መዘናጋት የወለደው ችግር

Wednesday, 15 November 2017 13:07

 

የዓለም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በየዓመቱ ህዳር 22 ቀን ይከበራል። በሽታው በተለይ በሀገራችን በወረርሽኝ ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጿል። የበሽታው አሳሳቢነት አሁንም ቀጥሏል።

በ2010 እ.ኤ.አ ብቻ 70ሺህ ኢትዮጵያዊያን በኤች አይ ቪ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ይሄንን ቁጥር ለመቀነስ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ያለው ጽ/ቤቱ በዚህም ስራ ምክንያት በ2015 ዓ.ም በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎችን ቁጥር በ70 በመቶ መቀነስ መቻሉን ገልጿል።

ነገር ግን ከወራት በፊት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የለቀቀው መረጃ እንዳመለከተው በኢትዮጵያ ያለው የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭት ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ከፍ ማለቱን ነው። በሀገሪቱ በ2009 ዓ.ም ጽ/ቤቱ አደረኩት ባለው ጥናት ማረጋገጥ የተቻለው ደግሞ 718 ሺህ 550 ዜጎች ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር ይኖራሉ። በሀገሪቱ ያለው የቫይረስ ስርጭትም 1 ነጥብ 185 በመቶ ነው። ይሄ ደግሞ ስርጭቱን ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ከፍ አድርጎታል። የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት አንድ በሽታ ስርጭቱ ከ1 በመቶ በላይ ከሆነ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ደርሷል ይባላል።

በተደረገው ጥናት ማረጋገጥ የተቻለውም የቫይረሱ ስርጭት ከገጠር የሀገሪቱ ክፍል ይልቅ በከተማው አካባቢ ከፍተኛ ነው። ከዚህም የተነሳ በከተማ ከሚኖሩ ዜጎች መካከል 127ሺህ 619 የሚሆኑት ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ። በከተሞች ያለው የቫይረሱ ስርጭት ሲነፃፀር የሚያመለክተው ደግሞ በአዲስ አበባ ያለው የቫይረሱ ስርጭት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው። ይኸውም በከተማዋ ያለው የቫይረሱ ስርጭት 4 ነጥብ 9 በመቶ ሆኗል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን መቃረብን አስመልክቶ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚያመጣቸው መረጃዎች ተመሳሳይ ናቸው። ለበርካታ ዓመታት ለኤች አይ ቪ ቫይረስ የበለጠ ተጋላጭ የተባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ይፋ ይደረጋል። በዚህም መሠረት ዋና ተጋላጭ ናቸው የተባሉት በቅደም ተከተል ሲቀመጡ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ተንቀሳቃሽ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የረጅም ርቀት ተሽከርካሪ ሾፌሮች፣ የህግ ታራሚዎች እንዲሁም የግንባታ ዘርፍ ሠራተኞች ናቸው። በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ያለው የቫይረሱ ስርጭት ደግሞ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ለምሳሌ ያህል በሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ያለው የቫይረሱ ስርጭት መጠን ለበርካታ ዓመታት 23 በመቶ ነው። በተንቀሳቃሽ ሠራተኞች ዘንድ 5 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም በነጋዴዎች ዘንድ 5 ነጥብ 4 በመቶ እንደሆነም ጥናቱ አመልክቷል። በተጨማሪም በረጅም ርቀት ሾፌሮች ዘንድ 4 ነጥብ 9 በመቶ፣ በህግ ታራሚዎች ዘንድ 4 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ ስራ ላይ በተሰማሩ ዜጎች ዘንድ ያለው የቫይረሱ ስርጭት 2 ነጥብ 9 በመቶ እንደሆነ ነው በጥናቱ ማረጋገጥ የተቻለው።

ኤች አይ ቪ በብዛት ተሰራጭቶ የሚታየው በአብዛኛው አምራች በሆነ የህብረተሰብ ክፍል መሆኑ ደግሞ ሌላው የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያጎላው ነገር ነው። ለዚህ ችግር ከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው የተባሉት እድሜቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት ያሉ ወጣቶች እና ታዳጊዎች መሆናቸውም ጥናቱ አስቀምጧል። የኤች አይ ቪ ጉዳይ ሲነሳ ሌላው የችግሩን አስከፊነት የሚጠቁመው የቫይረሱ ስርጭት ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ባደገበት አሁኑ ወቅት እንኳን ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ነው። አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው። በዚህም የተነሣ በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ዜጎች በቫይረሱ እየተያዙ መሆናቸውን የጽ/ቤቱ ጥናት አመልክቷል። የግንዛቤ ክፍተቱን በተመለከተ ወንዶች 69 በመቶ እንዲሁም ሴቶች 49 በመቶዎቹ ብቻ በሽታውን ስለመከላከል እውቀት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል። ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ ከሆኑ እና ከ15 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ወጣቶች መካከል 39 በመቶ ወንዶች እና 24 በመቶ ሴቶች ብቻ በቂ የሆነ ግንዛቤ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።

ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት እንደ ምክንያት ከተቀመጡ ነገሮች መካከል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣቶች ለተለያዩ መጤ ባህሎችና ሱሶች ተጋላጭ መሆን፣ የወሲብ ፊልሞች፣ መጠጦች እና ጫት እንዲሁም የሺሻ እና የማሳጅ ቤቶች በየቦታው መስፋፋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት እና የማህበራዊ ሚዲያው ተደራሽነት ከምንጊዜውም በላይ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ እንዲጋለጡ እያደረጋቸው መሆኑን ጽ/ቤቱ ያደረገው ጥናት አመልክቷል። ጽ/ቤቱ በ2030 (እ.ኤ.አ) ኤች አይ ቪ ከማህበረሰብ ጤና ስጋትነት አሰውግዳለሁ የሚል ግብ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቢገልጽም አሁንም ግን ቫይረሱ በወረርሽኝ ደረጃ ጉዳት እያደረሰ ነው። ከሁሉም በላይ ስለበሽታው የታየው መዘናጋት የቫይረስ ስርጭት ደግሞ እንዲያንሰራራ አድርጎታል ተብሏል።

የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ አዲስ በቫይረስ የሚጠቁ ዜጎችን ቁጥር ወደ 80ሺህ ዝቅ ለማድረግ እንዲሁም በቫይረሱ እና ከቫይረሱ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ችግሮች ሣቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎችን ቁጥር ወደ ግመሽ ሚሊዮን ዝቅ ለማድረግ መታቀዱን ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ገልፆ ነበር። ነገር ግን አሁን የሚስተዋለው ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ እጥረት እቅዱን ለማሳካት ረጅም ርቀትን መጓዝ እንደሚያስፈልግ ነው። ቀደም ሲል በተሰራው ስራ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎችን ቁጥር በ2010 ከነበረበት 0 ነጥብ 28 በመቶ በ2015 ወደ 0 ነጥብ 03 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል። ነገር ግን አሁን እየወጡ ያሉት መረጃዎች የሚያመለክቱት ብዙ ጥረት እንደሚጠይቅ ነው።

ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተውም የቫይረሱን ስርጭት ከመቆጣጠር በተጨማሪም ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ዜጎች የፀረ ኤች አይ ቪ መድሐኒትን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ትኩረት ያስፈልገዋል። እንደመረጃው ከሆነ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ ህፃናት መካከል 20 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው መድሐኒቱን እየተጠቀሙ የሚገኙት። እነዚህ መረጃዎች የሚያመለክቱትም ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ነው። ቁኑን ጠብቆ በዓል ከማክበር በዘለለ ከስር ጀምሮ መስራት እንደሚያስፈልግ የተገኙት መረጃዎች ይጠቁማሉ።  

  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
706 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1041 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us