ኮሌስትሮልን በተፈጥሮ

Wednesday, 28 February 2018 12:46

 

በሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ ሁለት አይነት ኮሌስትሮሎች ይገኛሉ። ሰውነታችን በተፈጥሮው ጥሩ (Happy or good) ኮሌስትሮል እና መጥፎ (bad or lousy) ኮሌስትሮሎች ይገኙበታል። ከስማቸው መረዳት እንደምንችለውም ጥሩ የሆነው የኮሌስትሮል አይነት በደማችን ውስጥ በብዛት ሲገኝ ሰውነታችን ጤንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያደርገው ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ መጥፎው ኮሌስትሮል ሲበዛ በተለይ ልብ ነክ ጤንነታችን በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ ይወድቃል።


መጥፎው የኮሌስትሮል አይነት በተፈጥሮው ደም በቀላሉ እንዲረጋ እና የደም ስሮች እንዲዘጉ የማድረግ አደጋን ያደርሳል። ጥሩው ኮሌስትሮል ደግሞ ይሄንን መጥፎ ኮሌስትሮል ከደም ስሮች ሰብስቦ ወደ ጉበት የማጓጓዝ ስራ ይሰራል። ጉበትም ይሄንን መጥፎ ኮሌስትሮል ከሰውነት ያስወግዳል። ጥሩ ኮሌስትሮል ከዚህ በተጨማሪም ደም ስሮች በቀላሉ እንዳይሞቱ የመጠበቅ ጠቀሜታ አለው። እነዚህን ኮሌስትሮሎች በተፈጥሮ ከምናገኘው በተጨማሪም ከተለያዩ የምግብ አይነቶች እናገኛቸዋል። የጤና ባለሞያዎችም ጥሩ የሆነውን ኮሌስትሮል በብዛት ልናገኝባቸው የምንችላቸውን የምግብ አይነቶች በየጊዜው ይፋ ያደርጋሉ። ጥሩ የሆነ ኮሌስትሮልን በብዛት ልናገኝባቸው ከምንችለው ምግቦች መካከል የእንቁላል አስኳል፣ አጃ፣ አቮካዶ እንዲሁም አንዳንድ ጥራጥሬ እህሎች ተጠቃሽ ናቸው።

 

ጥራጥሬ

 

በዚህ የምግብ ምድብ ስር በርካታ ጥራጥሬዎችን መዘርዘር ይቻላል። ዋና ዋናዎቹም ባቄላ፣ አተር እና ምስር ናቸው። በካናዳ ሜዲካል አሶሲዬሽን ጆርናል ላይ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው አንድ ሰው በየቀኑ ከሶስት እስከ አራት ሲኒ መጠን ያለው የጥራጥሬ ምግብ ቢመገብ በደም ውስጥ ያለውን የመጥፎ ኮሌስትሮል መጠን በ5 መቶ መቀነስ ይችላል። እነዚህ የጥራጥሬ አይነቶች በቀላሉ ማግኘት የሚቻል፣ ለመመገብ ቀላል እና ጥሩ የሆነ ጣዕምም ያላቸው በመሆናቸው በዕለት ምግብ ውስጥ ቢካተቱ በተፈጥሮ ከፍተኛ የጥሩ ኮሌስትሮል ምንጭ ናቸው ይላል መረጃው።

 

አቮካዶ

 

አቮካዶ ከምግብነት ይልቅ የመድሐኒትነት ባህሪያቸው ከሚያመዝን የምግብ አይነቶች ተርታ የሚመደብ ነው። ከእነዚህ የመድሐኒትነት ጠቀሜታዎች መካከል አንዱ ደግሞ በደም ውስጥ የሚኖረው ጥሩ ኮሌስትሮል መጠን እንዲጨምር ማድረግ ነው። በፔንስሊቫኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ በተደረገ ጥናት ማረጋገጥ እንደተቻለው አቮካዶን አዘውትረው የሚጠቀሙ ሰዎች በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን መጥፎ ኮሌስትሮል መጠን በ14 ሚሊግራም መቀነስ ችለዋል። አቮካዶ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል እና ለአመጋገብም የሚመች በተፈጥሮ የተገኘ የጥሩ ኮሌስትሮል ምንጭ መሆኑንም በጥናቱ ማረጋገጥ ተችሏል።

 

አጃ

 

አጃ ለብዙ የጤና ችግሮች እንደመፍትሔ ከሚያገለግሉ የምግብ አይነቶች መካከል ተጠቃሽ ነው። ከኮሌስትሮል ጋር ያለውን ግንኙነት ስንመለከት ደግሞ አጃ ኮሌስትሮልን የመቀነስ ባህሪይ አለው። በታይ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተውም አጃ በደም ውስጥ የሚገኘውን መጥፎ የሆነ ኮሌስትሮል መጠን የመቀነስ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ለጥናቱ ሲባል አጃ በተለያየ መንገድ የተካተተባቸውን የምግብ አይነቶች አዘውትረው የተመገቡ ሰዎች ምንም አጃን ካልተመገቡት ጋር ሲነፃፀሩ መጥፎ የሆነው ኮሌስትሮል 10 በመቶ እንዲሁም በአጠቃላይ በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን ኮሌስትሮል መጠን በ5 በመቶ መቀነስ ችለዋል።


አጃ በተፈጥሮው በደም ውስጥ የሚገኙትን ኮሌስትሮሎች የሚቀንስ በመሆኑ፤ ጥሩ የሆነውን ኮሌስትሮል በብዛት እንዳይቀንሰው ለማድረግም የሶዲየም ማእድን ይዘታቸው ዝቅተኛ ከሆነ አትክልቶች ጋር መመገብ የበለጠ ጠቃሚ መሆኑን ባለሞያዎች ይመክራሉ። ከአጃ ጎን ለጎን እንደ ዝኩኒ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ እንጉዳይ እንዲሁም ነጭ ሽንኩርት እና እንቁላልን መጠቀም የበለጠ ውጤት ለማምጣት እንደሚያግዝም ነው ጥናቱ ያመለከተው። በተጨማሪም እንደ ኮኮናት፣ ቀረፋ፣ ዱባ እና ዝንጅብል ያሉ ተጨማሪ ነገሮችን በተለያዩ መንገዶች ከአጃ ጋር አቀናጅቶ መመገብ በደማችን ውስጥ የሚገኘው መጥፎ ኮሌስትሮል መጠን እንዲቀንስ በተቃራኒው ደግሞ የጥሩ ኮሌስትሮል መጠን እንዲጠበቅ ያደርጋል።

 

ለውዝ

 

ለውዝ የሚሰጠው ጠቀሜታ ጠቃሚ (ጥሩ) የሆነውን ኮሌስትሮል መጠን ከፍ የማድረግ ነው። በጆርናል ኦፍ ኒውትሪሽን ላይ ጥናትን መሰረት አድርጎ የታተመ መረጃ እንደሚያመለክተው ለውዝ በተለይ የልብ እና ከልብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች ላሉባቸው ሰዎች ጥሩ የሆነውን ኮሌስትሮል መጠን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በጥናቱ ላይ የተሳተፉ እና የልብ ህመም ያለባቸው ሰዎች ለውዝን ከቁርስ በፊት እንዲመገቡ ተደርጎ ጥሩ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ከቁርስ በፊት 10 ግራም የለውዝ መጠንን የተመገቡ ሰዎችም ጥሩውን ኮሌስትሮል በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችለዋል። በተከታታይ ለ6 ሳምንታት ከቁርስ በፊት ለውዝን የተጠቀሙ ሰዎችም ይሄን ጥሩ ኮሌስትሮል መጠናቸውን ከ12 እስከ 14 በመቶ ከፍ ማድረግ የቻሉ ሲሆን፣ ለ12 ሳምንታት ሲጠቀሙ ደግሞ ከ14 እስከ 16 በመቶ ከፍ ማድረግ ችለዋል።


አንድ ሰው 8 ፍሬ ለውዞችን እንኳን በቀን ውስጥ መመገብ ከቻለ በደሙ ውስጥ የሚገኘውን ጥሩ ኮሌስትሮል በብዙ መጠን መጨመር እንደሚችል ነው መረጃው የሚጠቁመው። በተጨማሪም ለውዝን በጥሬውም ሆነ ተፈጭቶ በፈሳሽ መልክ የተዘጋጀውን መመገብ የሚሰጠውን ጠቀሜታ እንደማይቀንሰው ተገልጿል። ለውዝን በተለያዩ መንገዶች መጠቀም ቢቻልም በተለይ ዝንጅብል እና የተለያዩ የእንጆሪ ዝርያዎችንም አብሮ መጠቀም እንደሚቻል እና በዚህም የሚገኘው ውጤት ከፍተኛ እንደሆነ መረጃው ይፋ አድርጓል።


አረንጓዴ ሻይ

 

ለልብ ህመም አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ በደም ውስጥ የሚገኘው መጥፎ ኮሌስትሮል መጠን ከፍ ማለት ነው። ምንም እንኳን በደም ውስጥ ያለው ጥሩ ኮሌስትሮል መጠን ከፍተኛ ቢሆንም የመጥፎው ኮሌስትሮል መጠን ከፍተኛ ከሆነ ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላችን ከፍተኛ ይሆናል። ይሄንን ከመጥፎ ኮሌስትሮል መጠን ማሻቀብ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የልብ ህመም ለመከላከል ከሚያግዙ ነገሮች መካከል አንዱ ደግሞ አረንጓዴ ሻይ ነው።


በአሜሪካን ጆርናል ኦፍ ክሊኒካል ኒውትሬሽን ላይ የታተመ መረጃ እንደሚያመለክተው አረንጓዴ ሻይን አዘውትሮ መጠጣት የጥሩውን ኮሌስትሮል መጠን ሳይነካ የመጥፎውን ኮሌስትሮል መጠን በከፍተኛ ደረጃ የመቀነስ ጠቀሜታ አለው። አረንጓዴ ሻይ በደም ውስጥ የሚገኘውን ጥሩ ኮሌስትሮል ከመቀነስ በተጨማሪም በጥሩው ኮሌስትሮል ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተፅዕኖን የማያደርስ በመሆኑ በዚህ ረገድ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው። መረጃው እንዳመለከተውም አዘውትረው አረንጓዴ ሻይን የሚጠቀሙ ሰዎች የመጥፎ ኮሌስትሮል መጠናቸውን በ2 ሚሊግራም እንዲሁም አጠቃላይ የደማቸውን ኮሌስትሮል መጠን በ7 ሚሊግራም መቀነስ ችለው ተገኝተዋል።


ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች እግረመንገዳቸውን እንደሚገልፁትም ለመጥፎ የደም ኮሌስትሮል መብዛት የሚያጋልጡት በአብዛኛው ከአኗኗር ዘይቤያችን ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው። ከእነዚህ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዘው ከሚተገበሩ ነገሮች መካከልም ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ እንቅስቃሴ የሌለው እና ለረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ መቀመጥን የሚያዘወትር አኗኗር እንዲሁም ሲጋራ ማጨስ ናቸው። እነዚህ ምክንያቶች በአብዛኛው በቀላሉ ሊወገዱ የሚችሉ ነገር ግን የሚያስከትሉት መዘዝ በቀላሉ የማይታለፍ በመሆኑ አስቀድሞ መጠንቀቅን ይመክራሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
506 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 221 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us