ጤናማ አፍ የመላው ሰውነት ጤንነት መስታወት ነው

Wednesday, 28 March 2018 12:47

 

የዓለም የአፍ ጤና ቀን በየአመቱ ማርች 20 ቀን ይከበራል። እለቱ በሃራችንም መከበር ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የአፍ ጤና ከመላው የሰውነት ክፍል ጤንነት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎች ይገልጻሉ። የአሜሪካ ጥርስ ጤና ማህበር እንደሚገልፀው ደግሞ “አፍ የሌላው ሰውነት ማሳያ መስታወት ነው” ሲል ያስቀምጠዋል። የአፍ ጤና መታወክ ለመላው ሰውነት ጤንነት መታወክ ምልክትም ነው። የአፍ ጤንነት ከሌላው የሰውነት ክፍሎች ጤንነት ጋር ያለው ቁርኝት ምን እንደሆነ ማስገንዘብም ቀኑ የሚከበርበት ዋናው አላማ ነው። የዓለም ጤና ድርጅትም አለም አቀፉን የአፍ ጤና ቀን አስመልክቶ የተለያዩ ግንዛቤ መፍጠሪያ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።

 

የሰው ልጅ አፍ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች ያሉበት የሰውነት ክፍል ነው። ከእነዚህ ባክቴሪያዎች መካከል የተወሰኑት ለሰውነት ጎጂ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግም ምንም ዓይነት ጉዳት በሰውነት ላይ የማያደርሱ ናቸው። አፋችን ንፁህ እና ጤናማ ከሆነ የእነዚህ ባክቴሪያዎች መኖር አያስቸንቀንም። ነገር ግን የአፋችን ጤንነት ያልተጠበቀ ከሆነ እነዘህ ጎጂ ባክቴሪያዎች በአፋችን ውስጥ ኢንፌክሽን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታዎችን ያገኛሉ። በዚህን ጊዜ ሰውነታችን እነዚህን ጎጂ ባክቴሪያዎች ለመቋቋም እና ለመታገል ስለሚገደድ ሌሎች ኢንፌክሽኖችን ለመቋቋም ይቸገራል።


ችግሩ እዚህ ላይ ብቻ የሚያቆም ሳይሆን ሌሎች ተያያዥ ችግሮችንም እንደሚያመጣ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል። ሰውታችን ይሄንን ኢንፌክሽን ለመቋቋም ሲል የተለያዩ ኢንዛይሞችና በርካታ ኬሚካሎችን ያመነጫል። እነዚህ ኢንዛይሞች እና ኬሚካሎችም የድድ ህዋሳትን እና ጥርስን የሚደግፉ አጥንቶችን የማበስበስ እና የመጉዳት ባህሪይ አላቸው። በተጨማሪም እነዚህ ወደሰውነት የሚለቀቁ ኬሚካሎች በልብ ህዋሳት እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።


ሌላው የአፍ ጤንነት እና የሰውነት ጤንነትን ቁርኝት የሚያጠናክረው የባክቴሪያ ወደሌላ ሰውነት መዛመት ባህሪይ ነው። እንደማንኛውም ባክቴሪያ በአፍ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎችም ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የመዛመት ባህሪይ አላቸው። በመሆኑም እነዚህ ባክቴሪያዎች ከአፋችን በመነሳት ወደ ልብ፣ ወደ ጉበት እንዲሁም ወደ ጣፊያ በመዛመት በእነዚህ የሰውነት ክፍሎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ያደርሳሉ። በእነዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት የአፍ ጤንነት መታወክ በአጠቃላይ ከስኳር ህመም፣ ከልብ ህመም፣ ከመተንፈሻ አካላት ህመም እንዲሁም ከተወሰኑ የካንሰር ህመሞች ጋር ተያያዥነት አለው። የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በ2015 በዓለማችን ላይ 56 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 39 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች የሞቱት ተላላፊ ባልሆኑ የህመም አይነቶች ምክንያት ነው። ከእነዚህ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች በቀዳሚነት የተቀመጡት የልብ ህመም፣ ካንሰር፣ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች እና የስኳር ህመም መሆኑን ያስቀመጠው የድርጅቱ መረጃ፤ ለእነዚህ በሽታዎች ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከልም የአፍ ጤና መታወክ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ያስረዳል። በአፍ ጤና መታወክ ምክንያትም በአለማችን ላይ በየዓመቱ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሰዎች እንደሚታመሙ ተገልጿል።


የአፍ ጤናን የሚያስተጓጉሉ ነገሮች በአብዛኛው በግለሰብ ባህሪይ እና የአኗኗር ዘይቤ ሳቢያ የሚከሰቱ እና የሚባባሱ መሆናቸውን ነው የድርጅቱ መረጃ የሚጠቁመው። እነዚህ ባህሪያት እና ያልተስተካከለ የኑሮ ዘይቤ የተባሉትም ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር፤ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ የሆነ አልኮልን መጠጣት፣ እንዲሁም የአፍን ንፅኅና አለመጠበቅ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና ተዘጋጅተው በታሸጉ ምግቦች እንዲሁም በተለያየ ለስላሳ መጠጦች ውስጥ የሚገኝ ስኳርን መጠቀም እንዲሁም በተለያዩ መልክ የሚገኙ የትንባሆ ዝርያዎችን መጠቀም ለድድ ህምም እና ለጥርስ መበስበስ ከመዳረጉም በተጨማሪ ለስኳር ህመም፣ ለልብ ህመም እንዲሁም ለመተንፈሻ አካላት ህምሞች እና ለአፍ ካንሰር በማጋለጥ በዓለማችን ላይ ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት መንስኤ ነው ይላል የድርጅቱ መረጃ። ከ200 በላይ ለሆኑ ህመሞች መንስኤ እንደሆነ የሚገልጸው ከመጠን ያለፈ የአልኮል ተጠቃሚነት ከሚያስከትላቸው የጤና መታወኮች መካከልም የአፍ ካንሰር እና የጥርስ መበስበስ ተጠቃሾች ናቸው። በአልኮል ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የስኳር ይዘት ጥርስን በቀላሉ የማበላሸት እና የማበስበስ ባህሪይ አለው።


ጤንነቱ ያልተጠበቀ አፍ በመላው የሰውነት ክፍሎች ላይ የጤና መታወክን እንደሚያስከትለው ሁሉ ጤናማ አፍ ደግሞ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ጤናማ ተግባራትን ለማከናወን ያግዛል። የመጀመሪያው ጠቀሜታም የስኳር ህመምን መቆጣጠር ማስቻሉ ነው። የስኳር ህመምተኛ ሰው በደሙ ውስጥ ስኳርን ወደ ሃይል ለመቀየር የሚያግዘው የኢንሱሊን ሆርሞን እጥረት አለበት። በአፍ ውስጥ የሚፈጠር የባክቴሪያ መቆጣት ይሄንን ችግር በማባባስ ኢንሱሊን ስራውን በአግባቡ እንዳያከናውን ያደርገዋል። በዚህም ሳቢያ የስኳር ህመሙን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል። ስለዚህ የአፍ ጤንነትን መጠበቅ ከላይ የተጠቀሰውን ችግር በቁጥጥር ስር ለማዋል ያግዛል።


የልብ ህመም ካለባቸው ሰዎች መካከል 91 በመቶዎቹ የድድ ህመም እንዳለባቸው የድርጅቱ መረጃ ያለመለክታል። የልብ ህመም እና የድድ ህመም በአብዛኛው ተመሳሳይ መንስኤዎች እንደሏቸው የሚገልፁ ጥናቶችም አሉ። እንደጥናቶቹ መረጃም በአፍ ውስጥ የሚፈጠሩ የሰውነት መቆጣቶች በደም ስሮች ላይም የመቆጣት እድልን የማሻቀብ ባህሪይ ስላላቸው ለልብ ህመሞች እና ለስትሮክ የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።


ጤንነቱ ያልተጠበቀ አፍ በተለይ በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ችግር የከፋ ነው። የድድ ህመም ያለባቸው ሴቶች የመወለጃ ቀናቸው ያልደረሰ ልጆችን የመውለድ፤ ቀናቸው ደርሶ ቢወልዱም ከሚፈለገው ያነሰ ክብደት ኖሯቸው የሚወለዱ ልጆችን የመውለድ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በእርግዝና ወቅት በሰውነት ላይ የሚከሰቱ የሆርሞን ለውጦች ሴቶች ለድድ ህመም የሚኖራቸውን ተጋላጭነት ይጨምረዋል የሚሉት ተመራማሪዎቹ፣ ግማሽ ያህሎቹ ሴቶችም የዚህ ችግር ተጋላጭ ናቸው ይላሉ።


በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት አንድ ሰው ጤናማ አፍ አለው የሚባለው ከማንኛውም አፍ እና የፊት ጤንነት መታወክ ነጻ ሲሆን እንዲሁም ከአፍ እና ከጉሮሮ ኢንፌክሽን እና ቁስለት የፀዳ፣ የድድ እና የጥርስ ህመም እና መበስበስ የሌለበት ሲሆን፣ ጥርሱ ያልወለቀ እና በሌሎች ተያያዥ ህመሞች ምክንያት የመንከስ፣ የማኘክ፣ ፈገግታ የማሳየት፣ የመናገር እና ሌሎች ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ ተግባራትን ለማከናወን የማይቸገር ሲሆን ነው። ድርጅቱ እንዳስቀመጠውም ከአፍ ጤንነት መታወክ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና እክሎች በታዳጊ ሀገራት ላይ ላሉ ሰዎች እጅግ ወድ ከሆኑ በሽታዎች መካከል በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
639 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1011 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us