ያለቀናቸው የሚወለዱ ህጻናት ጉዳይ

Wednesday, 22 November 2017 12:32

 

ህዳር ወር የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የተወለዱ ህጻናት ወር ተብሎ በመላው ዓለም እንዲታሰብ ተወስኗል። ዘንድሮም በዓለም ለ7ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ “ያለቀናቸው የሚወለዱ ህጻናት የጤና አገልግሎት ጥራት እናምጣላቸው” በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ ይገኛል። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ወሩን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረው ይገኛል። የዓለም ጤና ድርጅት እና ከህጻናት ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚሰሩ አካላትም የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርሰ የሚወለዱ ህጻናትን በተመለከተ ከግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸውን መረጃዎች ይፋ አድርገዋል። አንድ ህጻን የመወለጃ ቀኑ ሳይደርሰ ተወልዷል የሚባለው ከእርግዝና ጀምሮ ከ37 ሳምንታት በፊት የሚወለድ ሲሆን ነው። በዓለማችን ላይም በየዓመቱ 320 ሺህ ህፃናት የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ ይወለዳሉ።

ህፃናት የመወለጃ ቀናቸው ከመድረሱ በፊት እንዲወለዱ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል አብዛኞቹ ልንከላከላቸው የምንላቸው ናቸው። ዋና ዋናዎቹም ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች መጋለጥ፣ በቤት ውስጥ ለሚጨሱ ጭሶች (የከሰል፣ የማገዶ እንጨት እና ኩበት) የሚኖር የረጅም ጊዜ (ተደጋጋሚ) መጋለጥ እንዲሁም በወሊድ ወቅት መታፈን ናቸው።

እነዚህ ከመውለጃ ቀናቸው ቀድመው የሚወለዱ ህጻናት ከሌሎቹ በተለየ መልኩ አደገኛ እና አስጊ የሚሆኑባቸው ቀናት የመወለጃ ቀናቸው ሰሞን ያሉ ቀናት እና ከተወለዱ በኋላ ያሉት ቀጣይ ጥቂት ቀናት ናቸው። በእነዚህ ቀናት ውስጥም ህጻናቱ በጤናቸው ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ተከትሎ የሚያሳዩዋቸው አደገኛ የተባሉ ምልክቶች አሉ። እነዚህ ምልክቶችም የሚከተሉት ናቸው። ህፃኑ የመተንፈስ ችግር የሚያሳይ ከሆነ አደገኛ ምልክት ነው። ይህ ችግር በሁለት መልኩ የሚታይ ሲሆን፤ ህጻኑ በዝቅተኛ ደረጃ የሚተነፍስ ከሆነ (በደቂቃ ውስጥ ከ20 ላነሰ ጊዜ የሚተነፍስ) እና የሚያቃስት ከሆነ አሊያም ደግሞ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ከ60 ጊዜ በላይ የሚተነፍስ እና ደረቱ ላይ ያለመመቸት እና የመንኮራከር ድምጽ ካለ ለህጻኑ አደገኛ ምልክቶች ናቸው። ሌላው በዚህ የህጻኑ ሁኔታ ላይ አደገኛ የሚባለው ምልክት መንዘፍዘፍ ወይም መንቀጥቀጥ ነው። ይሄ የመንቀጥቀጥ ስሜት ሊከሰት የሚችለው ህጻኑ በሚወለድበት ወቅት ብዙ የደም መፍሰስ ችግር ገጥሞት ወይም በቂ የሆነ ፈሳሽ ማግኘት ሳይችል ቀርቶ በተፈጠረ ድርቀት አሊያም ደግሞ በትውከትና በተቅማጥ ብዙ ፈሳሽ ከሰውነቱ ወጥቶ ሊሆን ይችላል። ህጻኑ በሚወለድበት ወቅት ብዙ ደም የፈሰሰው ከሆነ ከመንዘፍዘፍ በተጨማሪም የፊት መገርጣት ያሳያል። ይህ ምልክት ደግሞ ህጻኑ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ይጠቁማል።

የህጻኑን ሰውነት መንዘፍዘፍ ተከትሎም እጆቹ እና እግሮቹ የመቀዝቀዝ ምልክት ያሳያሉ። በተጨማሪም በተወሰነ ደረጃ ራስን የመሳት ምልክት ሊያሳይ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም የመወለጃ ጊዜው ሳይደርስ የተወለደ ህጻን ድንገተኛ የሰውነት መኮማተር ምልክት ሊያሳይ ይችላል። ድንገተኛ የሰውነት መኮማተር ሊከሰት የቻለው ምናልባትም በአደገኛ ባክቴሪያዎች ከመመረዝ፣ በወሊድ ወቅት ከመታፈን፣ ወይም ከቲታነስ የተነሳ ሊሆን ይችላል።

የመወለጃ ቀኑ ሳይደርስ የተወለደ አንድ ህጻን በእናቱ እና በባለሞያ እገዛ ጡት እንዲጠባ ይደረጋል። ነገር ግን ህጻኑ ጡት ለመጥባት ፍላጎት ካጣ ወይም አቅም የሌለው ከሆነ በህጻኑ ጤንነት ላይ የሚታይ ሌላው አደገኛ ምልክት ነው። ህጻኑ ጡት ለመጥባት አለመፈለጉ ወይም አቅም ማጣቱ ከባክቴሪያ ኢንፌክሽን ወይም በሚወለድበት ወቅት በገጠመው መታፈን አሊያም ካለው አነስተኛ ክብደት የተነሳ ሊሆን ይችላል።

የመወለጃ ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህጸናት በመደበኛ ቀናቸው ከሚወለዱ ህጻናት በተለየ መልኩ ለበርካታ የጤና ችግሮች የተጋለጡ ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለተለያዩ መመረዞች (ኢንፌክሽኖች) በብዛት የተጋለጡ  ናቸው። እነዚህን ህጻናት በዋናነት ከሚያጠቋቸው ኢንፌክሽኖች መካከል በቀዳሚነት የሚቀመጡትም የቆዳ፣ የአይን እንዲሁም የጉሮሮ ኢንፌክሽኖች ናቸው። በባክቴሪያ ኢንፌክሽን የተጠቁ የመወለጃ ጊዜያቸው ያልደረሰ ህጻናት ደማቸው ይመረዛል። ደማቸው ከተመረዙ ህጻናት መካከል 30 በመቶ ያህሉ ለማጅራት ገትር የተጋለጡ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ህጻናት ምንም አይነት የማጅራት ገትር ምልክት አያሳዩም። በተጨማሪም የደም መመረዝ ብዙ ጊዜ ከሳንባ ምች ጋር የተያያዘ ነው።

ሌላኛው የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ ከተወለዱ ህጻናት ጋር ተያይዞ ሊያሳስበን የሚገባው አደገኛ ምልክት ቢጫ መሆን ነው። ይህ ችግር ከቀለም ቢጫ መሆን በዘለለም አንጎል ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የህፃኑ ቢጫ መሆን በሶስት ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። የመጀመሪያው የአካል ቢጫ መሆን ሲሆን፤ ይሄንኛው ችግር ከሰባት እስከ አስር ቀናት ብቻ የሚቆይ ይሆናል። የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ ከሚወለዱ ህጻናት መካከል 80 በመቶዎቹ ለዚህ ችግር የተጋለጡ ናቸው።

ሁለተኛው የቢጫነት ምክንያት ከደም አይነቶች አለመስማማት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሊሆን ይችላል። ይሄንኛው የቢጫነት ችግር ህጻኑ በተወለደ 24 ሰዓታት ውስጥ የሚከሰት ነው።

በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የህጻኑ ቢጫ መሆን ሊከሰት የሚችለው በኢንፌክሽን ምክንያት ነው። ህጻኑን ቢጫ እንዲሆን የሚያደርጉትም የባክቴሪያ እና የቫይረስ ኢንፌክሸኖች ናቸው። ህጻኑ ከመወለዱ በፊትም ሆነ ከተወለደ በኋላ ኢንፌክሽን አጋጥሞት ከሆነ ከተወለደ በኋላ ባሉት 24 ሰዓታት ውስጥ በየትኛውም ሰዓት ላይ የቢጫነት ችግር ሊፈጠር ይችላል። የህፃኑ ቢጫ መሆን አደገኛነቱ በተለያዩ ምክንያቶች ይጨምራል። ሁልጊዜም ህጻኑ ከተወለደ በኋላ ባሉት 36 ሰዓታት ውስጥ የሚከሰት ከሆነ እንዲሁም ቢጫነቱ ፊት ላይ ጀምሮ ወደ ሌላ የሰውነት ክፍሎች የሚሰራጭ ከሆነ እና እጅና እግሩ ጭምር ቢጫ የሚሆን ከሆነ አደገኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ይጠቁማል። በተጨማሪም ህጻኑ ያለው ክብደት አነስተኛ ከሆነ እና ከዚሁ ችግር ጎን ለጎን በኢንፌክሽን የተጠቃ ከሆነ አደገኛነቱን ያመለክታል።

ከላይ የተጠቀሱት አደገኛ ምልክቶች የመወለጃ ቀኑ ሳይደርስ ለተወለደ ህጻን እጅግ አሳሳቢ ምልክቶች ናቸው። እነዚህን ምልክቶች በፍጥነት በመረዳት በባለሞያ እና በሞያው የታገዘ ክትትል ማድረግ ካልተቻለ ለህጻኑ ህይወት በጣም አሳሳቢ ይሆናል። ችግሩን ለማስቀረት ቀዳሚው አማራጭም ህጻኑ በጤና ተቋም እንዲወለድ እና ተገቢውን ክትትል እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ወቅቱን የጠበቀ እና ተገቢው ክትትል በብቁ ባለሞያ ማድረግ ከተቻለም የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ በመወለዳቸው ምክንያት የሚከሰተውን ሞት 75 በመቶ መቀነስ ይቻላል።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
636 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1060 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us