በአይናችን ላይ ያነጣጠረውን ቴክኖሎጂ እንዴት እንቋቋመው?

Wednesday, 11 January 2017 14:20

ስልጣኔና የቴክኖሎጂ መስፋፋት ያበረከቱልን በርካታ መልካም ነገሮች የመኖራቸውን ያህል ከእነዚህ ነገሮች ጎን ለጎን በተለይ በጤናችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ይዘው የሚመጡ በርካታ ጉዳቶች አሏቸው። ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ደግሞ ከአብዛኞቻችን የእለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የማይጠፋው ተንቀሳቃሽ ስልክ /ሞባይል/ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በተለይ ስማርት ስልኮች በብዙዎች እጅ ላይ የሚስተዋሉ ዘመን አፈራሽ መሣሪያዎች ሆነዋል። በአይን ጤንነት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሰሩ ተቋማት ታዲያ እንደስማርት ስልክ እና ኮምፒውተሮች እንዲሁም ታብሌቶች ላይ ለረጅም ጊዜ አፍጥጦ መቆየት በአይናችን ጤንነት ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት ልብ ባንለው እንጂ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢው ጉዳይ ነው ይላሉ። በባርሴሎና ህክምና ዩኒቨርስቲ የአይን ጤና አጠባበቅ ኢንስቲቲዩት እና ቪዥን ካውንስል የተባለ በአይን ጤንነት ላይ ያተኮረ ተቋምም በቅርቡ ያደረጉትን ጥናት ይፋ አድርገዋል።

ጥናቱ እንደሚለው ምንም እንኳን እኛ ልብ ባንለውም በቀን ውስጥ ካሉት ሰዓታት ውስጥ አብላጫውን የምናሳልፈው እነዚህ ከላይ በተጠቀሱ ዲጂታል ስክሬቶች ላይ በማፍጠጥ ነው። በአማካይም አንድ ሰው ከ24 ሰዓታት ውስጥ 6ቱን ሰዓት በእነዚህ እስክሪኖች ላይ አፍጥጦ ያሳልፋል። በዚህም ሳቢያ አይናችን ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ከእነዚህ ስክሪኖች ለሚወጣ ጨረር ተጋላጭ ይሆናል። በአሜሪካ በተደረገ ጥናትም 65 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ለዚህ ጨረር ካላቸው ተጋላጭነት የተነሳ ለአይን መወጠር የተጋለጡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ህፃናትና ታዳጊዎች ጭምር ገና በታዳጊነታቸው ለነዚህ መሣሪያዎች ያላቸው ተጋላጭነት እየጨመረ በመምጣቱ የሚያስከትላቸው ጉዳቶችም በዚያው መጠን እየጨመረ መጥቷል። ይሄንንም በህክምናው ዲጂታል አይ ስትሬን (Digital Eye strain) ይሉታል።

ዲጂታል አይ ስትሬን ምንድን ነው?

ዲጂታል አይ ስትሬን የሚባለው አካላዊ ስሜት አይን ለረጅም ጊዜ ከዲጂታል መሣሪያዎች ለሚወጣ ጨረር በሚጋለጥበት ወቅት የሚፈጠር ስሜት ነው። ይህ ስሜት በአይን ላይ የሚከሰት ምቾት የሚነሳ የመወጠር ስሜት ነው። ይህ በዲጂታል ስክሪኖች ብርሃን ሳቢያ የሚከሰት ስሜት በአይን መወጠር ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን አይንን ማድረቅ፣ ለክፍተኛ የራስ ምታት መዳረግ፣ በአይን ላይ ብዥታን መፍጠር እየከፋ ሲሄድም እይታን እስከመጨረሻው የማሳጣት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ጥናቱ እንደሚገልፀውም አብዛኞቻችን ለእነዚህ ጉዳቶች የመደራጋችን ስሜት መስማት የሚጀምረን ለተከታታይ ሁለት ሰዓታት በቅርብ ርቀት እና በመካከለኛ ርቀት ላይ እነዚህን ዲጂታል ስክሪኖች አተኩረን ስንመለከት ነው። በአይን ላይ እነዚህ ጉዳቶች እንዲደርሱ የሚያደርገውም በእነዚህ ዲጂታል ስክሪኖች ላይ ብዙ ላይት የተባሉ ጎጂ ንጥረ ነገሮች በፍጥነት እየተባዙ በመምጣታቸው ምክንያት ነው። ይሄ ብሉ ላይት የተባለ ንጥረ ነገር ደግሞ እንደ ስማርት ስልክ፣ ታብሌት፣ ጠፍጣፋ ስክሪን ያላቸው ቴሌቭዥኖች እና የኮምፒውተር ስክሪኖች የሚያመነጩት ከፍተኛ ኃይል ያለው ብርሃን ነው። ይሄንን ብርሃንም ለረጅም ጊዜ አተኩረን ስንመለከተው ብርሃንን ተቀብሎ ምስልን ወደ አእምሮ የሚልከውን እና ሬቲና የሚባለውን የአይናችንን ክፍል በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ ነው። ይሄ ጎጂ ብርሃን የአይን እይታችንን ብቻም ሳይሆን ተፈጥሯዊውን የእንቅልፍ ሽክርክሪታችንን የማዛባት ጉዳትም አለው።

እንዴት መከላከል ይቻላል?

ለእነዚሁ መሣሪያዎች ያለን ተጋላጭነት የማይቀር እና ግዴታ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ ከጨረሩ መራቅ ካልተቻለ ቢያንስ መከላከል የሚቻልበት ሁኔታ መኖር አለበት። የመጀመሪያው የመከላከያ መንገድ ለእነዚህ ጨረር አመንጪ ቁሳቁሶች ያለንን ተጋላጭነት መቀነስ ነው። ከዚህ ውጪ ግን ረጅም ሰዓታትን ከእነዚህ ቁሶች ጋር ማሳለፍ የግዴታ ከሆነ ሊወሰዱ የሚገባቸው ቀላል እርምጃዎችን ጥናት አቅራቢዎቹ ጠቁመዋል። እነዚህ እርምጃዎችም ተጋላጭነታችንን ባያስቀሩትም በአይናችን ላይ የሚከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ ግን ጠቃሚ ናቸው።

የ20-20-20 ህግን መተግበር

አይናችን ከጡንቻዎች የተሰራ እንደመሆኑ በየጊዜው እንቅስቃሴ ያስፈልገዋል ይላሉ ባለሞያዎቹ። አይኖቻችን ይሄንን እንቅስቃሴ የሚያደርገው ደግሞ በተወሰነ ሰዓት የትኩረት አቅጣጫውን በመቀያየር ነው። ይህ ህግ እንደሚለውም በየ20 ደቂቃው አይናችን የ20 ሰኮንዶች እረፍት እንዲያደርግ በማድረግ በ20 ጫማ ርቀት ላይ ያለ ነገርን እንዲመለከት ማድረግ ነው። ይሄንን በማድረግም አይናችንን በመመልከት የሚገጥመው ድካም እንዲቀንስለት እና ጤናማ እንዲሆን ያግዘዋል።

አይን ማርገብገብ

በአንድ ነገር ላይ ትኩር ብለን በምንመለከትበት ወቅት አይናችንን መርገብገብን እንዘነጋለን። ነገር ግን አይን የሚርገበገበው በደመ ነፍስ መርገብገብ ስላለበት ብቻ አይደለም። ይልቁንም የአይናችን ኳስ እርጥበት እንዲያገኝ እና እንዳይደርቅ ለማድረግ ነው። በመሆኑም በአንድ ነገር ላይ ለረጅም ጊዜ በምናተኩርበት ወቅት አይናችን እርጥበት ያጣና የደረቀ ይሆናል። ጥናቱ እንደሚለውም በአንድ ነገር ላይ በምናተኩርበት ጊዜ የአይናችን የመርገብገብ መጠን እስከ 30 በመቶ ይቀንሳል። በዚህም ሳቢያ አይናችን ለመድረቅ እና ለመወጠር ይዳረጋል። ስለዚህ በእነዚህ ኃይለኛ ብርሃን አመንጪ የሆኑ ነገሮች ላይ ለረጅም ጊዜ የምናተኩር ከሆነ አይናችንን ማርገብገባችንን መዘንጋት የለብንም።

ብርሃኑን መመጠን

የምናተኩርባቸው ጨረር አመንጪ ቁሳቁሶች የሚያመነጩት ብርሃን መጠን ወደ አይናችን የሚሄደውን ብርሃን መጠን ይወስነዋል። የሚመነጨው ብርሃን ኃይለኛ እና ብዙ ከሆነ ወደ አይናችን የሚሄደውም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ጨረር ይሆናል። ይሄ ብቻም አይደለም። በቁሳቁሶች ዙሪያ ያለው ብርሃን ከፍተኛ ሲሆን፤ ነፀብራቅ የሚኖረው ሲሆን፤ ይሄ ብርሃን አነስተኛ በሚሆንበት ወቅት ወይም በቂ እና የተመጣጠነ ብርሃን ሳይሆን ሲቀር ደግሞ አይናችን ትኩረት የበለጠ እስክሪኑ ላይ እንዲያተኩር ያደርገዋል። በመሆኑም በክፍል ውስጥ ያለውን ብርሃን ማመጣጠን ያስፈልጋል።

ርቀትን መጠበቅ

ሌላው ለዚህ ጎጂ ጨረር የመጋለጥ እድላችንን የምንቀንስበት መንገድ ከምናተኩርበት ቁስ ስክሪን ጋር ያለንን ርቀት በመጨመር ነው። ይበልጥ ወደ ስክሪኖቹ እየቀረብን በመጣን ቁጥር ከስክሪኖቹ ላይ የመነጩት የብርሃን ሃይሎች በፍጥነት እና በብዛት ወደ አይናችን የመዛመት አጋጣሚን ስለሚያገኙ በአይናችን ላይ ጉዳት የማድረስ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል። በመሆኑም እነዚህን የዲጂታል ስክሪን መሳሪያዎች በምንጠቀምበት ወቅት በስክሪኑ እና በአይናችን መካከል የሚኖረው ርቀት ቢያንስ 20 ኢንች ያህል መሆን ይኖርበታል። በዚህም ወደ አይናችን የሚገባውን ጨረር መጠን መቀነስ እና የአይናችንን መወጠርም መከላከል ይቻላል።

ከመኝታ በፊት ከእነዚህ መሣሪያዎች መራቅ

አብዛኞችን እነዚህን ዲጂታል ስክሪን መሣሪያዎች በብዛት ከምንጠቀምባቸው ጊዜያት መካከል ዋናው ወደ እንቅልፍ ለመሄድ በአልጋችን ላይ ጋደም በምንልበት ወቅት ነው። ወደ እንቅልፍ ከማምራታችን አስቀድመን ስልኮቻችን መነካካት የሚቀናን ግፋ ሲልም እንቅልፍ ሲጥለን ብቻ ከእነዚህ መሳሪያዎች የምንለይ አለን። ነገር ግን ይሄ ልምድ ለአይናችን ጤንነት አደገኛ በመሆኑ ማስወገድ እንዳለብን ነው ባለሞያዎቹ እየገለፁ ያሉት። ወደ መኝታችን ከመሄዳችን አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ እነዚህ ዲጂታል ስክሪን ያላቸው መሳሪያዎች ላይ ማተኮር የአይናችን ለብሉ ላይት ያለው ተጋላጭነት በእጥፍ እንዲጨምር ያደርገዋል ይላል ጥናቱ። በአብዛኛው በእንቅልፍ ሰዓት ላይ እነዚህን መሳሪያዎች የምንጠቀመው መብራት አጥፍተን ወይም ደብዛዛ ቀለም ያለው አምፑል ተጠቅመን ከሆነ ደግሞ አይናችን ሙሉ ትኩረቱ በስክሪኑ ላይ ስለሚሆን አይናችን ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ ይሆናል ይላሉ ባለሞያዎቹ። በመሆኑም ወደ መኝታችን ከማምራታችን አስቀድሞ ከእነዚህ መሳሪያዎች ጋር ያለንን ንክኪ ማቋረጥ ይኖርብናል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2152 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 115 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us