የሴቶች ጤናን ያስቀደመው “ምቹ” ክሊኒክ

Wednesday, 21 February 2018 11:47

 

የጤናማ እናቶች ወር በቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በስፋት ሲከበር ቆይቶ ባለፈው ጥር 29 ቀን 2010 በድምቀት ተጠናቋል። ኮሌጁ በተለይ የእናቶች ጤናን በተመለከተ እየሰጠ ያለው አገልግሎት በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የጤና ተቋማት ሁሉ ቀዳሚው ያደርገዋል። የጤናማ እናቶች ወርን አስመልክቶ በኮሌጁ የማህፀንና ፅንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊው ዶክተር ታደሰ ኡርጌ፣ የኮሌጅ ህክምና ዘርፍ አገልግሎት ምክትል ፕሮቨስት ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ እንዲሁም ሲስተር ፍቅርተ እሸቴ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።


በኮሌጁ በየወሩ ለአንድ ሺህ ያህል ነፍሰ ጡር ሴቶች የወሊድ አገልግሎት ይሰጣል። ከእነዚህ አገልግሎቱን ከሚያገኙ እናቶች መካከልም በኦፕሬሽን (በቀዶ ህክምና) የሚወልዱት ሴቶች ከ35 በመቶ በላይ ናቸው። ዶክተር ብርሃኔ እንደሚገልጹትም ይህ አሃዝ የአለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት የሚሰጠው አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን የሚጠቁም ነው። (የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው መስፈርቱም ጤናማ የሆነ እና ጥራቱን የጠበቀ የወሊድ አገልግሎት ተሰጥቷል የሚባለው የወሊድ አገልግሎቱን ካገኙት ሴቶች መካከል ከ30 እስከ 35 በመቶዎቹ በቀዶ ህክምና ሲወለዱ ነው።)


ኮሌጁ ለእናቶች አስፈላጊውን የስነ ተዋልዶ እና ሌሎች አገልግሎቶች ለመስጠት ያግዘው ዘንድ ራሱን የቻለ ምቹ የተባለ ክሊኒክ አቋቁሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ክሊኒኩ ከተቋቋመ ሁለት አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ ክሊኒክም በርካታ ሴቶች እና እናቶች አገልግሎቱን በማግኘት ላይ ይገኛሉ። በክሊኒኩ አምስት አብይ አገልግሎቶ እንደሚሰጡ ነው ሲስተር ፍቅርተ የሚናገሩት። ከአገልግሎቶቹ መካከልም ዋና ዋናዎቹ የቤተሰብ እቅድና የምክክር አገልግሎት፣ የአፍላ ወጣቶች የስነ ተዋልዶ አገልግሎት፣ ሁሉን አቀፍ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት (እስከ 28 ሳምንታት ያለ ጽንስ ማቋረጥን ጨምሮ)፣ የተለያዩ የእግርዝና መከላከያዎችን መስጠት እንዲሁም ተገደው ተደፍረው ለሚመጡ ሴቶች የሚሰጡ ተያያዥ አገልግሎቶች እና አጠቃላይ አገልግሎቶች ናቸው። በተጨማሪም እናቶች ከወሊድ በኋላ (post natal) የሚሰጧቸው አገልግሎቶችን በዚህ በምቹ ክሊኒክ እንዲወስዱ ተደርጓል።


ክሊኒኩ የቤተሰብ ምጣኔን በተመለከተ ከሴቶች በተጨማሪም ወንዶች ቋሚ የሆነ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴን እንዲጠቀሙ ይሰራል። ለሴቶች ከሚሰጠው ማህጸን ማስቋጠር በተጨማሪም ለወንዶች የዘር ፍሬ ማውጣት አገልግሎት ይሰጣል።


የረጅም እና የአጭር ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሐኒትን መጠቀም ለማይችሉ ሴቶች የቋሚ የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ባለቤታቸው እንደሚኬድ የገለፁት ሲስተር ፍቅርተ፣ ይሄ ስራም ብዙ ምክክርን የሚጠይቅ እንደሆነ ይናገራሉ። “በሀገራችን ወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያን ለመጠቀም ብዙም ፍቃደኛ አይደሉም” ያሉት ሲስተር ፍቅርተ፤ በሁለት ዓመታት ውስጥ ቋሚ የሆነ የወሊድ አገልግሎት መስጠት የተቻለው ለሶስት ወንዶች ብቻ (ሁለቱ ከገጠር የመጡ ሲሆን፤ አንዱ ከከተማ የመጣ) መሆኑም ተናግረዋል። በተለይ በከተማ አካባቢ የሚገኙ ወንዶች አገልግሎቱን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ነው ባለሞያዋ የሚገልፁት። “የገጠር ወንዶች ከከተማ ወንዶች የተሻለ ያለውን ሁኔታ ይቀበሉታል ይላሉ። ለወንዶች የሚሰጠው ቋሚ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ የዘር መተላለፊያ መንገዶቹን (የዘር ፍሬ) የመቋጠር ስራ ሲሆን፤ ከሴቶች ይልቅ የወንዶቹ በጣም ቀላል እና የሃያ ደቂቃ ስራ መሆኑን የገለፁት ባለሞያዋ፤ ይሄ በመደረጉም በወንዱ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያመጣ አብራርተዋል። አንድ ወንድ በዚህ መልኩ ቋሚ የሆነ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴን ቢጠቀም በግብረ ስጋ ግንኙነት ላይም ሆነ በሚኖረው ስሜት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያመጣ ተብራርቷል። ነገር ግን በቂ የሆነ ግንዛቤ ባለመኖሩ ብዙ ወንዶች አገልግሎቱን ለመጠቀም ፈቃደኛ አይሆኑም።


ቀደም ሲል የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በነርሶች ብቻ ይሰጥ እንደነበር የተናገሩት ሲሰተር ፍቅርተ አሁን ግን ከፍተኛ አማካሪዎች በተካተቱበት መንገድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ለአገልግሎት ፈላጊዎች ምቹ የሆነ አሰራርን ለመፍጠር ይረዳ ዘንድም አገልግሎቱ 24 ሰዓት እንደሚሰጥ ነው ሲስተር ፍቅርተ የሚገልፁት። “አፍላ ወጣቶች አንዳንድ ጊዜ ያልተፈለገ እርግዝና ያጋጥማቸውና በምሳ ሰዓት አሊያም በሌላ ጭር ባለ ሰዓት ነው የሚመጡት። ቅዳሜ እና እሁድም ክሊኒክ ክፍት ነው። በማንኛውም ሰዓት መጥተው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል” ይላሉ ሲስተር ፍቅርተ። ክሊኒኩ ስራ በሰራባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥም ከሰባት ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ሰጥቷል።


ጽንስ ማቋረጥን በተመለከተ ከተለያዩ ጤና ተቋማት የሚመጡ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ሴቶች ስለሚኖሩ በአማካሪዎች የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። በተጨማሪም ከአረብ ሀገራት የሚመጡ ሴቶች ታስረው በሚቆዩበት ወቅት የፅንሱ እድሜ ከፍ ብሎ ፅንሱን ለማስወጣት የመምጣት ሁኔታ ይኖራል። እነዚህ ሴቶችም በአማካሪዎች ታግዘው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል።


ሌላው በክሊኒኩ የሚሰጠው አገልግሎት በክሊኒኩ የወለዱ እናቶች ሌሎች ተያያዥ የሆኑ የጤና እክሎች ካሉባቸው እዚያው አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚደረጉበት ሁኔታ ነው። እዚያ ወልደው የልብ ህመም ህክምና ወይም የዲያሊሊስ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ሴቶች ካሉ ሁሉንም አገልግሎት እዚያው በክሊኒኩ ውስጥ እንዲያገኙ ተደርጓል። በሁለት ወራት ውስጥም ከመቶ በላይ የሆኑ አገልግሎቶች ተሰጥተዋል።


ምቹ ክሊኒክ ከዚህ በተጨማሪም የማህጸን ጫፍ ካንሰር፣ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲሁም የመካለከል አገልግሎቶችን ሴቶች እዚያው እንዲያገኙ ያደርጋል። ኮሌጁ በተለይ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምልክቶች ሲታዩ ወደ በሽታ ከመቀየራቸው በፊት ህክምና ለማድረግ የሚያግዝ ማእከል አቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የጡት ካንሰር ከተከሰተም የቀዶ ህክምና አገልግሎትም እየተሰጠ ይገኛል።


እናቶች ወደ ኮሌጁ ክሊኒክ ሲመጡ አገልግሎቱን በቀላሉ ተግባብተው መረዳት እንዳይችሉ ከሚያግዷቸው ነገሮች መካከል አንዱ ቋንቋ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ታደሰ፤ ይሄንን ክፍተት ለመሙላትም ከጥበቃ ሰራተኞች ጀምሮ የጤና ባለሞያዎቹ በኦሮምኛ ቋንቋ እንዲሰለጥኑ መደረጉን ገልፀዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኦሪሚፋ ዲፓርትመንት ጋር በመተባበር ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ዶክተር ታደሰ ተናግረዋል።


ኮሌጁ የወሊድ እና ተዛማጅ አገልግሎቶችን ከሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ግማሽ ያህሎቹ ከአዲስ አበባ ዙሪያ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ መሆናቸውን ዶክተር ታደሰ ገልጸዋል። በመሆኑም ወደ ኮሌጁ ከሚመጡት እናቶች ችግሮች ውስብስብነት አንፃር የሞት አደጋ የሚደርስበት አጋጣሚም አለ። የከፋ ችግር ያለባቸው እናቶች በአብዛኛው ወደ ኮሌጁ እንዲመጡ ስለሚደረግም በሆስፒታሉ የሚስተዋለው የእናቶች ሞት አጠቃላይ በነገር ደረጃ ካለው የበለጠ ሊሆን ይችላል ብለዋል ዶክተር ታደሰ። ከተቋማት ጋር ሲነፃፀር ግን ዝቅተኛው ነው ብለዋል ዶክተር ታሰደ። ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ጭምር በመሆኑም ወደ ህክምና ሳይገቡ ገና በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ የሚሞቱ እንዳሉም ተገልጿል። ብዙውን ጊዜ የሞት አደጋ የሚያጋጥመውም ከሩቅ ቦታ በሚመጡ እና በወቅቱ ሊደረስላቸው ባለመቻሉ በተጎዱ እናቶች ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን ስተው እና የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ እና ህይወታቸው የሚያልፍ እናቶች አሉ። የእናቶችን ሞት ከሚገመግም ኮሚቴ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም በ2009 ዓ.ም ኮሌጁ ለ11ሺህ እናቶች የወሊድ አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ እናቶች ውስጥ 13 ብቻ ህይወታቸው አልፏል። ይህም ሆኖ ሞት በእያንዳንዱ ቤት ሲገባ የሚፈጥረው የሀዘን ስሜት ከባድ በመሆኑ በቀላሉ የማታይ እንዳልሆነ ዶክተር ብርሀኔ ተናግረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
446 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 224 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us