የቅጂ መብት ክርክር ያስነሳው የሰማዕታት ሐውልት

Wednesday, 09 April 2014 12:04

በኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ምንነት

-    የፈጠራ ስራ አመንጪው ያሉት ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ መብቶች

-    እስከ ሰበር ድረስ ያከራከረው የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሐውልት ቀራፂና የአሰሪው ማኅበር ክርክር ምን ነበር

-    ክርክሩስ በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ በዋነኛነት የምናወጋው ስለቅጂና ተዛማጅ መብቶች (copyright and neighboring rights) ነው። ለማሳያነት ደግሞ የምናነሳው የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ የተሰራውን ሐውልት ወይም ቅርፅ አስመልክቶ የተነሳ የቅጂ መብት ጥሰት ላይ በፍ/ቤት የተደረገ ክርክርና ለክርክሩ እልባት የሰጠውን የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ነው። ይመቻችሁ።

ታሪኩ እንዲህ ነው….

1. የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሐውልት ለማሰራት ውድድር ተደረገ?

በ1990 ዓ.ም በወቅቱ የአዲስ አበባ የደርግ አፈናና ጭፍጨፋ ተፈራጆች ሰብአዊ መብት ማኅበር ተብሎ ይጠራ የነበረው ማኅበር አንድ የውድድር ማስታወቂያ ያወጣል። ማስታወቂያው በቀይ ሽብር ለሞቱ ሰዎች መታሰቢያ ሐውልት ለማሰራት ነበረ። ማስታወቂያው ላይ ማኅበሩ በውድድሩ ከ1 እስከ 3 ለሚወጡ ሰዎች የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥና ከሽልማቱ በኋላ የሐውልቱ ባለቤት እንደሚሆን ያሳውቃል። ስራቸውን ለውድድሩ ካቀረቡት አርቲስቶች መካከል አንዱ አቶ ኤልያስ አሰጋኸኝ ይባላሉ። በውድድሩ ማሸነፍ አለማሸነፋቸው ሳይታወቅ አምስት ዓመታት ካለፈ በኋላ በ1995 ዓ.ም የቀይ ሽብር ሰማዕታት ወዳጆችና ቤተሰቦች ማኅበር ይቋቋምና የቀድሞውን ማኅበር ስራዎችና ለውድድር የቀረቡትን ሐውልቶች ጭምር ተረክቦ ስራውን ይቀጥላል። አቶ ኤልያስ እንዴት ነው ወይ አሸንፈሀል ወይ አላሸነፍክም በሉኝና ቁርጤን ልወቀው እያሉ ተመላልሰው ቢጠይቁም፤ ማኅበሩ መልስ ሳይሰጣቸው ተጨማሪ አምስት ዓመታት አለፈ።

2. የአቶ ኤልያስ ቅርፅ ተመርጦ በፖስታ ቴምብር ላይ ወጣ

አቶ ኤልያስ ቁርጡ አልታወቅ ያለውንና ስራቸውን አስረክበው ከተወዳደሩ አስር ዓመት ያስቆጠረው የሐውልት ውድድር ጉዳይ ሲከነክናቸው ቆይቷል። ነሐሴ 20 ቀን 2000 ዓ.ም በአንድ አጋጣሚ አቶ ኤልያስ ለቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት የተወዳደሩበትን ሐውልት ምስል በፖስታ፣ በቴምብር ላይ ታትሞ ወጥቶ ያዩታል። እሳቸው ሳያውቁ ለፈጠራ ስራቸው ተገቢውን ክፍያና ጥቅም ሳያገኙ ስራቸው በጐን በቴምብር ላይ የመውጣቱ ሚስጥር ያልገባቸው አቶ ኤልያስ ጉዳዩን ለማጣራት እላይ ታች ይላሉ።

ባደረጉት ማጣራትም፤ ቴምብሮቹን ያሳተመው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሲሆን፤ ቁጥራቸው 60,000 የፖስታ ቴምብሮችን አሳትሞ አንዱን በብር 3 በመሸጥ 180,000 ብር ማግኘቱን ይደርሱባታል።

እንዴት እኔ ሳላውቅና ሳልፈቅድ ስራዬን በቴምብር አሳትመህ ትሸጣለህ ብለው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትን አቶ ኤልያስ ጠየቁ። ድርጅቱም ቴምብሮቹን ያተምኩት የቀይ ሽብር ሰማዕታት ወዳጆችና ቤተሰቦች ማኅበር ግንቦት 19 ቀን 2000 ዓ.ም ለሚከበረው የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ እንዲሆኑ በቴምብር ይታተሙ ብሎ የአቶ ኤልያስን ሥራ ጨምሮ ሦስት ምስሎችን ስለላከልኝ ነው። የፖስታ አገልግሎት ድርጅትን ለኃላፊነት የሚመራው የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ታህሳስ 2 ቀን 2000 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ እነኚህ ምስሎች በቴምብር እንዲታተሙ በማዘዙ መሆኑን ይገልፅላቸዋል። አቶ ኤልያስ የሰማእታት ማኅበሩንም ሆነ ፖስታ ቤትን በተደጋጋሚ የቅጂ መብታቸውን እንዲያከብሩ ቢጠይቁም ተገቢውን መልስ ሊያገኙ ስላልቻሉ መብታቸውን በሕግ ከማስከበር ውጭ ሌላ አማራጭ አጡ።

3. ቀራፂው ከሰሱ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም አንድ ክስ ቀረበለት። ከሳሹ አቶ ኤልያስ አሰጋኸኝ ሲሆኑ፤ ተከሳሾች ደግሞ 1ኛ የቀይ ሸብር ሰማዕታት ወዳጆችና ቤተሰቦች ማኅበር፣ 2ኛ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ናቸው። ክሱ ከላይ ያነሳነውን የሰማዕታት ሐውልት በ1990 በወጣ የውድድር ማስታወቂያ ሰርተው ያስረከቡት አቶ ኤልያስ በሐውልት ከነቅርፅ ውድድሩ ማሸነፋቸው ሳይገለፅላቸው 1ኛው ተከሳሽ የራሱ ቅርፅ አስመስሎ በመገናኛ ብዙሀን ገልጿል። 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የቅርፁን ምስል የያዙ ስልሳ ሺህ ቴምብሮችን አሳትሞ አንዱን በሦስት ብር በመሸጥ አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ብር ሰብስቧል። ተከሳሾች አቶ ኤልያስ በስራው ላይ ባለቤትነት ያላቸውን የፈጠራ ባለቤትነት መብት በመጣስ ከቅርፁ ማግኘት የሚገባቸውን አንድ መቶ ሺህ ብር በማሳጣት የብር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ጉዳት አንዲደርስብኝ አድርገዋል። በተጨማሪም የፈጠራ ባለቤትነት መብቴ በመጣሱ ለደረሰብኝ የሕሊና ጉዳት አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ተክሎበት በድምሩ ብር አምስት መቶ ሰማንያ ሺህ ብር እንዲከፍሉኝ ይወሰንልኝ የሚል ነው።

ተከሳሾች በሰጡት መልስ 1ኛ ተከሳሽ የሆነው የቀይ ሽብር ሰማዕታት ወ/ቤ/ማ ከሳሽ አቶ ኤልያስ ቅርፁን አስረከብኩ የሚሉት በ1990 ነው። እኔ ግን የተቋቋምኩት በ1995 በመሆኑ ከከሳሹ የተቀበልኩት ቅርፅ ስለሌለ ከውልም ሆነ ከሕግ የሚመነጭ ግንኙነት ስለሌለን ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ ብሏል። በተጨማሪም በቴመብር ላይ ምስሉ የወጣው ቅርፅና የአቶ ኤልያስ ቅርፅ ልዩነት ስላላቸው ክሱ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ብሎ ተከራከረ።

በሁለተኛነት የተከሰሰው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ ከሳሽ ወጣ ስለሚሉት ውድድር የማውቀው ነገር የለም። ቴምብሮቹን ያተምኩት 1ኛ ተከሳሽ ይታተሙ ብሎ የሦስት ቅርጾችን ምስል ስለላከልኝ ነው፡ በታተሙት ቴምብሮች ላይ ያለው ምስልና የከሳሹ የአቶ ኤለያስ ስራ የተለያዩ ናቸው። የጠየቁት የካሳ መጠንም የተጋነነ ነው ሲል ምላሽ በመስጠት ተከራከረ።

ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር አድምጦ ማስረጃቸውን ከመረመረ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ የሆነው የቀ/ሸ/ሰ/ወ/ቤ/ማኅበር ከከሳሽ ከአቶ ኤልያስ ፍቃድና እውቅና ውጭ 2ኛ ተከሳሽ ለሆነው ለፖስታ አገልግሎት ድርጅት ቅርጾቹ እንዲታተሙ በማዘዝ ማሳተሙን አረጋገጠ። የአቶ ኤልያስ ስራ ባለ ሦስት አውታር (three dimension) የሆነ አዲስ ሥራ (original) በመሆኑ በቴምብር ላይ የታተመው ባለ ሁለት ገፅታ ምስል ቢሆንም፤ የከሳሹን የቅጂ መብት ባለመጠበቁ የቅጂ መብት ጥሰት ፈፅሟል። 2ኛ ተከሳሽ ግን ምስሉን ያተመው ከ1ኛ ተከሳሽ በደረሰው ትዕዛዝ እንጂ በራሱ ባለመሆኑ የከሳሹ የቅጂ መብት አለመከበሩንም ስለማያውቅ ኃላፊነት የለበትም ሲል የኢትዮጵያ ፖስታ ቤት ድርጅትን ከቀረበበት ክስ በነፃ አሰናበተው።

አቶ ኤልያስ የጠየቁትን ካሳ በተመለከተ በውድድሩ ላሸነፈ ሰው ይከፈላል የተባው የሽልማት ገንዘብ ብር 12,900 ስለነበር ከሳሽ ማግኘት እችላለሁ ብሎ ያቀረበው የገንዘብ መጠን በማስረጃ የተረጋገጠ ባለመሆኑ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁ410/96 ላይ የተቀመጠው የህሊና ጉዳት ካሳ ብር አንድ መቶ ሺህ ለከሳሽ እንዲከፈል ወሰነ።

በውሳኔው ቅር የተሰኘው የቀ/ሽ/ሰ/ወ/ቤ/ ማኅበር ይግባኝ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት አቀረበ። ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ግን ይግባኙን አልተቀበለውም። በዚህ ውሳኔ ተስፋ ያልቆረጠው ማኅበሩ የሕግ ስህተት በስር ፍ/ቤቶች ተፈፅሟል ሲል ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረበ።

ዋነኛ የክርክር ነጥቦቹ ከሳሽ አቶ ኤልያስ የቅርፅ ስራውን አስረከብኩ የሚሉት በ1990 ዓ.ም ሆኖ ክሱን ያቀረቡት ደግሞ የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1845 መሰረት የአስር ዓመት የይርጋ ገደብ አልፎታል። በቴምብር ላይ የታተመው ስራና የአቶ ኤልያስ ስራ ምንም ግንኙነት እንደሌለው በምስክሮች በመረጋገጡ የስር ፍ/ቤቶች ካሳ እንድከፍል የወሰኑብኝ ውሳኔ የሕግ ስህተት ተፈፅሞበታል የሚሉ ናቸው

አቶ ኤልያስ ለሰበር አቤቱታው በጠበቃው በአቶ ያለልኝ ተሾመ በኩል ያቀረበው ክርክር ያቀረብኩት ክስ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1845 የይርጋ ድንጋጌን የሚመለከት አይደለም። ከውል ውጪ ለደረሱ ጉዳቶች ክስ የማቅረቢያው ጊዜ ጉዳቱ መድረሱ በታወቀ በሁለት ዓመት ጊዜ ነው። የቅጂ መብቴን መጣሱን ያወኩት ነሐሴ 20 ቀን 2000 ዓ.ም በመሆኑ ክሱን ያቀረብኩት የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም ሁለት ዓመት ሳያልፍ ነው። ማንኛውም በምድር ላይ ያለ ባለ ሦስት ገፅታ (dimension) ስራ በምስል ሊወጣ የሚችለው በሁለት ገፅታ መሆኑ ተፈጥሮአዊ በመሆኑ ክርክሩ ውድቅ እንዲደረግና የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ እንዲፀና የሚጠይቅ ነበር።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ ከማየታችን በፊት እስቲ ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን አዋጅ በመጠኑ እንዳሰው።

የቅጂ መብት ምንድን ነው

ከሚታወቀው ነገር ስንጀምር የስነ-ጽሁፍም ሆነ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ከማዝናናት ባሻገር ለአንድ ሀገር ሁለገብ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ። በፈጠራ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ደግሞ ስራዎቻቸውን የሚሰሩት ተሰጥኦዋቸው ስለሆነ ራሳቸውን ለማስደሰት ወይም ኀሳባቸውንና ስሜታቸውን በጥበባዊ መንገድ አሳምረው ለመግለፅ ብቻ አይደለም። ብዙውን ጊዜ የፈጠራ ስራቸው የሚተዳደሩበት እንጀራቸውም ነው። በመሆኑም በእነሱ የፈጠራ ስራ የሚጠቀመው ማኅበረሰብ ለስራቸውና ከሥራዎቻቸው ማግኘት ለሚገባቸው ጥቅሞችና መብቶች እውቅና ካልሰጣቸውና ተገቢውን ጥበቃ ካላደረገላቸው ይጐዳሉ። በሀገራችን ለብዙ ጊዜ እንደታዘብነው የበይ ተመልካች ይሆኑና በአርቲስቶቹ ስራ ኅብረተሰቡ እየተጠቀመ እየወደዳቸው እያከበራቸው እያደነቃቸው በአስከፊ ድህነት ውስጥ ለመውደቅ ይገደዳሉ። እናስ…

እናማ ለነዚህ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የተጠናከረ ጥበቃ ለመስጠት ሰኔ 17 ቀን 1996 ዓ.ም ለቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ለማድረግ አዋጅ ቁጥር 410/1996 ወጥቶ በስራ ላይ ይገኛል።

በዚህ አዋጅ አንቀፅ 2(8) መሠረት የቅጅ መብት ማለት ከአንድ ስራ የሚመነጭ የኢኮኖሚ መብት ሲሆን፤ አግባብነት ባለው ጊዜ የሞራል መብቶችንም የሚጨምር ነው። ተዛማጅ የሚባሉት መብቶች ደግሞ የከዋኝ፣ የድምፅ ሪከርዲንግ ፕሮዲውሰር፣ የብሮድካስቲንግ ድርጅት በሥራው ላይ ያሉት መብቶች ናቸው።

ለአዋጁ የቅጂ መብቶቻቸው ጥበቃ የተደረገላቸው ማንኛውም አይነት ስራዎች አይደሉም። የተለያዩ አይነት ሥራዎች ስላሉ አዋጁ ጥበቃው የሚመለከታቸውን ሥራዎች በአንቀፅ 2(30) ስር በሰጠው ትርጓሜ የሥነጽሁፍ፣ ኪነ-ጥበብ እና ሳይንሳዊ መስኰች ውጤት መሆኑን በመግለፅ በመፅሐፍና መፅሔት በጋዜጣ የኮምፒውተር ፕሮግራም፣ ንግግር፣ ሌክቸር፣ ስብከት፣ ድራማ፣ ድራማዊ ሙዚቃ የመድረክ ውዝዋዜ ሌሎች የመድረክ ስራዎች

-    የሙዚቃ፣ የኦዲዮ ቪዥዋል፣ የኪነ-ህንፃ ሥራ

-    የስዕል፣ የቅብ፣ የሐውልት፣ የቅርፃ ቅርፅ፣ የሕትመት፣ የፊደል ቅርፅ፣ ጥልፍ እና ሌላ የስነ-ጥበብ ስራ ፎቶ ግራፉ እና ስእላዊ መግለጫዎችን ሌሎች የስነ-ጥበብ የኪነ-ጥበብ እና የስነ-ጽሁፍ ስራዎች መሆናቸውን በዝርዝር ያስቀምጣል።

ከላይ ያነሳነው ክርክር የሐውልት ቅርፅ ስራን የሚመለከት በመሆኑ የቅጂ መብት ጥበቃ የሚደረግላቸው ሥራዎች ውስጥ የሚወድቅ መሆኑን ልብ በሉ። የቅጂ መብት ጥበቃ ለማግኘት ደግሞ የሥራው አላማና የጥራት ደረጃው ከግምት ውስጥ ባይገባም በአዋጁ አንቀጽ 6 መሠረት ጥበቃ ለማግኘት ወጥ (ኦርጅናል) መሆን ወይም ተቀርጾ ግዙፍነት ካገኘ የሥራው አመንጪ ስራውን በማውጣቱ ብቻ ጥበቃ እንደሚያገኝ ይደነግጋል። የሥራው አመንጪ የሚባለው ደግሞ አንድን የአእምሮ ውጤት የሆነ ሥራ የፈጠረ ሲሆን፤ የኮምፒውተር ፕሮግራም ከሆነ ፕሮግራሙን የፈጠረው የፎቶግራፍ ሥራ ከሆነ ደግሞ በጥንቅሩ ኃላፊ የሆነው ሰው የሥራው አመንጪ እንደሆነ በአንቀፅ 2(2) ላይ የተሰጠው ትርጓሜ ያስረዳል።

የፎቶ ስራዎችን በተመለከተ ሥራዎቹ ወጥ ከመሆን በተጨማሪ የአንድ ስራ አካል መሆን ወይም በመፅሐፍ መልክ መታተም ወይም ደግሞ የአመንጪውን ወይም የወኪሉን ስምና አድራሻ መያዛቸው ጥበቃውን ለማግኘት አስፈላጊ መሆኑ በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።

ከውጭ ስራዎች በተጨማሪ የመጀመሪያ ስራን መሰረት ያደረጉ የትርጉም የማመሳሰል፣ የቅንብር ስራውን የሚቀይር ወይም የሚያሻሽሉ ወይም ቢይዙት በአመራረጡ ኦርጅናል የሆነና በሚነበብ መሳሪያ ወይም በሌላ ያለ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የቅኔ ስብስብ ወይም ዳታቤዝን የመሳሰሉ ሰብስቦችም ጥበቃ የተደረገላቸው ሲሆን ለእነኚህ ጥበቃ መሰጠቱ የመጀመሪያው ስራ ያለውን ጥበቃ እንደሚያስቀር በአዋጁ አንቀጽ 5 ላይ ተገልጿል።

ኢኮኖሚያዊ መብቶች

ቀደም ብለን እንደጠቀስነው የቅጂ መብት ሁለት መብቶችን ያካተተ ነው። ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ ወይም ህሊናዊ መብቶች ናቸው። የኢኮኖሚያዊ መብቶች የሚባሉት የአንድን የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች የተጠበቁለት ስራ በሚመለከት የሥራው አመንጪ ወይም በሕግ ወይም በውል የስራው ባለቤት የሆነ ሰው ስራውን በተመለከተ በራሱ ለመስራት ወይም ሌላ ሰው እንዲሰራ ፈቃድ ለመስጠት የተጠበቁለት መብቶች ናቸው። እነኚህ መብቶች ሥራውን ማባዛትን፣ መተርጐምን፣ የመለወጥ፣ ማሻሻል ወይም ወደሌላ ቅርፅ መለወጥን ሙሉ በሙሉ በራሱ በስራው አመንጪ ወይም የሥራው ባለቤት ፍቃድ እንዲሰሩ አዋጁ ይደነግጋል። በተጨማሪ ዋናውን ወይመ የስራውን ቅጂ ለህዝብ ማቅረብ መሸጥ ወይም ማከራየት፣ የሥራውን ቅጂ ወይም ዋናውን በሌላ ስራ ማካተት ለህዝብ እይታ ማቅረብ፣ ስራውን መከወን፣ በመገናኛ ብዙሀን ወይም በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ለህዝብ ማቅረብም የሥራው አመንጪ ወይም የስራው ባለቤት መብት ነው።

ወጥ የስነ ጥበብ ስራዎች ድርሰቶች ጥንቅሮች በተመለከተ ደራሲው በመጀመሪያ ስራዎቹ ሲቀርቡ ብቻ ሳይሆን በድጋሚ ለሽያጭ ሲቀርቡ ከሚገኘው ገቢ ላይ ተገቢውን ድርሻቸውን የማግኘት መብት አላቸው። የሥራው አመንጪ በህይወት ባይኖርም እንኳን ወራሾቹ በድጋሚ ተሰርተው ወይም ወይም ተቀናብረው ለገበያ ከሚቀርቡ ስራዎች የሚገኘውን ጥቅም የመጋራት መብት አዋጁ ሰጥቷቸዋል። ይህ የኢኮኖሚያዊ መብት በዋነኛነት የሥራው የፈጠራ ባለቤት ስራዎቹን እራሱ በማባዛት፣ በማሻሻል፣ በመከወን ለህዝብ በማቅረብ ገቢውን የማግኘት መብቱን ያስጠበቁ ናቸው። እራሱ የማይሰራው ከሆነ ዳግም ባለቤትነቱን ለሌላ አካል በሽያጭ በኪራይ ወይም በስጦታ በማስተላለፍ የገንዘብ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የተቀመጡ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ የሞራል መብት የሚባሉት የአንድ ስራ አመንጪ ኢኮኖሚያዊ መብቱን ለሌላ ሰው ቢያስተላልፍም ባያስተላልፍም የሥራው ባለቤት መሆኑ እንዲታወቅና እንዲገለፅ መብት አለው። በፈቃደኝነት ስሙ እንዳይገለፅ ወይም በብዕር ስም ለመጠቀም ካልወሰነ በስተቀር የስራው አመንጪነት እንደተጠበቀ ነው። ሥራው ተዛብቶ፣ ተቆራርጦ፣ ተቀያይሮ ሲቀርብ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ክብሩን የሚነኩ ከሆነበት መቃወም መብቱ ነው። በተጨማሪም ስራውን የማሳተም መብቱም ከህሊናዊ መብቶች አንዱ ሆኖ ተጠብቋል።

ሰበር ምን አለ    

በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሐውልት ቅርፅ የአቶ ኤልያስ አሰጋኸኝን ስራ የቀ/ሸ/ሰ/ወ/ቤተ ማኅበር ካለፈቃድ የስራው ባለቤት እራሱ እንደሆነ አድርጐ በቴምብር መስሉን በማሳተሙ በስር ፍ/ቤት የህሊና ጉዳት ካሳ መቶ ሺህ ብር ተፈርዶላቸው ማኅበሩ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ብሎ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ማመልከቱን መነሻችን ላይ ተመልክተናል።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ ማኅበሩ ያቀረበውን የ10 ዓመት የይርጋ ገደብ መቆጣጠር ያለበት አቶ ኤልያስ ስራውን ካስረከቡበት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ሳይሆን መብታቸው መጣሱን ካወቁበት ከነሐሴ 20 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በመሆኑ ክሱ የቀረበው የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም ስለሆነ የይርጋ ገደቡ አላለፈም በሚል ውድቅ አደረገው። በፍሬ ጉዳዩ ላይም የአቶ ኤሊያስ ለውድድር ያቀረቡት ሐውልት ምስል በማኅበሩ አማካኝነት በቴመብር ምስል ታትሞ ካለ ባለቤቱ ፍቃድና እውቅና በመሰራጨቱ ማኅበሩ ላደረሰባቸው የሞራል (የህሊና) ጉዳት መቶ ሺህ ብር ካሳ መወሰኑ አግባብ ነው በሚል የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ አፅንቶታል።

ለዛሬ በዚሁ ይብቃን።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
6945 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1077 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us