የማህፀን እጢዎች ገራም ከሚባሉት እጢዎች አንዱ ነው

Wednesday, 20 December 2017 12:58

 

ፆታን መሠረት አድርገው በስፋት ከሚከሰቱ ችግሮች መካከል አንዱ የማህፀን እጢ  ነው። የማህጸን እጢዎች በአብዛኞቹ ሴቶች ላይ የሚገኙ ቢሆኑም እጢዎች ብዙ ጊዜ ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ ስለሚቆዩ መኖራቸውን የሚያውቁት በአጋጣሚ ነው። እኛም ለዛሬው በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ባለሞያ አነጋግረን የሚከተለውን መረጃ ይዘን ቀርበናል። ባለሞያዋ ዶክተር ቤተል ደረጀ ናቸው። ዶ/ር ቤተል በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በማህጸንና ፅንስ ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰርነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

ሰንደቅ፡- የማህፀን እጢ ወይም ማዮማ የሚባለው በህክምናው ምንን ይገልፃል?

ዶ/ር ቤተል፡- የማህጸን እጢዎች ወይም ደግሞ ፋብሮይድስ የሚባሉት በአብዛኛው የሚታወቁት ማዮማ በሚል ነው። እነዚህ እጢዎች በጣም ብዙ ሰዎች ላይ ይገኛሉ። እነዚህ እጢዎች ወደ ካንሰር የመቀየር እድላቸው በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ገራም ከሚባሉ እጢዎች መካከል ናቸው። የማህጸን እጢዎች ከሁሉም የእጢ አይነቶች መካከል ሴቶችን በብዛት የሚያጠቁ እጢዎች ናቸው።

ሰንደቅ፡- እነዚህ እጢዎች እንዲፈጠሩ የሚያደርጓቸው መንስኤዎች ይታወቁ ይሆን? ከታወቁስ ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ቤተል፡- የማህፀን እጢዎች የሚከሰቱባቸው መንስኤዎች በግልፅ አይታወቁም። ነገር ግን እነዚህ እጢዎች የራሳቸው የሆነ አንድ መነሻ ህዋስ አላቸው። ሁሉም እጢዎች ከዚያ ህዋስ ላይ በመነሳት እየተራቡ እና እየተባዙ ያድጋሉ። እጢዎቹ የሚነሱባቸው ህዋሳት በማህጸን ግድግዳ ላይ ያሉ የጡንቻ ህዋሳት ናቸው። ነገር ግን መንስኤያቸው ይሄ ነው ተብሎ የሚታወቅ አይደለም።

ሰንደቅ፡- እጢዎቹ በብዛት በሴቶች ላይ የሚገኙ ናቸው። ከፆታ ውጪ ግን የበለጠ ለዚህ ችግር ተጋላጭ የሚያደርጉ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ቤተል፡- እጢዎቹ በብዛት የሚታዩት የመውለድ እድሜ ክልል ላይ ያሉ ወይም ከ15 እስከ 49 ዓመት ባሉ ሴቶች ላይ ነው። እጢዎቹ በብዛት የሚስተዋሉትም እድሜ እየገፋ ሲሄድ ነው። በአጋጣሚ ከተመረመሩ ሴቶች ውስጥ ስንመለከተው በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሴቶች መካከል ከ12 እስከ 25 በመቶዎቹ እነዚህ እጢዎች ይገኙባቸዋል። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ተቋረጠው የወጡ ማህጸኖች ላይ በተደረገ ምርመራ እንደተረጋገጠው ከእነዚህ መካከል እስከ 80 በመቶዎቹ የማህጸን እጢዎች አሏቸው። ስለዚህ እጢዎቹ በብዛት ቢኖሩም ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ እንጂ በአብዛኛው በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

ሌላው ለዚህ ችግር አጋላጭ ነገር ዘር ነው። ከነጮች ይልቅ ጥቁሮች ለእነዚህ ችግር የበለጠ ተጋላጮች ናቸው። ከነጭ ሴቶች ይልቅ ጥቁር ሴቶች ከሁለት እስከ ሶስት እጥፍ ለዚህ ችግር ተጋላጮች ናቸው። እነዚህ እጢዎች በጥቁር ሴቶች ላይ ገና በትንሽ እድሜ የመከሰት እንዲሁም በፍጥነት የማደግ ባህሪይ አላቸው። በ20ዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ጥቁር ሴቶች ማዮማ ሊኖራቸው የሚችል ሲሆን፤ በነጭ ሴቶች ላይ ግን በብዛት ሊከሰት የሚችለው ከ35 ዓመት በኋላ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ እጢዎቹ ኖረው ምልክት አያሳዩም። እጢዎቹ እያደጉ ሲሄዱ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚያዩዋቸው ምልክቶች አሉ። እነዚህ ምልክቶች በአጠቃላይ ከነጭ ሴቶች ይልቅ በጥቁር ሴቶች ላይ ከባድ ህመም አላቸው። ወደ ህክምናውም ሲመጣ በጥቁሮች ላይ በቀላሉ ማከም ስለማይቻል ማህፀን ቆርጦ የማውጣት ህክምና የመሰጠት እድሉ ሰፊ ነው። ይሄ ማለት በእጢው ምክንያት ማህጻናቸውን የማጣት እድላቸው ለጥቁር ሴቶች 39 በመቶ ሲሆን፤ ለነጭ ሴቶች ግን 16 በመቶ ነው።

የወር አበባ በትንሽ እድሜያቸው ማየት የጀመሩ ሴቶችም የበለጠ ለችግሩ የተጋለጡ ናቸው። በተለይ ደግሞ ከእስር ዓመት በታች ሆነው የወር አበባ ማየት የጀመሩ ሴቶች የበለጠ ተጋላጮች ናቸው። በተቃራኒው ግን የወለዱ ሴቶች እንዲሁም አርግዘው ፅንሱ ከአምስት ወራት በላይ ሆኖት ያስወረዳቸው ሴቶች በእጢዎቹ የመጠቃት እድላቸው ዝቅተኛ ነው። ይሄ የሚሆነውም በእርግዝና ወቅት በማህጸን ግድግዳ ላይ የሚከሰቱ ለውጦች እጢዎቹ በቁጥር እንዲቀንሱ ወይም እንዲሟሽሹ ስለሚያደርጋቸው ነው።

ወደ አመጋገብ ስንመጣ ደግሞ አትክልት ከሚበሉ ሴቶች ይልቅ ስጋን አዘውትረው የሚመገቡ ሴቶች የበለጠ ለማህጸን እጢ የተጋለጡ ናቸው። በተጨማሪም አልኮል በተለይም ቢራ የሚያዘወትሩ ሴቶች የበለጠ ተጋላጮች ናቸው። በተጨማሪም ከፍተኛ የደም ግፊት ያላቸው ሴቶች ለማህፀን እጢዎች ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው።

ሰንደቅ፡- የማህፀን እጢዎችን በተለያዩ መንገዶች መከፋፈል እንደሚቻል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዋና ዋናዎቹ የማህጸን እጢ አይነቶች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ቤተል፡- እነዚህን እጢዎች በማህፀን ውስጥ ባላቸው አቀማመጥ የሚለያዩ ናቸው። እንደየቦታቸውም የየራሳቸው ምልክት እና ተግባር አላቸው። ብዙ ጊዜ የሚከፋፈሉትም በማህጸን ውስጥ ባላቸው አቀማመጥ ነው። ጠቅለል ባለ መልኩም እነዚህ እጢዎች ብዙ ጊዜ የሚቀመጡባቸው አራት ቦታዎች አሉ። አንደኛው የማህፀን ግድግዳ ውስጥ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከውስጠኛው የማህጸን ግድግዳ ተነስቶ ልጅ ወደሚያድግበት (cavity) የሚያድግ ይሆናል። ሶስተኛው ወደ ውጪኛው የማህፀን ክፍል (ወደ ሆድ ወይም ወደ እንቁላል ማምረቻ) የሚያደግ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጣም ተለቅ ሲሉ ከውስጠኛው ክፍል አድገው ማህጸን ሲገፋቸው ልጅ እንደሚወለደው በታችኛው የማህፀን ክፍል ወጥተው ሊገኙ ይችላሉ። እንደዚህ ሲሆን ብዙ ጊዜ ኢንፌክሽን ይኖራል። ስለዚህ መድማትም ይኖራል። ስለዚህ እንደየቦታቸው የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች እና የሚያመጧቸው ችግሮችም የተለያዩ ይሆናሉ።

ሰንደቅ፡- የማህፀን እጢዎች በአብዛኞቹ ሴቶች ላይ ቢገኙም ብዙ ጊዜ ግን ምንም አይነት ምልክት አያሳዩም። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሊያሳዩዋቸው የሚችሉት ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ቤተል፡- አብዛኞቹ ምልክት ስለሌላቸው በአጋጣሚ ነው መኖራቸው የሚታወቀው። ምልክት ሲኖራቸው ግን ሁሉንም አይነቶች የሚያጠቃልሉ ሶስት አይነት ምልክቶችን ያሳያሉ። የመጀመሪያው ምልክት የወር አበባ መዛባት ነው። የወር አበባ መዛባት ሲባል ብዙ ጊዜ ቀኑን ጠብቆ ይመጣል። ሲመጣ ግን በመጠንም በሚቆይበት ቀንም ይበዛል ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ  የሚቆይበት ጊዜ ሳይጨምር መጠኑ ብቻ ሊጨምር ይችላል። ወይም ደግሞ መጠኑም ጨምሮ የሚቆይበት ቀንም ሊበዛ ይችላል። ይሄ ደግሞ ብዙ ደም ስለሚፈሳት የደም ማነስ ያስከትልባትና የደም ማነስ  ምልክቶችን ማሳየት ትጀምራለች። የወር አበባው በሚወርድበት ጊዜም ከፍተኛ ህመም ስለሚፈጥር በእለት እንቅስቃሴ ላይ ከህመም አልፎ እስከ መሳቀቅ ያሉ ችግሮችን ያስከትላል።

ወደ ማህፀን የውስጠኛው ክፍል የሚያደርጉት እና የማህጸን ግድግዳ ውስጥ ያሉት እንደዚህ አይነት ስሜት ይፈጥራሉ። ወደ ሆድ እቃ ውስጥ የሚያደርጉት ግን ብዙ ጊዜ ምልክት ሊያመጡ ይችላሉ።

ሁለተኛው ምልክት ደግሞ የህመም ምልክት ነው። ችግሩ ያለባቸው ሴቶች ማህጸኔን ይከብደኛል ወይም ይጫነኛል የሚል ስሜት እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሄንኛው ምልክት ሁልጊዜም የሚያያዘው ከእጢዎቹ ብዛት እና መጠን ጋር ነው። አንዳንድ ሴቶች ትናንሽ እጢዎች ይኖራቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ ልክ እንደ የዘጠኝ ወር እርጉዝ የሚያክል ያደገ ማህፀን ይኖራቸዋል። ስለዚህ የእጢው መጠን ሲጨምር ከመጫን ስሜቱ በተጨማሪም ሽንት ቶሎ ቶሎ የመምጣት፣ ሰገራ የመድረቅ እና የመከልከል ስሜት ሊሰማ ይችላል። ሌላው የህመም ምልክት የወር አበባ በሚመጣ ጊዜ የሚፈጠር ህመም ነው። ማህጸን በተፈጥሮው በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ በፍጥነት ማስወገድ ይፈልጋል። የወር አበባ ሲመጣ ወይም ምጥ ሲኖር የህመም ስሜት የሚሰማው ማህጸን በውስጡ ያለውን ነገር ጨምቆ ለማስወጣት ስለሚፈልግ ነው። ስለዚህ እጢም ሲኖር ማህፀን ለማስወጣት ስለሚታገል እጢው ያለባት ሴት በወር አበባ ወቅት ህመም ይሰማታል። በሌላ በኩል ደግሞ እጢው የሚመጣው ከኋለኛው የማህጸን ክፍል ሲሆን የግብረስጋ ግንኙነት በሚያደርጉበት ወቅት ከፍተኛ ህመም ይሰማቸዋል። በዚህ ምክንያት ግንኙነት እስከማቆም የሚደርስ ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል።

ሌላኛው የህምም ምልክት ደግሞ ከውጭኛው የማህጸን ክፍል የሚነሱት እጢዎች የሚያመጡት ህመም ነው። እነዚህ እጢዎች ሲያደጉ እና ከማህጸን ጋር የተያያዘበት ነገር ቀጠን ያለ ሲሆን፣ በራሳቸው ላይ በመጠምዘዝ ከባድ ህመም ያስከትላል። ህመሙ ብዙ ጊዜ ወደ ሆስፒታል የሚያስመጣ ስለሆነ በኦፕራሲዮን ነው የሚታከመው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እነዚህ እጢዎች ከነበሩበት ይዘት የመቀየር (degenerate) የማድረግ ባህሪይ አላቸው። አንዳንዱ በተለያዩ ምክንያቶች ውስጡ ተበልቶ ውሃ የቋጠረ ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዱ ጮማ አዘል ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከእርግዝና ጋር በጣም ያድጉና የሚደርሳቸው ደም ስለሚያንስ ውስጣቸው ይሞታል። በዚህ ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ ህመም ያስከትላሉ።

ሶስተኛ አብይ ምልክት የመራባት አቅምን ማዳከም ነው። በእዚህ ላይ የሚያመጡት ችግር እንደ እጢዎቹ መጠን እና የተቀመጡበት ቦታ ይለያያል። እጢው ከውጪ የማህፀን አፍ ላይ ከተቀመጠ የወንድ የዘር ፍሬ እንዲገባ አይፈቅድም። ስለዚህ ይህች ሴት በምንም አጋጣሚ ልታረግዝ አትችልም። የመውለድ እድሉ የሚኖራት ያንን እጢ በማንሳት ብቻ ነው። እጢዎቹ ከውስጠኛው የማህፀን ግድግዳ አድገው የሚገኙ እጢዎች ደግሞ ልጅ የሚያድግበትን ክፍል ያልተስተካከለ ያደርጉታል። ያ ያልተስተካከለ የማህፀን የውስጠኛው ግድግዳ ፅንስ ተቀብሎ ለመያዝ አይችልም። መያዝ እንኳን ቢችል ፅንሱ በሆነ ጊዜ ሊወርድ ይችላል። እድል ገጥሞት ፅንሱ ቢያድግ እና ጥሩ ከሄደ የመወለጃ ቀኑ ሳይደርስ የመውለድ እድሉ ከፍተኛ ይሆናል። ይሄ የሚሆነውም እጢው በግድግዳው እና በእንግዴ ልጁ መካከል ስለሚኖር እንግዴ ልጁ የመልቀቅ ባህሪይ ስለሚኖው ፅንሱ በቂ ምግብ እንዳያገኝ እና እናትየዋ እንድትደማ ምጥም ያለጊዜው እንዲመጣ ያደርገዋል።

እጢው ያለው በማህጸኑ የላይኛው ክፍል ሲሆን ደግሞ እያደገ መጥቶ ቱቦዎቹን ሊዘጋቸው ይችላል ቱቦዎቹ ሲዘጉ ደግሞ የወንድ ዘር ወደ ውስጥ መግባት አይችልም። የሴቷ የዘር ፍሬም ወደዚህ መምጣት አይችልም። ስለዚህ ያቺ ሴት ማርገዝ አትችልም ማለት ነው። እነዚህ የማህፀን እጢዎች ወጣ ያለ ባህሪይም አላቸው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ እጢዎች አንዳንድ ሆርሞኖችን ሊያመርቱ ይችላሉ። ከእነዚህ ሆርሞኖች መካከል ኢሪትሮፖየት የሚባል ሆሞን ያመርታሉ። ይሄ ሆርሞን ስራው ቀይ የደም ሴሎች እንዲመረቱ እና በደሟ ውስጥ እንዲበዙ ያደርጋል። ይሄ ደግሞ የደሟን ውፍረት በመጨመር ፖሊሳይት የተባለ ችግረ ያመጣባታል።

ሰንደቅ፡- እነዚህ ምልክቶች ከአብዛኛው መታየት አለመቻላቸው ችግሩን መኖር አለመኖር ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ታዲያ በምን መልኩ ነው ምርመራ ማድረግ እና ማከም የሚቻለው?

ዶ/ር ቤተል፡- ብዙዎቹን በቀላሉ በእጅ በመመርመር እና የኋላ ታሪካቸውን በመስማት ብቻ ማወቅ ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ ማህጸን አድጎ ይታያል። በተጨማሪም የተለያዩ ገፅታዎች ይኖሩታል። እጢው አንድ ብቻ ከሆነ የማህጸን ገፅታው ብዙ አይረበሽም። ብዙ ከሆነ ግን እንደ ኮረብታ የመሰለ ገፅታ ስለሚኖረው በእጅ በመመርመር ብቻ ይታወቃል። ለማረጋገጥ ግን በአልትራሳውንድ መጠቀም በቂ ነው። በጣም ከባድ ሲሆን እና እንዲህ አይነት ባህሪይ ካላቸው ካንሰሮች ለመለየት አስቸጋሪ ሲሆን ግን ኤም አር አይ ይታዘዛል።

ወደ ህክምናው ስንመጣ ብዙ አይነት ህክምናዎች አሉ። የመጀመሪያው ህክምና አቆይቶ መከታተል ነው። አንዲት ሴት በአጋጣሚ ሁለት በሁለት ወይም ሁለት በሶስት የሆኑ እጢዎች ተገኙብሽ ብትባል ችግር ስለማያመጡ ህክምና ላያስፈልገው ይችላል። ይህች ሴት 46 ዓመት አካባቢ ከሆነች ክትትል ብቻ ይደረጋል። እጢዎቹ በባህሪያቸው የሆርሞን እገዛ ስለሚያስፈልጋቸው የወር አበባ ሲቆም እድገታቸውም ይቆማል። ስለዚህ እንዲህ መከታተል እና እስከምታርጥ መጠበቅ በቂ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መጠኑ በጣም ትልቅ ሲሆን ሁለት አማራጮች ይኖራሉ። አንደኛው በኦፕራሲዮን ማከም ነው። ነገር ግን በኦፕራሲየን ሲታከም ማህፀን ወጥቶ ሊወገድ ይችላል። ይህች ሴት ልጅ ያልወለደች ከሆነች ወይም ማህጸኗን በጣም የምትፈልገው ከሆነ ደግሞ በመድሀኒት እንድትታከም ይደረጋል። የዚህኛው ህክምና አላማ የዕጢውን መጠን መቀነስ ነው። ይሄም ኦፕራሲዮን ሲሰራ እጢውን ከማህፀኑ ለይቶ ለማውጣት እንዲመች ለማድረግ እንጂ በመድሃኒት ብቻ እጢው አይጠፋም። በመድሐኒቱም በመታከምም የእጢውን መጠን ከ35 በመቶ እስከ 65 በመቶ መቀነስ ይቻላል። እነዚህ መድሃኒቶች ብዙ ጊዜ የሚሰጡት ከኦፕራሲዮን በፊት ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ነው። በዚህ ጊዜ በላይ ከተሰጡ ግን ጉዳታቸው ይበዛል። እነዚህ መድሀኒቶች የሴትነት ሆርሞኖች የሚያመነጨውን ፒቱታሪ እጢ ስለሚዘጉት ያቺ ሴት የማረጥ አይነት ስሜት እንዲሰማት የማድረግ ጉዳት አላቸው። መድሃኒቱ ከአንድ ዓመት በላይ የሚወሰድ ከሆነም የአጥንት መሳሳትን ያመጣል። ከመድሐኒቱ ጋር አብረው የሚሰጡት የህመም ማስታገሻዎች ግን በእጢው መጠን ላይ ለውጥ አያመጡትም። ጠቀሜታቸው ከእጢው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ህመሞችን ለመቀነስ ነው።

ዋና ህክምና የሚባለው ኦፕራሲዮን ነው። ኦፕራሲዮኑ ሁለት አማራጮች አሉት። አንደኛው ማህጸን ማውጣት ነው። እጢዎቹ የሚመነጩት ከማህጸን ግድግዳ ላይ ስለሆነ ማህፀኑ ሲወጣ ችግሩ አይኖርም። አንዲት ሴት አርባ አመቷ ቢሆናት፣ ልጆች ወልዳ የበቃች ከሆነ እና እጢው ትልቅ ከሆነ እጢውን ብቻ ከማውጣት ይልቅ ማህፀኑን ማውጣት ኦፕራሲዮኑን ቀለል ያለ ያደርገዋል። ሌላኛው አማራጭ እጢዎቹን ማውጣት ነው። እጢዎቹን ከማህፀን ግድግዳ ላይ ለቅሞ በኦፕራሲዮን ማውጣት ነው። በእኛ ሀገር የምንጠቀምበት ሌሎች ሀገራት የሚጠቀሙበት አማራጭ ደግሞ ወደ ማህጸን የሚወጣውን የደም ቧንቧ በመዝጋት እጢው እንዲሟሽሽ የማድረግ ህክምና አለ። የማህጸን እጢዎች ተመልሰው ሊተኩ ስለሚችሉ ሲያስወጡ ያስወጡበት አላማ በቅድሚያ ሊታሰብበት ይገባል። እጢውን ያስወጣችው ለመውለድ ከሆነ ሌላ ሳይተካ ቶሎ መውለድ አለባት።  ነገር ግን ሰውነቷ ወደ ነበረበት ሁኔታ ተመልሶ ለመውለድ የተወሰነ ጊዜ ሊያስፈልጋት ይችላል። እጢዎቹ በጣም ብዙ ከሆኑ እና የማህፀን ግድግዳ ብዙ ቦታ ተቆርጦ እጢዎቹ የወጡ ከሆነ ማህፀኗ ማማጥ ስለማይችል በኦፕራሲዮን መውለድ አለባቸው። ይሄንን የሚወሰነው ደግሞ ያከማት ባለሞያ ነው። ይሄ መረጃ ለሴቷ በደንብ ሊደርሳት እና በሄደችበት ሁሉ ባለሞያ ሊያውቅ ይገባል።  

    

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
951 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 72 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us