“በርካታ የኦቲዝም ተጠቂዎች በቤት ውስጥ ነው ያሉት”

Wednesday, 13 December 2017 12:44

 

በህጻናት ላይ የሚከሰቱ የአእምሮ እድገት ችግሮች በርካታ አይነት ናቸው። አንደኛውን ችግር ከሌላው በቀላሉ መለየት ከባድ በመሆኑ በደፈናው የአእምሮ ችግር እንላቸዋለን እንጂ የየራሳቸው መገለጫ አላቸው። ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱ ኦቲዝም ነው። ይህን ችግር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡን ባለሞያ ጋብዘናል። ባለሞያው ዶክተር ዮናስ ባህረጥበብ ሲሆኑ፤ ዶ/ር ዮናስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአእምሮ ህክምና ክፍል ውስጥ መምህር እና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአእምሮ ህክምና ሐኪም ናቸው።


ሰንደቅ፡- ኦቲዝም ከሚለው ቃል እንጀምርና ይህን ቃል በአማርኛው ምን በሚለው ልንተካው እንችላለን? ችግሩስ ምንድን ነው?


ዶ/ር ዮናስ፡- ኦቲዝም የሚለው ቃል ኦተስ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ትርጉሙም እኔ ራሴ ማለት ነው። ኦቲዝምን ስንገልፀው የአእምሮ እድገት መዛባት ችግር በሚለው ልንገልጸው እንችላለን። በህጻናት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ የአእምሮ እድገት መዛባቶች አሉ። ስለዚህ ኦቲዝምም አንዱ የህጻናት አእምሮ እድገት መዛባት ነው።


ሰንደቅ፡- በህፃናት ላይ የሚከሰቱ ሌሎች የአእምሮ እድገት መዛባቶች ካሉ ኦቲዝምን ከእነዚህ ችግሮች በመለየት የሚያግዙ ዋና ዋና ምልክቶች ምን ምን ናቸው?


ዶ/ር ዮናስ፡- የኦቲዝም ችግር ሶስት መሠረታዊ የሆኑ መለያ ምልክቶች አሉት። የመጀመሪያው ምልክት ተግባቦት አለመኖር ነው። ኦቲዝም ያለበት ህጻን ከማንም ጋር ምንም አይነት የቋንቋ ተግባቦት አይኖረውም። ሁለተኛው መለያ ምልክቱ ደግሞ ተደጋጋሚነት ያለው ባህሪ ማሳየት ነው። ህፃኑ አንድ ነገርን በተደጋጋሚ የማድረግ፤ በአንድ መጫወቻ ብቻ ለረጅም ጊዜ መጫወት እና ሌሎች ተደጋጋሚነት ያላቸው ነገሮችን የመፈፀም ባህሪም ይኖረዋል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ህጻኑ ከማህበራዊ ህይወት የተገለለ ይሆናል።


ተግባቦት ስንል ህጻን ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ በቋንቋም ባይሆን በተለያዩ መንገዶች ተግባቦት ማድረግ አለበት። እናቱን ሲያይ መደሰት፤ አንዳንድ ነገሮችን ሲያይ መሳቅ በአጠቃላይ መከፋቱንም መደሰቱንም መግለጽ መቻል አለበት። የኦቲዝም ችግር ያለበት ህጻን ግን እነዚህን ነገሮች አያደርግም። ምንም አይነት ተግባቦት አይኖረውም። አንድ ልጅ ሶስት ዓመት ሞልቶት አፉን መፍታት ሲኖርበት ካልፈታ ወይም አፉን ከፈታ በኋላ ወደ ኋላ ተመልሶ መናገር ካቃተው ህጻኑ የኦቲዝም ተጠቂ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይሄ ብቻ ኦቲዝም ነው ለማለት አያሰደፍርም። ሌሎቹ ምክንያቶችም አብረው መታየት ይኖርባቸዋል። ህጻኑ ከማህበራዊ ህይወት ሙሉ ለሙሉ ራሱን ማግለል፣ ከልጆች ጋር ወይም ከቤተሰብ ጋር አብሮ ያለመጫወት፣ ሊያስቁት ሲሞክሩ አለመሳቅ እና ከአንድ ነገር ጋር ብቻ መጫወት ያሳያል።


ሰንደቅ፡- ከአእምሮ ህመም ጋር በተያያዘ አብዛኞቹ ህመሞች መንስኤያቸው ያለመታወቅ ሁኔታ አለ። የኦቲዝም መንስኤዎችስ ምን ምን ናቸው?


ዶ/ር ዮናስ፡- የኦቲዝም መንስኤው በትክክል አይታወቅም። ለችግሩ ብዙ ነገሮች መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል። ለምሳሌ ችግሩ የዘር ግንድን ተከትሎ ሊሄድ እና ሊወረስ ይችላል። በተጨማሪም በወሊድ ጊዜ የሚበከሰቱ ችግሮች፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ የተለያዩ ህመሞች፣ ከተወለዱ በኋላ በተለይ በጭንቅላት ላይ የሚደርሱ ኢንፌክሽኖች ለኦቲዝም ሊያጋልጡ ይችላሉ። ለተለያዩ የአካባቢ ብክለቶች መጋለጥም የኦቲዝም ችግር ሊያስከትል ይችላል። በአጠቃላይ ለኦቲዝም እንደ መንስኤ የሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ሁሉም ግን ከመላምት የዘለሉ አይደሉም።


ሰንደቅ፡- የኦቲዝም ችግር ምልክቶች መለየት የሚቻለው ከሶስት ዓመታት ጀምሮ ነው የሚሉ መረጃዎች አሉ። ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ግን ገና ከወራት እድሜ ጀምሮ ሊታዩ የሚችሉ ይመስላል። ህክምናውስ ምን ይላል?


ዶ/ር ዮናስ፡- የኦቲዝም ምልክቶቹ ገና ከህፃናንት እድሜ ጀምሮ መታየት ይጀምራሉ። ህጻኑ ገና የአንድ ወር እድሜ እያለው ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ህጻኑ ትክ ብሎ ግድግዳ ብቻ ሊያይ ይችላል፤ በአንድ ወይም በሁለት ወር እድሜው እናቱ ወዲያ ወዲህ ስትል አይኑን ማንከራተት ሲኖርበት ከኦቲዝም ጋር ያለ ልጅ ግን ያንን ላያደርግ ይችላል። ሶስት ወይም አራት ወር ሲሆናቸው ልጆች ዝም ብለው የሚስቁት ሳቅ (Social smile) የማሳየት ባህሪይ አላቸው። ይሄንኛው ግን ላያሳይ ይችላል። እነዚህን ነገሮች ከዚህ እድሜ ጀምሮ ማየት ይቻላል። ነገር ግን በትክክል ለመለየት እስከ ሶስት ዓመት ሊፈጅ ይችላል። በተለይ ለእኛ ነገር ከተለያዩ ባህላዊ ነገሮች ጋር በማያያዝ ልጄ እንዲህ ነው ለማለት ወላጆች ይቸግራቸዋል። ህጻኑ አፉን ካልፈታ ማር በልቶ ነው፣ አባቱም አፉን ቶሎ አልፈታም ነበር ወይም አብሮት የሚያወራ ሰው ስለሌለ እና ቴሌቪዥን ላይ አተኩሮ ስለሚውል ነው እየተባለ በግልጽ አይታወቅም። ወላጆች ስለ ኦቲዝም ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ሲሆን በግልፅ ለመገንዘብ ያዳግታል። ኦቲዝም ችግር አዲስ ሳይንስ ስለሆነ እንኳን ለመደበኛው ሰው ቀርቶ ለጤና ባለሞያውም ለመለየት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ስለ ችግሩ በቂ እና የላቀ ግንዛቤ ላለው ሰው ከወር ጀምሮ ምልክቶቹን ማየት እና መለየት ይቻላል።


ሰንደቅ፡- አንዳንድ ጊዜ የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ህጻናት ወላጆቻቸውን የመንከስና የመቧጨር የመሳሰሉ ባህሪያትን ያሳያሉ። ራሳቸውን እንደመሳት የሚያደርጋቸውም ይኖራሉ። ይሄን ደግሞ ከሚጥል በሽታ ጋር የሚያያዙትም አሉ። ችግሩ ከሌሎች ህመሞች ጋር ያለው ተያያዥነት ምን ይመስላል?


ዶ/ር ዮናስ፡- ኦቲዝምና ተያያዥ ህመሞች የሚባል ነገር አለ። ከእነዚህ የኦቲዝም ተጓዳኝ ከሆኑ ህመሞች መካከል አንደኛው የሚጥል በሽታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በራሱ ወይም በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ ነው። ኦቲዝም ብዙ ጊዜ ከሚጥል በሽታ ጋር ይያያዛል። በቁጥር ይሄን ያህል ነው ብሎ መጥራት ቢያስቸግርም በአብዛኛው የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ልጆች የሚጥል በሽታም ተያይዞ ይኖርባቸዋል። በዚያ ምክንያት የሚጥል በሽታ ምልክት ወይም የባህሪይ ለውጥ ሊያሳዩ ይችላሉ። ሁለተኛው ተጓዳኝ ህመም በራስ ላይ ወይም በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ ነው። ሁሉም ባይሆኑም አንዳንዶቹ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ራሳቸውን ይመታሉ፤ ራሳቸውን ከግድግዳ ጋር ያጋጫሉ፤ ራሳቸውን ይነክሳሉ። እነዚህ ከኦቲዝም ጋር የሚመጡ ተጓዳኝ ችግሮች ናቸው። በእነዚህ ድርጊቶቻቸው ህጻናቱ የመሰበር እና የመድማት እንዲሁም የመቆረጥ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ወላጆችም በዚህ ሳቢያ በጣም ሲቸገሩ ይታያሉ።

ሰንደቅ፡- የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ልጆች ብዙ ጊዜ በሆነ ነገር ልቀው የሚወጡበት ሁኔታ ይኖራል። ችግሩ የአእምሮ እድገት መዛባት ከሆነ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?


ዶ/ር ዮናስ፡- በኦቲዝም የተጠቁ ህጻናት ብዙ ጊዜ በአንድ ነገር የተለየ ችሎታ ይኖራቸዋል። ለምሳሌ ቁጥር በመደመር እና በመቀነስ እንዲሁም በማባዛትና በማካፈል ከሂሳብ ማሽን እኩል ሊሆኑ ይችላሉ። ከእድሜያቸው በላይ በስእል የላቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ኮምፒውተር እና ሞባይል ላይ፣ እንደ ቫዮሊን እና ፒያኖ ያሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመጫወት የላቀ ችሎታ ያለቸው የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች አሉ። ይሄ የላቀ ችሎታቸው ከምን የመነጨ ነው የሚለውን መመለስ ይከብዳል። ነገር ግን አንድን ነገር አጥብቆ በመያዝ እና ደጋግሞ በመስራት የሚመጣ ነው። እነዚህ ልጆች አንድን ነገር ዛሬም ነገም እስከ ዓመት ድረስ ሊደጋግሙ ስለሚችሉ ልቀትን ይፈጥራል። ይሄ የላቀ ችሎታቸው በአለማችን ላይ ብዙ ነገሮችን እንዲፈጥሩ እና እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል።


ሰንደቅ፡- ወደ ህክምናው ስንመጣ፤ ኦቲዝምን አክሞ ማዳን ስለማይችል ከችግሩ ጋር ሆኖ የተሻለ ህይወትን መምራት ለመቻል የሚደረገው ህክምና ምን ይመስላል?


ዶ/ር ዮናስ፡- ህክምናው የልጁን ሁኔታ በጥሩ መንገድ መገምገም ይጠይቃል። እያንዳንዱ የኦቲዝም ተጠቂ የተለያየ ነው። በጣም ግራ እስከሚገባን ድረስ አንዱን ከኦቲዝም ጋር የሚኖር ልጅ ከሌላው ለመለየት በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ልጆቹ በደንብ ተገምግመው ጠንከራ እና ደካማ ጎናቸው መለየት እና በጠንካራ ጎናቸው ላይ መስራት ይኖርበታል። በግምገማው ወቅት እንደ የሚጥል በሽታ እና ራስን የመጉዳት ችግሮች ካሉ ተለይተው መውጣት መታከም አለባቸው። የኦቲዝም ህክምና የሚጀምረው ወላጆች ስለኦቲዝም ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማድረግ ሲሆን ይሄም የመፍትሄውን 50 በመቶ ይይዛል። ወላጆች ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ ከእነሱ ምን እንደሚጠበቅ ማስገንዘብ ያስፈልጋል። በመቀጠል ግን ተጓዳኝ ችግሮች ካሉ እነሱን ማከም ያስፈልጋል። እንደ ልጁ ሁኔታ በማየትም በመደበኛ ትምህርት ቤት ትንሽ እንዲቆይ የሚያስችል ከሆነ እንዲቆይ ማድረግ ይቻላል። መደበኛ ትምህርት ቤት መግባት የማይችሉ እና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት መማር ያለባቸው ከሆኑም በዚያ መልኩ እንዲማሩ ማድረግ ይቻላል። ኦቲዝም መድሀኒት የለውም ግን ተጓዳኝ ችግሮችን በማከም እና ወላጆች ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ልጁ ከእድሜው ጋር እየተሻሻለ እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል። በዚህ መልኩ አንዳንዶቹ የተስተካከለ እድገት ካላቸው ልጆች ጋር እኩል የሚመጡ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ይቀራረባሉ። ስለዚህ ችግሩን ለማከም አንድ መድሀኒት ሳይሆን እንደየ ልጆቹ የተለያየ መንገድን መከተል ያስፈልጋል። በእኛ ሀገር ባለው ሁኔታ በአብዛኛው የወላጆች ኃላፊነት ነው የሚሆነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በደንብ መረዳት፤ በአለማችን ላይ ያሉት ዘመናዊ ህክምናዎች መረዳት እና በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል።


ሰንደቅ፡- አንዲት እናት የኦቲዝም ችግር ያለበት ልጅ ከወለደች በኋላ ድጋሚ ስትወልድ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያለ ልጅ የመውለድ ሁኔታዋ ምን ይመስላል? ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ፍራቻ ይታያል።


ዶ/ር ዮናስ፡- የመደጋገም እድል ይኖረዋል። ነገር ግን ከእናትየዋ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል። አንዲት እናት የመጀመሪያ ልጇ በኦቲዝም ውስጥ እየኖረ ከሆነ ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ ልትፈራ ትችላለች። ይሄን ለመቅረፍ ደግሞ ከህክምና ባለሞያ ጋር የአባትየው እና የእናትየዋ ታሪክ መጠየቅ አለበት። ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮችም ተጠንተው የህክምና ባለሞያዎቹ አዎ እንዲህ ሊሆን ይችላ ሊሉ ይችላሉ።


ሰንደቅ፡- በሀገራችን ስለችግሩ ካለው የግንዛቤ እጥረት የተነሳ ወደ ህክምና ለመምጣት ብዙ ችግር አለ። አሁን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? በህክምና ወቅትስ የሚገጥማችሁ ችግር ምንድን ነው?


ዶ/ር ዮናስ፡- ሀገራችን ለኦቲዝም ገና አዲስ ነው። ገና ባለፉት 30 ዓመታት ነው ችግሩ እየታወቀ ያለው። አንዳንድ ጥናቶች ቢኖሩም ስርጭቱን ግን ሊናገሩ አይችሉም። ብዙ በኦቲዝም ችግር ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ግን ያሉት በቤት ውስጥ ነው። ለዚህ ተብለው የተሰሩ ማእከላት በጣም ጥቂት ናቸው፤ ያለው ግንዛቤም አነስተኛ ነው። በቀጣይ ግን ኦቲዝም በህክምና እና በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካቶ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። እነዚህ ነገሮች ሲደረጉ ብዙ ነገሮችን ቀላል ያደርጋል።


በህክምናው ወቅት የሚስተዋለው ችግር የአቅም ችግር ነው። ህክምናው በጣም ውድ ነው። ወላጆች ለሌሎች ልጆቸው እና ለሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችም ትኩረት መስጠት ስለሚኖርባቸው ችግሩ ላለበት ልጅ ብዙ ትኩረት ያለመስጠት ችግር ይኖራል። ሌላው ደግሞ በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ልጆች ትምህርት የሚያገኙበት ሁኔታ አለመኖር ነው። በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተካተው እንዲማሩ የማድረግ ሁኔታም አለመኖሩ ህክምናውን ፈታኝ ያደርገዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
479 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 71 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us