መድሐኒትነታቸው የሚያመዝን ፍሬዎች

Wednesday, 03 January 2018 17:01

ብዙዎቻችን በቅርባችን እና በቀላሉ ልናገኛቸው የምንችላቸውን ነገሮች ለምግብነት የማዋል ልማድ አለን። ነገር ግን አንዳንድ እንደተራ ነገር በምናያቸው እና በእለት ምግባችን ውስጥ በማናካትታቸው የምግብ ዘሮችን ምክንያት የምናጣቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ልብ ማለት ይገባናል። በዚህ ረገድ ከከተማ ይልቅ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በርካታ የእህል ዝርያዎችን በምግባቸው ውስጥ በማካተት የተሻሉ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታል። በመሆኑም አንዳንድ የእህል እና የጥራጥሬ ዝርያዎች ለጤንነታችን ያላቸውን ጠቀሜታ መረዳት እና በተቻለ አቅም በእለት ምግባችን ውስጥ ማካተት ይመከራል። በቀላሉ ልናገኛቸው የምንችላቸው እና በጤናችን ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ጥራጥሬዎች ግሎባል ሂለንግ የተባለው ድረ-ገፅ አስፍሯቸዋል። በድረገፁ ላይ የስነ ምግብ ተመራማሪ እና ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ኤድዋርድ ጊብሰን የራሳቸውን የጥናት ውጤት እና የሌሎች በመስኩ የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሰው በዚህ መልኩ አቅርበውታል።


ተልባ


ተልባ ከፍተኛ የሆነ የአሰር መጠን ካለባቸው ጥራጥሬዎች መካከል አንዱ ነው። በተልባ ውስጥ በቀላሉ ሊሟሙ የሚችሉ እና መሟሟት የማይችሉ የቃጫ አይነቶች ይገኛሉ። ይሄ የቃጫ ይዘቱም ተልባ አንጀታችንን የማፅዳት አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጎታል። በተጨማሪም በሰውነታችን ውስጥ ተከማችቶ የሚገኝ አላስፈላጊ ስብን ለማስወገድ ያግዛል። በተልባ ውስጥ ሌላው በስፋት የሚገኘው ነጥረ ነገር ኦሜጋ 3 የተባለው ነው። ይህ ንጥረ ነገር መጥፎ ኮሌስትሮል (low density lipoprotein (LDL) እንዲቀንስ ያደርገዋል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም የተልባ ፍሬን አዘውትሮ በመጠቀም ብቻ በአማካይ 10 ሚሊ ሊትር መጥፎ ኮሌስትሮልን ከሰውነታችን ማስወገድ እንችላለን። እነዚህ መጥፎ ኮሌስትሮሎች ለልብ ህመም የማጋለጥ እድል ስላላቸው እግረ መንገድም የልብ ህመም እና ተያያዥ ችግሮችን ለመከላከል ያግዛል።


ሌላው የተልባ ፍሬ ጠቀሜታ በተለይ በሴቶች ላይ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶችን መከላከል ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በተልባ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ለካንሰር መንስኤ የሆኑ እጢዎች እድገት እንዳይጨምር በማድረግ የጡት ካንሰርን የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። በተልባ ውስጥ የሚገኙት ፓይቶስትሮጂንስ የተባሉት ንጥረ ነገሮች ስትሮጂን ከሚባለው የሴቶች ሆርሞን ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ሴቶችን በተለየ መልኩ የሚያጠቁ የካንሰር አይነቶችን ለመከላከል ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም በወንዶች ላይ የሚከሰተውን የሽንት ፊኛ ካንሰር የመከላከል ጠቀሜታ አለው።


ተልባ ከላይ ከተጠቀሱት ጠቀሜታዎች በተጨማሪም በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን የሚቀንሱ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ በመያዙ ለስኳር ህመም የመጋለጥ እድላችንን በብዙ እጅ ይቀንሳል። ከዚህ ውጪም የተልባ ፍሬን አዘውትሮ በመመገብ በሽታ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ፣ ያግዛል። ይህ ፍሬ በኦሜጋ 3 ንጥረነገር በጣም የበለፀገ በመሆኑ ሰውነታችን የደም ሴሎችን በብዛት እንዲያመርት በማድረግ ያለውን የበሽታ መከላከል አቅም ከፍ ለማድረግ ያግዛል። ተልባ በተለያዩ ማእድኖች እና ቫይታሚኖች የበለፀገ በመሆኑ በእየእለት ምግባችን ውስጥ ማካተት በርካታ ተያያዥ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል። በ28 ግራም የተልባ ፍሬ ውስጥ 152ካሎሪ፣ 7 ነጥብ 8 ግራም አሰር፣ 5 ነጥብ 2 ግራም ፕሮቲን፣ 6 ነጥብ 5 ግራም ኦሜጋ 3 እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችም ይገኛሉ።


የዱባ ፍሬ


በሀገራችን ዱባን በተለያየ መልኩ አዘጋጅቶ የመመገብ የቆየ ልምድ ቢኖረንም ፍሬውን ለምግብነት ስናውለው ግን አይታይም። እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች በተለየ ምክንያት ሲጠቀሙት ብንመለከትም ስራዬ ብሎ እና እንደ ምግብ ቆጥሮ የሚጠቀመው ብዙ ሰው አይታይም። ነገር ግን የዱባ ፍሬ ከውጭኛው የዱባው ክፍል የበለጠ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው ጥናቶች ያመለክታሉ። የዱባ ፍሬ ጥሩ የሆነ የፎስፈረስ ማዕድን፣ የሞኖ አንስቹሬትድ ሰብ እንዲሁም የኦሜጋ 6 ስብ ምንጭ ነው። በተጨማሪም በዱባ ፍሬ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፓይቶስቴሮል የተባለ እና በደም ውስጥ የሚገኘውን ኮሌስትሮል ለመቀነስ የሚያግዝ ንጥረ ነገር ይገኛል።


የዱባ ፍሬ በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገሮች በህፃናት ሽንት ውስጥ የሚገኘው የካልሲየም መጠን እንዲቀንስ ያግዛል። ይሄን በማድረጉ ደግሞ የሚፈጠረውን የጣፊያ ጠጠር ለመከላከል ያግዛል። የጣፊያ ጠጠር የሚፈጠረው እንደ ካልሲየም ያሉ የተወሰኑ ማዕድናት በጣፊያ ውስጥ ተከማችተው ጠጣር ነገር በሚፈጥሩበት ጊዜ ነው። እነዚህ ጠጠሮች ልክ የኩላሊት ጠጠር አይነቶች ሲሆኑ፤ በሆድ አካባቢ ምቾት ይነሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘም በሽንት ፊኛ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን እና ከሽንት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችግሮች ለመከላከል የዱባ ፍሬ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በተጨማሪም በዱባ ፍሬ ውስጥ የሚገኙት ማእድናት ጣፊያ የተመጣጠነ እንቅስቃሴ እንዲኖረው በማድረግ መጠኑ ትልቅ የሆነ የሽንት ፊኛ ያላቸው ሰዎች እንዳይቸገሩ የማድረግ ጠቀሜታ አለው።


ሌላው የዱባ ፍሬ ጠቀሜታ ደግሞ ሴቶች የወር አበባ ማየት ሲያቆሙ (ሲያርጡ) የሚፈጠሩ ችግሮችን ማስታገስ ነው። ይኸውም በዚህ ጊዜ የሚከሰቱ እንደ ከፍተኛ የደም ግፊትን የማስተካከል፣ ጥሩ የሆነ ኮሌስትሮል High Density lipoprotein (HDL) መጠንን በመጨመር ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎችን ለመከላከል ያግዛል።


የሱፍ ፍሬ


የሱፍ ፍሬ ጥሩ የሆነ የፕሮቲን፣ ሞኖአንሳቹሬት ስብ እንዲሁም ቫይታሚን ኢ ምንጭ ነው። የሱፍ ፍሬ ብዙውን ጊዜ በሰውነት ላይ የሚከሰቱ መቆጣቶችን (inflammation) ከመከላከል ጋር በተያያዘ ባለው ጠቀሜታ ተጠቃሽ ነው። በተለይ በመካከለኛ እድሜ እና በእርጅና እድሜ ላይ ባሉ ሰዎች ላይ የሚከሰተውን መቆጣት (inflammation) የመከላከል ጠቀሜታው የጎላ ነው። በዚህም ከሰውነት መቆጣት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የልብ ህመም እና ተያያዥ ችግሮችን ለማሰወገድ ያግዛል። በስድስት ሺህ ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተውም በአንድ ሳምንት ውስጥ አምስት ጊዜ ያህል የሱፍ ፍሬን የሚመገብ ሰው ሲክሬቲቨ የተባለው እና የሰውነት መቆጣትን የሚከላከል ንጥረ ነገርን በብዛት ስለሚያገኝ ከሰውነት መቆጣት ችግር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ህመሞች በከፍተኛ ደረጃ መከላከል ችሏል።


የሱፍ አበባ ከዚህ በተጨማሪም ፎሌት በተባለው ንጥረ ነገር የበለፀገ በመሆኑ በተለይ ለሴቶች እጅግ ጠቃሚ ነው። በዚህም በሴቶች ላይ በወር አበባ ጋር የተያያዙ ህመሞችን ለመከላከል ይጠቅማል የሚሉት ባለሞያው፣ በተጨማሪም በሱፍ ፍሬ ውስጥ የሚገኙት ከፍተኛ መጠን ያላቸው ጤናማ ስቦች፣ አንቲኮክሲዳንቶች፣ ቫይታኖች እንዲሁም የሴሌኒየም እና ኮፐር ማእድናት በሰውነት ውስጥ የሚከሰተውን የሴሎች መሞት የመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስቀምጠዋል። በሱፍ ፍሬ ውስጥ በብዛት የሚገኘው ፓይቶ ኬሚካለስ የምግብ ልመት ጤናማ እንዲሆን በማድረግ፣ ሰውነታችን በቂ የሆነ የአሰር መጠን እንዲያገኝ በማድረግ ያልተፈለገ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስም ያግዛል።


የሰሊጥ ፍሬ


ሰሊጥ ከጥንት ጀምሮ ለምግብነት በብዛት የሚውል የጥራጥሬ ዝርያ ነው። ይህ ዝርያ ደግሞ ከምግብነት ይልቅ ባለው የጤና ጠቀሜታ ይታወቃል። ሰሊጥ ከፍተኛ የሆነ የካልሲየም፣ ማግኒዚየም፣ ዚንክ እንዲሁም ብረት እና ፎስፈረስ ማእድናት ክምችት ያለበት ነው። የሰሊጥ ፍሬ በአፈጣጠሩ እና በያዛቸው በርካታ ንጥረ ነገሮች ከሌሎች የተለየ ዘር ነው። በሰሊጥ ውስጥ የሚገኙት ቫይታን ቢ1 እና ፀረ-ኮሌስትሮል ኬሚካሎችም ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊትን ለመከላከል፣ የጉበትን ጤንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ጭንቀትን ለመከላከል፣ የሰውነት ኢንፍላሜሽንን ለመቀነስ እና በአጥንት ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስቀረት ያግዛል። በተጨማሪም በጡንቻ ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ የሰሊጥ ፍሬ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
516 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 71 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us