በፀረ-ተባይ መድሐኒት የተጠቁ አትክልትና ፍራፍሬዎች

Wednesday, 08 November 2017 19:16

 

 

በአትክልትና በፍራፍሬዎች ላይ ፀረ-ተባይ መድሐኒቶችን በብዛት መጠቀም ለሴቶች አስጊ ነው ተባለ። በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት እንዲሁም በኖርዌይ የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት አትክልትና ፍራፍሬዎችን ከተባይ ለመከላከል በማሰብ አገልግሎት ላይ የሚውሉት ፀረ-ተባይ መድሐኒቶች በሴቶች ላይ የመውለድ ችግር ያስከትላሉ። በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት  የሥነ-ምግብ እና የወረርሽኝ በሽታ አሶሺየት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጆርግ ቻቬሮ እንደገለፁትም በተለይ እንደ ጥቅል ጐመን፣ ቃሪያ እና የተለያዩ የእንጆሪ ዝርያዎች ላይ ፀረ-ተባይ መድሐኒቶችን በውስጣቸው የማስቀረት ባህሪይ ስላላቸው እነዚህን መጠቀም በሴት ልጅ ላይ የመውለድ ችግር ይፈጥራል።

 

በ325 ሴቶች ላይ የተደረገው ጥናት እንዳረጋገጠውም ለፀረ-ተባይ መድሐኒት በስፋት የተጋለጡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የተመገቡት የመውለድ ችግር ገጥሟቸዋል። በጥናቱ ላይ እድሜያቸው በአማካይ 35 ዓመት የሆነ ሴቶች እንዲሳተፉ የተደረገ ሲሆን በውጤቱ ማረጋገጥ የተቻለውም የፀረ-ተባይ መድሐኒት በሴቶች መውለድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ነው። ሴቶቹ ማርገዝ አለመቻል ብቻም ሳይሆን በህይወት ያለ ህፃን የመውለድ እድላቸው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በቀን ውስጥ ከሁለቴ በላይ እነዚህን አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚጠቀሙ ሴቶች ለመውለድ ችግር የመጋለጥ እድላቸው በብዛት ከማይጠቀሙት ጋር ሲነፃፀር በ18 በመቶ ከፍ ብሏል። ጥናቱ እግረ መንገዱን ለሌላ ጥናት መንገድ እንደከፈተ ነው የተገለፀው። ይኸውም የፀረ-ተባይ መድሐኒቶች በሴቶች ላይ ከእርግዝና ወቅት ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲከሰት እንዲሁም በሽንት ውስጥ የሚኖረው የፕሮቲን መጠን ከፍ እንዲል ያደርገዋል። በተለይ በተፈጥሮ መንገድ የማይለሙ እና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ክትትል እየተደረገባቸው የሚበቅሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ለዚህ አጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል።

 

ከጥናቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት ግሬስ ሙሬቲ እንደገለፁትም በአሁኑ ጊዜ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ፀረ-ተባይ መድሐኒቶችን በዘፈቀደ እና በልማድ ስለሚጠቀሙ ችግሩን የከፋ እያደረገው መጥቷል። አምራቾቹ የተለያዩ ፀረ-ተባይ መድሐኒቶችን በመቀላቀል ጭምር የመጠቀም ልምድ ስላላቸው ምን ያህል እና ምን አይነት ኬሚካሎችን እየተመገብን መሆኑን እንኳን የምንረዳበት መንገድ የለም ብለዋል።

 

አትክልትና ፍራፍሬዎች ለፀረ-ተባይ መድሐኒቶች አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ የጠቀሰው ጥናቱ፤ ፀረ-ተባይ መድሐኒት ከሚደረግባቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች መካከል አንድ ሦስተኛ አካባቢዎቹ የመድሐኒቱ ቅሪት በላያቸው ላይ ይከማቻል። እነዚህ የፀረ-ተባይ ቅሪቶች ደግሞ ለተለያዩ የካንሰር አይነቶች የማጋለጥ እድል አላቸው። በተጨማሪም እንደ ፓርኪንሰንስ ላሉ ከአንጐል ጋር ተያያዥነት ላላቸው ችግሮች እንዲሁም በሽታ የመከላከል አቅምን የማዳከም ተፅዕኖ አላቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለማችን ላይ እየተስፋፉ የመጡት ምግብ ወለድ በሽታዎችም በአብዛኛው ከእነዚህ የአትክልትና ፍራፍሬዎች ለፀረ-ተባይ መድሐኒቶች መጋለጥ ጋር የተያያዘ ነው። በተለይም እንደ ሄፒታይተስ ኤ እና የተለያዩ ኢንፌክሽኖች የፀረ-ተባይ መድሐኒቶች የበዙባቸውን የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች ከመጠቀም ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አላቸው ተብሏል።

 

ዶክተር ቻቫሮ እንደገለፁትም እነዚህ አትክልትና ፍራፍሬዎች ሴቶች እንዳያረግዙ ከማድረግም በተጨማሪ ለውርጃ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል። እንደዚህ አይነት አትክልትና ፍራፍሬዎችን ከተጠቀሙ ሴቶች 79 በመቶዎቹ ከመደበኛው ወጣ ያለ እና የተለየ ልጅ የመውለድ እድል ያላቸው ሲሆን፤ 88 በመቶዎቹ ደግሞ በህይወት ያለ ህፃን የመውለድ እድላቸው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል። እነዚህን አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች በውሃ እንዲሁም በሌሎች የንፅህና ኬሚካሎች በማጠብ በውስጣቸው ያለውን የፀረ-ተባይ መድሐኒት ማስወገድ እንደማይቻል ያስቀመጠው ጥናቱ፤ ይልቁንም በተፈጥሮ መንገድ የበቀሉትን አገልግሎት ላይ በማዋል ራስን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። በተፈጥሯቸው ብዙም የፀረ-ተባይ መድሐኒት ቅሪቶችን የማይዙ የተባሉት አትክልትና ፍራፍሬዎችም አቮካዶ፣ ሽንኩርት፣ ጐመን፣ ካሮት፣ ስኳር ድንች እና አበባ ጐመን ናቸው።¾   

 

የፀረ-ባክቴሪያ መድሐኒቶች እጥረት አሳሳቢ ሆኗል

በየዓመቱ በዓለማችን ላይ 700 ሺህ ገደማ ሰዎች መድሐኒትን በተለመዱ ኢንፌክሽኖች ህይወታቸው የሚያልፍ ሲሆን፤ ከእነዚህ ኢንፌክሽኖች መካከልም መድሐኒትን የተመደ የሳንባ በሽታ፣ ወባ እና ኤች አይ ቪ ኤድስ ተጠቃሾች ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን እንዳስጠነቀቀውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ፀረ-ባክቴሪያ መድሐኒቶች መፈጠር አለመቻላቸው የዓለማችን ፈተና ሆኗል። በአሁኑ ወቅት ያሉት አብዛኞቹ ፀረ-ባክቴሪያ መድሐኒቶች ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሰጡ እንዲችሉ በማስተካከል የተሰሩ እንጂ አዳዲስ ፈጠራዎች አይደሉም ተብሏል። በመሆኑም አሁን ከመቼውም በላይ አዳዲስ የፀረ-ባክቴሪያ መድሐኒቶች መፈጠር የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው ብሏል ድርጅቱ። ይሄንን በአፋጣኝ ማድረግ ካልተቻለ ግን እስከ ፈረንጆቹ 2050 መድሐኒት በተለመዱ ኢንፌክሽኖች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር 10 ሚሊዮን ይደርሳል ሲል ከወዲሁ ግመቱን አስቀምጧል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምም የአዳዲስ ፀረ-ባክቴሪያ መድሐኒቶች ፈጠራ እና ግኝት እንዲሁም ኢንቨስትመንት ከመቼውም በላይ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መደረሱን አስገንዝበዋል። ይሄ ካልሆነ ግን ሰዎች የተለመዱ ኢንፌክሽኖችን ይፈሩ ወደነበረበት እና ወደ ሥጋት ጊዜ መመለሳችን የማይቀር ነው ብለዋል። ድርጅቱ በሪፖርቱ እንዳመለከተው በዓመት 250 ሺህ ሰዎችን የመግደል አቅም ያለውን መድሐኒት የተለመደ የሳንባ በሽታን ጨምሮ ሌሎች ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚያግዙ መድሐኒቶች እጥረት በስፋት እየተስተዋለ መሆኑ ነው። በመሆኑም የመድሐኒት አምራች ኩባንያዎችም ሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች እጅግ አደገኛ የሆኑ እና በቀናት እድሜ ውስጥ ሰዎችን የሚገድሉ ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚያግዙ መድሐኒቶችን በመፍጠር ስራ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
652 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 927 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us