ሀሰተኛ መድሐኒቶች የታዳጊ ሀገራት ፈተና ሆነዋል

Wednesday, 06 December 2017 13:17

 

የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን ያወጣው መረጃ በተለይ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት እጅግ አስደንጋጭ ነው። እንደ መረጃው ከሆነ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ከሚገኙ ህፃናት መካከል በየዓመቱ 169 ያህል ህፃናት በሀሰተኛ እና ጥራታቸውን ባልጠበቁ መድሐኒቶች ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ። ድርጅቱ በጉዳዩ ላይ ረዘም ያለ ጊዜን የወሰደ ሰፊ ጥናት ያደረገ ሲሆን፤ በጥናቱ ማረጋገጥ የተቻለውም እነዚህ ጥራት የሌላቸው እና ሀሰተኛ መድሐኒቶች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በስፋት በመሰራጨት ላይ ናቸው። የመድሐኒቶቹ አደገኛነት ደግሞ ህይወትን እስከማሳለፍ ደረጃ የደረሰ መሆኑ ተገልጿል።

ድርጅቱ ከ48 ሺህ በላይ በሆኑ የተለያዩ የመድሐኒት አይነቶች ላይ የተደረጉ የጥራት ፍተሻ ጥናቶችን የተመለከተ ሲሆን፣ የጥራት ግምገማ ውጤቶቹ እንዳመለከቱትም መድሐኒቶቹ ህመምን ከማስታገስ ይልቅ ችግሩን የማባባስ፣ በሽታዎችም መድሐኒትን እንዲላመዱ እና በቀላሉ በትክክለኛ መድሐኒቶችም መዳን እንዳይችሉ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጿል። በታዳጊ እና ደሃ ሀገራት በጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉት መድሐኒቶች ውስጥ አስር በመቶዎቹ የጥራት ጉድለት ያለባቸው መሆናቸውን ያረጋገጠው ጥናቱ፤ በተለይ የወባ በሽታን እና የባክቴሪያ ኢንፌክሽንን ለማከም ከሚያገለግሉ መድሐኒቶች መካከል 65 በመቶዎቹ ሀሰተኛ መድሐኒቶች ሆነው መገኘታቸውን ደርሶበታል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንደገለፁትም፤ ደረጃውን ባልጠበቀ እና በተሳሳተ መንገድ የተሰሩ የሳንባ ምች መድሐኒቶችን በመውሰድ ብቻ በየዓመቱ ከ169 ሺህ እስከ 72 ሺህ የሚደርሱ ህፃናት ህይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ። በተጨማሪም የኤድንበርግ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች እንዳረጋገጡት ለወባ በሽታ ተብለው በተሰሩ ሀሰተኛ እና ጥራታቸውን ባልጠበቁ መድሐኒቶች ምክንያት ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ብቻ በየዓመቱ 116 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ። እነዚህ ሀሰተኛ እና ከደረጃ በታች የሆኑ መድሐኒቶች በብዛት ተሰራጨተው የሚገኙት በታዳጊ ሀገራት ላይ መሆኑ ደግሞ የጉዳዩን አሳሳቢነት አጉልቶታል። ጥናቱ በገበያ ላይ ባሉ 48 ሺህ መድሐኒቶች ላይ የተካሄደ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 4 ሺህ 800 ዎቹ ሀሰተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ሀሰተኛ እና ከደረጃ በታች የሆኑ መድሐኒቶች ከሚያስከትሏቸው ችግሮች መካከል መመረዝ አንዱ ነው። እነዚህ መድሐኒቶች በመርዛማ ነገሮች የተሞሉ ሊሆኑ ስለሚችሉ በሽታውን ከመፈወስ ይልቅ ለተጨማሪ መመረዝ የማጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም የመድሐኒቶቹ ከደረጃ በታች መሆን የበሽታው የኢንፌክሽን መጠን ስር እየሰደደ እንዲሄድ፣ በሽታው እንዲጠነክር እና ለሞት እንዲያበቃ የማድረግ አደገኛ ችግሮችን ይፈጥራሉ። መድሐኒቶቹ የታለመላቸውን ግብ ከመምታት ይልቅ በሽታው ትክክለኛውን መድሐኒት ባለማግኘቱ ከመድሐኒቱ ጋር እንዲላመድ በማድረግ ችግሩን የበለጠ ያባብሱታል ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ሀሰተኛ እና ከደረጃ በታች የሆኑ መድሐኒቶች አስፈላጊውን እና በቂ የሆነውን ንጥረ ነገር ያልያዙ፣ ነገር ግን የተሳሳተ ቅመማ ቅመም እና ንጥረ ነገር የተጨመረባቸው እንዲሁም መድሐኑቶቹ የሚሰሩባቸው ንጥረ ነገሮች እና ቅመማ ቅመሞች በሚፈለገው መጠን ልክ ያልተካተተባቸው ናቸው ብሏል። በተደረጉ ጥናቶች ማረጋገጥ የተቻለውም እነዚህ በሀሰተኛ መንገድ ከትክክለኛው መድሐኒት ግር ተመሳስለው የሚሰሩ መድሐኒቶች በአብዛኛው የበቆሎ ዱቄት፣ የድንች ዱቄት እንዲሁም ቾክ (ጠመኔ) የተጨመረባቸው ናቸው። መድሐኒቶቹ ከሚሰሩበት የተሳሳተ ንጥረ ነገር በተጨማሪም የሚመረቱበት ሁኔታ የአደገኛነታቸውን መጠን ከፍ እንዳደረገውም ተረጋግጧል። መድሐኒቶቹ ንፅህና በሌለው ቦታ እና ሁኔታ እንዲሁም እውቀት እና ንፅህና በሌላቸው ሰዎች የሚመረቱ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ በባክቴሪያ የተበከሉ ናቸው። እነዚህ መድሐኑቶች ከመመረት ሂደታቸው ጀምሮ ጥንቃቄ የማይደረግባቸው በመሆናቸው የሚያደርሱት አደጋም በዚያው ልክ እስከሞት የደረሰ አስከፊ አደጋ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።

የሀሰተኛ እና ከደረጃ በታች የሆኑ መድሐኑቶች ተጠቂዎች በተወሰነ አካባቢ ያሉ ወይም በተወሰነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ እንደሌለ ነው ድርጅቱ ያስቀመጠው። ነገር ግን እነዚህ ተመሳስለው የሚሰሩ መድሐኒቶች ከትክክለኛው መድሐኒት በታች የሆነ ዋጋ ስላላቸው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ዜጐች ላይ ክንዳቸው ይበረታል ብሏል። በመሆኑም በእነዚህ ታዳጊ ሀገራት የሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ህፃናት ተመሳስለው በተሰሩ ሀሰተኛ መድሐኒቶች ምክንያት በየዓመቱ እየሞቱ ይገኛሉ። እነዚህ መድሐኒቶች ሰዎች ትክክለኛውን መድሐኒት በቀላሉ ማግኘት በማይችሉባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ሲሆኑ እና ጠንከር ያለ ቁጥጥር ሳይኖር ሲቀር ስለሚሰራጩ ሰዎች በቀላሉ የሚቀበሏቸው በመሆኑ የሚያደርሷቸው ጉዳቶችም ያንኑ ያህል መጠነ ሰፊ ነው።

በሀሰተኛ እና ከደረጃ በታች በሆኑ መድሐኒቶች በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ካሉ ሀገራት መካከል ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዎቹ እንደሆኑም ጥናቱ አመልክቷል። በአጠቃላይ ሲታይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ገበያ ላይ ካሉ መድሐኒቶች መካከል ከአስር መድሐኒት አንዱ ከደረጃ በታች የሆነ እና ሀሰተኛ መድሐኒት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ግጭት፣ ብጥብጥ እና አለመረጋጋት ባለባቸው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ዘንድ እነዚህ ሀሰተኛ መድሐኒቶች በስፋት ተሰራጭተው ይገኛሉ። እንደ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ደቡብ ምስራቅ እሲያ እንዲሁም ደቡብ አሜሪካን የመሳሰሉ ሀገራት ጭምር የዚህ ችግር ሰለባዎች መሆናቸውም በጥናቱ ተረጋግጧል።

ከትክክለኛው መድሐኒት ጋር ተመሳስለው የሚሰሩ ሀሰተኛ መድሐኒቶች በብዙ ነገሮቻቸው ከትክክለኛው ጋር ስለሚመሳሰሉ በቀላሉ ለመለየት አስቸጋሪ እንደሆነ የገለፁት ጥናቶቹ፤ ይሄ ባህሪያቸውም በዓለም ገበያ ላይ በስፋት እንዲሰራጩ ሁኔታዎችን ፈጥረውላቸዋል ብሏል። በአሁኑ ወቅት ያሉት ቴክኖሎጂዎች ሀገራት በቀላሉ መድሐኑቶችን ማምረት እንዲችሉ የሚያግዟቸው መሆናቸው፣ የኢንተርኔት አገልግሎቱ ግንኙነቱን የተሳለጠ በማድረጉ መድሐኒቶች በቀላሉ የዓለም ገበያን እንዲቀላቀሉ እና እንዲሰራጩ ማድረጉ ለእነዚህ ሀሰተኛ መድሐኒቶች መሰራጨት እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የማድረግ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል። በታዳጊ ሀገራት እና እንደ አፍሪካ ባሉ ሀገራት የተለመደው ራስን በራስ የማከም ባህልም በቁጥጥር እና በፍተሻ ጥራታቸው ተረጋግጦ ያላለፉ መድሐኒቶች በብዛት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው ተብሏል።

ከደረጃ በታች የሆኑ እና ሀሰተኛ መድሐኒቶች መሰራጨት የጀመሩት አሁን አይደለም ያለው የዓለም የጤና ድርጅት፤ ከአራት ዓመት በፊት (በ2013) 1 ሺህ 500 መድሐኒቶች ሀሰተኛ እና ከጥራት ደረጃ በታች እንደሆኑ ሪፖርት እንደደረሰው ገልጿል። እነዚህ መድሐኒቶችም ለልብ ህመም፣ ለስኳር ህመም፣ ለወሊድ መከላከያ፣ ለአእምሮ ጤና እንዲሁም ለካንሰር ህመም ታስበው የተሰሩ መድሐኒቶች ናቸው። በተጨማሪም ድርጅቱ ለቢጫ ወባ እና ለመንጋጋ ቆልፍ እየተሰጡ ያሉ ሀሰተኛ እና ከደረጃ በታች የሆኑ መድሐኒቶች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል። እነዚህ ሀሰተኛ መድሐኒቶች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐችን ህይወት እየቀጠፉ ከመሆናቸው ውጪ ደግሞ እነዚህ መድሐኒቶች ሀገራትን እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር እያስወጧቸው መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።      

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
447 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 75 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us