የኩላሊት ጤንነትን በምግቦች

Wednesday, 04 January 2017 14:44

 

የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች ህመሙ ከሌለባቸው ሰዎች በበለጠ ለከፍተኛ የሰውነት መቆጣት እና ከልብ ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱ ህመሞች የበለጠ ተጋላጮች ናቸው። በመሆኑም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የአንቲኦክሲደንት ይዘት ያላቸውን ምግቦች ማዘውተር ይጠበቅባቸዋል። እግረ መንገዳቸውንም በቂ ኃይል ለማግኘት የተመጣጠነ እና በተለይ ለዚህ ዓላማ የሚጠቅሙ የምግብ ዝርያዎችን በማዘውተር ህመሙን ለመቋቋም ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የእንግሊዝ ኩላሊት ህክምና ማዕከል ይመክራል። ምንም እንኳን እያንዳንዱ ሰው በየእለት አመጋገቡ ውስጥ የተመጣጠነ አመጋገብን መከተል ተገቢ ቢሆንም፣ የኩሊት ህመምተኞች ደግሞ በተለየ መልኩ ራሳቸውን ለመጠበቅ ያግዟቸዋል የተባሉ ጠቃሚ የምግብ አይነቶችን ማዕከሉ ዘርዝሯቸዋል።

 

ቀይ ቃሪያ

ቀይ ቃሪያ ስለኩላሊታቸው ጤንነት ለሚጨነቁ ሰዎች ቀዳሚው ምርጫ ነው። ቀይ ቃሪያ የፖታሲየም ማዕድን ይዘቱ ዝቅተኛ ሲሆን፣ ይህም የኩላሊትን ጤንነት ለመጠበቅ ጠቃሚው ነው። ይህ ቃሪያ የቫይታሚን ኤ፣ ሲ፣ ቢ6 እንዲሁም የፎሊክ አሲድ እና የአሰር ይዘቱ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ቀይ ቃሪያ የተወሰነ የካንሰር አይነቶችን ለመከላከል የሚጠቅመው ላይኮፔን የተባለው አንቲኦክሲደንት ጥሩ ምንጭ ነው። በመሆኑም ይህን ቀይ ቃሪያ ከተለያዩ የምግብ አይነቶች ጋር በመቀላቀል በጥሬው በመመገብ የኩላሊት ጤንነት ለመጠበቅ ያግዛል።

 

ጎመን እና አበባ ጎመን

ጎመን በተወሰኑ የአትክልት ዝርያዎች ውስጥ ብቻ በሚገኙ ፓይቶኬሚካሎች የበለፀገ አትክልት ነው። እነዚህ ኬሚካሎችም ፍሪራዲካሎችን በመሰባበር በሰውነታችን ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ያግዛሉ። በተጨማሪም እነዚህ ኬሚካሎች ካንሰርን እና ከልብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ህመሞችን የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። ሌላው በጎመን ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች ደግሞ ቫይታሚን ሲ እና ኬ፣ ቢ6፣ ፎሊክ አሲድ እና አሰር ናቸው። ጎመን የፖታሲየም ማዕድን ይዘቱ አነስተኛ በመሆኑም ለኩላሊት ጤንነት ተስማሚ የአትክልት ዘር ነው።

ሌላው የኩላሊት ህመምተኞች አዘውትረው እንዲመገቡ የሚመከረው የአትክልት ዝርያ አበባ ጎመን ነው። አበባ ጎመን በተፈጥሮ በከፍተኛ ቫይታሚን ሲ የበለፀገ የአትክልት ዘር ነው። አበባ ጎመን በተጨማሪም የፎሌት እና አሰር ይዘቱ ከፍተኛ ሲሆን፣ ጉበት መርዛማ ነገሮችን ሊያጠፋባቸው በሚችል ንጥረ ነገሮችም የበለፀጉ አትክልት ነው። በመሆኑም እነዚህ የአትክልት ዝርያዎች በተለያየ መልኩ በየእለቱ ምግብ ውስጥ በማካተት ከህክምና ጎን ለጎን የኩላሊት ህመምን መቋቋም ያስችላል።

 

ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት

በየዕለት ምግባችን ውስጥ የማይጠፋው ቀይ ሽንኩርት ምግብን ከማጣፈጥ በተጨማሪም ሌላ የጎላ ጠቀሜታ አለው። ቀይ ሽንኩርት ኩርቴሲን በተባሉ ፍላቨኖይድን የተሞሉ ናቸው። እነዚህ ውህዶች ደግሞ በደም ስር ውስጥ የሚገኙ ስቦችን ክምችት የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። በተጨማሪም እነዚህ ውህዶች ሃይለኛ አንቲኦክሲደንት በመሆናቸው የልብ በሽታን እና በርካታ የካንሰር ህመሞችን የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። ቀይ ሽንኩርት የሰውነት መቆጣትን የመከላከል ባህሪይ ያለው አትክልት በመሆኑ የኩላሊት ህሙማን ሁልጊዜ ከሚቸገሩበት ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ያግዛቸዋል። ቀይ ሽንኩርት የፖታሲየም ማዕድን ይዘቱ ዝቅተኛ ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ ክሮሚየም የተባለው እና የስብ፣ ፕሮቲኖች እና ካርቦሃይድሬቶችን ሜታቦሊዝም ሊያግዝ የሚችል ማዕድን ይዘቱ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ለኩላሊት ህመምተኞች ተስማሚ ከሚባሉ የአትክልት አይነቶች ይመደባል።

ሌላው ባለብዙ ጠቀሜታው የሽንኩርት አይነት ደግሞ ነጭ ሽንኩርት ነው። ነጭ ሽንኩርት ከምግብነቱ ይልቅ የመድሃኒትነት ባህሪው እንደሚያደላ ነው ባለሞያዎች የሚናገሩት። ነጭ ሽንኩርት በደም ውስጥ ያለውን ኮሌስትሮል የመቀነስ እና የሰውነት መቆጣትን የመካለከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ነጭ ሽንኩርት በአንቲ ኦክሴዳንት የበለፀገ እና የደም መርጋትንም ለመከላከል የሚያግዝ አትክልት ነው። ነጭ ሽንኩርት እነዚህን ጠቀሜታዎች መስጠት የሚችለው በጥሬው አገልግሎት ላይ መዋል ሲችል ነው። ከዚህ ውጪ ተፈጭቶ በሚዘጋጅ መልኩ መጠቀም የሚቻል ሲሆን፤ በደንብ ተቀቅሎ እና በስሎ የምንጠቀመው ከሆነ ግን በተለይ የደም መርጋት ችግርን ለመከላከል ያለው አቅም ይቀንሳል።

 

 

አፕል እና እንጆሪ

አፕል ወይም ፖም ሌላው የኩላሊት ህመምተኞች አዘውትረው እንዲመገቡት የሚመከር የፍራፍሬ አይነት ነው። በቀን አንድ አፕል የሚመገብ ሰው ዶክተር አያስፈልገውም ይላሉ ጠቀሜታውን የሚናገሩ ሰዎች። አፕል በተፈጥሮው ከፍተኛ የሆነ የአሰር ይዘት ያለው ሲሆን፤ የሰውነትን መቆጣት የመከላከል ባህሪውም ከፍተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪም አፕል በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። ከእነዚህ ጠቀሜታዎቹ መካከልም ጥቂቶቹ በደም ውስጥ የሚገኘውን ኮሌስትሮል መቀነስ፣ የሆድ ድርቀትን መከላከል፣ የልብ ህመምን መከላከል እና ካንሰር የሚኖረውን ተጋላጭነት መቀነስ ተጠቃሾቹ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉ ጠቀሜታዎቹ የሚልቀው ግን ለኩላሊት ህመምተኞች ተስማሚ መሆኑ ነው።

ከፍራፍሬዎች ሌላው የኩላሊት ህመምተኞችን ህመሙን እንዲቋቋሙ ያግዛል የተባለው የፍራፍሬ ዘር እንጆሪ ነው። የእንጆሪ ተፈጥሯዊ ይዘትን ስንመለከት በሁለት አይነት አንቲኦክሲደንቶች የበለፀገ፣ ከፍተኛ የሆነ የቫይታሚን ሲ ክምችት ያለው እንዲሁም ጥሩ የሆነ የአሰር እና ማግኒዚየም ማዕድን ምንጭም ነው። በዚህ ይዘቱ የተነሳም የሰውነት መቆጣትን፣ ካንሰርን እና የልብ ህመምን የመከላከል ጠቀሜታ አለው። እንጆሪ በተለያየ ቀለም እና ዝርያ የሚገኝ ሲሆን፤ ሁሉም የእንጆሪ ዝርያዎች በቫይታሚን ሲ እና ማግኒዚየም ማዕድን እንዲሁም አሰር የበለፀጉ ናቸው። በእንጆሪ ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች ለኩላሊት ሀሙማን ተስማሚ ከመሆናቸውም በላይ የካንሰር ሴሎችን እድገት የመግታት እና እጢዎች እንዳይፈጠሩ የማድረግ ባህሪይ አላቸው። አንዳንዶቹ የእንጆሪ ዝርያዎችም ባክቴሪያዎች የፊኛ የውስጠኛው ክፍል ላይ እንዳይጣበቁ በማድረግ ሽንት በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን አሲድ በብዛት እንዲያስወግድ የማድረግ አገልግሎት ይሰጣሉ።

 

የእንቁላል ነጩ ክፍል

የእንቁላል ነጩ (ፈሳሽ) ክፍል ከአስኳሉ ይልቅ የፕሮቲን ይዘቱ ከፍተኛ ነው። አብዛኛው የዚህ የእንቁላል ክፍል ፕሮቲን ሲሆን፤ በተጨማሪም የአሚኖ አሲድ ይዘቱ ከፍተኛ ነው። ይህ የእንቁላል ክፍል ከእንቁላል አስኳል እና ከስጋ ያነሰ የፎስፈረስ ይዘት አለው። በተጨማሪም የፖታሲየም ማዕድን ይዘቱ አነስተኛ በመሆኑ ለኩላሊት ህሙማን ተስማሚ ከሆኑ የምግብ አይነቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።

 

እንጉዳይ

እንጉዳይ ከያዛቸው ንጥረ ነገሮች መካከል ተጠቃሹ እና ከኩላሊት ጤንነት ጋር ተያያዥነት ያለው ቫይታሚን ዲ ነው። ይሄ ቫይታሚን ዲ የኩላሊት ተግባራትን የመቆጣጠር እና ጤናማ እንዲሆኑ የማገዝ አግልግሎት ይሰጣል። እንጉዳይ ደግሞ ጥሩ የዚህ ቫይታሚን አይነተኛ ምንጭ በመሆኑ ለኩላሊት ህሙማን ተስማሚ ነው። የፖታሲየም ይዘቱም አነስተኛ ነው።

 

የወይን ፍሬዎች

የወይን ፍሬ ጥሩ የሆነ የቫይታን ሲ ምንጭ ነው። ይሄ የቫይታሚን አይነትም ሰውነት በሽታን ለመከላከል ያለው አቅም እንዲዳብር የማድረግ እንዲሁም ባክቴሪያዎች በሰውነት ውስጥ እንዳይራቡ የማድረግ አገልግሎት አለው። የወይን ፍሬዎች በቀይ እና በአረንጓዴ እንዲሁም በወይንጠጅ ቀለም የሚገኙ ቢሆንም ሁሉም ለኩላሊት ህመምተኞች ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እነዚህ ፍሬዎች በተፈጥሯቸው ያላቸው የፖታሲየም ማዕድን ይዘት አነስተኛ መሆኑም ለዚህ አገልግሎት ተመራጭ ያደርጋቸዋል። በቀይ የወይን ፍሬ ውስጥ የሚገኙት ፍላቮኖድስ ለኩላሊት ከሚሰጡት ጠቀሜታ በተጨማሪም የደም መርጋትን ለመከላከልና የልብ ጤንነትን ለመጠበቅ ይጠቅማሉ። በተለይም ሪስቬራትሮል የተባለው በዚህ የወይን ፍሬ ውስጥ የሚገኘው ፍላቮኖድ ደግሞ የጡንቻ መፍታታትን ስለሚጨምር እና የደም ስሮችን ጤንነት ስለሚጠብቅ ጤናማ የሆነ የደም ዝውውርን በሰውነት ውስጥ እንዲኖር ያግዛል። በተጨማሪም የወይን ፍሬዎች ይዘት ከፍተኛ የሆነ የካንሰር ህመም እና የሰውነት መቆጣትን የመከላከል ባህሪይ አላቸው።

የኩላሊት ህሙማን ከህክምና ጎን ለጎን በአመጋገባቸው ላይም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው ማዕከሉ የሚያሳስበው። በተለይ የእንስሳት ተዋፅኦ የሆኑ እና ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያላቸውን እንዲሁም የፖታሲየም እና ፎስፈረስ ማዕድናት ይዘታቸው ከፍተኛ የሆነ ምግቦችን ማስወገድ ይኖርባቸዋል። የእንስሳት ተዋፅኦ የሆኑ ምግቦች የኩላሊት ህመም ባለባቸው ሰዎች ላይ የሰውነት መቆጣትን የማስከተል ባህሪይ አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የፎስፈረስ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆነ የምግብ አይነቶች የኩላሊት ጠጠር እንዲፈጠር የማድረግ ችግር ይፈጥራል። በመሆኑም በየእለት አመጋገብ ውስጥ የስጋ እና የወተት ተዋፅኦዎችን በመቀነስ እንዲሁም አልኮል ባለመጠቀም የኩላሊት ጤንነትን መጠበቅ እንዲሁም ከህመሙ ጋር በሰላም መኖር እንደሚቻል ይመክራሉ።

ይምረጡ
(14 ሰዎች መርጠዋል)
3051 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Addvvrt1.jpg
  • Adv.jpg
  • Advverttt.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1052 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us