ባህል ያመጣው ጣጣ

Wednesday, 18 January 2017 10:30

 

በተለያየ መልኩ በሴት ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ተግባራት ከድሮ ጊዜ ጀምሮ በአለማችን የተለያዩ ክፍሎች በስፋት ሲተገበሩ ቆይተዋል።  ከእነዚህ ተግባራት መካከል የሴት ልጅ ጾታዊ ጥቃት እና የሴት ልጅ ግርዛት ስር የሰደዱ እና ከተለያዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ጋር ተያይዘው የሚተገበሩ ናቸው።  እነዚህ ድርጊቶች ለፈጻሚዎቹ እና ለዚያ ማህበረሰብ የተለየ ትርጉም የሚሰጣቸው ተግባራት ይሁኑ እንጂ በተለያዩ ለሴቶች መብት በአጠቃላይ ለሰው ልጅ መብት በቆሙ አካላት ዘንድ ግን ከመብት ጥሰት ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው በመጥቀስ ይወገዛሉ።  ድርጊቶቹ የሴት ልጅን ብሎም የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብት ከመጣስ እንዲቆጠሩ የአለም ጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ህጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) በተለያዩ ጊዜ ሲገልፁ ቆይተዋል።  በዓለም አቀፍ ደረጃም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተብለው ተኮንነዋል።  እነዚህ እና መሰል አካላት ባደረጉት መጠነ ሰፊ ርብርብ አንዳንዶቹ ድርጊቶች እየቀነሱ የመጡ ሲሆን፣ በተቃራኒው ሌሎቹ ደግሞ እየጨመሩ መጥተዋል።  ድርጊቶቹን ለማስቀረት በይበልጥ የሚፈለገው የማህበረሰቡን ግንዛቤ መቀየር ሆኖ በመገኘቱም በዚህ ረገድ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።  በእነዚህም ስራዎች በተለይ በግርዛት ላይ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሳቢያ ለስቃይ የሚዳርጉ ሴት ታዳጊዎችና አዋቂ ሴቶች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል።

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየተነገረ ያለውም በኢትዮጵያ ለሴት ልጅ ግርዛት ያለው ግንዛቤ እየተስፋፋ፣ ድርጊቱም እየቀነሰ መምጣቱ ነው።  በተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ ሪፖርት እንዳደረገውም እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም በሀገሪቱ ከሚገኘው 94 ሚሊዮን ህዝብ መካከል 74 በመቶዎቹ ልጃገረዶችና አዋቂ ሴቶች ግርዛት የተፈፀመባቸው ሲሆን፤ ከአስር አመት በኋላ (በ2016) ይህ አሃዝ ወደ 65 በመቶ ዝቅ ብሏል።  ማህበረሰቡም ስለድርጊቱ ያለው አመለካከት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን ጥናቱ አመልክቷል።  ይሄንን ውጤት ማግኘት የተቻለውም ማህበረሰቡ ስለድርጊቱ በቂ እና ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖረው ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት እንደሆነ ተገልጿል።

እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ብቻ 23 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ልጃገረዶችና ሴቶች ግርዛት ተፈፅሞባቸው እንደነበረ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) አስታውሷል።  ይህ ቁጥርም ኢትዮጵያ ችግሩ ከተስፋፋባቸው የአፍሪካ ሀገራት ከግብፅ ተከትላ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓት ነበር።  በወቅቱ ይሄ ድርጊት በብዛት ተስፋፍቶ ይገኝ የነበረው በአፋር፣ በሶማሊያ እና ድሬዳዋ አካባቢዎች እንደነበረም ተገልጿል።  ከዚሁ በተቃራኒው ደግሞ ይህ የልጃገረዶችና ሴቶች ግርዛት በጋምቤላ ክልል ያለው ስርጭት ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።  በእነዚህ ክልሎች የነበረውን የስርጭት መጠን ሲገልጽም በ2007 እ.ኤ.አ. በአፋር ከሚገኙ ልጃገረዶችና ሴቶች መካከል 87 ነጥብ 4 በመቶዎቹ፣ በሶማሊያ 70 ነጥብ 7 በመቶዎቹ የዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተጠቂዎች ነበሩ።  የኢትዮጵያ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ድርጅት እንደጠቀሰው ደግሞ በዚሁ ዓመት በሀገሪቱ ከሚገኙ ብሔሮች መካከል 46ቱ  የሴት ልጅ ግርዛት ይካሄድባቸዋል።  መረጃው እንዳመለከተውም ግርዛቱ የሚፈፀመው እድሜያቸው እስከ 8 ቀን በሆነ ሴት ህጻናት ላይ ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ ይሄ በሴቶች ላይ የሚተገበር ግርዛት እንዲቀር ጠንክረው ከሰሩ እና ስለጉዳቱም በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ግንዛቤ እንዲፈጠር ካደረጉ ሀገራት አንዷ በመሆኗ ሌሎች ሀገራትም ፈለጓን እንዲከተሉ አርአያ ሆናለች።  ምንም እንኳን በአንዳንድ ሀገራት መሻሻል ቢታይም በሌሎች ሀገራት ደግሞ በርካታ ልጃገረዶችና ሴቶች የዚህ ድርጊት ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ።  ዛሬም በዓለማችን ላይ በ30 ሀገራት ውስጥ ብቻ 200 ሚሊዮን ግርዛት የተፈፀመባቸው ሴቶች ይኖራሉ ተብሏል።  ከእነዚህ ሴቶች መካከል ግማሾቹ የሚገኙት ደግሞ በግብጽ፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መሆኑን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።  ይሄ የሚያመለክተው ምንም እንኳን አዲስ የድርጊቱ ተጠቂዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም ዛሬም ድረስ ግን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ግርዛቱ ባስከተለባቸው የጤናና የህይወት ዝብርቅርቅ ውስጥ እንደሚኖሩ ነው።

የሴት ልጅ ግርዛት በተባበሩት መንግስታት ጉጂ ልማዳዊ ድርጊት ተብለው ከተፈረጁ ድርጊቶች መካከል አንዱ ነው።  በኢትዮጵያም ሆነ በተለያዩ ሀገራት ድርጊቱ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የብልት ትልተላ እና የብልት መሰፋትን የመሳሰሉ ጎጂ ድርጊቶች የሚከናወኑበት ድርጊት ነው።  ድርጊቱ አንድ ጊዜ ከተከናወነ በኋላ በሴቷ ቀጣይ ህይወት ላይ ጊዜ የማይሽረው ጠባሳን ጥሎ ያልፋል።  የአለም ጤና ድርጅትም የድርጊቱ ሰለባ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ጉዳቶች ሲል ከፋፍሎ ያስቀምጣቸዋል።

የአጭር ጊዜ ጉዳቶች

የመጀመሪያው የሴት ልጅ ግርዛት ጉዳት ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ነው።  ድርጊቱ በሚፈፀምበት ወቅት ነርቮችና ስስ የአባላዘር አካላት ስለሚቆረጡ ህመሙ ከፍተኛ ስቃይ የሚያስከትል ነው።  ድርጅቱ እንደሚለው ድርጊቱ በሚፈፀምበት ወቅት ማደንዘዣ የመጠቀም ልምዱ አነስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ በአግባቡ የመስራት እድሉ አነስተኛ በመሆኑ በሴቷ ላይ ከመጠን ያለፈ ስቃይ ያስከትልባታል።  ከዚህ በተጨማሪም ቁስሉ ለመዳን ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑም ሴቷ ከድርጊቱ በኋላ ለረጅም ጊዜ በህመም ስሜት ውስጥ እንድትቆይ ያደርጋታል።

ሌላው የአጭር ጊዜ ጉዳት ከልክ ያለፈ ደም መፍሰስ እና እብጠት ነው።  ግርዛቱ በሚከናወንበት ወቅት የደም ስሮች ወይም የደም ቧንቧዎች የመቆረጥ አጋጣሚ ከተፈጠረ ሴቷ ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ያጋጥማታል።  በዚህም ሳቢያ ህይወቷ እስከማለፍም ሊደርስ ይችላል።  ከዚህ በተጨማሪም ኢንፌክሽን (የማመርቀዝ) እንዲሁም የሰውነት መመረዝ የሚከሰት ከሆነም የሰውነት ማበጥ ችግር ሊገጥማት ይችላል።  በተለይ ድርጊቱ የሚፈፀመው ንፅህናቸው ባልተጠበቀ መሳሪያዎች ከሆነ ለእነዚህ ችግሮች የመጋጥ እድሏ ከፍተኛ ነው።  ከዚህ ጋር በተያያዘም ንፅህና በሌላቸው መሣሪያዎች የተነሳ ለኤች አይ ቪ ኤድስ እና ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ያጋልጣታል።

ለግርዛት የተጋለጠች ሴት ሽንት ለመቋጠር እንዲሁም ሽንት ለማስወጣት በምትሞክርበት ጊዜም ከሌላዋ በተለየ ትቸገራለች።  በተለይ በግርዛቱ ጊዜ የሰውነት ማበጥ ፣ ከፍተኛ መቁሰል ወይም አላስፈላጊ የሆነ እና ስር የሰደደ ጠባሳ ከተፈጠረባት በዚህ ረገድ ከፍተኛ ችግር ይገጥማታል።  ይሄ ደግሞ ከጤንነት መታወክ በተጨማሪም በስነ-ልቦናም ጭምር እንድትታወክ ያደርጋታል።

የረጅም ጊዜ ጉዳቶች

እነዚህ ከግርዛት ጊዜ  በኋላ በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳቶች በሴቷ የህይወት ዘመን በየትኛውም ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ ናቸው።  ድርጊቱ ከተፈፀመ ከረጅም ጊዜ በኋላም ቢሆን በጤናዋ ላይ እክል ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው።  የመጀመሪያውም በማህጸን ላይ የሚከሰት ቁስለት ነው።  ግርዛት ለተለያዩ የሰውነት መመረዞች የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ በማህጸን በኩል ያልተፈለገ ፈሳሽ መውጣት፣ ማሳከክ እንዲሁም ቁስለት የመፍጠር ችግር በሴቷ ላይ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ይችላል።  በዚህም የተነሳ በዳሌ አጥንቷ ላይ እና በጀርባ አጥንቷ ላይ የህመም እና የስቃይ ስሜት እንዲሰማት ያደርጋል።

በግርዛት ሳቢያ የሚከሰቱ ቁስለቶች፣ የሰውነት መመረዝ እና መመርቀዞች በጊዜ በህክምና መዳን ካልቻሉ በሽንት ማስወገድ ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።  የመጀመሪያም ሽንት በምትሸናበት ወቅት የህመም ስሜት መሰማት ነው።  ይሄ ሊሆን የሚችለውም የሽንት ቧንቧዎች በግርዛት ወቅት ጉዳት ስለሚደርስባቸው ነው።  በተመሳሳይም በወር አበባ ወቅት ሴቷ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንድትገባ ያደርጋታል።  የወር አበባዋ ቀኑን ጠብቆ እንዳይመጣ፤ በሚመጣባት እና በሚፈስበት ወቅትም መጠኑ የተለያየ እንዲሆንና የህመም ስሜትም እንዲሰማት ያደርጋታል።  ከዚህ ውጭ ግን ችግሩ እየተስፋፋ በመሄድ በሽንት ስርዓት ውስጥ ያሉት አካላት በሙሉ እንዲጠቁ ያደርጋቸዋል።  በተለይ ኩላሊት ተገቢውን ተግባር እንዳያከናውን በማድረግ የሽንት ስርዓቱ የተዛባ እንዲሆን ብሎም ከዚህ ጋር በተያያዘ ህይወቷ እንዲያልፍ ያደርጋታል።  በአብዛኞቹ የተገረዙ ልጃገረዶችና ሴቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰተውም ይሄን አይነቱ ችግር ነው።

ሌላው የተገረዙ ሴቶች በማንኛውም ጊዜ ሊያጋጥማቸው የሚችለው ችግር በምጥ እና በወሊድ ወቅት የሚከሰት ችግር ነው።  ይኸውም ረጅም ጊዜን የፈጀ ምጥ፣ የመውለጃ ጊዜ ያልደረሰ ልጅ ለመውለድ መገደድ እንዲሁም በማህፀን ውስጥ እያሉ የሞተ ልጅ ለመውለድ መገደድ ናቸው።  ምጡ ለረጅም ጊዜ ከመቆየቱ እንዲሁም አጋጣሚውም ይጨምራል።  ይህ ችግር በሴቷ ግርዛት ወቅት የነበረው ስቃይ የከፋ ከሆነ ደግሞ የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይመጣል።  ከዚሁ ከወሊድና ምጥ ጋር በተያያዘም የተገረዘች ሴት ለፊስቱላ ችግር የመጋለጥ እድሏ ከፍተኛ ነው።  በተለይ ምጡ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ በአብዛኛው ለፊስቱላ ችግር ትጋለጣለች።  በዚህም ሳቢያ ሽንትና ሰገራዋን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ የሆነ ደረጃ ላይ ትደርሳለች።  ከዚህ በተጨማሪም የግንኙነት የስሜት ህዋሳት በግርዛት ተቆርጠው ስለሚጣሉ ለግብረ ስጋ ግንኙነት ስሜት ማጣት፣ በግንኙነት ወቅት ህመም መሰማት እንዲሁም ወሲባዊ ግንኙነት ለማድረግ የስነ ልቦና ዝግጅት አለመኖር የተገረዘች ሴትን በህይወት ዘመኗ በማንኛውም ጊዜ ሊገጥሟት የሚችሉ ችግሮች ናቸው።   

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2640 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 110 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us