እርጅናን ሊያዘገዩ የሚችሉ ምግቦች

Wednesday, 11 April 2018 14:43

 

በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ ረጅም እድሜን በመኖር ቀዳሚዎች የሆኑት ህዝቦች የሞናኮ፣ የጃፓን እና የሲንጋፖር ዜጎች ናቸው። በእነዚህ ሀገራት ያሉ ዜጎች ረጅም ዕድሜን መኖር ብቻም ሳይሆን ጥሩ እና ጤናማ ህይወትን እንደሚመሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህ ረጅም እድሜ የመኖር ምስጢሩ የተለየ ነገር ሳይሆን ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት ስላላቸው እና ለዚህ ጠቃሚ የሆኑ የምግብ አይነቶችን በማዘውተራቸው ነው ይላል ሜዲካል ኒውስ። እርጅና ለፍጡራን ሁሉ የማይቀር የእድሜ ሽክርክሪት ቢሆንም ያለ ጊዜው ሲከሰት ግን ከዚህ ሽክርክሪት ውጪ ይሆናል። በአብዛኛው ብዙም ልብ ሳንል የምናደርጋቸው ነገሮች ቀን እየጨመረ ሲሄድ ይሄንን ክስተት ያስከትላሉ። በተለይ አመጋገብን በተመለከተ ለአፍ የጣፈጠ እና ቀላል የሆነን ነገር ሁሉ መመገብ የማርጀት ሂደቱን ማፋጠን ነው ይላል የሜዲካል ኒውስ ዘገባ። በመሆኑ በየዕለት የአመጋገብ ስርዓታችን ውስጥ ለተለያዩ የጤና እክሎች በመዳረግ የእርጅና ጊዜን ከሚያፈጥኑ ነገሮች ራስን መከላከል የሚቻልበትን መንገድ የተለያዩ ጥናቶችን በመጥቀስ ያቀርባል። እርጅናን ሊያዘገዩ የሚችሉ የምግብ አይነቶችም የሚከተሉት ናቸው ይላል ዘገባው።


ቦሎቄ


ቦሎቄ አይስፍላቮን በተባሉ እና ካንሰርን የመከላከል ጠቀሜታ ባለው ንጥረ ነገር የበለፀገ የእህል ዘር ነው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች በተጨማሪም የሰውነት መቆጣትን፣ እንዲሁም ባክቴሪያዎችን የመከላከል ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ውጤት የሆኑ የስትሮጂን አይነቶች ናቸው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ሰውነት ለመቆጣት የሚሰጠውን ምላሽ የማስተካከል፣ የሰውነት ህዋሳት ማርጀት ካለባቸው ጊዜ ቀድመው እንዳያረጁ የማድረግ እንዲሁም ረቂቅ በሽታ አምጪ የሆኑ ህዋሳትን (Microbes) የመከላከል እና የተወሰኑ የካንሰር አይነቶችን የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው።


ቦለቄ ከላይ ከተጠቀሱት ውህዶች በተጨማሪም ጄኒስቴን እና ዳይድዜይን የተባሉ የአይስፍላቮን አይነትን በብዛት የያዘ የእህል ዘር ነው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ የጡት ካንሰርን ለማከም የሚያገለግሉ ንጥረ ነገሮች እንደሆኑም ሜዲካል ኒውስ ቱዲይ የተባለው ተቋም ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ገልጿል። ይህ የእህል ዘር በተለይ የሰውነት ህዋሳት ያለጊዜያቸው እንዳያረጁ በማድረግ ያለ እድሜ የሚከሰትን እርጅናል በመከላከሉ ረገድ ያለውን ጠቀሜታ የጎላ ያደርገዋል።

 

ካሮት


በካሮት ውስጥ በብዛት ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች መካከል ዋናው እና ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ቤታ ካሮቲን የተባለው ንጥረ ነገር ነው። ይህ ንጥረ ነገር ካሮቱ የተፈጥሮ ቀለሙን እንዲይዝ የሚያግዝ ማቅለሚያ ነው። እነዚህ ማቅለሚያዎችም በሰውነታችን ውስጥ ባሉ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮች አማካነት ወደ ቫይታሚን ኤ ይቀየራሉ። (የሰው ልጅ ሰውነት ቫይታሚን ኤን በራሱ ማምረት የማይችል ሲሆን፤ ማግኘት የሚችለው እና አገልግሎት ላይ የሚያውለው ከምንመገባቸው ምግቦች ነው) ይሄ ከቤታ ካሮቲን የሚገኘው ቫይታሚን “ኤ” ም የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም እንዲጠናከር፣ የአይን እይታ የተስተካከለ እንዲሆን፣ ጤናማ የመራባት ሂደት እንዲኖር እንዲሁም የህዋሳት ግንኙነት ጤናማ እና የተስተካከለ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ሰፊ የሆነ ጠቀሜታ አለው።


ሌላውና ዋናው የዚህ ማቅለሚያ ጠቀሜታ የሰውነት ህዋሳት በፍሪራዲካልስ ምክንያት እንዳይጠቁ እና ያለጊዜያቸው እንዳያረጁ ማድረጉ ነው። ይሄ የሚሆነውም ማቅለሚያው ባለው የአንቲ ኦክሲደንትነት ባህሪይ ምክንያት ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዚህ ካሮቲኖድ በተባለ የተፈጥሮ ማቅለሚያ የበለፀጉ እንደካሮት ያሉ አትክልቶች ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰትን የአይን ጡንቻዎች መዳከም በመከላከል እና የእይታ መዳከምን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው።


በኒው ካስል ዩኒቨርስቲ በተደረገ ጥናት ማረጋገጥ የተቻለውም ካሮትን በተለይ በጥሬው መመገብ የምግብ ይዘቱን ሳይለቅ ለመመገብ ስለሚጠቅም ከበሰለው ይልቅ ተመራጭ ነው። የጥናቱ ተሳታፊ የሆኑት ዶክተር ክሪስቲን ኮራኒዲን እንደገለፁትም ካሮት ተቆርጦ ወይም ተከትፎ በሚቀቀልበት ወቅት የምግብነት ይዘቱ በቀላሉ ወደ ውሃ የመዛመት ባህሪይ ስላለው ቀቅሎ በመክተፍ እና ለውሃ የሚጋለጠውን የካሮት አካል መጠን በመቀነስ ማግኘት ያለብንን ጠቀሜታ ማግኘት ይቻላል።

 

አረንጓዴ አትክልቶች


አትክልትና ፍርፍሬዎች ለሰው ልጅ ጤንነት ያላቸው ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በተደጋጋሚ የሚጠቀስ እና ብዙዎችም የሚስማሙበት ነው። ከእነዚህ ጠቀሜታዎቹ መካከልም ያለ እድሜ የሚመጣ ማርጀትን መከላከል አንዱ ነው። በተለይ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው እንደ ጎመን፣ ሰላጣ እና ቆስጣ እና ሌሎችም ያለእድሜ የሚመጣን እርጅና ለመከላከል ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ጥናቶች አመልክተዋል። በአረንጓዴ አትክልቶች ውስጥ ከሌሎች የምግብ አይነቶች የበለጠ የቫይታሚን ሲ፣ ኢ እና ኬ ይዘት ያለው ሲሆን፤ በተጨማሪም እንደፖታሲየም፣ ካልሲየም እና ሴለኒም የተባሉ ማዕድናትም በብዛት ይገኛሉ። በተጨማሪም እንደ ሉቴን፣ ቤታ ካሮቲን እና ዚአክዛንቲን በተባሉ ተፈጥሯዊ እና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ናቸው።


አረንጓዴ አትክልቶች አረንጓዴ ቀለም እንዲኖራቸው በሚያደርግ ግሉኮሲ ኖሌት በተባሉ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ በመሆናቸው ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እነዚህ በአረንጓዴ አትክልቶች ውስጥ የሚገኙ ግሉኮሲኖሌቶችም ሰውነት ለጭንቀት፣ ለሰውነት መቆጣት እና በሽታ አምጪ ተዋሲያን ሲገጥሙት የሚሰጠውን ምላሽ በማስተካከል የተሟላ ጤንነት እንዲኖረን ያግዛሉ። ከዚህ በተጨማሪም እድሜ እየጨመረ ሲሄድ የሚከሰተውን የአስተሳሰብ እና የግንዛቤ ደረጃ ከሚቀንሱ ችግሮች በመከላከል ለአእምሮ ጤንነት ጠቃሚ ናቸው። እንደ ጎመን እና ቆስጣ ያሉት ባለአረንጓዴ ቀለም አትክልቶችም ከፍተኛ የሆነ የቫይታሚን ኬ ይዘት ስላላቸው የልብ ጤንነትን በመጠበቁ ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።


አረንጓዴ አትክልቶች በቫይታሚኖችና ማዕድናት ብቻም ሳይሆን በቀላሉ ሊሟሙ የሚችሉ አሰሮች (soluble fiber) የበለፀጉ ናቸው። ይህ ይዘታቸውም የደም የስኳር መጠን የተስተካከለ እንዲሆን፣ ትርፍ እና አላስፈላጊ የሆነ ስብ በሰውነት ውስጥ እንዳይከማች በማድረግ ያለ እድሜ ለማርጀት አንዱ ምክንያት የሆነውን ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለመከላከል ያግዛል።

 

ዓሳ


ስጋን አዘውትሮ መጠቀም ከጊዜ በኋላ ለተለያዩ የጤና እክሎች እንደሚዳርግ የተለያዩ ጥናቶች በየጊዜው ያስረዳሉ። የስጋ ተጠቃሚነታችን እየቀነሰ በሄደ ቁጥር ከስጋ ማግኘት ያለብን የፕሮቲን ንጥረ ነገርም እየቀነሰ ይሄዳል። ይሄንን ፕሮቲን መተካት ከሚቻልባቸው የምግብ አይነቶች አንዱ አሳ ነው። አሳ የፕሮቲን ይዘቱ ከፍተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ኦሜጋ 3 በተባለ ፋቲ አሲድ ይዘቱም ተጠቃሽ ነው። ይህ ፋቲ አሲድም እድሜ እየጨመረ ሲሄድ አይን በቂ የሆነ ማለስለሻ በማጣቱ ሳቢያ ለድርቀት ተዳርጎ ጠባሳ እንዳይፈጠር እና የእይታም ቭዥታ እንዳይፈጠርበት ያግዛል። በተጨማሪም እድሜን ተከትሎ የሚመጣን የማገናዘብ ችግር የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ስለሆነ አእምሮ እድሜ እንኳን ቢገፋ ጥሩ የማገናዘብ እና የማስታወስ ችሎታ እንደያዘ እንዲዘልቅ ያግዛል።


ሌላው በአሳ ውስጥ በብዛት የሚገኙት የፖታሲየም እና ሴሌኒም ማዕድናት ናቸው። የፓታሲየም ማእድን ይዘቱ ከልብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችግሮች ለመከላከል የሚያግዝ ሲሆን፤ የሴሌኒም ማዕድን ይዘቱ ደግሞ የታይሮይድ እጢን ጤንነት ለመጠበቅ ያገለግላል። ይህ የታይሮይድ እጢ በሰውነት የሚኖረውን የሆርሞኖች እንቅስቃሴ እና ተግባር የሚቆጣጠር እና ምግብ ወደ ሃይል የሚቀየርበትን ሂደት (metabolic processes) የሚከታተል እና የሚያስተካክል የዕጢ አይነት ነው።

 

አሲዳማ ፍራፍሬዎች


የተለያዩ የአሲድ አይነቶች ያሏቸው ፍራፍሬዎች ከአሲድነታቸው ጋር ተያይዘው የሚገኙ በርካታ የጤና ጠቀሜታች አሏቸው። ሲትሪክ አሲድ በተባለው የአሲድ አይነት ይዘታቸው የሚታወቁት እንደ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ መንደሪን እና የወይንፍሬ ያሉት የፍራፍሬ ዝርያዎችም ያለ እድሜ የሚከሰት እርጅናን የመከላከል ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። እነዚህ ፍራፍሬዎች ከአሲድ በተጨማሪም በቫይታሚን ሲ ይዘታቸው የታወቁ በመሆናቸው እና የአንቲ ኦክሲዳንትነት ባህሪይ ስላላቸው ለሰውነት መቆጣት ያለውን ተጋላጭነት የመቀነስ እና ኢንፌክሽንን የመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።


በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱትም እነዚህ ፍራፍሬዎች ከፍተኛ የሆነ ጤናማ ስኳር፣ ጠቃሚ አሰር፣ የፖታሲየም፣ ካልሲየም፣ ፎስፈረስ፣ ማግኒዚየም እና መዳብ ማዕድናት፣ ቫይታሚን ቢ-6 እንዲሁም ፎሌት ይዘት ያላቸው ናቸው። በተጨማሪም ልክ እንደካሮት እና መሰል አትክልቶች ካሮቲኖድ የተባለው ማቅለሚያ እና ጣዕም መፍጠሪያ ስላላቸው ካንሰርን የመከላከል፣ የልብ እና ከልብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችግሮች የማስወገድ እንዲሁም በአእምሮ ላይ የሚከሰትን ከእድሜ ቀድሞ የማርጀት ችግር እና ነርቮችን የሚያጠቃውን ችግር የመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። በተጨማሪም እንደ ካንሰር ያሉ እና ሌሎች ስር ሰደው የእድሜ ልክ ችግር የሚሆኑ የጤና እክሎችን በማስቀረት ከእድሜ ቀድሞ የሚከሰት እርጅናን ለመከላከል ያግዛሉ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
703 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1022 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us