የቶንሲል ህመም ከልብ ህመም ጋር ይያያዛል

Wednesday, 27 December 2017 12:32

 

የቶንሲል በሽታ ህጻናትን በብዛት ከሚያጠቁ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው። ይሄ በሽታ በህፃናት ላይ በብዛት ይከሰት እንጂ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የማጥቃት አቅም አለው። ቶንሲልን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንዲሰጡን ዶክተር አሰፋ ተስፋዬን አነጋግረናል። ዶ/ር አሰፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአንገት በላይ ህክምና ክፍል ኃላፊ፣ ሀኪም እና መምህር ናቸው።

ሰንደቅ፡- ቶንሲል የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ የምንጠቀምበት እንደ ህመም መጠሪያ ነው። በህክምናው ሲገለፅ ቶንሲል የትኛው የሰውነት ክፍላችን ነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ቶንሲል የሰውነታችን መከላከያ ሴሎች የሚራቡበት እና የሚከማቹበት ክፍል ነው። በአብዛኛው የሚታወቁ ከአፋችን ጀርባ ግራና ቀኝ ያሉት ቶንሲሎች ናቸው። ነገር ግን እዚያ አካባቢ አራት ቶንሲል ነው ያለው። አንደኛው የሚገኘው ከምላሳችን የመጨረሻው ክፍል ሲሆን፤ ሁለቱ ደግሞ የሚገኙት ከአፍንጫችን ጀርባ የመጨረሻው ክፍል ላይ ነው። ሌላው ደግሞ አፍንጫና ጆሮን የሚያገናኝ ቱቦ አለ። በተለይ የአፍንጫችን ጀርባ ላይ ያለው የመጨረሻው ቱቦ ዳርና ዳር ላይ ቶንሲሎች አሉ። እነዚህ ቶንሲሎች በቀለበት የተያያዙ ናቸው። የሰውነታችን የመከላከያ ሴሎች ከሚከማቹበት ውስጥ በአይን የሚታየው ይሄ ከአፋችን መጨረሻ የሚገኘው ቶንሲል ነው። ስለዚህ ቶንሲል ዋንኛ ቅጽበታዊ ምላሽ የሚሰጥ የመከላከያ ሴሎች ያሉበት የሰውነት ክፍል ነው። መጠኑን ስናየው ከሁለት ዓመት አስከ ዘጠኝ አመት ባለው እድሜ የቶንሲል መጠን እየጨመረ ነው የሚሄደው። ምክንያቱ ደግሞ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ቅፅበታዊ ምላሽ የሚሰጠው ይሄ ሴል ስለሆነ በዚህ መካከል የሴሎች መራባት አለ፤ ከባእድ ነገሮች ጋር በሚያደርገው ግጭት መጠኑ ይጨምራል። ከዚያ እድሜ በኋላ ግን መጠኑ እየቀነሰ ይሄዳል።

ሰንደቅ፡- ቶንሲል ይሄን ያህል ለሰውነታችን ጠቃሚ ክፍል ከሆነ ወደ ችግርነት (ህመምነት) የሚቀየረው መቼ ነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ወደ ችግር የሚቀየረው ቶንሲል ሲቆጣ ነው። የቶንሲል መቆጣት በሶስት ደረጃዎች ይከፈላል። አንደኛው ቅፅበታዊ የቶንሲል መቆጣት ነው። ይሄንኛው የቶንሲል መቆጣት ባእድ ነገሮች በተለይ እንደ ጀርም ያሉ ነገሮች አፋችን ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ቅፅበታዊ ምላሽ ሲሰጥ የሚፈጠር መቆጣት ነው። ሁለተኛው መቆጣት ደግሞ ዘግየት ብሎ ከአራት ሳምንት በኋላ የሚመጣ መቆጣት ነው። ሶስተኛው ደግሞ ተደጋግሞ የሚመጣ የቶንሲል መቆጣት ነው። ድግግሞሽ የሚባለው በስድስት ወራት ውስጥ አራት ጊዜ የሚከሰት የቶንሲል ችግር ነው።

ሰንደቅ፡- ቶንሲል የመቆጣት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚያደርጉት ዋና ዋና መንስኤዎች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር አሰፋ፡- የቶንሲል መቆጣትን ከሚያመጡት ነገሮች ዋንኛው ጀርሞች ናቸው። ከጀርሞች ግን 80 በመቶ የሚሆነው ቫይረስ የተባለው ጀርም ነው። የመጀመሪያውን ቁጥር የሚይዙት የቶንሲል መቆጣት ተጠቂዎች በቫይረስ ሳቢያ የተጠቁ ናቸው። ሁለተኛው መንስኤ ባክቴሪያ ነው። ስለቶንሲል ሲነሳ በደንብ መታወቅ ያለበት ከልብ ህመም ጋር ተያያዥነት ያለው የቶንሲል በሽታ ነው። 20 በመቶ የሚሆነው የቶንሲል በሽታ የሚመጣው በባክቴሪያ ነው። ከእነዚህ ባክቴሪያዎች ውስጥ እጅግ ጠንቅ እና ዋና የልብን በሽታ የሚያመጣው ስትሪቶኮኮስ የተባለው ባክቴሪያ ነው። በዚህ ባክቴሪያ ከተጠቁት የቶንሲል በሽተኞች ውስጥ ከ37 እስከ 45 በመቶ የሚሆኑት በልብ በሽታ ይጠቃሉ። የቶንሲል አደገኛነትም የሚገለፀው እዚህ ላይ ነው።

ሰንደቅ፡- የቶንሲል በሽታ በብዛት የሚያጠቃው ህፃናትን እንደሆነ ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪስ በዚህ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ይኖሩ ይሆን?

ዶ/ር አሰፋ፡- የቶንሲል በሽታ በህጻናት ላይ (እድሜያቸው ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሆኑ ልጆች ላይ) በጣም ጎልቶ ይታያል። በጣም ትንሽ ስርጭት የሚታየው ደግሞ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት እና ከ50 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው። የቶንሲል በሽታ በባህሪው የደሃ ሀገር ህዝብን የሚያጠቃ በሽታ ነው። በሽታው ከድህነት ጋር የተያያዘ ነው። ስትሪቶኮኮስ የተባለውን ባክቴሪያ የሚያመጣውን እና ልብን የሚያጠቃውን ቶንሲል ስንመለከት የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከ80 እስከ 90 በመቶው የሚገኘው በአፍሪካ፣ እሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነው። ይህ ችግር በእነዚህ አካባቢዎች በተለይ ክረምት ሊገባ ሲል፣ ክረምት መውጫው ላይ እንዲሁም በበልግ ወቅት በወረርሽኝ መልክ ይከሰታል። በከተማ ከሚኖሩ ሰዎች የበለጠም በገጠር የሚኖሩ ሰዎች ተጋላጮች ናቸው።

ሰንደቅ፡- የቶንሲል በሽታ ሲባል ብዙውን ጊዜ የሚታወቀው በጉሮሮ አካባቢ የሚሰማ ህመም እና ምግብ ለመዋጥ መቸገር ናቸው። ሌሎች የሚስተዋሉ ምልክቶችስ ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ከዚህ ልብ ከሚያጠቃው የቶንሲል ህመም ብንጀምር የመጀመሪያው ምልክት ትልቅ ቁርጥማት  ነው። በተለይ በትላልቅ አንጓዎች ላይ የእጅ ወይም የእግር አንጓ አሊያም የጉልበታችን መጋጠሚያ ላይ እየተዘዋወረ የሚያጠቃ ቁርጥማት ይሰማል። በተጨማሪም ከፍተኛ ትኩሳት ይኖራል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የልብ ድካም ይኖራል። የልብ ምት ፍጥነት መጨመርና የምግብ አለመስማማት የዚህ ልብ የሚያጠቃ የቶንሲል አይነት ምልክቶች ናቸው። በሽታው እጅግ ገዳይ በሽታ ስለሆነ ሰዎች እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ መጠርጠር አለባቸው። በአሁኑ ሰዓት 20ሚሊዮን ሰዎች በዚህ በሽታ ተጠቅተዋል። በየዓመቱ 400 ሰዎች በዚህ በሽታ የሚያዙ ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች ከ30 እስከ 40 በመቶዎቹ ይሞታሉ። በተለይ የህፃናት የልብ ሀኪሞች ከሚያዩዋቸው የልብ ድካም ችግሮች መካከል ከቁጥር አንድ ላይ የሚቀመጠው ይሄ በስትሪቶኮኮስ ባክቴሪያ የሚመጣ በሽታ ነው። በሽታው የልብ ጡንቻዎችን ያደክማል፣ ደም የሚወጣበትንና የሚገባበትን መስኮቶች የማስፋት ጉዳት ያደርሳል።

ወደ ሀገራችን ስንመጣ ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት በተመላላሽ ክፍል ተኝተው ከሚታከሙት ታካሚዎች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው በቶንሲል በሽታ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ነው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዙት ህጻናት ናቸው። ወደሆስፒታል የሚመጡት በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች ታይተው እና የተለያዩ መድሀኒቶች ወስደው ስለሆነ በህፃናት ላይ ቶንሲል በጣም አድጎ እና በአተነፋፈሳቸው ላይ ችግር ኖሯቸው ነው የሚመጡት። በዚህ በአምስት ዓመት ውስጥ በኦፕሬሽን ከአንገት በላይ ከሚታከሙ ህፃናት መካከል በቁጥር አንድ ላይ የሚገኘው የቶንሲል ቀዶ ጥገና ነው። በሳምንት ውስጥ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ6 ህጻናት በላይ እናክማለን። ይሄ ሁሉ እየተደረገ ግን አሁንም ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ወረፋ የሚጠብቁ ህጻናት አሉ።

የቶንሲል በሽታ ምልክቶችን ለማወቅ በተለያየ ደረጃ መመልከት ይኖርብናል። በእድሜ ስናየው ህፃናት አጣዳፊ የሆነ የቶንሲል በሽታ ሲኖራቸው የመጀመሪያ ምልክታቸው 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬት የሚደርስ ትኩሳት ነው። ወዲያው ደግሞ ማንቀጥቀጥ እና ማዝለፍለፍ ይከሰታል። ይሄ ምልክት በአንድ ሰዓት ውስጥ ሶስት አራት ጊዜ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ወላጆች በዚህ ሰዓት ትኩሳቱን የማብረድ ስራ መስራት ያስፈልጋቸዋል። ሁለተኛው ምልክት ደግሞ ማስታወክ፣ ማቅለሽለሽ እና የምግብ አለመሳማማት ይታያል። ህፃናቱ መናገር ስለማይችሉ የመንቀጥቀጥ እና የመዝለፍለፍ ምልክት ከታየ ወላጆች መጠርጠር ያለባቸው የጆሮ ኢንፌክሽን እና የቶንሲል በሽታን ነው። ይሄ ሁኔታ በቀጣይ ለሚጥል በሽታ የማጋለጥ ሁኔታ አለው። በተጨማሪም የህፃናቱ ታምቡር የማበጥና የመቅላት ምልክት ያሳያል። የሰውነት መክሳትም ሌላው ምልክት ነው። በአዋቂዎች ላይ ስንመለከት ደግሞ አጣዳፊ የሆነ ትኩሳት፣ ምግብ ለመዋጥ መቸገር፣ ቁርጥማት እና ብርድብርድ የማለት ስሜት ይሰማቸዋል። በዚህ ሰዓት ምርመራ ሲደረግ በባክቴሪያ የተጠቃ ቶንሲል ከሆነ በነጭ የተሸፈነ እና በጣም ትልቅ የሆነ እንዲሁም ቶንሲሎቹ የመቁሰል እና አንገት አካባቢ ንፍፊቶች የማበጥ ሁኔታ መኖር እንዲሁም ምላስ የተቀቀለ መምሰል እና መድረቅ ይታያል።

በሁለተኛ ደረጃ የሚመጡት የቶንሲል ምልክቶች ደግሞ ከቶንሲል ጋር ተያያዥነት ያላቸው በሽታዎች ምልክቶች ናቸው። በእነዚህ መካከልም በእንቅልፍ ሰዓት የአተነፋፈስ ሁኔታ መቀየር፣ ይስተዋላል። ይሄም በየተወሰነ ድግግሞሽ ማንኮራፋት ይታያል። ማንኮራፋት ማለት ሰውነታችን በቂ ኦክስጅን ባለማግኘቱ መጨናነቁን የሚገልፅበት ደወል ነው። ይሄ የሚፈጠረው ቶንሲሉ ለረጅም ጊዜ በመቁሰሉ ያብጥና አየር በአግባቡ እንዳይተላለፍ ስለሚያደርገው ነው። ይሄ የሚከሰተው እድሜያቸው ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት በሆነ ህጻናት ላይ ነው። እነዚህ ህፃናት በጣም ያልባቸዋል፣ ሲተኙ በጣም ተጣጥፈው ነው የሚተኙት፣ ሽንታቸውን በላያቸው ላይ የመልቀቅ፣ በእንቅልፍ ልባቸው ተነስተው መሄድ፣ ድንገት ማልቀስ እና የመባነን ችግር ይኖርባቸዋል።

ሌላኛው ምልክት ደግሞ በቶንሲል ምክንያት የሚፈጠረው የልብ ህመም ምልክት ነው።  ይሄንኛው ምልክት የልብ ድካም፣ ትኩሳት፣ የእግር ማበጥ፣ ቁርጥማት ስሜቶች ይሰማሉ። በድንገት የሚከሰት የቶንሲል መቆጣት ይከሰትና ቶንሲሉ መግል ይይዛል። ይሄ መግልም ከቶንሲሉ ጀርባ ባለው ሽፋን ውስጥ ይከማችና አየር ስለማያስተላልፍ ከፍተኛ ህመም ይፈጥራል። ይሄ ችግር ካለ በአፋጣኝ ቀዶ ጥገና መደረግ እና መግሉ መወገድ አለበት። ይሄ ካልሆነ ግን በህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ከዚህ በተጨማሪም የአፍ ጠረን መቀየር፣ በአነጋገር ላይ ለውጥ ማምጣት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ማስከተል ዋና ዋና ምልክቶቹ ናቸው። በተለይ ቶንሲሉ መግል ከያዘ የተከማቸው መግል ካልወጣ እስከ ህይወት ማሳጣት ይደርሳል። ኢንፌክሽኑ ከተሰራጨ አንጎላችን ላይ ሊወጣ ይችላል። ሳንባችን ላይም ሊወጣ ይችላል። አየር የሚተላለፈው በዚህ ቦታ ስለሆነ በቂ አየር ካልተገኘ አንጎል ከጥቅም ውጪ ይሆናል። አንድ የአንጎል ክፍል ለተወሰኑ ደቂቃዎች ኦክሲጅን ካጣ ይሞታል። ስለዚህ አንጎላችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል።

ሰንደቅ፡- የቶንሲል በሽታን ያመጣሉ ተብለው በዘልማድ ከሚቀመጡ ነገሮች መካከል አንዱ ቀዝቃዛ ነገሮችን መጠቀም ነው። ሳይንሱ ይሄንን እንዴት ያስቀምጠዋል? ምን ያህል ትክክል ነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ለቶንሲል በሽታ ከሚያጋልጡ ነገሮች መካከል በግልጽ የሚታወቁ አሉ። በአፋችን ውስጥ ከአካባቢው ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ባክቴሪያዎች አሉ። እነዚህ ባክቴሪያዎች አካባቢያቸው ለየት በሚልበት ጊዜ ወደ መርዛማነት ይቀየራሉ። አካባቢያቸውን የሚለውጡት ነገሮች ደግሞ ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በረዶን አብዝተው የሚጠቀሙ ሰዎች፣ ሲጋራ የሚያጨሱ፣ ጫት የሚቅሙ ሰዎች የበለጠ ተጋላጮች  ናቸው። ሌላኛው ደግሞ ይሄንን ስትሪቶኮኮስ ባክቴሪያን በቶንሲል ውስጥ ተሸካሚ የሆኑ ነገር ግን ምልክት የማያሳዩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ወላጆች ወይም ሞግዚቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ህጻናት በመቅረብ፣ በማውራት፣ በማስነጠስ ወይም በማሳል ባክቴሪያውን ወደ አየር ስለሚለቁት በአየር ላይ ቆይቶ ወደ ህጻናት ቶንሲል በመግባት ሌላው የቶንሲል በሽታ ምክንያት ይሆናል። በቤት ውስጥ በተደጋጋሚ የቶንሲል በሽታ የሚይዛቸው ሰዎች ካሉ ቤተሰቡ በአጠቃላይ ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል።

ሌላው ለበሽታ መንስኤ የሚሆነው የአልኮል መጠጥ ነው። በተጨማሪም የአለርጂ ተጠቂዎች ተጋላጮች ናቸው። አለርጂ ስንል ልክ እንደ አፍንጫ አለርጂ ሁሉ በአፋችን ውስጥ፣ በአፍንጫችን ውስጥ እንዲሁም የቶንሲል አለርጂ አለ። እነዚህ የአለርጂ ተጠቂዎች የበለጠ በቶንሲል በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ናቸው። በተጨማሪም የቶንሲል በሽታ በዘር ይከሰታል። በተለይ ስትሪቶኮኮስ የተባለው ባክቴሪያ የሚጣበቅበት የቶንሲል ክፍል ያላቸው እና ለዚህ ዝግጁ የሆነው የሚፈጠሩ ሰዎች አሉ። ሌላኛው ለዚህ ችግር አጋላጭ የሆነው የአካባቢ አየር ሁኔታ ነው።

ሰንደቅ፡- የቶንሲል ህመም ይሄን ያህል ከባድ ህመም ከሆነ ህክምናው ምን ይመስላል? አላማውስ ምንድን ነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- የህክምናው ዋና አላማ ጀርሙን ማጥፋት ነው። ጀርሙ የሚጠፋበት መንገድ ደግሞ ራሱን የቻለ ዘዴ አለው። ነገር ግን የታመመ ቶንሲል ሁሉ ፀረ ጀርም ያስፈልገዋል ማለት አይደለም። በአብዛኛው ቶንሲል የሚመጣው በቫይረስ ስለሆነ ይሄ ደግሞ በአብዛኛው የሚያስፈልገው እረፍት ነው። በቫይረስ የተጠቁትን በቀላሉ መለየት ይቻላል። ትኩሳቱ ቀለል ያለ፣ ህመሙ ቀላል እና ሲታይ ጥቂት ቀላ ያለ ነው። ህመሙም በሶስት በአራት ቀናት ውስጥ ስለሚጠፋ እረፍት ማድረግ ነው የሚያስፈልገው። ነገር ግን ሲታይ በጣም ያበጠ፤ መግል የያዘ እና ቁስለት ያለው ከሆነ መድሀኒት መጀመር አለበት። መድሐኒቱም በሶስት ደረጃዎች ይከፋፈላል። ነገር ግን በአብዛኛው እኛ ጋር የሚመጡት ሰዎች ሁለተኛውን ደረጃ ታክመው የሚመጡ ናቸው። ይሄ ደግሞ ባክቴሪያው መድሐኒቱን ስለሚላመድ በቀላሉ በመድሐኒቱ ለማከም ያስችግራል።

ሁለተኛው የቶንሲል ህክምና ችግሩ ከመድረሱ በፊት ማስወገድ፤ ችግሮች ካሉም ማከም ነው። መግል ይዞ ከሆነ መግሉን ማስወገድ፣ የእንቅልፍ ችግር ካመጣ ወይም ከልብ ጋር ተያያዥነት ካለው ቶንሲሉን ማውጣት እና በልብ ላይ ተከታታይነት እንዳይኖረው የሚሰጥ መድሃኒት አለ። እዚህ ላይ ልናተኩርበት የሚገባው ቤዛንቲ ፔንሲን የሚባለው መርፌ ነው። ይሄ መድሐኒት በአሁኑ ሰዓት በአለማችን ላይ ለተወሰኑ በሽታዎች ብቻ ነው የሚሰጠው። መድሐኒቱ ለቶንሲል በሽታ የሚያገለግልበት የተወሰኑ ምክንያቶች ናቸው። የመጀመሪያው ምክንያት ስትሪቶኮኮስ የተባለው ባክቴሪያ በልብ ላይ ጉዳት ካደረሰ በየሶስት ሳምንቱ ከአምስት እስከ አስር ዓመት መወሰድ አለበት። ከዚህ ውጪ ግን ይህ መድሐኒት ለአጣዳፊ የቶንሲል በሽታ ምንም አይነት ጥቅም የለውም። እንዲያውም ከተወሰደ በኋላ ለቁስለት፣ ለአለርጂ፣ ትንፋሽ ለማጠር የማጋለጥ ሁኔታ አለው። ነገር ግን በሽተኞችም መርፌውን ይወዳሉ፣ ወጥ የሆነ የመድሐኒት አጠቃቀም ባለመኖሩም በብዛት ይሰጣል።

ሌላው ደግሞ መከላከል ነው። መከላከል ማለት በህክምና ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነው። በመከላከል የግለሰብን ጤንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ማስወገድ እንዲሁም በሃገር ላይ የሚፈጠረውን ጫና መቀነስ ይቻላል። በዚህ ደግሞ የሚቀድመው እውቀት ነው። ቶንሲል ገዳይ በሽታ መሆኑ መታወቅ አለበት ። አንድ ህፃን ከፍተኛ ትኩሳት ካለው እና የማንቀጥቀጥ እና የማዝለፍለፍ ምልክት ከታየበት ከመንፈሳዊ ነገር ጋር ከማያያዝ ይልቅ ቶንሲል መሆኑን በመገንዘብ ወደ ህክምና መውሰድ ያስፈልጋል። እነዚህ ምልክቶች የበሽታው ባህሪዎች መሆናቸውን ባለሞያውም የማሳወቅ ግዴታ አለበት። ቶንሲል ቀዶ ህክምናም ሌላው የመከላከያ ዘዴ  ነው። የቶንሲል በሽታው በልብ ላይ ጫና እንዳይፈጥር እና እንዳያዳክመው ለማድረግ የቶንሲል ቀዶ ህክምና ይደረጋል። እዚህ ላይ ግን ማንኛውም የተቆጣ ቶንሲል ቀዶ ህክምና ያስፈልገዋል ማለት አይደለም። ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ቶንሲሎች በተወሰነ ምክንያት ብቻ ነው። የመጀመሪያ ምክንያት ማንኮራፋት ሲኖር፣ የሰውነት መቀነስ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ መተኛት ሲያቅት፣ ቶንሲሉ ሲታይ ትልቅ ከሆነ ቶንሲሉ በቀዶ ህክምና እንዲወጣ ይደረጋል። ቶንሲልን በቀዶ ህክምና በማውጣት የሰውነት የመከላከያ አቅም አይጎዳም። ሰውነት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የአቅም መከላከያ ሴሎች የተከማቹበት ቦታ አለው። ነገር ግን እንደ ክፉኝ ያሉ ወረርሽኞች ሲከሰቱ ከቶንሲል የሚለቀቁ በጣም አስፈላጊ የሆኑ መከላከያዎች አሉ። በዚያ ሰዓት በእርግጥ ቶንሲል አይወገድም።

ቶንሲል ሊወጣ የሚችልበት ሌላው ምክንያት የቶንሲል በሽታው ከልብ ጋር ተያያዥነት ሲኖረው ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ ቶንሲሉ ካልተወገደ  ያ ልብ በተደጋጋሚ በዚያ ባክቴሪያ ይጠቃል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ቶንሲል መወገድ ያለበት የቶንሲል በሽታው ድግግሞሽ ሲኖረው ነው። ድግግሞሽ ማለት በአንድ አመት ውስጥ ከአምስት እስከ ስድስት ጊዜ እና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው። ሳይንቲስቶች እንዳስቀመጡት በአመት ውስጥ ከአምስት እና ከስድስት ጊዜ በላይ የቶንሲል ህመም የሚያጋጥመው ሰው ቶንሲሉ ካልወጣለት በቀላሉ ለልብ ድካም፣ ለሳንባ ህመም እና ለሌሎች ችግሮች ይዳረጋል። ድግግሞሽ በሶስት ደረጃ ነው የተቀመጠው። አንድ ልጅ በአንድ ዓመት ውስጥ ለአምስት ወይም ለስድስት ጊዜ፣ በሁለት ዓመት በተደጋጋሚ አራት ጊዜ ወይም ሶስት ጊዜ ከተከሰተ፣ ለሶስት ዓመት ደግሞ በየአመቱ ሁለት ሁለት ጊዜ ከታተመመ በእርግጠኝነት ቶንሲሉ መወገድ አለበት። ወደ አዋቂ ስንመጣ ደግሞ ቶንሲሉ ሲመረመር የቀኙ እና የግራው የመጠን ልዩነት ካለው በእርግጠኝነት መወገድ አለበት። ምክንያቱም አንዳንድ ከመከላከያ ኃይል ጋር ተያያዥነት ያላቸው የካንሰር አይነቶች የሚገለፁት ቶንሲል ላይ ስለሆነ ነው። እነዚህ ካንሰሮች አንዱን ቶንሲል በጣም ትልቅ አድርገው ሌላኛውን ደግሞ በጣም ትንሽ ያደርጉታል። ስለዚህ እንዲህ አይነት ምልክት ካሳየ ቶንሲሉ ተወግዶ ምርመራ መደረግ አለበት።

ሌላው የቶንሲል ቀዶ ህክምና የሚያስፈልገው መጥፎ የአፍ ጠረን ሲያስቸግር ነው። የአፍ ጠረን መጥፎ መሆን በሌላ የሰውነት ክፍላቸው ላይ ምንም ችግር እስከሌለ ድረስ ምክንያቱ የቶንሲል መቆጣት ነው። ስለዚህ ቶንሲሉ በቀላሉ ከተወገደ ሰላማዊ ኑሮን ለመኖር ያግዛል። መግል የያዘ ቶንሲልም በቀጥታ መወገድ ይኖርበታል። ቶንሲል አንድ ጊዜ መግል ከያዘ በተደጋጋሚ የመያዝ እድሉ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ በመጀመሪያ መግሉን በማስወገድ በቀጣይ ቶንሲሉ እንዲወገድ ይደረጋል። ቶንሲል እጅግ አደገኛ በሽታ በመሆኑ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ እና የሚያስፈልገውን የህክምና አይነት ማወቅ ያስፈልጋል። ጉሮሮ አካባቢ የሚፈጠሩ የህመም ስሜቶች ሁሉ የቶንሲል ህመም ማለት አይደለም። መታወቅ የሚችለው በባለሞያ ነው። በተለይ ህፃናት ላይ እነዚህ ምልክቶች የሚታዩ ከሆነ በአፋጣኝ መታከም አለባቸው ቆይተው ከመጡ ግን ችግሩ ስር እየሰደደ ህክምናውም ውስብስብ ይሆናል።

ሰንደቅ፡- በሽታው ካልታከመ የመግደል አቅሙ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በወቅቱ ባይታከም ከዚያ በኋላስ ሊያስከትላቸው የሚችለው ተጓዳኝ ችግሮች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ቶንሲል የሚገኘው በአፍንጫችን ጀርባ አካባቢ ነው። ስለዚህ እነዚህ ቶንሲሎች ላይ ጉዳት በሚደርስበት እና በማይታከምበት ጊዜ እዚያ አካባቢ የሚገኙ ስጋዎችን የማቁሰል ሁኔታ ስለሚኖር መግል የማስያዝ እንዲሁም የአፍ ጠረንን የመቀየር ሁኔታ አለው። በተጨማሪም ሰውነታችንን ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ያጋልጣል። ሌላው ደግሞ የቶንሲል መቆጣቱ ተደጋጋሚ ሲሆን በልብ ላይ ጫና መፍጠር እንዲሁም አየር በቀላሉ ለማግኘት መቸገር ይገጥማል። ከቶንሲል ጋር ተያይዘው እንደሳይነስ መቆጣት፣ የጆሮ ኢንፌክሽን እና መምገል በህፃናት ላይ ይከሰታል። ይሄ ነገር ካልታከመ ደግሞ የመስማት ችሎቸውን እየቀነሰው ይሄዳል። በተጨማሪም በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራል። ሌሊት በቂ የሆነ እንቅልፍ ማግኘት ስለማይችሉ ቀን ትምህርታቸውን ለመከታተል መቸገር፣ በትምህርት ሰዓት ማንቀላፋት እና እንደልባቸው ከሌሎች ልጆች እኩል ለመጫወት መቸገር ይገጥማቸዋል።

ሰንደቅ፡- እንጥል መቁረጥ የቶንሲል በሽታን ለማከም በባህላዊ መንገድ አገልግሎት ላይ የሚውል ተግባር ነው። ምንም እንኳን ድርጊቱ ወንጀል ቢሆንም የሚያስከትላቸው ችግሮች በምን ይገለፃሉ?

ዶ/ር አሰፋ፡- እንጥል የምንላት አፋችንን ስንከፍት መካከል ላይ ተንጠልጥላ የምትታይ ስጋ ናት። በመሠረቱ እንጥል መቆረጥ የለባትም። እኔ በስራዬ ላይ እንደገጠመኝ በእንጥል መቆረጥ ሳቢያ ከፍተኛ ደም ፈሷቸው ለረጅም ጊዜ በሆስፒታል ውስጥ ተኝተው እና በኢንፌክሽን ተሰቃይተው የዳኑ ሰዎችን አውቃለሁ። እነዚህ ሰዎች አተነፋፈሳቸው ላይ ችግር ተፈጥሮባቸው ጉሮሯቸው ላይ ቀዳዳ ሰርተን ነው ያዳናቸው። እንጥልን መቁረጥ ወንጀልም ነው ከሳይንሱ ጋር የሚሄድም አይደለም። እንጥል መቁረጥ ማለት ሰውን መግደል ነው። እንጥል ከተወገደ የቶንሲል በሽታ አይኖርም የሚል አሉባልታ አለ። ነገር ግን ትክክል አይደለም። እንጥል በባለሞያ የሚወገድባቸው ምክንያቶች እጅግ ውስን ናቸው። በአዋቂ ላይ እጅግ ረዝሞ ትንታ ሲያስቸግረው፤ በጣም ማንኮራፋት ሲኖር እና በቂ እንቅልፍ ማግኘት ሲያቅተው እንጥሉ ብቻ ሳይሆን እዚያ አካባቢ ያሉ ስጋዎች ተቆርጠው ወጥተው ሰፊ የአየር መተላለፊያ እንዲኖር የሚደርግበት ሁኔታ ይኖራል።

       

   

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
1044 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 74 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us