የማይድን የጨጓራ ህመም

Wednesday, 21 March 2018 13:17

 

በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ሰዎች ዘንድ ተንሰራፍተው ከሚታዩ ህመሞች መካከል አንዱ የጨጓራ ህመም ነው። የጨጓራ ህመም የሚያሳያቸው ምልክቶች ከሌሎች ህመሞች ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ቢሆንም ብዙዎቻችን ግን ስሜቶቹን አጠቃለን የጨጓራ ህመም መገለጫ ስናደርጋቸው ይታያል። ባለሞያዎች ግን ይህን የጨጓራ ህመም በተለያየ መልኩ ይገልፁታል። እኛም ዛሬ የጨጓራ ቁስለትን በተመለከተ ባለሞያ አነጋግረን የሚከተለውን መረጃ ይዘን ቀርበናል። ባለሞያው ዶክተር አባተ ባኔ ናቸው። ዶክተር አባተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ሐኪምና መምህር እንዲሁም የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ናቸው። በተጨማሪም የጉበት፣ የጨጓራ እና የአንጀት ህክምና ስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው።


ሰንደቅ፡- የጨጓራ በሽታዎች የተለያዩ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ የጨጓራ ቁስለት ይገኝበታል። የጨጓራ ቁስለት ምንድን ነው ከሚለው ብንጀምር?


ዶ/ር አባተ፡- ስሙ እንደሚገልፀው ችግሩ ጨጓራ ሲቆስል የሚከሰት ነው። ነገር ግን በርካታ ይሄንን ህመም የሚመስሉ ህመሞች ስላሉ በሚያሳያቸው ምልክቶች ነው መለየት የሚቻለው። የጨጓራ ህመም የሚባለው ከእምብርት በላይ ባለው ክፍል ላይ የሆድ ህመም ሲኖር፣ ከምግብ በኋላ እንደማቅለሽለሽ፣ ማግሳት እና የሆድ መነፋት አልፎ አልፎ ትውከት እና የምግብ ፍላጎት ማጣት ያሉ ያለመመቸቶች መፈጠር ምልክቶች ሲኖሩ ነው። እነዚህ ምልክቶች የጨጓራ ህመም ጠቋሚ ምልክቶች ቢሆኑም ሙሉ ለሙሉ የጨጓራ ህመምን ብቻ በእርግጠኝነት የሚያሳዩ አይደሉም። የጨጓራ ህመም የሚመስሉ የትንሹ አንጀት ህመም፣ የሀሞት ከረጢት ህመም ወይም የጣፊያ ህመም አልፎ አልፎም እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ የልብ ህመም እና የቆሽት ህመም እንዲሁም የኩላሊት ህመሞች እነዚህን ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። ስለሆነም በተጨማሪ ምርመራ ነው መለየት የሚቻለው።


የጨጓራ ቁስለት ስንል የጨጓራ መላጥንም ይጨምራል። እነዚህ የጨጓራ መላጥ ምልክቶች ያሉባቸው ሰዎች የምግብ ቱቦ ወይም ጨጓራ ካልሆነም ትንሹ አንጀት ሲታመም የጨጓራ ግድግዳ መቆጣት፣ መላጥ፣ ቁስለት፣ እብጠት ወይም ካንሰር ድረስ ሊሄድ ይችላል። ስለዚህ ለሀኪሞች ጭምር ለመለየት አስቸጋሪ ስለሚሆን በምርመራ ብቻ ነው መለየት የሚቻለው።


ሰንደቅ፡- የጨጓራ ቁስለትን ሊያመጡ የሚችሉት ነገሮች ምን ምን ናቸው? በሀገራችን የበለጠ አጋላጭ የሆኑትስ ምን ምን ናቸው?


ዶ/ር አባተ፡- በእኛ ሀገር በብዛት ጨጓራን እና ትንሹን አንጀት ሊያቆስል የሚችለው ነገር የጨጓራ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ነው። ኤች ፖሎሪ የሚባል ባክቴሪያ ነው ለዚህ ችግር የሚያጋልጠው። ይህ ባክቴሪያ ከሰው ወደ ሰው በምግብ እና በመጠጥ መበከል የተነሳ የሚተላለፍ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የጨጓራን ግድግዳ ሊያስቆጡ የሚችሉ ነገሮች አሉ። እንደ አልኮል፣ መድሐኒቶች፣ ሲጋራ እንዲሁም ሌሎች በሽታዎች ጨጓራን ሊያስቆጡ እና ሊያቆስሉ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ስር እየሰደደ ሲሄድ ለዚህ ጨጓራ መቁሰል መንስኤ የሚሆኑ የጨጓራ ካንሰሮች አሉ።
ሌላው ደግሞ የጨጓራ አሲድ ከመጠን በላይ መመንጨት ነው። የጨጓራ አንድ ስራ አሲድ ማመንጨት ሲሆን፤ አሲድ ከመጠን በላይ ከመነጨ ወደ ጨጓራ ቁስለት ሊያመራ ይችላል።


ሰንደቅ፡- አንዳንድ ሰዎች ላይ የጨጓራ ህመም የመደጋገም እና ያለመዳን ሁኔታን ያሳያል። ይሄ ከምን የመነጨ ነው?


ዶ/ር አባተ፡- የማይድን እና ተደጋጋሚ የሆነ የጨጓራ ህመም ስሜቶች የተለመዱ ናቸው። ይሄ የሚሆነው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው የጨጓራ ህመሙ ታውቆ በአግባቡ ካልታከመ ህመሙ ሊቀጥል ይችላል። ምርመራ አድርጎ መነሻው ባክቴሪያ ከሆነ ባክቴሪያው ካልታከመ ወይም መጠጥ እና ቅመማ ቅመም የበዛባቸው ምግቦች ከሆኑ እነሱን ካልቀነሰ በሽታው ለጊዜው ሻል ቢለውም ተመልሶ ሊቀሰቀስበት ይችላል። በተጨማሪም የጨጓራ ቁስለቱን ደረጃ አውቆ መድሐኒት ለተወሰነለት ጊዜ ካልተወሰደ ተመልሶ ሊያም ይችላል። ወይም ደግሞ የሚሰጠው መድሐኒት ከሚፈልገው በታች ከሆነ እና ለሁለት ሳምንት መሰጠት ያለበት ህክምና ለአንድ ሳምንት ብቻ ከተሰጠው በሽታው ተመልሶ ሊከሰት ይችላል። የጨጓራ ህመም የሚመላለስበት እና ሙሉ ለሙሉ የማይድንበት አንዱ ምክንያትም ይሄ ነው።


ሁለተኛው እና ብዙ ሰዎች የሚቸገሩበት ደግሞ የሰውነት አሰራር መረበሽ (functional dispensia) የሚባለው የጨጓራ ህመም ነው። እነዚህ ሰዎች በኢንዶስኮፒ እና በሌሎች መሣሪያዎች ሲታዩ ጨጓራቸው ምንም ችግር የለበትም። እነርሱ ግን የህመሙ ስሜቶች ይሰሟቸዋል። ይሄ የሚከሰተው ከጨጓራ መቁሰልና መጥበብ ሳይሆን ከሰውነት አሰራር ስርዓት መረበሽ ጋር ተያይዞ ነው። ሰውነታችን የሚሰራው በኤሌክትሪክ፣ በነርቭ እና በሆርሞን ቁጥጥር እንደመሆኑ መጠን ያ የአሰራር ስርዓት ሲረበሽ ይሄ አይነቱ ክስተት ይከሰታል። ሰውነታችን ከላይ ከአእምሮአችን ጀምሮ በነርቭ ስርዓት እንዲሁም ከውስጥ በሆርሞን ስርዓት ቁጥጥር ስር ስለሆነ ሲያንስ እየተጨመረ ሲበዛ ደግሞ እየተቀነሰ በስርዓት እና በፈጣን ግንኙነት ነው የሚሰራው። እነዚህ ስርዓቶች ሲነበሹ ግን ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ።


በዚህ ደረጃ ላይ የሚታዩት ምልክቶችም የጨጓራ አሲድ መጠን መብዛት፣ ቀስ ብሎ እንደ እንሽላሊት ጉዞ የነበረው የአንጀት እንቅስቃሴ መፍጠን እና መረባበሽ ሲከሰት የመረባበሽ፣ የሆድ መነፋት፣ ቁርጠት እና መጮህ እንዲሁም ጋዝ ይፈጥራል። ጨጓራ በሚፈለገው እና በተገቢው መጠን አሲድ ሲረጭ አሲዱ በሽታን ለመከላከል ይጠቅማል። ነገር ግን ከሚገባው በላይ ከሆነ የነርቭና ሆርሞን ስርዓቶች ስለሚረበሹ ይሄ ስሜት ይፈጠራል። እነዚህ ሰዎች የባክቴሪያ መድሐኒት ቢሰጣቸውም የቁስለት መድሃኒት ቢወስዱም ለጊዜው ይሻላቸዋል እንጂ አይድንም። የዚህ ችግር መንስኤው የሰውነት ስርዓት መረበሽ እንጂ ቁስለት ስላልሆነ በእነዚህ መድሐኒቶች አይድኑም። እነዚህ ስሜቶች በሰውነት ክፍሎቻችን፣ በጨጓራችን ወይም በእንቅልፋችን ላይ የመረበሽ ስሜትን ይፈጥራሉ። ወይ ደግሞ ልባችን ከሚገባው በላይ በፍጥነት ይመታል። በዚህም ሳቢያ የምግብ አለመፈጨት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እንዲሁም እንቅልፍ የማጣት ችግር ይከሰትብናል። ይሄ ችግር በሀገራችን ብቻ የሚታይ ሳይሆን በመላው አለም ላይ በርካታ ሰዎች የሚቸገሩበት እና ሀኪሞች ጭምር የሚፈተኑበት ነው። ብዙውን ጊዜ ገንዘባቸውን እና ጊዜያቸውን ከማጥፋት ውጪ መፍትሄ አያገኙም። አንዳንድ ጊዜም የሀሞት ጠጠር ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ትርፍ አንጀት ሊሆን ይችላል እየተባለ በመላ ምት ኦፕሬሽን ይደረጋሉ። ምልክቶቹ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ስለሚመሳሰሉ እነዚህ በሽታዎች ናቸው ተብሎ ይጠረጠራል።


አሁን ግን በተለያዩ ሀገራት ያሉ የህክምና ጠቢባን ተቀምጠው መመሪያ አወጡ። አንድ ሰው ክብደቱ ካልቀነሰ፣ ሌሊት ሳይሆን ቀን ከሆነ የሚያመው፣ ኑሮውና ስራው ጭንቀት የሚበዛበት ከሆነ እና እነዚህ ነገሮችም ለረጅም ዓመታት የሚመላለሱ ከሆነ ችግሩ የሰውነት አሰራር ስርዓት መረበሽ እንጂ የቁስለት እንዳልሆነ የሚገልፅ መመሪያ ወጥቷል። እነዚህ ሰዎች አጋላጭ እና አባባሽ የሆኑ ነገሮችን በማስወገድና ምልክቶቹን ሊቀንሱላቸው የሚችሉ መድሐኒቶችን በመስጠት ይረዳሉ። በተለይ ስራቸው ጭንቀት ያለበት፣ ትዳር የፈቱ እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ያሉ ሰዎች፣ በሂሳብ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ለእንዲህ አይነቱ ችግር በብዛት የተጋለጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የሚሰሟቸው ስሜቶች ይረብሿቸዋል እንጂ አንዲት ኪኒን እንኳን ባይወስዱ ለህይወታቸው የሚያሰጋቸው ነገር የለም። እንደ ቁስለት እና ካንሰር ለሞት የሚያበቃ ሳይሆን የእለት እንቅስቃሴን የሚያዛባ እና ብዙ ወጪን የሚያስወጣ ነው።


ሰንደቅ፡- ይህ የጨጓራ ቁስለት በህፃናት ላይ የመከሰት እድሉ ምን ያህል ነው? ብዙ ጊዜ የጨጓራ ህመምን ከአዋቂዎች ጋር ነው የምናገናኘው።


ዶ/ር አባተ፡- የጨጓራ በሽታ በህፃናትም ላይ ሆነ በወጣቶች ላይ ይከሰታል። ግን ከአዋቂዎች ያነሰ ነው። በሀገራችን ያለውን የኤች ፓኖሪ ባክቴሪያ ስርጭት ስንመለከት 80 በመቶ ስለሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ለዚህ በሽታ ተጋላጮች ናቸው። የንፅህና ሁኔታ ገና ስለሆነ ምግብና መጠጦች የመበከል እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ህጻናትም የመጠቃት እድል አላቸው።


ሁለተኛውና የሰውነት አሰራር መረበሽ የምንለውም የጨጓራ ህመም በህጻናት ላይ የመከሰት እድል አለው። በቤት ውስጥ ጫና ያለባቸው እና ካላጠናችሁ ተብለው ጫና የሚደረግባቸው ልጆች ለዚህ ችግር ተጋላጮች ናቸው። ምግብ እንደበሉ ወዲያው ያስታውካቸዋል። በትምህርት ቤት በመምህራን ጫን ያለ ቁጥጥር እና የመገረፍ ሁኔታ ሲኖርባቸው ጫና ይፈጥርባቸዋል። በተለይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ህፃናቱ በጨዋታ እድሜ ላይ ስለሚሆኑ አስፈሪ ነገሮች ለዚህ ችግር ያጋልጣቸዋል። ፈተናን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ህጻናቱ ስለሚጨነቁ ከጭንቀት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠር ከመጠን ያለፈ አሲድ መመንጨት ይጋለጣሉ። በተጨማሪም ከወላጆቻቸው የተለዩ ህጻናትም ለዚህ የተጋለጡ ናቸው። ሌላው ደግሞ የጨጓራና ምግብ ማውጫ በር በተፈጥሮ የላላ ከሆነ ህፃናት ለዚህ ችግር ይጋለጣሉ። ይህ በር ስንውጥ የሚከፈት ሲሆን፣ ከዋጥን በኋላ ደግሞ ይዘጋል። በሩ የላላ ሲሆን ግን ከምግብ በኋላ የጨጓራ አሲድ ወደ ምግብ ቱቦ ይመለስና የምግብ ቱቦውን በማስቆጣት ደረት ላይ ግሳትን እና ስቅታን የሚያስከትል ቃር እንዲከሰት ያደርገዋል። በአጠቃላይ ግን ከሁለት ዓመት እድሜ ጀምሮ የጨጓራ ህመም ሊከሰት ይችላል።


ሰንደቅ፡- የጨጓራ ቁስለት እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል? ከተቻለስ መከላከያ መንገዶቹ ምን ምን ናቸው?


ዶ/ር አባተ፡- በሀገራችን በአብዛኛው ምክንያቱ ባክቴሪያ ነው። ስለዚህ የግል እና አካባቢ ንጽህናን በመጠበቅ መከላከል ይቻላል። በተጨማሪም ባክቴሪያው ስለሚተላለፍ በቤት ውስጥ ህመሙ ያለበትን ሰው በማሳከም በሽታውን መከላከል ይቻላል። ሶስተኛው መከላከያ መንገድ ደግሞ በሽታውን የሚያባብሱ እንደ አልኮል እና ሲጋራ ያሉትን ነገሮች ማስወገድ ነው። የራሳቸው የሆነ ጥቅም ቢኖራቸውም ቅመማ ቅመም የበዛባቸው ምግቦችም ሊያባብሱት ስለሚችሉ እነዚያንም መቀነስ ያስፈልጋል። መድሐኒት ሲወሰድም በሀኪም ትእዛዝና በአግባቡ መወሰድ ያስፈልጋል። በዘልማድ የሚወሰዱ መድሐኒቶች ሌላ ችግር ሊያስከትሉ ስለሚችሉ መድሐኒቶች ያለቦታቸው መርዝ ናቸው ይባላል። መጠኑ እና አወሳሰዱን አስተካክሎ ካልተወሰደ የማይጎዳው የሰውነት ክፍል የለም።


ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አመጋገባችን ነው። ስንመገብ በመጠኑ በመመገብ ጨጓራ እና አንጀትን አለማጨናነቅ ያስፈልጋል። ቅባት የበዛባቸው እና የሚያቃጥሉ ምግቦችንም ማስወገድ ይኖርብናል። እረፍት ላይ ስንሆን ከልብ በስተቀር ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ዘና ስለሚሉ ሌሊት ላይ ጨጓራችን ሙሉ ከሆነ እና በጣም ከጠገብን ጨጓራ ውስጥ ያለው ምግብና አሲድ ወደ ምግብ ቱቦ እና ወደ ደረት ይመለሳል። ይሄንን አሲድ ሊቋቋም የሚችለው ጨጓራ ብቻ ስለሆነ የምግብ ቱቦውን የማሳሳት እና የማቁሰል ችግር ስለሚያመጣ ማታ ላይ ከመኝታ በፊት ቢያንስ ሁለት ሰዓት ቀደም ብሎ መመገብ ያስፈልጋል። ጨጓራችን ሙሉ ሆኖ ከተኛን ግን አሲዱ ወደ አየር ቱቦ ድረስ በትንታ መልክ በመግባት አስም እና አለርጂ ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ ቀደም ብሎ እና በመጠኑ በመመገብ መከላከል ይቻላል። ትራስንም 30 ዲግሪ ከፍ በማድረግ መከላከል ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም አባባሽ ነገሮችን በማስወገድ የጨጓራ ቁስለትን ብቻም ሳይሆን ሌሎች ተያያዥ የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል። አሲድ እና ሀሞት በተደጋጋሚ ወደ ምግብ ቱቦ እና አየር ቱቦ ሲመለሱ የማቃጠል እና የማቁሰል ችግር በመፍጠር እስከ ካንሰር የደረሰ አደጋ ያስከትላል። በተጨማሪም በተለይ በአዋቂዎች ላይ የማይድን የአስም በሽታን ሊያስከትል ይችላል።


በአጠቃላይ ግን የጨጓራ ህመም ምልክቶች ከልብ፣ ከጣፊያ ከሀሞት ከረጢት፣ ከጉበት እና አንዳንድ ጊዜ ከልብ ህመም ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ችግሩ በህክምና እና በምግብ ጥንቃቄ እየተደረገበት ከሁለት ሳምንት በላይ ከቆየ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን እነዚህ ተመሳሳይ ህመሞች ስር እየሰደዱ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል። ይሄ እንዳይሆን ወደሚመለከተው የህክምና ባለሞያ በመሄድ መፍትሔ ማግኘት ያስፈልጋል። ምርመራውም በቀላሉ በኢንዶስኮፒ የሚደረግ ነው።


ሰንደቅ፡- ችግሩ ውስብስብ ከሆነ እና ከሌሎች ችግሮች ለመለየት አስቸጋሪ ከሆነ ህክምናውም ቀላል አይሆንም። እስካሁን ያለው ህክምና ምን ይመስላል?


ዶ/ር አባተ፡- ወደ ህክምናው ስንመጣ በሁለት መልኩ ነው የሚሰጠው። የመጀመሪያው በሽታውን ያመጣውን ነገር ማከም ነው የሚሆነው። የበሽታው መንስኤ ባክቴሪያ ከሆነ ባክቴሪያውን ማከም፣ ሌሎች ወደ ሆድ የሚገቡ መድሐኒቶችና የምግብ አይነቶት ካሉ እነዚያን ማስተካከል ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጨጓራ የሚያመነጨው አሲድ መብዛት ከሆነ ችግሩን የሚያመጣው ያንን አሲድ ሊቀነሱ የሚችሉ መድሐኒቶችን በመውሰድ እንዲሁም ባክቴሪያውን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሊያጠፋ የሚችል መድሐኒት ይሰጣል። በዚህ መልኩ ባክቴሪያን የሚያጠፉ መድሐኒቶችን በመስጠትና አሲዱን በመቀነስ ያለምንም ኦፕሬሽን በቁስለት ደረጃ ላይ የደረሰውን ጨጓራ ማዳን ይቻላል።


ከዚህ ደረጃ በላይ ሆኖ ጨጓራው የመቁሰልና የመድማት ደረጃ ላይ ከደረሰም በኢንዶስኮፒ መሳሪያ በቀላሉ ማዳን ይቻላል። በዚህ መሳሪያ በመጠቀም የሚደማውን ቦታ በመርፌ በመውጋት ወዲያው ቀጥ ማድረግ ይቻላል። በተጨማሪም መቆንጠጫ በሚመስሉ መሣሪያዎች የሚደማውን ቦታ በመቆንጠጥ ማዳን ይቻላል። በሶስተኛ ደረጃም በኢንዶስኮፒ በመጠቀም የሚደማው ቦታ ላይ ሙቀት በመስጠት የሚደማው ደም ስር እንዲኮማተር በማድረግ ማዳን ይቻላል።


የመጨረሻው እና ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚሰጠው ህክምና ኦፕሬሽን ነው። የጨጓራ እና የትንሹ አንጀት ብዙ ጊዜ ሲቆስል ሲድን እና ሲደጋገም የመኮማተር እና የመጥበብ ሁኔታ ስላለ ጠባሳ ስለሚፈጥር ይጠብና ከጨጓራ ወደ አንጀት ያለውን መተላለፊያ ይዘጋዋል። በዚህ ጊዜ ምግብ ወደውጪ ስለሚመለስ የሰውነት መክሳት ይፈጠራል። በዚህ ደረጃ ላይ ህክምና ካልተገኘም ጠባሳው ወደ ጨጓራ ካንሰር ያመራል። ለእነዚህ ችግሮች የሚያስፈልገው ህክምናም ኦፕሬሽን ነው። ስለዚህ ኦፕሬሽን የሚያስፈልገው የተጨማደደውን እና ጥበት የፈጠረውን የጨጓራ አንጀት መገናኛውና ለመክፈት ወይም ወደ ካንሰርነት ከተቀየረ ያንን ቆርጦ ለማውጣት ነው እንጂ ሌላው በቀላሉ በኢንዶስኮፒ ይታከማል።

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1343 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 939 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us