መቆም ድካምን ይቀንሳል

Wednesday, 14 March 2018 12:55

 

የሰው ልጅ ሰውነት የተሰራው ቀኑን ሙሉ ተቀምጦ ለመዋል አይደለም ይላል በሳንፎርድ ዩኒቨርስቲ የተደረገ አንድ ጥናት። የዘመናችን ሰዎች ያሉበት የአኗኗር ዘይቤ ደግሞ ከመቆም ይልቅ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በመቀመጥ እና በመተኛት እንዲያሳልፉ የሚያደርግ ነው ይላል ይሄው ጥናት። ነገር ግን መቀመጥ ለጊዜው ምቾት እንዲሰማን ቢያደርገንም ውሎ አድሮ የሚያስከትላቸው የጤና መዘዞች ግን በርካታ ናቸው። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስም ያልተፈለገ የሰውነት ክብደት፣ የደምና ስኳር መጠን መጨመር እንዲሁም መጥፎ የሆነው ኮሌስትሮል መጠን ማሻቀብ ተጠቃሾች ናቸው። በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የተደረገው ጥናት አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ጀምስ ሌቪን የመቀመጥን የጤና ጠንቅነት ሲገልፁም “መቀመጥ አዲሱ ሲጋር ማጨስ ነው። አንድ ሰው አብዛኛውን ጊዜውን ተቀምጦ በማሳለፉ ብቻ ሲጋራ ከሚያጨስ ሰው እኩል ለተለያዩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነቱን ይጨምረዋል” ብለዋል። ይሄንን የዘመናችን ወረርሽኝ የሆነ ለረጅም ጊዜ የመቀመጥ ልምድ አጥብቀው የሚያወግዙት የዘርፉ ባለሞያዎችም በተቃራኒው በመቆምና በመንቀሳቀስ ችግሩን ማስቀረት እንደሚገባ ይመክራሉ።

ችግሩን ለማስወገድ የተለየ ነገር መፍጠር እንደማያስፈልግ የገለፁት ዶክተር ጀምስ፤ ሰዎች የመቀመጥ ልማዳቸውን ወደመቆምና እንቅስቃሴ ወደማድረግ መቀየር ብቻ በቂ መሆኑን ያብራራሉ። በተለይ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስራ ምክንያት ተቀምጦ የሚያሳልፉ ሰዎች በየተወሰነ ሰዓት ልዩነት ከመቀመጫቸው በመነሣት የመቆም እና እንቅስቃሴ የማድረግ ከተቻለም ስራቸውን ቆመው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸት ቢችሉ መልካም ነው ብለዋል። በአጠቃላይም ከመቀመጥ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ቆሞ በማሳለፍ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጠቀሜታዎች ማግኘት እንደሚቻል በተለያዩ ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች አመልክተዋል።

ያልተፈለገ የሰውነት ክብደትን ያስቀራል

ከመቀመጥ ይልቅ በምንቆምበት ሰዓት ሰውነታችን የበለጠ ካሎሪዎችን የማቃጠል አቅም ይኖረዋል። በታዋቂው ማዮ ክሊነክ የተደረገ ጥናት ውጤት እንደሚገልጸው አንድ ሰው በቀን ውስጥ በተለያየ ጊዜ ቢያንስ ለስድስት ሰዓታት ያህል ቢቆም ያልተፈለገ የሰውነት ክብደቱን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይችላል። በሰባት ሺህ አዋቂ ወንዶችና ሴቶች ላይ በተደረገው በዚህ ጥናት ማረጋገጥ የተቻለውም በቀን ውስጥ ቢያንስ ለስድስት ሰዓታት የሚቆሙ ወንዶች ላልተፈለገ የሰውነት ክብደት ያላቸውን ተጋላጭነት በ59 በመቶ መቀነስ የቻሉ ሲሆን፤ ሴቶች ደግሞ 35 በመቶ መቀነስ ችለዋል።

የልብ ህመሞችን ይከላከላል

በአውስትራሊያ በተደረገ አንድ ጥናት ማረጋገጥ የተቻለው ሌላው የመቆም ጠቀሜታ ለልብ ህመሞች አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን ማስወገድ ነው። ጥናቱ እንደገለፀውም በምንቆምበት ወቅት በሰውነታችን ላይ የሚፈጠረው ለውጥ ጥሩ የሆነው ኮሌስትሮል መጠን እንዲጨምር በተቃራኒውም የመጥፎ ኮሌስትሮል መጠን እንዲቀንስ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። ቢያንስ በቀን ውስጥ ለሁለት ሰዓታት የሚቆሙ ሰዎች በደማቸው ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በአማካይ በ2 በመቶ መቀነስ ችለዋል። ተጨማሪ ሁለት ሰዓታትን በቆሙ ቁጥርም የጥሩ ኮሌስትሮል መጠናቸውን በዜሮ ነጥብ ዜሮ ስድስት በመቶ መጨመር እንዲሁም መጥፎውን ኮሌስትሮል በስድስት በመቶ መቀነስ ችለዋል። በዚህ ረገድ ወንዶችም ሴቶችም የሚያገኙት ጠቀሜታ ተመሳሳይ መሆኑን የገለፀው ጥናቱ፤ እነዚህ ጠቀሜታዎች ሲደማመሩም የልብን ጤንነት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ሲል አስፍሯል።

ለስኳር ህመም ያለውን ተጋላጭነት ይቀንሳል

የአሜሪካ ስኳር ህሙማን ማህበር መረጃ እንደሚጠቁመው ቁጭ ከማለት ይልቅ በመቆም በተለይ ደግሞ እንቅስቃሴ ማድረግ በደም ውስጥ ያለውን ስኳር መጠን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ያግዛል። እንደመረጃውም ለአምስት ደቂቃዎች ያህል ወዲያ ወዲህ በእግር በመዘዋወር ብቻ በደም ውስጥ ያለውን ስኳር መጠን በ34 በመቶ መቀነስ ይቻላል። በተለይ እድሜያቸው በገፉ ሰዎች እና በአረጡ ሴቶች ላይ ያለው ለውጥ የጎላ መሆኑን የገለፀው ጥናቱ፣ በቀን ውስጥ ቢያንስ ለስድስት ሰዓታት ቢቻል እንቅስቃሴ በታከለበት መልኩ በመቆም በደም ውስጥ ያለውን ኢንሱሊን ማስተካከል ይቻላል። በዚህም በተለይ አይነት ሁለት ለተባለው የስኳር ህመም ያለውን ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል ይላል የማህበሩ መረጃ።

ለካንሰር ያለውን ተጋላጭነት ይቀንሳል

ለረጅም ጊዜ መቀመጥ እንኳንስ ምንም አይነት የሰውነት እንቅስቃሴን ለማያደርጉ ቀርቶ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለሚያደርጉትም ለካንሰር ህመም ያላቸውን ተጋላጭነት እንደሚጨምርው መረጃዎች ያመለክታሉ። በተቃራኒው ግን መቆም የደም ዝውውር የተስተካከለ እንዲሆን፤ የሰውነት መቆጣት እንዲቀንስ እና ጤናማ የሆነ የሜታቦሊዝም ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ለተለያዩ ካንሰሮች ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሰዋል ይላል ከአሜሪካ ካንሰር ምርምር ኢንስቲቲዩት የተገኘው መረጃ። እንደመረጃው በየዓመቱ 50ሺህ ሰዎች በጡት ካንሰር ሳቢያ እንዲሁም ከ40ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በትልቁ አንጀት ካንሰር ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን፤ ዋንኛው የእነዚህ ካንሰር ተጠቂዎች ምክንያትም በቂ የሆነ እንቅስቃሴን አለማድረግ ነው።

የጀርባ ህመምን ይቀንሳል

በስታፎርድ ዩኒቨርስቲ በጀርባ አጥንት ላይ የተደረገ ጥናት እንዳረጋገጠው በመስሪያቤታቸው የሚያሳልፉትን ጊዜ በአብዛኛው ቆመው በመስራት እንደሆነ የገለፁ ሰዎች የጀርባ ህመም ብዙም አያጠቃቸውም። እንደጥናት ውጤቱ ስራቸውን ለረጅም ጊዜ ከመቀመጥ ይልቅ በየመካከሉ እየተቀመጡ እና አብዛኛውን ጊዜያቸውን ቆመው በመስራት እንደሚያሳልፉ የተናገሩ ሰራተኞች ውሏቸው ከጀርባ ህመም የጸዳ ሆኖ ተገኝቷል። ባለሞያዎቹ በስራ መካከል ቢያንስ ለ30 ደቂቃዎች መቆም ድካምን እና በጀርባ አካባቢ የሚፈጠረውን ህመምና ያለመመቸት ስሜት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ብለዋል።

አቅምን ለማዳበር እና ጥሩ ስሜት ለመፍጠር ያግዛል

በተለይ ስራን ቆሞ ማከናወን የሰውነት ጡንቻዎች በቅንጅት እንዲሰሩ ስለሚያደርጋቸው በስራው ላይ የሚውለው አቅም ጠንከር ያለ እንዲሆን ያግዘዋል። በተጨማሪም እንደጭንቀት እና ድካም ያሉ ስሜቶችን በማስወገድ በአንገት እና ጀርባ እንዲሁም ትከሻ አካባቢ የሚፈጠሩ አለመመቸቶችን በማስወገድ የተቀላጠፈ የስራ መንፈስን ይፈጥራል የሚለው የአውስትራሊያው ዩኒቨርስቲ ጥናት፤ እግረመንገዱንም ሰዎች በተረጋጋ እና በተነቃቃ ስሜት ስራቸውን ሰርተው የበለጠ ምርታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ይላል። ቆሞ ለመስራት የሚያገለግል ጠረጴዛን ተጠቅመው ስራቸውን እንዲሰሩ የተደረጉ ሰዎችም ምርታማነታቸው በየእለቱ በ45 በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል። በዚህ ጠረጴዛ ተጠቅመው ስራቸውን የሰሩ ሰዎችም ምርታማነታቸው በመጀመሪያው ወር ከነበረበት 23 በመቶ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ወደ 53 በመቶ ማሻቀብ መቻሉን ጥናቱ አመልክቷል።

ጡንቻዎችን ያጠነክራል

በሜልቦርን ዩኒቨርስቲ የአጥንት ህክምና ክፍል የተደረገ ጥናት እንደጠቆመው የሰውነታችን አጥንቶች ያለ እንቅስቃሴ ከመቀመጥ ይልቅ በአግባቡ አገልግሎት ላይ ስናውላቸው ጥንካሬያቸው እየጨመረ ይመጣል። በስራ ላይ ሆነን በምንቆምበት ጊዜ ደግሞ እግራችን፣ ቁርጭምጭሚታችን አካባቢ እንዲሁም የእግር መዳፋችን እና ጣቶቻችን በእኩል ደረጃ መሬት ላይ ስለሚያርፉ የበለጠ የመጠንከር እና እንደልብ መሳሳብ ይጀምራሉ። የጡንቻዎች እንደፈለጉት መለጠጥ እና መሳሳብም ድካምን በማስወገድ እና ስሜትን በማስተካከል ለስራ ያለውን ተነሳሽነት ይጨምረዋል ይላል ጥናቱ። በተጨማሪም ሰውነት የተስተካከለ ቅርፅ እንዲኖረው እና አጥንታችን ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ሰውነትን የመሸከም አቅም እንዲፈጠርለት ያግዘዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
469 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 223 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us