የአዛውንቶች ሥጋት የሆኑ ጉዳዮች

Thursday, 28 September 2017 14:36

 

ረጅም ዕድሜ መኖር የሁሉም ሰው ልጅ ቀዳማዊ ምኞት ነው። ይሄ ረጅም እድሜ ሲታሰብ ደግሞ ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ነገሮች አሉ። በተለይ በአሁኑ ጊዜ እድሜያቸው ከፍ እያለ የመጣ ሰዎችን በተለየ ሁኔታ የሚያሳስቧቸው የበሽታ አይነቶች ተለይተው ይቀመጣሉ። በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎች እንደሚገልጹት እድሜያቸው 65 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች በተለየ መልኩ የሚጠቁባቸው በሽታዎች አሉ ይላሉ። አለም አቀፉ የበሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ማዕከል (centers for disease control and prevention) እንደሚያስቀምጠው ደግሞ አንድ ሰው 65 ዓመት ከሞላው በኋላ በአማካይ 19 ነጥብ 3 ተጨማሪ አመታትን ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ ተጨማሪ ዓመታት ታዲያ በበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው። በአርካንሳስ ዩኒቨርስቲ ሜዲካል ሳይንስ የጄሪያትሪክስ (እድሜያቸው የገፉ ሰዎችን የጤና ሁኔታ የሚያጠና ሞያ) ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጂን ዌይ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊጠነቀቋቸው የሚገቡ ችግሮችን ዘርዝረዋል። ባለሞያው እንደሚያስጠነቅቁትም ማንኛውም በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው እነዚህን ችግሮች እንደሚከሰቱበት በመገንዘብ እንዴት አድርጎ ቀሪውን ዘመኑን በደስታ መኖር እንደሚችል መገንዘብ ይኖርበታል። ይሄንን ተገንዝበው ራሳቸውን መጠበቅ ከቻሉም 41 በመቶዎቹ የዚህ እድሜ ክልል ነዋሪዎች ጤናማ ህይወትን መምራት ይችላሉ።

 

የመገጣጠሚያ ህመም

የመገጣጠሚያ ህመም በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ከሚያጠቁ በሽታዎች ቀዳሚው ነው። የሜሪላንድ ብሔራዊ ስነ እድሜ ኢንስቲቲዩት በጥናት ተረጋግጧል እንዳለውም በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል 49 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ለዚህ ችግር ተጋላጮች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሰውነት መገጣጠሚያቸው ላይ በሚከሰቱ የእብጠት፣ የኢንፌክሽን ወይም የመቆጣት ችግር ሳቢያ እንደልባቸው ሰውነታቸውን ለማዘዝ ይቸገራሉ። ችግሩ በተለያዩ ኢንፌክሽኖች፣ ከቆየ ጠባሳ (trauma)፣ ከመገጣጠሚያ እና አጥንቶች መድከም እንዲሁም ከሜታቦሊዝም መዛባት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ችግሮቹ ከእድሜ መግፋት ጋር ተደማምረው በዚህ እድሜ ውስጥ ያሉ ሰዎች ያለ ሌላ ሰው እርዳታ ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስ እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል።

 

የልብ ህመም

የልብ ህመም እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች በብዛት ከሚሞቱባቸው በሽታዎች አንዱ ነው። እንደ ማዕከሉ ሪፖርት በ2014 ብቻ በአለማችን ላይ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ 489ሺህ 722 ሰዎች በልብ ህመም ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል። በጥናት ማረጋገጥ የተቻለውም በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል 37 በመቶ ወንዶች እና 26 በመቶ ሴቶች በልብ ህመም ይጠቃሉ። ለዚህ እንደ መነሻ ምክንያት የተቀመጠው ደግሞ ሰዎች ረጅም እድሜ እየኖሩ በሄዱ ቁጥር የደም ግፊታቸው እየጨመረ፣ የኮሌስትሮል መጠናቸው እያሻቀበ እንዲሁም ለስትሮክ የመጋለጥ እድላቸው እየሰፋ መምጣቱ ነው። እነዚህ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ደግሞ የልብ ህመም እንዲከሰት ብሎም እንዲባባስ የማድረግ ጉዳት ያስከትላሉ።

 

ካንሰር

ማዕከሉ ባካሄደው ጥናት መሠረት በአለማችን ላይ በ2014 ከተመዘገቡ የአዛውንት ሞት አደጋዎች መካከል ካንሰር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 413 ሺህ 885 አዛውንቶች ህይወታቸውን በካንሰር ህመም ምክንያት አጥተዋል። እንደ አጠቃላይ ሲታይም 28 በመቶ የሚሆኑት ወንድ አዛውነቶች እንዲሁም 21 በመቶ የሚሆኑ ሴት አዛውነቶች ለተለያዩ የካንሰር አይነቶች ተጋላጭ ናቸው። ጉዳዩን አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ እነዚህ አዛውንቶች ህመሙ እንዳለባቸው የሚረጋገጠው ለካንሰር ብለው ሳይሆን ለሌላ ህመም ህክምና በሚመረመሩበት ጊዜ መሆኑ  ነው።

 

የመተንፈሻ አካላት ችግር

የመተንፈሻ አካላት የጤና እክሎች የታችኛው እና የላይኛው በሚል የሚከፈሉ ሲሆን፣ አዛውንቶች በአብዛኛው በታችኛው መተንፈሻ አካላት የጤና እክል ይጠቃሉ። በ2014 ብቻም 124ሺህ 693 አዛውንቶች በዚህ ችግር ሳቢያ ህይወታቸውን በማጣታቸው ችግሩ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ብዙ አዛውንቶችን ከሞቱባቸው ችግሮች በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ከእነዚህ የታችኛው ክፍል የመተንፈሻ አካላት ችግር ከሚባሉት ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰው የአስም በሽታ ነው። በመሆኑም በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚኖሩ አዛውንቶች መካከል 10 በመቶዎቹ ወንዶች እና 13 በመቶዎቹ ሴቶች የአስም በሽታ ተጠቂዎች ናቸው። በተጨማሪም 10 በመቶዎቹ ወንዶች እና 11 በመቶዎቹ ሴቶች በጉሮሮ መቁሰል ወይም መተንፈስን በሚያውክ የሳንባ በሽታ የተጠቁ ናቸው። ይሄ ብቻም ሳይሆን እነዚህ ሰዎች ለሳንባ ምች፣ ለሳንባ ኢንፌክሽን እንዲሁም ለተለያዩ የሳል ህመሞች ተጋላጭ ናቸው። እነዚህን በሽታዎች አዛውንቶች በቀላሉ ሊቋቋሟቸው ስለማይችሉ አዛውንቶችን ገዳይ ከሆኑ ስምንት ዋና ዋና በሽታዎች ተርታ ይመደባሉ።

 

የአልዛይመርስ በሽታ

በ2014 ብቻ 92 ሺህ 604 እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆነ አዛውንቶች ከአልዛይመርስ በሽታ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል ሲል የማእከሉ ሪፖርት ያመለክታል። የአልዛይመርስ ማህበር እንደገለፀው ደግሞ ከዘጠኝ አዛውንቶች እድሜያቸው 65 እና በዚያ በላይ ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ በአልዛይመርስ በሽታ ይያዛል። በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከልም 11 በመቶዎቹ ለዚህ በሽታ ይጋለጣሉ ብሏል ሪፖርቱ። ይሄ ብቻም ሳይሆን ለመሰል የአእምሮ ጤና ችግሮች እና እክሎች፣ በአግባቡ ማስተዋል አለመቻል እና ለሌሎች ከአእምሮ ጋር ተያያዥ ለሆኑ የጤና ችግሮች በብዛት ተጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል።

 

የአጥንት መሣሣት ችግር

እድሜ እየተገፋ በሄደ ቁጥር ልክ እንደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሁሉ አጥንትም ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣል። ከዚህ ውስጥ ቀዳሚው ደግሞ የአጥንት መሣሣት ነው። የአጥንት መሣሣት እነዚህ አዛውንቶች በፈለጉት መጠን መንቀሳቀስ እና ራሳቸውን ችለው ድርጊቶችን ማከናወን እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም የአጥንታቸው መሣሣት እና እጅግ ቀላል መሆን ሰውነታቸውን ለመሸከም እንዲያቅተው እና በቀላሉ እንዲሰበሩ ያደርገዋል።

 

የስኳር ህመም

65 ዓመት እና ከዚያ በላይ የእድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሰዎች መካከል 25 በመቶዎቹ የስኳር ህመም ተጠቂዎች መሆናቸውን የማዕከሉ ሪፖርት ያመለክታል። በ2014 ብቻ 54ሺህ 161 አዛውንቶች በዚህ ህመም ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። በአብዛኛው በአኗኗር ዘይቤያቸው በአንድ ቦታ መቀመጥን የሚያዘወትሩ እና ብዙም እንቅስቃሴ የማያደርጉ በመሆናቸው ለዚህ ችግር የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

 

 

የነርቭ ህመም

ሌላው ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ሊያሳስብ የሚገባው የነርቭ ህመም ነው። ይሄንኛውም የነርቭ ህመም (Shingles) ብዙ ጊዜ በአንደኛው የሰውነት ክፍል ላይ ጉዳት የሚያደርሰው የነርቭ ህመም አይነት ነው። ህመሙ ሲጀምር ከባድ ህመም ያለው ነው። ከማእከሉ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ የችግሩ ተጠቂ ነው።

 

ድብርት እና ድህነት

እድሜያቸው የገፉ ሰዎች እና አዛውንቶች በአብዛኛው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከሌሎች ተገልለው በመሆኑ ለድብርት የተጋለጡ ናቸው። ከስራ ገበታ ውጪ መሆን፣ ከብዙ ሰዎች ጋር አለመገናኘት እንዲሁም እንደልብ ተንቀሳቅሶ የፈለጉትን ነገር ማከናወን አለመቻል ደግሞ ለድብርት ከሚዳርጉ ነገሮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ይላል ማእከሉ። የድብርት ችግር በራሱ ችግር ከመሆኑ በተጨማሪም በሽታ የመከላከል አቅምን ይቀንሳል፣ ኢንፌክሽኖችን የመቋቋም ኃይልንም ያሳጣል።

ሌላው ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው እና ለዚህ ለድብርትም እንደ ምክንያት የሚወሰደው ድህነት ነው። እነዚህ ሰዎች ያሉበት እድሜ በጡረታ ከስራ ገበታ የሚገለሉበት እና የራሳቸው የሆነ ገቢ የማይኖራቸው ጊዜ በመሆኑ ለድህነት ተጋላጭ ናቸው። በ2015 የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በ2013 ብቻ እድሜያቸው 65 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሆናቸው አዛውንቶች መካከል 45 በመቶዎቹ ከድህነት ወለል በታች ናቸው። ከወንዶች ይልቅ ደግሞ ሴቶች በዚህ እድሜያቸው ከባድ ድህነት ውስጥ ይገባሉ። ድህነትና የፈለጉትን ነገር ማድረግ አለመቻላቸው እንደ ድብርት እና ጭንቀት እንዲሁም ተያያዥ ለሆኑ የጤና እክሎች ያጋልጧቸዋል።        

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
621 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 830 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us