ቅመም ከማጣፈጫም በላይ ነው

Friday, 12 January 2018 16:59

 

 

እንዲህ እንዳሁኑ የበዓላት ሰሞን ሲሆን አብዛኞቻችን የምንመገባቸው ምግቦች ቅባታቸው እና የቅመም መጠናቸው ከአዘቦቱ ጊዜ በርከት ያለ ይሆናል። ቅባታማ እና ቅመም የበዛባቸው ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ ለብዙዎቻችን የምግባችንን ጣዕም ለማሳመር የምንፈልገው ቢሆንም የሚያስከትልብን የጤና ስጋትም ያንኑ ያህል ነው። የጤና ባለሙያዎችም በየጊዜው የሚመክሩን እንዲህ አይነት ምግቦችን መጠቀም እንደሌለብን ነው። በተለይ ስር የሰደዱ የበሽታ አይነቶች ተጠቂ የሆኑ እና በተለየ ሁኔታ በሀኪም የተከለከሉ ሰዎች ከእነዚህ ምግቦች አበክረው እንዲርቁ ይታዘዛሉ። በተቃራኒው ደግሞ በጉዳዩ ላይ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ አካላት በተለይ ቅመም እና ተፈጥሯዊ ማጣፈጫዎችን በምግባችን ውስጥ በማካተት በርካታ ጥቅሞችን ማግኘት እንደምንችል አስቀምጠዋል። እኛም በዚህ በበዓል ሰሞን ላይ ሆነን ባለሞያዎች ስለጉዳዩ ያስቀመጧቸውን መረጃዎች እንዲህ አቅርበናቸዋል።


ሲኤን ኤን ባለፈው የፈረንጆች ወር በሰራው ዘገባ ቅመም ያላቸው ምግቦችን መመገብ በምግባችን ውስጥ የምናካትተውን የጨው እና የስኳር መጠን ለመቀነስ ያግዛል ብሏል። በቻይና ዩኒቨርስቲ ከ600 በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የተደረገውን ጥናት ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንዳመለከተውም ቅመማ ቅመሞች በውስጣቸው የሚይዟቸው ንጥረ ነገሮች፣ ምግቦች የተለየ ጣዕም እንዲኖራቸው በማድረግ ጨው እና ስኳርን ከምግባችን ውስጥ እንድንቀንስ ያግዙናል። በቻይና ሰርደ ሚሊታሪ ህክምና ዩኒቨርስቲ የደም ግፊት እና የልብ ህክምና ፕሮፌሰር እና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ዢሚንግ ዡ እንደገለፁት ቅመም ያላቸውን ምግቦች ስንመገብ አንጎላችን ውስጥ የሚፈጠረው ስሜት ልክ ጨውን ስንመገብ የሚሰማው አይነት ስሜት ስለሆነ፤ የጨው መጠን አነስተኛ ቢሆን እንኳን ጨው የማነሱን ስሜት መለየት አይቻልም። በጥናቱ ማረጋገጥ የተቻለውም ቅመማ ቅመም የገባባቸውን ምግቦች አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች በቀን ውስጥ ከሚወስዱት ጨው መጠን በ2 ነጥብ አምስት ግራም ያነሰ መውሰድ መቻላቸውን ነው። የሚመገቡትን የጨው መጠን በመቀነሳቸውም ያላቸው የደም ግፊት አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በተመሳሳይ የማቃጠል ስሜቱ በምግብ ውስጥ ጣፋጭ ነገር በብዛት እንዳንጠቀም ያግዛል ይላል ጥናቱ። ይሄ ስሜት ለምግቡ የሚሰጠው ጣዕም ጣፋጩን ስለሚተካ የስኳር መጠንን ለመቀነስም ያግዛል። ጠቅለል ሲደርግም ከእነዚህ ቅመማ ቅመሞች የምናገኛቸው ጠቀሜታዎች የሚከተሉት ናቸው።


1. የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ
እንደ ቃሪያ ያሉ የማቃጥል ስሜት የሚሰጡ ቅመማ ቅመሞች የገቡበትን ምግብ ስንመገብ የሰውነታችን ሙቀት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርገዋል። የሰውነት ሙቀት መጠን ከፍ ማለት ደግሞ ሰውነታችን ምግብን ወደ ሃይል የሚቀይርበት ስርዓት (metabolism) ፍጥነት እንዲጨምር ያደርገዋል ይላል ከፐርዴ ዩኒቨርስቲ የተገኘ መረጃ። እንደመረጃው ከሆነ እነዚህ የማቃጠል ስሜት የሚፈጥሩ ቅመማ ቅመሞች የሜታቦሊዝም ፍጥነቱን እስከ አምስት በመቶ እንዲሁም የሰውነትን ስብ የማቃጠል ፍጥነት እስከ 16 በመቶ የመጨመር ባህሪይ አላቸው። በዩኒቨርስቲው የስነ ምግብ ተመራማሪዋ ዶክተር ፓሜላ ፔኬ እንዳሉትም ይህ የማቃጠል ስሜት የሚፈጥር ቅመም የሜታቦሊዝም ስርዓቱን ለማሳለጥ የሚያግዘው ቡናማ ስብ በብዛት እንዲመነጭ የማድረግ ጠቀሜታም አለው። በመሆኑም እነዚህን የስርዓት መፋጠኖች በመፍጠር የሰውነታችን ክብደት በቀላሉ እና በፍጥነት ለመቀነስ ያግዛል።


2. የልብ ህመም ይከላከላል
በሜሪላንድ ህክምና ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ሚሼል ሚለር እንደሚሉት ደግሞ እነዚህ ቅመሞች የልብ ህመምን የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። በተለይ ቃሪያ፣ ሚጥሚጣ እና እርድ ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄደው የደም ዝውውር ጤናማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በእነዚህ ቅመሞች ውስጥ የሚገኘው ካፕሴሲን የተባለ ንጥረ ነገር የደም ስሮች እንዲሰፋ በማድረግ ለደም ዝውውሩ የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርገዋል። በተጨማሪም በእርድ ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር የሰውነት መቆጣትን የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ የደም ሴሎች በቀላሉ እንዳይሞቱ እና እንዳይጎዱ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በተጨማሪም መጥፎ የሆነ ኮሌስትሮል በሰውነት ውስጥ እንዳይከማች የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በዚህ ምክንያትም ከደም ዝውውር ጋር ተያይዞ የሚከሰት የልብ ህመምን ለመከላከል ያላቸው ጠቀሜታ ቀላል የሚባል አይደለም ይላል ጥናቱ።


3. ካንሰርን ይከላከላል
በእርድ ውስጥ የሚገኘው ኮርኩሚን የተባለ ንጥረ ነገር የካንሰር ህዋሳት እንዳያድጉ እና እንዳይባዙ የማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ዶክተር ፒኬ የገለፁት። ይህ ንጥረ ነገር ከመጀመሪያው ጀምሮ ከተመገቡት ለካንሰር ህመም የሚያጋልጡ የካንሰር ህዋሳት እንዳይፈጠሩ የማድረግ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፤ ከተፈጠረ በኋላም እድገታቸውን ለመግታት ያገለግላል። በሎስ አንጀለስ በአይጦች ላይ በተደረገ ጥናት 80 በመቶ የሽንት ፊኛ ካንሰር ህዋሳትን እንደገደለም ተረጋግጧል። በአጠቃላይም በእነዚህ በቃሪያ እና በእርድ ውስጥ የሚገኘው ካፕሲይሲን የተባለ ንጥረ ነገር የጡት ካንሰር፣ የማህጸን ጫፍ ካንሰር እና የሆድ ካንሰርን የመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል።


4. ህመምን ለማስታገስ
ከአጥንት እና በጡንቻ ጋር የተያያዙ ህመሞችን እንዲሁም ራስ ምታትን ለማስታገስ ከሚያገለግሉ ተፈጥሯዊ ነገሮች መካከል ቅመሞች ተጠቃሽ ናቸው። ጥናቶች እንዳመለከቱት ከላይ የተጠቀሱት አይነት ስሜቶች በሚሰሙበት ወቅት በቦታው ላይ በእነዚህ ቅመሞች በመያዝ ህመሙን ማስታገስ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ቅመማ ቅመሞች የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም እንዲጨምር የማድረግ ጠቀሜታ ስላላቸው በሽታን በቀላሉ ለመቋቋም እና ረጅም እድሜን ለመኖርም ያግዛሉ።
የቅመማ ቅመም ጣዕምን ለመልመድ በተለይ ጀማሪ ለሆነ ሰው አስቸጋሪ መሆኑን የገለፁት ባለሞያዎች፣ ቀስ በቀስ በየእለት ምግብ ውስጥ በማካተት ሰውነት እንዲለምዳቸው ማድረግን ይመክራሉ። በተጨማሪም በተለየ ሁኔታ ቅመማ ቅመሞችን እንዳይመገቡ የተከለከሉ ሰዎች እነዚህን ቅመሞች ከመጠቀማቸው በፊት የህክምና ባለሞያዎችን ማማከር እንዳለባቸው ነው ባሞያዎች ደጋግመው የሚያሳስቡት። ከላይ የተጠቀሱትን ጠቀሜታዎች ልናገኝባቸው እንችላለን የተባሉት የቅመማ ቅመም ዝርያዎችም ቀይ ቃሪያ፣ እርድ፣ ቅርንፉድ፣ ዝንጅብል፣ ነጭ ሽንኩርት እንዲሁም ናና ቅጠል ናቸው።


5. የደም ግፊትን ያስተካክላል
ቫይታሚን ሲ እና ቫይታሚን ዲ በተፈጥሯቸው የልብ ግድግዳ ጡንቻዎችን የማጠንከር ጠቀሜታ አላቸው። እነዚህ ቅመማ ቅመሞች ደግሞ በአብዛኛው እነዚህን የቫይታሚን አይነቶች የያዙ ናቸው። በመሆኑም የልብ ግድግዳ ጡንቻዎች ጠንካራ እና ጤናማ መሆን በሰውነታችን ውስጥ የሚዘዋወረው ደም ስርዓቱ የተስተካከለ እንዲሆን ስለሚያደርገው ያልተፈለገ የደም ግፊት መጠን እንዳይፈጠር ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም በሰውነታችን ውስጥ ጥሩ ስሜት የሚፈጥሩ ሆሞኖች በብዛት እንዲመነጩ በማድረግ ጥሩ እና ዘና የሚያደርግ ስሜት እንዲሰማን ያግዛል።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
438 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 73 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us