ብዙም ያልታወቀው የታይሮይድ ችግር

Wednesday, 11 October 2017 13:38

 

11የታይሮድ እጢ በታችኛው የአንገታችን ክፍል ላይ የሚገኝ እና እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የሰውነት ተግባራትን የሚያከናውኑ ሆርሞኖችን የሚያመነጭ እጢ ነው። በዚህ እጢ ላይ የሚደርሱ እክሎች የአብዛኛውን ሰውነታችንን ተግባራት በማዛባት ለከፍተኛ የጤና እክል ያጋልጣሉ። ምንም እንኳን በሽታው በተለይ በአሁኑ ወቅት በበርካቶች ላይ የሚስተዋል ቢሆንም፤ በቂ የሆነ ግንዛቤ ካለመኖሩ የተነሳ መፍትሄ ለመፈለግ ጥረት ሲደረግ እምብዛም አይታይም። የታይሮይድ ኤክስፖርት የሆኑት እና በአሜሪካ ታይሮይድ ማህበር ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ዶክተር ሞኒካ ሳካሩልስ ቀጣዩን መረጃ አስፍረዋል።


የታይሮድ እጢ የቢራቢሮ ቅርፅ ያለው እና በጣም ትንሽ መጠን ያለው እጢ ነው። ምንም እንኳን መጠኑ ትንሽ ቢሆንም በሰውነታችን ውስጥ የሚከናወኑ በርካታ ዋና ዋና ተግባራትን ይቆጣጠራል። ከዚህ እጢ የሚመነጨው ሆርሞን የአተነፋፈስ ስርዓትን፣ የልብምትን፣ የምግብ ልመትን እንዲሁም የሰውነት ሙቀት መጠንን ይቆጣጠራል። ይህ እጢ እክል ገጥሞት ማምረት ያለበትን ያህል ሆርሞን ማመንጨት ሳይችል አሊያም ከሚጠበቅበት መጠን በላይ ሲያመነጭ ታዲያ ሰውነታችን ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣል። እጢው ማመንጨት ከሚጠበቅበት መጠን በታች የሆነ ሆርሞን ሲያመነጭ የሚቆጣጠራቸው የሰውነት እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ ዘገምተኛ ይሆናሉ። በአብዛኛውም ሰዎች የሚጠቁት በዚህ የሆርሞን ማነስ ችግር ነው። ነገር ግን ከአንድ መቶ ሰዎች መካከል አንዱ ከመጠን ላለፈ የሆርሞን መመንጨት (ሃይፐርታይሮይዲዝም) ያጋለጣል።


የታይሮይድ ሆርሞን መዛባት በአብዛኛው ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ እንዲሁም እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ይከሰታል። በተጨማሪም የዚህ እጢ ሆርሞን መዛባት ችግር ካለበት ቤተሰብ የሚወለዱ ሰዎችም ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። የታይሮይድ መዛባት ሊከሰት የሚችለው የሰውነት ህመምን የመቋቋም ሲስተም የራሱን ሴሎች ከአገልግሎት ውጪ ሲያደርጋቸው ነው። ይሄ የሚከሰተውም ለዚህ ችግር ምክንያት በሆኑ በሽታዎች ሳቢያ ነው። የታይሮይድ ሆርሞን ከሚፈለገው በላይ እንዲመነጭ የሚያደርገው ግራቬስ የተባለው ህመም ሲሆን፤ ከሚፈለገው መጠን በታች የሆነ ሆርሞን እንዲመነጭ የሚያደርገው ህመም ደግሞ ሀሺሞቶ ይባላል።


አንድ ሰው በታይሮይድ እጢ ችግር ምክንያት ህመም ሲያጋጥመው በቀላሉ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። አብዛኞቹ የችግሩ ምልክቶች ከሌሎች ችግሮች ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ቢሆንም የደም ምርመራ በማድረግ ግን ምልክቶቹን መለየት ይቻላል። የታይሮድ ሆርሞን እጥረት የተከሰተባቸው ሰዎች የሚያሳዩዋቸው ዋና ዋናዎቹ ምልክቶችም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፤ ሆድ ድርቀት፣ ድብርት፣ አላስፈላጊ የሆነ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ብርድን ለመቋቋም መቸገር፣ የልብ ምት መቀነስ እንዲሁም የመገጣጠሚያ እና የጡንቻ ህመም ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ታይሮይድ እጢ ከሚፈለገው መጠን በላይ የሆነ ሆርሞንን በሰውነት ውስጥ ሲያመነጭ የራሱ የሆነ ምልክቶች ያሳያል። እነዚህ ምልክቶችም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፣ ለመተኛት መቸገር፣ ሙቀትን ለመቋቋም መቸገር፣ የጡንቻ መዛል፣ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ማላብ፣ ፈጣን እና ከተለመደው የተለየ የልብ ምት፣ ተቅማጥ እንዲሁም ምክንያታዊ ያልሆነ የሰውነት ክብደት መቀነስ ይጠቀሳሉ።
የታይሮይድን እጢ ከሚያጠቁት ነገሮች መካከል ሌላው ካንሰር ነው። ነገር ግን ታይሮይድ እጢ በካንሰር ሲጠቃ ብዙም ምልክቶች ስለማያሳይ ለማወቅ ከባድ ነው። አንዳንድ ጊዜ አንገት አካባቢ ትናንሽ እብጠቶችን የሚያሳይ ቢሆንም እነዚህ እብጠቶች የካንሰሩ ውጤት መሆን አለመሆናቸው በምርመራ ብቻ የሚረጋገጥ ነው የሚሆነው ይላሉ ዶ/ር ምኒካ። ችግሩ የታይሮይድ እጢ ካንሰር ከሆነ በካንሰር የተጠቃውን አካል ቆርጦ በማውጣት አብዛኛውን ማከም ይቻላል።
የታይሮይድ እጢ ችግር ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በብዛት እንደመከሰቱ በእርግዝና ወቅት በሴቷም በጽንሱም ላይ ጉዳት ያደርሳል። ችግሩ ኖሮበት ህክምና ያላደረገች ነፍሰ ጡር ሴት ጽንሱን ለማስወረድ፣ የመውለጃ ጊዜዋ ሳይደርስ ለመውለድ ትገደዳለች። ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች አልፋ ብትወልድ እንኳን ህፃኑ የሚኖረው የአንጎል እድገት ዘገምተኛ እንዲሆን ያደርገዋል።
የአሜሪካ ታይሮይድ ማህበር መረጃ እንደሚያመለክተውም ሴቶች ከወንዶች ከአምስት እስከ ስምንት እጥፍ በዚህ ችግር የመጠቃት እድል አላቸው። ከስምንት ሴቶችም አንዷ በህይወት ዘመኗ በዚህ ችግር ትጠቃለች።
የታይሮይድ እጢ ችግር በተለያዩ ህክምናዎች ሊታከም ቢችልም በአንድ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ መዳን ግን አይችልም። ህክምናው እድሜ ልክ ክትትል የሚጠይቅ ነው። ህክምናውን ማድረግ ካልተቻለ ግን በርካታ ተያያዥ የሆኑ የጤና እክሎችን ያስከትላል። ለአብነት ያህልም የልብ እና ከልብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች፣ የአጥንት መሣሣት እንዲሁም መውለድ አለመቻልን ሊያስከትል ይችላል።
ለታይሮይድ እጢ ችግር መንስኤዎች በግልጽ የሚታወቁ እና እነዚህ እነዚህ ተብለው የሚጠቀሱ መንስኤዎች የሉም። ቀድሞ ከአዮዲን ማዕድን እጥረት ጋር ተያይዞ ይከሰታል የሚል እሳቤ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ለዚህ ችግር አጋላጭ የሆኑ የምግብ አይነቶች እንዳሉም ተጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪም ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንዲሁም ብዙ እንቅስቃሴ አለማድረግ ለዚህ ችግር መንስኤ ይሆናሉ የሚል ግምት እየተሰጠ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። በሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ኬሚካል የታይሮይድ እጢ እንዳይነቃቃ የማድረግ ባህሪይ ስላለው ለችግሩ የማጋለጥ እንዲሁም ችግሩን የማባባስ ባህሪይ አለው።
በሌላ በኩል ደግሞ የምንመገበው ምግብ እና የምንጠጣው ውሃ በውስጡ የሚኖረው የአዮዲን ማዕድን መጠን በጣም ያነሰ ወይም የበዛ ከሆነ ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድላችን እንዲጨምር ያደርገዋል። በተጨማሪም በባህሪያቸው በታይሮይድ እጢ ላይ እብጠት እና እንደ እንቅርት ያሉ ችግሮችን የሚፈጥሩ የምግብ አይነቶች አሉ። እነዚህን ምግቦች መጠቀምም ለዚህ ችግር ያለውን ተጋላጭነት ይጨምረዋል።
ሌላው ለዚህ ለዚህ ችግር አጋላጭ የሆነው ነገር ደግሞ ለጨረር ያለው ተጋላጭነት ነው። በተለይ የታይሮይድ እጢ የሚገኝበት አንገት አካባቢ ለጨረር ከመጋለጥ በተጨማሪም ለጨረር የተጋለጠ ወተት፣ ውሃ እንዲሁም ምግብን መመገብ ለዚህ ችግር ያጋልጣል። የታይሮይድ እጢ ችግር እንደ አብዛኞቹ ህመሞች ከጭንቀት ጋርም የሚያያዝ ነው። የሚወዱትን በሞት መለየት፣ የጋብቻ መፍረስና ፍቺ እንዲሁም የመኪና አደጋን በመሳሳሉ ችግሮች ሳቢያ የሚከሰት ጭንቀት የታይሮይድ እጢ ችግርን የማምጣት እንዲሁም የማባባስ ባህሪይ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪም ለአንገት የሚድረጉ ቀዶ ህክምናዎች፣ የተወሰኑ ኬሞቴራፒዎች ለዚህ ችግር ያለውን ተጋላጭነት የሚጨምሩ ናቸው።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
1486 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 928 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us