የጠፋችው ሚስት

Wednesday, 02 April 2014 12:31

ኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ጠፍታ የተመለሰችው ሚስትና በባሏ የመጣ እዳን የሚመለከተው ክርክር በምን ተቋጨ?

-    የመጥፋት ውሳኔ እንዴት እና መቼ ይሰጣል

-    የመጥፋት ውሳኔ የሚያስከትላቸው ውጤቶች?

-    የጠፋው ሰው ከመጣስ ምን ይደረጋል?

ታሪኩ እንዲህ ነው ፡-

1. ሚስት ጠፋች

ወ/ሮ ውቢትና አቶ ዝቋላ በሐዋሳ ከተማ ተጋብተው አብረው በመኖር ላይ ሳሉ በ1999 ዓ.ም በመካከላቸው ንፋስ ገባና ተጣሉ። ወ/ሮ ውቢትም ከቤቷ ጠፍታ ወደ ዱባይ ሀገር መኰብለሏ ተሰማ። ለሁለት ዓመታት ያህል የወ/ሮ ውቢት ወሬ አልተሰማም። ይሄኔ በ2001 ዓ.ም አቶ ዝቋላ ለፍ/ቤት አመለከቱና ጉዳዩን የማየት ስልጣን ባለው የሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የመጥፋት ውሳኔ ተሰጠባቸው። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 84(ሀ) መሠረት የአንደኛው ተጋቢ መጥፋት ጋብቻውን ስለሚያፈርሰው የወ/ሮ ውቢትና የአቶ ዝቋላ ጋብቻ ፈረሰ።

2. ባል ወንጀል ሰራ

አቶ ዝቋላ ጋብቻውን በመጥፋት ውሳኔ ከፈረሰ በኋላ ከ2001 መጨረሻ እስከ 2002 ዓ.ም ባለው ጊዜ ከግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በሕገወጥ መንገድ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ ከሐዋሳ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ሂሳብ ላይ ሦስት ሚሊዮን አምስት ሺህ ብር ከዜሮ ሦስት ሳንቲም ከግብረአበሮቹ ጋር በመውሰድ በወንጀለ ተከሶ ተቀጣ። አቶ ዝቋላ ከወንጀል ቅጣቱ በተጨማሪ ከግብረአበሮቹ ጋር ያጐደለውን ገንዘብ እንዲከፍል በየካቲት 11 ቀን 2003 ዓ.ም ውሳኔ ተሰጠበት።

3. የጠፋችው ሚስት ተመለሰች

ጠፍታለች ተብሎ በፍ/ቤት የተወሰነባት ወ/ሮ ውቢት ድንገት ከተሰወረችበት ብቅ አለችና የመጥፋቷን ውሳኔ ወደሰጠው ፍ/ቤት ቀርባ “ኧረ አለሁ አልጠፋሁም!” ስትል አመለከተች። ይሄኔ ፍ/ቤቱ ሕጉ በሚያዘው መሠረት ወ/ሮ ውቢት ጠፍታለች በማለት የሰጠሁትን ውሳኔ አለመጥፋቷን በአካል ቀርባ ስላረጋገጠችልኝ ሽሬዋለሁ ሲል ውሳኔ ሰጠ።

4. ጠፍታ የተመለሰችው ሚስት ንብረት ይሸጥ ተባለ

አቶ ዝቋላ በወንጀል የተቀጣበትን ሦስት ሚሊዮን አምስት ሺህ ብር ከዜሮ ሦስት ሳንቲም (ምናለ ሳንቲሟ እንኳን ብትቀርበት) እንዲተካ በፍትሐብሔር ክስ ተመሰርቶበት ተወስኖበት አልነበር። የአፈፃፀም መዝገብ ተከፈተና ገንዘቡ የተወሰደበት የሐዋሳ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ገንዘቡን ለማስመለስ ንብረት ሲያፈላልግ ወ/ሮ ውቢትና አቶ ዝቋላ በትዳር ላይ እያሉ ያፈሯቸውን በአቶ ዝቋላ ስም የተመዘገበ አንድ ቤት በወ/ሮ ውቢት ስም የተመዘገበ ቤት ተሸጠው አቶ ዝቋላ ለበላው ገንዘብ መተኪያ ይዋልልኝ ሲል አመለከተና ፍ/ቤቱም ንብረቶቹ ተሸጠው ለእዳው መክፈያ ይዋሉ ሲል ትዕዛዝ ሰጠ።

ጠፍታ የተመለሰችው ሚስትም እንዴት ጠፍታለች ተብሎ ትዳራችን ከፈረሰ በኋላ ለመጣ እዳ የኔም ንብረት ይሸጣል እኔ ምን አገባኝ አለች። እዳውን ያመጣው አቶ ዝቋላ በሰራው ወንጀል በመሆኑ በስሜ የተመዘገበው ቤት እና በጋብቻ ካፈራነው የጋራ ንብረት የሚደርሰኝ ግማሽ ድርሻ ሊነካብኝ አይገባም ብላ ፍ/ቤቱ የሰጠውን የአፈፃፀም ትዕዛዝ ተቃወመች።

የፍርድ ባለመብት የሆነው የሐዋሳ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤትም በክልሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 72 እና 79 በመጥቀስ ንብረቱ በአንደኛው ተጋቢ ስም ቢመዘገብም የጋራ እንደሆነ ይቆጠራል ወ/ሮ ውቢት በስሟ የተመዘገበው ቤት የግሏ ስለመሆኑ ያቀረበችው ማስረጃ እንደሌለና በባልየው በአቶ ዝቋላ ምክንያት የመጣው እዳ ከጋብቻው የጋራ ሀብት ሊከፈል እንደሚገባና እዳው የጋራ ሀብታቸው መሸፈን ካልተቻለ ከባል ወይም ከሚስት የግል ሀብት ጭምር እንዲከፈል ተደንግጓል በማለት የወ/ሮ ውቢት በስሟ የተመዘገበው ቤት የግሏ ስለመሆኑ ያቀረበችው ማስረጃ እንደሌለና በባልየው በአቶ ዝቋላ ምክንያት የመጣው እዳ ከጋብቻው የጋራ ሀብት ሊከፈል እንደሚገባና እዳው በጋራ ሀብታቸው መሸፈን ካልተቻለ ከባል ወይም ከሚስት የግል ሀብት ጭምር እንዲከፈል ተደንግጓል በማለት የወ/ሮ ውቢት መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግ ጠየቀ።

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይህን ክርክራቸውን መርምሮ ቤቶቹ የጋራቸው ቢሆኑም እንኳን አቶ ዝቋላ የገቡበት እዳ ለጋራ ጥቅም የዋለ መሆኑን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ስላላስረዳ ከሁለቱም ቤቶች ላይ የወ/ሮ ውቢት ከፊል ድርሻ ለእዳው መክፈያ ሊውል አይገባም ሲል ብይን ሰጠ።

የከተማዋ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት በዚህ ውሳኔ ቅር ተሰኝቶ ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቀረበ። ጠ/ፍ/ቤቱም በክልሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 79(2) መሠረት ከተጋቢዎቹ ከአንዱ በግል የሚጠየቀው እዳ ከግል ሀብቱ መከፈለ እንዳለበት፤ ሆኖም በቂ ካልሆነ ግን የጋራ ሀብታቸው ተሸጦ የሚስትየዋም ድርሻ ለእዳው መክፈያ መዋል አለበት ሲል ውሳኔ ሰጠ።

ጠቅላይ ፍ/ቤቱ የከፍተኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ አሻሻለው እንጂ አልሻረውም። ከፍተኛው ፍ/ቤት የለም የሚስትየው ድርሻ ሊነካባት አየገባም ሲል። ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ደግሞ በባልየው ድርሻ እዳው ካልተሸፈነ የሚስትየውም ድርሻ መጨመር አለበት ነው ያለው። ወ/ሮ ውቢት የሕግ ስህተት ተፈፅማል ስትል ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብትጠይቅም፤ ሰበር ሰሚ ችሎቱም በኔ በኩል ተፈፀመ የምለው የሕግ ስህተት የለም ሲል ውሳኔውን አፀናው።

ወ/ሮ ውቢት የመጨረሻው የዳኝነት አካል ለሆነው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ህዳር 25 ቀን 2004 ዓ.ም በመ.ቁ 74791 የሰበር አቤቱታ አቀረበች። አቤቱታዋ ባሌ ወንጀሉን ፈፅሞ ወደዚህ እዳ የገባው ጋብቻችን በመጥፋት ውሳኔ ከፈረሰ በኋላ ነው። ከዚያም በኋላ በድጋሚ አልተጋባንም። ስለዚህ እዳው የእኔን ድርሻ ይመለከታል በማለት የክልሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት ተፈፅሞበታል ይሻርልኝ የሚል ነው።

ባላጋራዋም ወ/ሮ ውቢት የተሰጠበትን የመጥፋት ውሳኔ ቀርባ አሽራዋለች። ውሳኔው የተሻረው ከነውጤቱ በመሆኑ ፍቺ እንዳልተፈፀመና እዳውም የመጣው በጋብቻ ጊዜ እንደሆነ የሚቆጠር በመሆኑ ገብቻቸው መፍረሱንም ስላላስረዳች ጋብቻው ፀንቶ ባለበት ጊዜ በአንደኛው ተጋቢ የመጣ እዳ ከጋራ ንብረት መከፈል አለበት በሚል የተወሰነ ውሳኔ የሕግ ስህተት አልተፈፀመበትም በማለት ተከራከረ።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ክርክራቸውን መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል። እስቲ ውሳኔውን ገምቱ? ከሰበር ውሳኔ በፊት የፍ/ብሔር ሕጋችን ስለ መጥፋት ምን እንደሚል እናንሳ።

የመጥፋት ውሳኔ እንዴት ይሰጣል

ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ሊጠፉ ይችላሉ። በሚጠፋበት ጊዜ ታድያ ከእነሱ መኖር ጋር የተሳሰሩ መብቶችና ግዴታዎች ሁሉ አብረዋቸው አይጠፉም። በመሆኑም ሌሎች ከጠፋው ሰው ጋራ የወል ወይም የሕግ ትስስር ያላቸው ሰዎች በጠፋው ሰው ምክንያት የሚያገኙት መብት ወይም የሚላቀቁት ግዴታ ይኖራል። በመሆኑም እነኚህን መብቶችም ለመጠቀም ወይም ግዴታዎቹን ቀሪ ለማድረግ የፍ/ብሔር ሕጋችን ከቁ. 154-173 ያሉትን 19 አንቀጾች መጥፋትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን አስፍሯል።

ሰው ጠፋ የሚባለው መቼ ነው?

እኛ ለግማሽ ቀንም የት እንደሄደ ያላወቅነውን ሰው ጠፋ ልንል እንችላለን። በየግድግዳው ከፎቶ ጋር ተለጥፈው የምናያቸው የቤተሰብን ወይም የፈላጊን ጭንቀት የሚገልፅ አፋልጉኝ ማስታወቂያዎች በአንድ ቀን በሁለት ቀን ጠፋ የሚሉትን ሰው ያያችሁ የሚሉ ናቸው። አንድን ሰው በፍ/ቤት ጠፍቷል ለማለት ግን ከጠፋ ሁለት ዓመት የሞላው መሆን አለበት። የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥ ማንኛውም ባለጉዳይ ማለትም ከጠፋው ግለሰብ ጋር የሚያስተሳስር የወል ወይም የሕግ ግንኙነት ያለው መሆን አለበት ማመልከት እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 154(1) ይደነግጋል። ሕጉ ባለጉዳይ የሚላቸው ከመጥፋት ውጤቱ ከሚገኝ መብት ወይም ከሚቀር ግዴታ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎችን ነው። በመሆኑም ናፈቀኝ ብሎ ማፈላለግ እንጂ የመጥፋት ውሳኔ ማሰጠት አይቻልም።

የመጥፋት ውሳኔ የሚሰጠው የጠፋው ሰው ዋና መኖሪያ ያለው ፍ/ቤት ሲሆን፤ የከተማ ነክ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቶች ካሉአቸው ስልጣኖች አንዱ የመጥፋት ውሳኔ መስጠት ነው።

ማፈላለግ

ፍ/ቤቶች የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጡ ጥያቄ ሲቀርብላቸው የጠፋበት ቀን ሁለት ዓመት ያለፈው መሆኑን ብቻ ማረጋገጥ አይበቃቸውም። እራሱ የጠፋው ግለሰብ ወይም ሰውየውን አይቻለሁ። ስለ ሰውየው ሰምቻለሁ የሚል ሰው ካለ እንዲቀርብና እንዲያሳውቅ ማስታወቂያ እንደሚያወጡ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 155 ይደነግጋል። የማስታወቂያውን አወጣጥ ሁኔታን የሚወስኑት ዳኞቹ ሲሆኑ፤ ጠፋ የተባለው ሰው በሚኖርበት ቦታ እና ማስታቂያው ይጠቅማል ብለው በገመቱት ቦታ እንዲተዋወቅ ያደርጋሉ። በአሁኑ ጊዜ ፍ/ቤቶች ማስታወቂያውን የሚያስወጡት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ነው። በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግን ጠቃሚ በሚመስላቸው በማንኛውም ቦታ እና በተለይም በጠፋው ሰው መኖሪያ ቦታ ምርመራ እንዲያደርግ ማዘዝ እንደሚችሉም ስልጣኑ ተሰጥቷቸዋል።

በዚህ መለኩ ጠፋ የተባለው ሰው ወይም መኖሪያውን አውቃለሁ የሚል ሰው ካልቀረበ የመጥፋት ውሳኔ ይሰጣሉ። ለውሳኔው መሰረት የሚያደርጉትም፤

-    ጠፋ የተባለው ሰው መሞቱ የሚመስል የታያቸው እንደሆነ ነው። በነገራችን ላይ መጥፋት የመመለስ እድል ሊኖርበት ቢችልም ውጤቱ ከሞት ጋር ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው በተወሰነ ስፍራ አለመኖሩ ብቻ ጠፋ ሊያስብለው አይችልም። በመሆኑም ሁኔታዎቹ ጠፋ የተባለው ሰው ሞቶ መሆን አለበት የሚያስብሉ ሆነው ሲገኙ ነው። ለፍ/ቤቱ የመጥፋት ውሳኔ መሰረት የሚሆነው። በተለይም ደግሞ ግለሰቡ ነብረቱን የሚያስተዳድር ወኪል ማድረግ አለማድረጉና አለሁ ለማለት ሊከለክሉት የቻሉትን ምክንያቶች መመርመር እንዳለባቸው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 157 ይደነግጋል።

ሆኖም ፍ/ቤቱ ጠፋ የተባለው ሰው መሞቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከቀረበላቸው መሞቱን የሚያስታወቅ ውሳኔ እንደሚሰጡ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 161 ይፈቅዳል። ለምሳሌ በጠፋው የማሌዥያ አውሮፕላን ውስጥ አንድ ያገር ልጅ ነበር ብለን ብንልና ወሬውም ምኑም ሳይሰማ ሁለት ዓመታት ቢያልፍ ዳኞች ጥያቄ ከቀረበላቸው ግለሰቡ ሞቷል ብለው ውሳኔ ሊሰጡ ይችላሉ።

ሕጉ ድንገት ጠፋ የተባለው ሰው ብቅ ቢልስ ብሎ ለጥንቃቄ ይረዳ ዘንድ ፍ/ቤቶች የመጥፋት ውሳኔውን እስከ አንድ ዓመት ለማቆየት ወይም ውሳኔውን ቢሰጡም ውጤቱን እስከ አንድ ዓመት ተፈፃሚ አንዳይሆን ማገድ እንደሚችሉ በቁ. 158 ላይ ደንግጓል።

የመጥፋት ውሳኔ ምን ያስከትላል

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 168 መሠረት ጋብቻ የመጨረሻው የመጥፋት ውሳኔ በተሰጠበት ቀን የጠፋው ሰው ጋብቻ ይፈርሳል። የጠፋው ተጋቢ ባል ወይም ሚስት ሌላ ማግባት ይችላሉ። ጠፋ የተባለው ሰው ራሱ ካልሆነ ሌላ የሚቃወማቸው የለም። ሆኖም ዐቃቤ ሕግ በማያከራክር አካኋን ሰውዬውን አለመጥፋቱን ካረጋገጠ። በጋብቻ ላይ ጋብቻ ነው ብሎ የጠፋ ከተባለው ሰው የትዳር አጋር ጋር የሚፈፀመውን ብቻ ሊቃወመው ይችላል።

መጥፋቱ የተወሰነበት ሰው የመጨረሻ ወሬዎቹ ከደረሱ በኋላ የሚደርሰው የውርስ ድርሻ ያለበት ውርስ ከተጀመረ የእርሱ ድርሻ ከግምት ሳይገባ ይቀጥላል። ሆኖም ፍ/ቤቶች የውርሱን ንብረት የሚደርሳቸው ሰዎች ዋስ ወይም ማረጋገጫ እንዲሰጡ ማስገደድ ይችላሉ። በተጨማሪም በጠፋው ሰው መሞት መብት የሚያገኙ ሰዎችም በተመሳሳይ መብታቸውን መጠቀም የሚችሉ ሲሆን፤ ዳኞችም ዋስ ሊያስጠሯቸው ይችላሉ።

ግዴታን በተመለከተ ደግሞ የቀለብ፣ የጡረታ እና የሕይወት የመድን ዋስትና እና ሌሎች ከሰውየው መኖር ጋር የሚያያያዙ ግዴታዎች ቀሪ ይሆናሉ። ኑዛዜም ካለ ኑዛዜው እንዲከፈት ይደረጋል።

የመጥፋት ውሳኔን የሚያስቀሩ ሁኔታዎች

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 170 መሠረት

-    ጠፋ የተባለው ሰው ሲመጣ

-    ጠፋ ተብሎ ከተወሰነ በኋላ በህይወት መኖሩ ሲረጋገጥ

-    የመጨረሻ ስለሱ የተሰማበት ጊዜ ተብሎ ከተወሰነው ቀን በሌላ ጊዜ መሞቱ ሲረጋገጥ ውሳኔው ቀሪ ይሆናል።

የጠፋው ሰው ከተመለሰ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 171 መውረስ ንብረቶቹን በሚገኙበት አኳሃን የተሸጡም ካሉ የተሸጡበትን ዋጋ እና ዋና ገንዘቡን በሥራ ላይ በማዋል የተገኙ ንብረቶችን መልሶ ሲወስድ ገቢዎችን ግን ይዞታውን ይዘው ለነበሩ ሰዎች ይቀራሉ። በተንኰል ወይም ንብረቱን በመጥፎ ሁኔታ የጐዳ ሰው ካለ ግን ተጠያቂ ነው።

ሰበር ምን አለ?

እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰው ጠፍታ የተመለሰችው የወ/ሮ ውቢት እና ባሏ ገንዘቡን የጐደለበት የሐዋሳ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ክርክር ላይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጥር 17 ቀን 2005 ይህን ውሳኔ ሰጠ።

አቶ ዝቋላ ባለዕዳ የሆነበትን ገንዘብ የማጉደል ወንጀል የፈፀመው ወ/ሮ ውቢት ላይ የመጥፋት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ነው። ወ/ሮ ውቢት ከዚያ በኋላ ተመልሳ በመምጣቷ የተሰጠባት የመጥፋት ውሳኔ መሻሩ ንብረቷን መልሶ የማግኘት መብቷን ቢያጐናፅፋትም ጠፋ የተባለው ሰው በመመለሱ በመጥፋቱ ፈርሶ የነበረውን ጋብቻ በድጋሚ የሚቀጥለው መሆኑን የፍ/ብ/ሕጉ አይደነግግም። የጋበቻው መፍረስ ዘላቂ ውጤት ያለው እንጂ የጠፋው ሰው ሲመጣ የሚሰረዝ አይደለም።

     ወ/ሮ ውቢትና አቶ ዝቋላ ወ/ሮ ውቢት ከተመለሰች በኋላ በድጋሚ ለመጋባታቸው ወይም በቀድሞው የትዳር ሁኔታ አብረው ለመኖራቸው የቀረበ ማስረጃ የለም። በመሆኑም ጋብቻዋ በመጥፋት ውሳኔ ከፈረሰ በኋላ ባል በግሉ ለሰራው ወንጀል ላመጣው እዳ መክፈያ መሆን ያለበት የባል የአቶ ዝቋላ ድርሻ ብቻ ነው እንጂ የሚስት የወ/ሮ ውቢት ድርሻ ለእዳ መክፈያ ሊሆን የሚችልበት የሕግ አግባብ የለም በሚል የከፍተኛ ፍ/ቤቱን ውሳኔ በውጤት ደረጃ በማፅናት የጠ/ፍ//በቱን እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቱን ውሳኔ ሽሯል። ጠፍታ የተመለሰችው ሚስት ወ/ሮ ውቢትም ጠፋች ተብሎ ከተወሰነ በኋላ ባሏ በሰራው ወንጀል ላመጣው እዳ ለእሷ የሚደርሳት ግማሽ የጋብቻ ንብረት ድርሻ ለእዳ መክፈያ ከመሆን እንዲድን ተወስኖላታል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
9952 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 941 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us