የአልኮል ጉዳት ከእፆችም ይብሳል

Wednesday, 14 February 2018 11:57

 

የአልኮል የጤና ጠንቅነት በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል። ከሰሞኑ ደግሞ አንድ ጥናት እንዳመለከተው አልኮልን መጠጣት በአንጎል ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከአንዳንድ እፆች የበለጠ መሆኑን አመልክቷል። በኮሎራዶ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት ይፋ እንዳደረገውም አልኮል በሰው ልጅ አንጎል ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ማሪዋና እና ካናቢስ የተባሉ እፆች ከሚያደርሱት የባሰ ነው ይላል።


በተደረገው ጥናት ማረጋገጥ የተቻለውም አልኮል የሚጠጡ ሰዎች በረጅም ጊዜ ውስጥ በአንጎላቸው ውስጥ የሚገኙ ዋይት ማተር እና ግሬይ ማተር የተባሉ ክፍሎችን መዋቅር የማዛባት ጉዳት ያደርሳል። የጥናቱ መሪ የሆኑት እና በዩኒቨርስቲው የስነልቦና እና ኒውሮሳይንስ ትምህርት ክፍል ባልደረባዋ ዶክተር ራሄል ታየር እንደገለፁትም አልኮልን የሚጠቀሙ ሰዎች እነዚህን እፆች ከሚጠቀሙት በባሰ መልኩ በአንጎላቸው የተለያዩ ክፍሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ ነው።


ባለሞያዋ እንደገለፁት ግሬይ ማተር የተባለው የአንጎል ክፍል በአንጎል የላይኛው ክፍል ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በአብዛኛውም የነርቭ ህዋሳትን የሚይዝ አካል ነው። ዋይት ማተር የሚባለው ደግሞ ወደ ውስጠኛው የአንጎል ክፍል ውስጥ የሚገኝ እና ለሌላው የሰውነት ክፍሎች የኤሌክትሮኒክ መልዕክት የሚያስተላልፉ የነርቮች ስሮች የበቀሉበት የአንጎል ክፍል ነው። በመሆኑም እነዚህ ሁለት የአንጎል ክፍሎች በአልኮል ምክንያት መጠናቸው እየቀነሰ ሲመጣ አንጎል የተቀናጀ ተግባር ለማከናወን ስለሚሳነው በየእለቱ በሚያከናውናቸው ተግባራቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራል ብለዋል ባለሞያዋ።


በጥናቱ እንደተረጋገጠውም በተለይ ለረጅም ዓመታት የአልኮል መጠጥን የጠጡ ሰዎች በአንጎላቸው ውስጥ የሚገኙት የእነዚህ የግሬይ እና የዋይት ማተር መጠን በጣም ቀንሶ ተገኝቷል። የእነዚህ የግሬይ እና ዋይት ማተር መጠን መቀነስ እንደማሪዋና ያሉ እፆችን ከሚጠቀሙ ሰዎች በበለጠ በእነዚህ የአልኮል መጠጥ ተጠቃሚዎች ላይ የከፋ ሆኖ ተገኝቷል።


በአልኮል ላይ የተደረገ ሌላ ጥናት እንዳለከተው ደግሞ ከመጠን በላይ የሆነ አልኮልን መጠጣት ለአንጎል መመረዝ ይዳርጋል። በኒውዮርክ ሮችስተር ህክምና ማዕከል የተደረገ ጥናት እንዳለመከተው የአልኮል መጠጥን ለረጅም ጊዜ የሚጠጡ ሰዎች ለአንጎል መመረዝ (inflammation) ያላቸው ተጋላጭነት ከማይጠጡት የበለጠ ሆኖ ተገኝቷል። በዩኒቨርስቲው የተደረገ ጥናት እንዳመለከተውም በዚህ በረጅም ጊዜ የአልኮል ተጠቃሚነት ምክንያት ከሚደርሱ ጉዳቶች መካከል አንጎል ነገሮችን ለማገናዘብ፣ ለማስታወስ እንዲሁም የተረጋጋ እና የተቀናጀ ተግባርን ለማከናወን እንዲቸገር ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በተጨማሪም በነገሮች ግራ መጋባት እና ውሳኔ ለመስጠት መቸገርም በአልኮል ተጠቃሚዎች ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው። በአጠቃላይ ሲታይም አልኮል የአንጎልን የማገናዘብ እና የማመዛዘን ችሎታ የመቀነስ እና የማዳከም ችግሮችን ያስከትላል።


የማሪዋና እፅን በተመለከተ የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት በተለይ ይሄንን እፅ የሚጠቀሙ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ከባድ ለሆነ የአስተሳሰብ እና አመለካከት መዛባት የሚዳረጉ ከመሆናቸውም በላይ ለልብ ህመም እና ሌሎች ተያያዥ ለሆኑ ውስብስብ የጤና እክሎች ተጋላጮች ናቸው። በዚህ ረገደም በማሪዋና ሳቢያ የሚደርሰው የጤና ችግር ሲጋራን በማጨስ ከሚደርሰው ችግር የላቀ ነው።


የአልኮል መጠጥም ሆነ እንደ ማሪዋና ያሉ እፆች የጤና ጠንቅ ተብለው በአለም ጤና ድርጅት ከተዘረዘሩ ቀዳሚ ነገሮች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው። የአለም ጤና ድርጅት እንደሚገልፀውም አልኮልን በመጠጣት ብቻ አንድ ሰው ከ200 በላይ ለሆኑ የጤና እክሎች ሊዳረግ ይችላል። በአሁኑ ወቅት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የአለማችን ሰዎችን የአልኮል መጠጥን የሚጠጡ ሲሆን፤ በየዓመቱም 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከአልኮል መጠጥ ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ ችግሮች ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።


በመስኩ ጥናት ያካሄዱ ባለሞያዎች የአልኮል መጠጥ ከ60 በላይ ለሆኑ የጤና እክሎች እንደሚያጋልጥ ያስቀምጣሉ። በሰሜን ካሮላይና ዩኒቨርስቲ ቻፕል ሂል የህክምና ትምህርት ቤት የተደረገ ጥናት እንዳስቀመጠውም ከእነዚህ የጤና እክሎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።


ከመጠን ያለፈ አልኮልን መጠቀም በሰውነት ውስጥ ኦክሲጅን ተሸካሚ ቀይ የደም ህዋሳት መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ለደም ማነስ ያጋልጣል። በተያያዘም አልኮል የደም ፕላትሌቶች እርስ በርሳቸው በመጣበት ደም በቀላሉ እንዲረጋ ስለሚያደርግ እንደ ስትሮክ እና ድንገተኛ የልብ ህመም ለመሳሰሉት ችግሮች ያጋልጣል። በተጨማሪም በሰውነት ውስጥ የሚኖረው የደም ዝውውር ጤናማ ስለማይሆን ለከፍተኛ የደም ግፊት የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።


አልኮል በባህሪም የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ለተለያዩ የመመረዝ በሽታዎች ያለውን ተጋላጭነት ይጨምረዋል። በመሆኑም አልኮልን አብዝተው የሚጠቀሙ ሰዎች ለሳንባ ምች፣ ለሳንባ በሽታ እንዲሁም ለሌሎች የኢንፌክሽን በሽታዎች ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው።


ሌላው ከዚህ ከአልኮል ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የጤና እክል በአንጎል ጤና ላይ የሚከሰቱ ተያያዥ ችግሮች ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዱ የአእምሮ መሳት (dementia) ነው። የሰው ልጅ እድሜው እየጨመረ ሲሄድ የአንጎሉ መጠን በአስር ዓመት ውስጥ 1 ነጥብ 9 በመቶ እየቀነሰ የሚሄድ ሲሆን፤ የአልኮል መጠጥ ሲጨመርበት ከዚህ በበለጠ ፍጥነት እየቀነሰ ይሄዳል። በመሆኑም በተለይ ለማስታወስ የሚያግዘው የአንጎል ክፍል በፍጥነት እንዲጎዳ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም የአልኮል መጠጥ ለሚጥል በሽታ የማጋጥ እንዲሁም በሽታውን የማባባስ ጉዳትን ያደርሳል።


በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ ጥናት እንዳመለከተው እጅግ በጣም ጥቂት መጠን ያለውን አልኮል መጠጣት በአንጎል ውስጥ የሚኖሩትን የማያስፈልጉ እና መርዛማ ነገሮች ለማስወገድ ያግዛል። የጥናቱ መሪ የሆኑት ዶክተር ማይክን ኔደርጋርድ እንደገለፁትም በቀን በጣም ጥቂት መጠን ያለውን አልኮል መጠጣት በአንጎል የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ተከማችተው የሚገኙ ነገሮችን ለማጠብ (ለማስወገድ) ስለሚያግዝ አንጎል ከመርዛማ እና ጥቅም ከማይሰጡ ነገሮች የፀዳ በመሆን ተግባራቱን ለማከናወን ያግዘዋል። በዚህ መልኩ ከአንጎል ሊወጡ የሚችሉት እንደ ቤታ አሚሎይድ እና ታይ ፕሮቲንስን የተባሉ ነገሮች ሲሆኑ፤ እነዚህ የአንጎል ተረፈ ምርቶች ከአንጎል መወገዳቸው ደግሞ እንደ አልዛይመርስ ላሉ ችግሮች የመጋለጥ እድላችን እንዲቀንስ ያግዛል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
541 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 220 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us