻቸው መካከል ክፍተት ሲኖር ጥርሶች ወደ ክፍቱ ቦታ መንሸራተት ባህሪይ አላቸው። በዚህ ጊዜ ለሌላው ጥርስ ቦታ እየያዙበት ይመጣሉ። ይሄ ደግሞ ለዘለቄታውም በጥርሳቸው ላይ መዛባትን ያስከትላል። በተፈጥሮ ቋሚ ጥርሶች አበቃቀል እና አቀማመጥ ላይ ችግር ይፈጥራል። በኋላ ላይ አርቴፊሻል ጥርስን መትከል በሚያስፈልግበት ጊዜ ለመትከልም አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ በትንሽነት እድሜያቸው ወጪ ገቢ ጥርሶችን መትከሉ የጥርስ ቦታው እንደተጠበቀ እንዲቆይ ለማድረግም ሆነ ለልጆች ስነልቦና ጠቃሚ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ፡- አንዳንድ ጊዜ በተለይ ቋሚ ጥርሶች ከተተከሉ በኋላ የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ። ጥርሶቹ ከድድ እየሸሹ ወደታች የመርዘም እንዲሁም ከሌሎቹ ለየት ብለው የመበለዝ ነገር ይስተዋላል። ይሄ ከምን የመነጨ ችግር ነው?

ዶ/ር ሽመልስ፡- የጥርሱ መበለዝ ጥርሱ ከተሰራበት ቁስ የመነጨ ነው። አሳ ነባሪ ጥርስ ከሆነ ከሌሎቹ በተለየ የመበለዝ ባህሪይ አለው። አሳ ነባሪም ሆኖ እንደየቁሱ ጥራት ሊለያይ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ግን በየጊዜው ንጽህናው የማይጠበቅ ከሆነ የመበለዝ ባህሪይ ሊያመጣ ይችላል። የተፈጥሮ ጥርስም ቢሆን ካልተጸዳ እንደሚበልዘው ሁሉ ይሄም ከቆሸሸ ይበልዛል። ጥርሶቹ ከተተከሉ በኋላ ወደታች የመርዘማቸው ችግርም ቢሆን ከመቆሸሽ ጋር የተገናኘ ነው። አርቴፊሻል ጥርስ ብቻም ሳይሆን የተፈጥሮ ጥርስም አንዳንድ ጊዜ ረዝሞ እናገኘዋለን። ይሄ የሚሆነው ድዱ ስለሚሸሽ ነው። በመቆሸሽ ምክንያት ኢንፌክሽን እየተፈጠረ ድድ እና አጥንት ይሸሻሉ። በዚህ በመመረዝ ምክንያት ድድና አጥንት ሲሸሹ ስሩ ይረዝምና ጥርስ የረዘመ ይመስላል። ብዙ ጊዜ የሚገጥመውም እንዲሁ አይነት ችግር ነው።

ሰንደቅ፡- አርቴፊሻል ጥርሶች ሲታሰቡ ብዙ ጊዜ ምግብ ከማኘክ እና ከፊት ውበት ጋር ተያይዘው ነው የሚነሱት። ነገር ግን ከዚህ በተጨማሪ የሚሰጡት ጠቀሜታ ይኖር ይሆን?

ዶ/ር ሽመልስ፡- አርቴፊሻል ጥርሶች በመሰራታቸው ከጉዳታቸው ይልቅ ጥቅማቸው ይበልጣል። ጥርስ በተፈጥሮው ሁለት አይነት ጠቀሜታዎች አሉት። ይኸውም የውበት ጥቅም እና የአገልግሎት ጥቅም (esthetic and functional) ጠቀሜታ አለው። ውበትን እንኳን ብንተወው ከአገልግሎት አንፃር ጥርሳችን ማኘክ አለበት። ጥርስ ሲያኝክ ደግሞ ምግብ ከማድቀቅ በተጨማሪም ጠቀሜታ አለው። ጥርስ ሲያኝክ አንድ ሶስት በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጡንቻዎች ስራ ይሰራሉ። እነዚህ ጡንቻዎች ስራ ከሰሩ የፊታችን ጡንቻዎች ከመሟሸሽ ይጠበቃሉ ማለት ነው። ይሄ ብቻ አይደለም፣ አጥንትም ጭምር ጤናማ እንዲሆን ጥርስ ማኘክ አለበት። የሚያኝክ ጥርስ ያለበት ድድ እና ጥርሱ ተነቅሎ ባዶውን የቆየ ድድ ተመሳሳይ ይዘት አይኖረውም። ጥርስ የሌለበት ድድ እንደ ምላጭ የሳሳ እና አጥንቱንም ቀጭን እና ለመጥ ይሆናል። ስለዚህ እዚህ ድድ ላይ አርቴፊሻል ጥርስ ሲተከልበት ጥርሱ ሲያኝክ ግፊት ይፈጠርበታል። በዚህም ግፊት ምክንያት አጥንቱ መሸሹን ያቆማል። ጡንቻ እየሰራ  ካልሄደ እየሟሸሸ ነው የሚመጣው። እነዚህ የፊት ጡንቻዎች በጣም ስስ ስለሆኑ የሚያኝክ ጥርስ ከሌለ በቀላሉ ይሟሽሻሉ። ከዚህ አንፃር በፊት ገጽታ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል። አጥንትም የሚሸሽ ከሆነ እንደዚሁ የፊት ገጽታን ይቀይረዋል። ይሄ ተፅዕኖ የሚኖረው በፊት ጥርሶች ላይ ጭምር ነው። በጣም ያረጁ እና ጥርሳቸው ያለቀ ሰዎች ከአፍንጫቸው በታች ያለው እና አንድ ሶስተኛው የፊታቸው ክፍል ያጠረ ነው የሚሆነው። ፊታቸው ረዘም ያለ እና ሰልካካ የነበሩ ሰዎች ጥርሳቸው ካለቀ የታችኛው የፊታቸው ክፍል ያጠረ እና ምራቃቸውን መሰብሰብ የማይችሉ ይሆናሉ። ስለዚህ ይሄ ክፍተት በአርቴፊሻል ጥርስ ሲተካ ወደ ቀድሞ ገፅታቸው የመመለስ እድል ይኖራቸዋል።

ሰንደቅ፡- ከፊል አርቴፊሻል ጥርስ ሆኖ በቋሚነት በሚተከልበት ወቅት ከጎኑ ያለው የተፈጥሮ ጥርስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትልበት ሁኔታ ይኖር ይሆን?

ዶ/ር ሽመልስ፡- ተፅዕኖ የሚኖረው ብሪጅ በሚባለው መንገድ የሚሰራ ከሆነ ነው። ይሄንኛው አሰራር ተሸካሚዎቹን በመሞረድ እና አርቴፊሻል በማልበስ የሚሰራ ስለሆነ ለውጥ ይመጣባቸዋል። ስለዚህ በተሻለ አቅም አርቴፊሻል ጥርስ ገብቶ እንዲህ አይነት ነገሮች እንዳይፈጠሩ ፈጥኖ ወደ ህክምና መሄድ ይመከራል። ጥርሳችን ላይ ጣፋጭ፣ ቀዝቃዛ ወይም ሙቅ ነገርን ስንጠቀም የሚመጡ ለውጦችን ተከታትሎ በመታከም የተፈጥሮ ጥርስን ለማቆየት መሞከር ይመከራል።

ሰንደቅ፡- በተፈጥሮም ሆነ በአበቃቀል ችግር ሲገጥም በአርቴፊሻል ጥርሶች የመተካት ፍላጎት ይስተዋላል። ይሄ በህክምናው እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ሽመልስ፡- ብዙ ጊዜ አርቴፊሻል ጥርሶችን ለውበት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። የተፈጥሮ ጥርሳቸው ገጦባቸው ወይም ተወላግዶባቸው ከሆነ በአርቴፊሻል ጥርስ መተካት ብቻ ነው መፍትሄው ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ። ነገር ግን ለሁሉም ጥርስ ውበት አርቴፊሻል ጥርስ ብቻ አይደለም ያለው። እንዲያውም ጥርሱን በአርቴፊሻል ከመተካት ይልቅ በሌላ ዘዴዎች ተጠቅሞ የተፈጥሮ ጥርሶችን ማስተካከል ይቻላል። ምክንያቱ ደግሞ የተፈጥሮ ጥርስ በምንም የማይተካ እና ውድ ነገር ነው። ለውበትም የተፈጥሮ ጥርስን የሚያክል ነገር አይኖርም።

ሰንደቅ፡- ማኝኛውም ህክምና ከጥቅሙ ጎን ለጎን ጉዳት እንዳለው ሁሉ አርቴፊሻል ጥርስ መትከሉም የራሱ ጉዳት ሊኖረው ይችላልና በተለይ በድድ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ምንድን ነው? ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄስ ምነድን ነው?

ዶ/ር ሽመልስ፡- እነዚህ አርቴፊሻል ጥርሶች ከሚሰራባቸው ቁሶች አንፃር እስከ አሁን የተረጋገጠ ጉዳት የለም። ነገር ግን ከአገጣጠማቸው የተነሳ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ከድዱ እና ከጥርሱ ጋር ያለው የአገጣጠም ሂደት ትክክል ካልሆነ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ለምሳሌ ከሚፈለገው በላይ ጉልበት (ኃይል) ከተጠቀምን እና ድድ የመቆጣት ነገር ከተፈጠረበት በረጅም ጊዜ ጉዳት ሊያደርሰ ይችላል። እነዚህ በአገጣጠም ጊዜ የሚከሰቱ ችግሮች ለዕጢ እና ከዚህም ለከፋ ነገር ሊዳርጉ ይችላሉ። ምክንያቱም በትክክል ካልተገጠመ የሆነ ቦታ ላይ የመላጥ፣ የመፈግፈግ፣ እና የማበጥ ሁኔታ ሲፈጠር ሰውነት እየተቆጣ ሌላ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ሌሎችም እንደዚህ ሲገጠሙ በድድ ውስጥ በከፍተኛ ኃይል ከተገጠሙ ድዱ ላይ የማበጥ፣ የመድማት እና የኢንፌክሽን ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ ግን ከእቃዎቹ የተነሳ የሚያስከትለው ጉዳት እስካሁን አልታወቀም።     

ጥንቃቄን በተመለከተ ከተፈጥሮው ጥርስ የበለጠ ንጽህናቸው መጠበቅ አለበት። በተጨማሪም ጥንካሬ ያላቸውን ነገሮች ለማኘክ አለመሞከር ያስፈልጋል። ጥርሱ ሴራሚክ ከሆነ ጥንካሬው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ከዚያ ውጪ ከሆነ ግን ጠንካራ ነገሮችን ለመንጨት እና ለማኘክ መሞከር አይገባም። በተረፈ በጥርሳቸውም ሆነ በድዳቸው ላይ ማንኛውንም አይነት ለውጥ ሲያስተውሉ በፍጥነት በባለሞያ መታየት እና መታከም ይኖርባቸዋል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2189 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Addvvrt1.jpg
  • Adv.jpg
  • Advverttt.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1054 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us