ስለስፖንሰርና ማስታዊቂያ ሕጋችን ምን ይላል?

Wednesday, 26 March 2014 12:20

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-        በማስታዊቂያ አዋጁ የተከለከሉ ማስታወቂያዎች ምን ይመስላሉ

 1.             -       አንድን ማስታወቂያ ሕገ ወጥ ወይም አሳሳች የሚያስብሉት ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው?

-        ማስታወቂያዎቻችን የማስታወቂያ አዋጁን ድንጋጌ እያከበሩ ነው?

-        ስፖንሰር ማድረግ ከማስታወቅ በምን ይለያል?

-        ስፖንሰር ማድረግ የማይችሉ ተቋማትና ስፖንሰር የማያደርጉ ፕሮግራሞች የትኞቹ ናቸው?

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ባለፈው ሳምንት ስለማስታወቂያዎቻችን መጨዋወት ጀምረን ነበር። ለመሆኑ በየመገናኛ ብዙሃኑ የምናያቸው፣ የምንሰማቸውን የምናነባቸው በየአደባባዩ በግድም በውድም ቀልባችንን ለመሳብ የሚሻሙት ማስታወቂያዎች የሚመሩት በየትኛው ሕግ ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዱንን ነጥቦችም አንስተናል። በሕጉ ላይ የታወቁትን የማስታወቂያ አይነቶች ጠቅሶ ለማስታወቂያ ስራ ውስጥ ድርሻ ያላቸው የማስታወቂያ አስነጋሪ ወኪልና አሰራጭን ሚና ተመልክተናል። ከይዘትና ከአቀራረብ አንፃር የማስታወቂያ አዋጁ ከማንኛውም ማስታወቂያ ምን ምን ነገሮችን ይጠብቃል የሚለውንም በመጠኑ ነካክተነዋል።

እንደ አንዳንድ ማስታወቂያዎችንን እንዳይሆንብኝ እንጂ አላማችን የአምዳችን አንባቢዎች “ስንዴውን ከእንክርድዱ እንደሚባለው” ሕጋዊ ማስታወቂያዎችን ከሕገወጦቹ መለየት እንዲችሉ ብቻ ነው። ስለዚህ እንቀጥልበትና አንዳንድ የታዘብናቸውን ማስታወቂያዎች እያማን የቱ ጋር ሕጉን እንደጣሱ ለማየት እንሞክራለን። ታላቁ ይሁን ታናሹ ባናውቅም በመገናኛ ብዙሃኖቻችን መንትያው ሊያውም ተመሳሳዩ (Identical) የመሰለውን ስፖንሰርንዎ እናነሳዋለን።

1.የተከለከሉ ማስታወቂያዎች፡-

የማስታወቂያ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 759/04 ሕግን ወይም መልካም ስነምግባርን እንደሚፃረር ተደርገው የሚቆጠሩ ብሎ የከለከላቸው የማስታወቂያዎች ይዘቶች አሉ። በአዋጁ አንቀፅ 7 ላይ የተተቀሱትን እንመልከት

          ሰብዓዊ ክብርንና እኩልነት- የማስታወቂያ አዋጁ ከሕገ መንግስታችን እና በሌሎች ሕጎቻችን እውቅና የተሰጣቸው መብቶችና ነፃነቶች በማስተዋወቅ ስም እንዳይጣሱ የበኩሉን ጥበቃ አድርጓል። በአዋጁ አንቀፅ 7(1) ማንኛውም ማስታወቂያ የሰው ልጅን ስብእና፣ ነፃነት ወይም እኩልነትን የሚያከብርና እውቅና የሚሰጥ መሆን አለበት። እነኚህን የሰብዓዊ ክብር፣ የእኩልነትና የነፃነት መገለጫዎችን የሚፃረሩ ምስሎች፣ አነጋገሮችን ወይም ንፅፅሮችን የያዙ ማስታወቂያዎች ሕግን ወይም መልካም ምግባርን የሚፃረሩ ናቸው። በተለይም ደግሞ ቋንቋን፣ ፆታን፣ ዘርን፣ ብሔርን፣ ብሔረሰቦችን፣ ሙያን የሚሰነዝሩ ነቀፌታዎች ትችቶች አስተያየቶች ንፅፅሮች ሕገ ወጥ ናቸው። ሌሎች መልክቶችም ቢሆኑ ሰዎን የብሔረሰቦችን የቋንቋን የዘርን የሃይማኖት የእምነት፣ የፆታ፣ የሙያ እኩልትን ክብርንና ነፃነትን የሚያስተጋቡ መሆን አለባቸው ማለት ነው።

በተጨማሪ የግለሰብን፣ የብሔር ፣ ብሔረሰብን ወይም የህዝብ መልካም ሥነ ምግባር ወይም ሰብዓዊ ክብርን የድርጅቶችን መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፍ ማስታዊቂያም በሕገ ወጥነት ተፈርጇል።

የሀገራችንም ሆነ የክልሎቻችን ሰንደቅ አላማን፣ አርማን ፣ ብሔራዊ መዝሙርን ወይም ገንዘብን የሚያንቋሽሽ ወይም የሚዋርድ ማስታወቂያም ከሕገወጥ የማስታወቂያን አይነቶች አንዱ ሲሆን የሰራዊቱን ክብርን ገለልተኛነት ለመጠበቅ ሲባል ከአንቀፅ 7(1) ላይ የመከላከያም ሆነ የፖሊስ የደንብ ልብስን ፣ ምልክትን ወይም ሽልማትን በመልበስ ወይም በማድረግ የንግድ ማስታወቂያ ማስተዋወቅም ሕገ ወጥ ነው።

          የሕብረተሰብና የግለሰቦች ደህንነት የሚጋሩ- ሌላው በማስታወቂያ አዋጁ ጥበቃ የተደረገለት የህብረተሰቡ ደህንነት ሲሆን አመፅ፣ የሃይል ተግባር ሽብር ግጭት ወይም የፍርሃት ስሜት እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ማስታወቂያን ሕጉ አይፈቅድም። ይህ ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰቡን አካላዊና አእምሮአዊ ጤንነት ወይም ደህንነትን ለጉዳት የሚያጋጡ ድርጊቶችን እንዲፈፅሙ ማነሳሳትም አዋጁ አንቀጽ 7(6) ላይ ሕገ ወጥ ነው ተብሏል።

ከተፈቀደ ድምፅ በላይ በመጠቀም በየአደባባዩ የድምጽ ብክለት እየፈጠሩ መረበሽም በሕጉ ላይ በግልፅ ሕገ ወጥ ተብሎ ቢቀመጥም በእምነት ተቋማት አካለባቢና በገበያ ስፍራዎች ላይ የጆሮ ታምቡር በሚበጥሱ ድምፀ ማጉያዎች ማስጮኽ ግን በከተማችን እየተለመደ እንደ ህጋዊ ተግባር እየተቆጠረ መጥቷል።

ሌላው ደግሞ የትራፊክ ደህንነት የሚመለከት ሲሆን ማስታወቂያዎች ከፍጥነት በላይና አለጥንቃቄ ማሽከርከርንም ሆነ መንገድ አለአግባብ መጠቀምን የሚያበረታቱ መሆን የለባቸውም። የአካባቢ ጥበቃም በማስታወቂያ አዋጁ ላይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ስለሆነ ማስታወቂያዎች የትራፊክ ደህንነትም ሆነ የአካባቢ ጥበቃን የሚቃረኑ መሆን እንደ ሌለባቸው ተጠቅሷል።

እንደአሁኑ ግንዛቤው ሳይዳብር ኤች አይቪ ኤድስን የሚመለከቱ ማስታወቂያዎች ከማስጠንቀቅ ከማስተማር ይልቅ በማስደንገጥና በማስፈራራትላይ ያተኮሩ ስለነበሩ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖቻችን እንዲገለሉ ተስፋ እንዲቆርጡ ቫይረሱም እንዲስፋፋ አድርገው እንደነበር ይታወቃል። በመሆኑም ማስታወቂያዎች በተለይም በኤች አይቪ ቫይረስ በደም ውስጥ ያለበትን ሰው በሌሎች ህመሞች የተያዘን ሰው እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ክብርና ስነ ልቦና የሚነኩ ሲሆኑ ሕገ ወጥ ናቸውና ኃላፊነትን ያስከትላል።

በልማት አዘልና ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ የፅሁፍ፣ የምስል፣ የስእል፣ የፊልም ወይም መሰል አቀራረብን የያዙ ማስታወቂያዎችም ሕገወጥ ሲሆኑ በአንዳንድ ሆቴሎችና የምሽት ቤቶች ግን የሚታየው ከዚህ በተቃራኒው ነው። ግለሰብን በሚመለከት የምንመለከታቸው ማስታወቂያዎች ይህን ማሟላታቸውን ባላውቅም ሕጉ የግለሰብን ስም፣ ምስል ወይም ፎቶ ግራፍ ካለግለሰቡ ፈቃድ መጠቀምን አይፈቅድም። በተጨማሪ በሕግ ጥበቃ የተደረገላቸው የኪነጥበብ ወይም የፈጠራ ሥራ የሚመለከተው ሰው ሳይፈቅድ መጠቀምም ሕገወጥ መሆኑ በሕጉ ተገልጿል። ማስታወቂያዎችን የሚታጀቡባቸው ሙዚቃዎች ተገቢው ፈቃድ ተጠይቆባቸው ይሆን?

በአጠቃላይ ማስታወቂያ እንደሚተዋወቀው ነገር በተለያየ ሕጎች የተቀመጠ መብቶችን ግዴታዎችን ሊመለከት የሚችል በመሆኑ ይዘቱና አቀራረቡ በሌሎች ሕጎች የተከለከለ ወይም ማንኛውንም ሕግ እንዲጣስ የሚያነሳሳ መሆን እንደሌለበት በአዋጁ አንቀጽ 7(12) ላይ ተደንግጓል።

          አሳሳች ማስታወቂያዎች፡- በማስታወቂያ ላይ መዋሸት ክልክል ነው። የሚተዋወቀው ምርት የተመረተበትን ሀገር፣ ቀን፣ የምርቱን ባህሪ ንጥረ ነገሩን፣ ክብደቱን፣ መጠኑን እና ተቀባይነቱን በተመለከተ የሀሰት መረጃ መስጠት ማስታወቂያውን በይዘቱ ወይም በአቀራረቡ አሳሳች ወይም ተገቢ ያልሆነ ማስታወቂያ ያደርገዋል።

አሁንም በተጨባጭ የምናያቸው ማስታወቂያዎችን ላይ ተግባራዊ ሲሆን ባይታይም አዋጁ በአንቀጽ 8(3) አንድ ምርት ወይም አገልግሎት የሌለውን ጥቅም ጥራት፣ መአዛ፣ ጣዕም፣ ንጥረነገር፣ ጥንካሬ፣ እድሜ ወይም ብርካቴ እንዳለው አስመስሎ ማቅረብ በማስታወቂያ ሕጉ ላይ ግን በግልፅ ክልከላ ተደርጎበታል።

የሚተዋወቁት ምርቶች፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ሊያበቃ የተቃረቡ ወይም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ መሆን የለባቸውም።

በተለይም የህፃናትን ጤናማ እድገትና ደህንነት ለመጠበቅ የዱቄት ወተትን ወይም መሰል ምግብን ከስድስት ወር በታች ለሆኑ ህፃናት ከእናት ጡት በላይ የሚመረጥ ወይም የማይተናነስ እንደሆነ አድርጎ ማስተዋወቅም አሳሳችና ያልተገባ ማስታወቂያ ነው።

የሌላውን ምርት በማነፃፀር ማንቋሸሽ ወይም ከዚህ አገር መጣ የእከሌ ሀገር ጠበብት የተጠበቡበት እያሉ የውጭ ሀገር ምርት ተመራጭ እንዲሆን ለማድረግ የሀገር ውስጥ ምርትን ማንቋሸሽም ያልተገባ የማስታወቂያ አቀራረብ ሲሆን የሌላ ሰውን ምርት ወይም አገልግሎት እንደራስ አድርጎ የሚያስተዋውቅ ማስታወቂያም ተከልክሏል። አንዳዴ አስተዋዋቂዎች የእከሌን ምርት ካልተጠቀሙማ እያሉ ያለ እነሱ አስተዋዋቂ ምርት ሌላ ኑሮ ወይም ሕይወት የሌለ ቢኖርም ያልተሟላ ያስመስሉብናል። ሆኖም ይህ የንግድ ውድድር መርህን መተላለፍ በመሆኑ በአዋጁ ላይ የተከለከለ የማስታወቂያ አቀራረብ ነው።

የአንዱን ምርት ከሌላው ጋር የሚያሳስት አሻሚ ማስታወቂያ፤ በገበያ ውስጥ የሌለውን እንዳለ አሰስመስሎ ማቅረብም በትክክለኛ ዋጋ እየሸጡ በነጻ ወይም በቅናሽ እንዲሸጡ አድርጎ ማስተዋወቅ ተከልክሏል።

የእገሌ ድርጅት ተሸላሚ እገሌ ከሚባል አለም አቀፍ ድርጅት የጥራት ተሸላሚ እያሉ እራስን አንደኛ አይደለም ከሀገር ከአለም በአንደኝነት እንደተመረጡ አድርጉ ማስተዋወቅም ትዝብትን ማትረፉ ብቻ ሳይሆን ሕጉ አይፈቅደውምና ኃላፊነት ሊያስከትል ይችላል።

የቋንቋ አጠቃቀምን በሚመለከት ሕጉ በሀገራችን ማስታወቂያው በተሰራጨበት ቋንቋ ፍቺ የሌለው ካልሆነ በስተቀር የሀገራችንን ቋንቋ ደባልቆ በጉራማይሌ ቀላቅሎ ማቅረብንም በአንቀጽ 8(9) ላይ ያልተገባ የማስታወቂያ አቀራረብ አድርጌ እቆጥረዋለሁ ብሏል። የሚሰማና የሚጠይቅ ጠፋ እንደጂ ሕጉ ይህንን ድንጋጌ አስቀምጧል።

በአራት መቶ ብር አራት መቶ ጥቅም የሚል አንድ ማስታወቂያ ትዝ ይለኛል ግነትም ሲበዛ ውሸት መሆን አይቀርም። በተጨማሪ ሕጉ አክስዮኖች ያስገኛሉ የሚባውን እርግጠኛ ያልሆነ የትርፍ ድርሻ በዚህ መልኩ ማቅረብን ከልክሏል የሌላ ሽልማት ወይም ዋስትና እንደሚሰጥ አድርጎ ማቅረብ ያልሆነውን ቆርጦ የሚቀጥል የሀሰት ምስክርነትን ማቅረብ በማስረጃ ሊረጋገጥ የማይችልን የመጀመሪያው፣ ብቸኛው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ከዚህ ቀደም ያነበረ፣ ወደር የሌለው እና መሰል ማወዳደሪያዎችን የያዙ ማስታወቂያዎችን ሕጉ ቢከለክልም ማስታወቂያዎችን ግን በነዚህ ቃላቶች እያሰለቹን ይገኛሉ።

ከአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናትን የሚመለከቱ ማስታወቂያዎችም በአንቀጽ 10 ላይ አስተሳሰባቸውን ሊጎዳ በሀገርና በቤተሰብ ላይ ያላቸውንና ፍቅርና እምነት የሚያሳጣ፣ ህፃናቱ በማስታወቂያ ያዩትን ነገር ካልወለዳችሁ እንዲሉ የሚተዋወቀውን ነገር ካላገኙ የበታችነት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ወይም ህፃናት ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚያሳይ ወይም መሰል ማስታወቂያዎችን ማሰራጨትም ተከልክሏል።

2.ስፖንሰር፡-

ስፖንሰር ማለት በአዋጁ አንቀጽ 2(14) መሰረት ፕሮራምን ወይም ማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድን ስፖንሰር ማድረግ ወይም የሚከፈለውን ክፍያ መክፈል ማለት ሲሆን ሆኖም ግን ስፖንሰር ስላደረገ የፕሮግራሙ ይዘትና የጊዜ ሰሌዳ በስፖንሰሩ ተፅእኖ ስር መውደቅ እንደሌለበት በተለይም በፕሮግራሙ ይዘት ውስጥ የስፖንሰሩ መርት ወይም አገልግሎት እንዲሸጥ ወይም እንዲከራይ መቀስቀስ የለበትም በማት የማስታወቂያ አዋጁ አንቀጽ 15(1) ደንግጓል። ስፖንሰር አድራጊን ማመስገን አላማውንና መሰል ምልክቶችን ለማስተላፍ የሚወስደው ጊዜ ከፕሮግራሙ የአየር ጊዜ 10 ከመቶ በላይ መሆን የለበትም። በተጨማሪ ማስታወቂያ እንዳይነገርባቸው የተከለከሉ ወይም የተገደቡ ምርቶችን የሚያመርት ድርጅትም ፕሮግራሞችንም ሆነ ማስታወቂያዎችን ስፖንሰር ማድረግ አይችልም።

የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ከተከለከሏቸው ነገሮች አንዱ ስፖንሰር መሆንን ነው። ማስታወቂያንም ሆነ ፕሮግራምን ስፖንሰር ማድረግ እንደማይችሉ የአዋጁ አንቀጽ 15(5) ደንግጓል።

ስፖንሰር የማይደረጉ ፕሮራሞችም አሉ። በአዋጁ አንቀጽ 16 መሰረት፡-

 • የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይይቶች
 • የዜና እና ወቅታዊ ጉዳይ ዘገባ የስፖርት፣ የአየር ትንበያና የቢዝነስ ዘገባዎች ከሌሎች ዜናዎች ተለይተው ከቀረቡ ሕጉ እስፖንሰር እንዲደረጉ ይፈቅዳል።
 • የህፃናት ፕሮግራም ደግሞ ስፖንሰር እንዳይደረግ የተከለከለው በንግድ ከሆነ የተወሰኑ ድርጅቶች ብቻ ነው።

የማስታወቂያ አዋጁ እንደየማሰራጫ መንገዶቹ በዝርዝር ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎችንም ለማንሳት የራሳቸውን ጊዜ ይሻሉና ሌላ ቀን ልመለስባቸው ለዛሬ እዚህች ጋር እናሳርግ ቻው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
7613 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 934 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us