የፀሐይ ገፀ በረከቶች

Wednesday, 07 February 2018 13:14

 

ሰውነታችን ከመጠን በላይ ለሆነ ፀሐይ ብርሃን በሚጋለጥበት ወቅት ከቆዳችን ጀምሮ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ ጉዳት ይደርሳል። ነገር ግን ተመጣጣኝ እና በቂ የሆነ የፀሐይ ብርሃንን ማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታዎች አሉት። ብዙዎቻችን የፀሐይ ብርሃን ከሚፈጥርብን የሙቀት፣ የወበቅ እና ሌሎች ስሜቶች የተነሳ ፀሐይን የመፍራት እና የመሸሽ ልምድ አለን። ፀሐይ መሞቅንም ስራ እንደመፍታት እንቆጥረዋለን። ነገር ግን ለሰውነታችን በቂ የሆነ የፀሐይ ብርሃን ማግኘት መገመት ከምንችለው በላይ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ባለሞያዎች ይናገራሉ። የዓለም ጤና ድርጅት እና ታዋቂው ማዩ ክሊኒክም የፀሐይ ብርሃን ለሰው ልጆች ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት መረጃዎችን አስፍረዋል። በዛሬው ፅሑፋችንም በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች የያዟቸውን መረጃ ልናካፍላችሁ ነው።


የፀሐይ ብርሃን እና ጨለማ የቀናት መለዋወጥን ከማብሰራቸው በተጨማሪ አንጎላችን ሆርሞን የሚያመነጭበትን ሁኔታ የማመቻቸት ጠቀሜታ አለው። ሰውነታችን ተመጣጣኝ በሆነ ደረጃ ለፀሐይ ብርሃን ሚጋለጥበት ወቅት አንጎላችን ሴሮቶኒን የተባለውን ሆርሞን የሚያመነጭበት ፍጥነት እንዲጨምር ያደርገዋል። ይህ ሆርሞን ደግሞ የሰው ልጅ ስሜት የተረጋጋ፣ የተስተካከለ እና ትኩረቱ የተሰበሰበ እንዲሆን ያግዘዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነታችን ለጨለማ በሚጋለጥበት ወቅት አንጎላችን ሜላቶኒን የተባለውን ሆርሞን የሚያመነጭበት ፍጥነት እንዲጨምር ያግዘዋል። ይሄ ሜላቶኒን የተባለው ሆርሞን ደግሞ ሰውነታችን የእንቅልፍ ስሜት እንዲሰማው እና በተረጋጋ ሁኔታ እንቅልፍ እንዲወስደን የማድረግ ጠቀሜታ አለው።


በተቃራኒው ስንመለከተው ደግሞ አንድ ሰው በቂ የሆነ የፀሐይ ብርሃን ማግኘት ካልቻለ አንጎሉ የሚያመርተው የሴሮቶኒን ሆርሞን መጠኑ እንዲቀንስ ያደርገዋል። በዚህ ሆርሞን መጠን መቀነስም የሜላቶኒን ሆርሞን መጠኑ እንዲያሻቅብ ያደርገዋል። በዚህ ጊዜም የወቅት መቀያየርን ተከትሎ ለሚከሰት ችግር (seasonal affective disorder) ያጋልጣል። እንዲህ አይነቱን ችግር ማከም የሚቻለውም ፎቶቴራፒ በተባለ እና አንጎል የሴሮቶኒን ሆርሞን ማመንጨት ሂደቱን እንዲያፈጥን እግረመንገዱም ሜላቶኒን ሆርሞን መጠኑ እንዲቀንስ በሚያደርግ ህክምና ነው። የሳይካትሪ እና ኒውሮሳይንስ ጆርናል መረጃ እንደሚያመለክተውም የተመጣጠነ የፀሐይ ብርሃን ከወር አበባ ቀደም ብሎ የሚከሰት ድብርትን ለማስቀረት፣ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰትን ድባቴ ለማስታገስ እንዲሁም ከብስጭት እና ከንዴት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ስሜቶችን ለመከላከል ያግዛል። በተጨማሪም አንጎል ነገሮችን ለማቀናጀት እና ለማስታወስ የሚያግዘው ነርቭ እንዲያድግ ያደርጋል ይላሉ የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ኒውሮ ሳይንቲስቱ ዴቪድ ሊዌሊን።


የሰው ልጅ አጥንት በተለይ በለጋ እድሜ በቂ የሆነ ቫይታን ዲን ማግኘት ካልቻለ በአጥንቱ ላይ የአጥንት መሳሳት፣ የአጥንት መበላት እንዲሁም የአጥንት መጣመምን ያስከትላል። ቫይታሚን ዲን በብዛት ከምናገኝባቸው ነገሮች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ የፀሐይ ብርሃን ነው። ሰውነታችን አልትራቫዮሌት ቢ ለተባለው የፀሐይ ጨረር በሚጋለጥበት ወቅት ቆዳችን ቫይታን ዲን እንዲፈጥር ያደርገዋል። ይሄ ቫይታን በሰውነታችን ውስጥ በበቂ ሁኔታ መመረት መቻሉም ብላይ የተጠቀሱትን በአጥንት ላይ የሚከሰቱ ጉዳቶች በመከላከል ረገድ አቻ አይገኝለትም። የአለም ጤና ድርጅት እንደሚመክረውም በሳምንት ውስጥ ከአምስት እስከ 15 ደቂቃ ያህል እጅን፣ ክንድን እና ፊትን ያለምንም መከለያ ለፀሐይ ማጋለጥ በቂ የሆነ ቫይታን ዲን ለማግኘት ያግዛል።


የፀሐይ ብርሐን ከካንሰር ህመም ጋርም በሁለት መልኩ ተያያዥነት አለው። ከሚፈልገው መጠን በላይ ለፀሐይ ጨረር መጋለጥ ለቆዳ ካንሰር ያለውን ተጋላጭነት እንደሚጨምረው መረጃዎች ያመለክታል። በተቃራኒው ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነ የፀሐይ ብርሃንን ማግኘት የካንሰር ህመምን ለመከላከል ያገለግላል። ከአካባቢ አየር ጋር በተያያዘ የተደረጉ ጥናቶች እንዲሚያመለክቱትም በአለማችን ላይ የቀኑ ርዝመት አጭር በሆነ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የቀኑ ርዝመት ረጅም በሆነ አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ ለበርካታ የካንሰር አይነቶች የመጋጥ እድላቸው ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎችን የበለጠ ያጠቃሉ የተባሉት የካንሰር አይነቶችም የማህጸን ካንሰር፣ የፕሮስቴት ካንሰር፣ የጣፊያ ካንሰር እንዲሁም የትልቁ አንጀት ካንሰር ናቸው።


የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚገልፀው የፀሐይ ብርሃን በትክክል ለሚያስፈልገው ሰው በአስፈላጊው መጠን ከተሞቀ በርካታ የጤና እክሎችን ለማከም ያግዛል። የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ከምናገኛቸው የጤና ፈውሶች መካከል በአጥንት እና በመገጣጠሚያ ላይ የሚደርሱ ህመሞች፣ ሪህን፣ የታይሮይድ ችግር እንዲሁም በአንጀት እና መሰል የሰውነተ ክፍሎች ላይ የሚደርስ መቆጣትን ለመከላከል ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም በቆዳ ላይ የሚከሰቱ እንደ ብጉር፣ የሚያሳክክ የቆዳ በሽታ እንዲሁም የወፍ በሽታ የሚባለውን በሽታ ለማከም ባለሞያዎች እንደ አስፈላጊነቱ ከሚያዟቸው ህክምናዎች መካከል አንዱ ተመጣጣኝ የሆነ የፀሐይ ብርሃን ነው።


በኤደንበርግ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነ የፀሐይ ብርሃን ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊትን ለመከላከል ያግዛል። የሰው ልጅ ቆዳ ላይ የፀሐይ ብርሃን በሚያርፍበት ወቅት ናይትሪክ ኦክሳይድ የተባለ ውህድ ወደ ደም ስሮቻችን ይገባል። ይህ ውህድም በሰውነታችን ውስጥ የሚኖረው የደም ዝውውር የተረጋጋ እንዲሆን እንዲሁም የደም ግፊቱም የተስተካከለ እንዲሆን ያግዛል ይላሉ በዩኒቨርስቲው መምህር እና ደርማቶሎጂው ዶክተር ሪቻርድ ዌለር። ባለሞያው እንደገለፁትም የፀሐይ ብርሃን ከዚህ በተጨማሪም ለልብ ድካም፣ በስትሮክ እና ለተያያዥ ችግሮች ያለውን ተጋላጭነት የመቀነስ ጠቀሜታ አለው።


ተመጣጣኝ ከሆነ የፀሐይ ብርሀን በተለይ የአልዛይመርስ ህመም ላለባቸው ሰዎች ከህመሙ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን በማስወገድ ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የአሜሪካ ህክምና ማህበር መረጃ ይገልጻል። እንደመረጃው ለፀሐይ ብርሃን የመጋለጥ እድልን ያገኙ የአልዛይመርስ ህመም ተጠቂዎች የፀሐይ ብርሀን ከማያገኙት በተሻለ መልኩ ለድብርት፣ ለቅዠት እንዲሁም ለመባነን እና ሌሊት ላይ በሚኖር የስሜት መረበሽ ያላቸው ተጋላጭነት በእጅጉ ቀንሶ ተገኝቷል።


ከፀሐይ ብርሃን የምናገኘው ሌላው ጠቀሜታ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም መጠናከር ነው። ሰውነታችን ለፀሐይ ብርሃን በሚጋለጥበት ወቅት የሚያመነጨው የነጭ ደም ሴሎች መጠን እንዲጨምር ያግዘዋል። እነዚህ የነጭ ደም ሴሎች ዋናው አገልግሎታቸው በሽታን የመከላከል እንዲሁም ሰውነት የተለያዩ መመረዞችን እና መቆጣቶችን መቋቋም እንዲቻል ማገዝ ነው። በመሆኑም በቂ የሆነ የፀሐይ ብርሃን ማግኘት ሰውነት እንዚህን የደም ሴሎች በብዛት በማመንጨት በሽታን የመከላከል አቅሙን እንዲያዳብር ያግዘዋል።


አንድ ሰው ለፀሐይ ብርሃን ለምን ያህል ጊዜ ቢጋለጥ ከላይ የተጠቀሱትን ጠቀሜታዎች ሊያገኝ ይችላል? የሚለው ጥያቄ እንደየሰው ሁኔታ የተለያየ መሆኑን ነው ባለሞያዎች የሚገልፁት። ከመጠን ላለፈ የፀሐይ ብርሃን መጋጥ ጨረሩ የሴል ዘረመሎችን በመጉዳት ለካንሰር እንድንጋለጥ ሊያደርገን ይችላል። በመሆኑም በአለም ጤና ድርጅት ሆነ በሌሎች በጉዳዩ ላይ በሚሰሩ ተቋማት እንደተገለፀው ለሰው ልጅ ተመጣጣኝ ነው ተብሎ የተቀመጠው የፀሐይ ብርሃን ተጋላጭነት በአንድ ቀን ውስጥ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ነው። ከዚህ ጊዜ በላይ ለፀሐይ ብርሃን ለመጋለጥ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ካሉ ግን የተለያዩ የፀሐይ ጨረርን ሊከላከሉ የሚችሉ መከለያዎችን መጠቀምን ይመክራሉ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
460 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 222 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us