የወንዶች ሥጋት የሆኑ የጤና ችግሮች

Wednesday, 18 April 2018 13:13

     የወንዶች ጤና ኔትዎርክ (MHN) እንደሚገልፀው ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በከፍተኛ መጠን በለጋነት እድሜያቸው የመሞት እድል አላቸው። ተቋሙ ሴንተር ፎር ዲዝዝ ኮንትሮል (CDC) ያደረገውን ጥናት ጠቅሶ ባወጣው መረጃ የገለፀውም ወንዶች ከሴቶች በበለጠ ዋና ዋና ገዳይ በተባሉ በሽታዎች ሳቢያ በወጣትነት እድሜያቸው ይሞታሉ። ምንም እንኳን በሽታን በመቋቋም ረገድ ወንዶች የበለጡ ናቸው ተብሎ ቢታሰብም ወደ እውነታው ሲመጣ ግን ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት በለጋነት እድሜያቸው ይሞታሉ። ይህ ክስተት ቀደም ሲል ከነበረበት መጠንም እየጨመረ መምጣቱን ያስነበበው ዘገባው፤ ለአብነት ያህልም እ.ኤ.አ. በ1920 ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ በህይወት የመኖር እድላቸው በአንድ ዓመት ይበልጥ ነበር። አሁን ባለው መረጃ መሠረት ግን ሴቶች ከወንዶች ይልቅ አምስት ተጨማሪ ዓመታትን በህይወት የመኖር እድል አላቸው።

የወንዶች ጤና ኔትዎርክ የቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር ጂን ቦንሆም እንገለጹትም ወንዶች በህይወት የመኖሪያ እድሜያቸው እንዲያጥር ምክንያት የሆነው እነዚህ የበሽታ አይነቶች በከፍተኛ ደረጃ ወንዶችን የሚያጠቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ወንዶች ጤንነታቸውን የመከታተል ልምድ ስለሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም በማህበረሰቡ ዘንድ ስለ ወንድ ልጅ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ሌላው ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ቦንሆም አስቀምጠዋል። በየትኛውም ማህበረሰብ ዘንድ ወንዶች ጠንካራ እና ህመም የማይሰማቸው አድርጎ ማሰብ ውጤቱ ለእንዲህ አይነት ችግር መንስኤ ነው ብለዋል። በየጊዜው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በባለሞያ በመታየት ረገድ ሴቶች በ33 በመቶ ከወንዶች በልጠው መገኘታቸውንም መረጃው አመልክቷል። ወንዶች በዚህ ደረጃ ከሴቶች የበለጠ በወጣትነት እድሜያቸው እንዲቀጠፉ የሚያደርጋቸው የበሽታ አይነቶች በአብዛኛው መከላከል የሚቻል በሽታዎች ናቸው ያለው መረጃው ዋና ዋናዎቹንም እንደሚከተለው አስቀምጧቸዋል።

የልብ ህመም

ምንም እንኳን የልብ ህመም ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ሞት ቀዳሚው ምክንያት ቢሆንም፤ ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በእጥፍ ቁጥር የበለጠ በዚህ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን በወጣትነታቸው ያጣሉ ይላል የተቋሙ ጥናት። የልብ ህመም መገለጫ የሆኑ ምልክቶች የሚታዩበት ጊዜ በተመሳሳይ እድሜ ላይ ባሉ ወንዶችና ሴቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው የገለፀው መረጃው፤ ይኸውም ምልክቶቹ በወንዶች ላይ መገለጥ የሚጀምሩት ከሴቷ በአስር ዓመት በፊት ነው ብሏል። በዋኪ ፎረስት ዩኒቨርስቲ ህክምና ትምህርት ቤት የማህበረሰብ ጤና መምህሩ ዶክተር ግሪጎሪ ቡርኬ እንደገለፁትም የመጀመሪያው ድንገተኛ የልብ ድካም ችግር የሚፈጠርበት አማካይ እድሜ ለወንዶች 65 አመት ገደማ ሲሆን፣ ለሴቶች ደግሞ 70 ዓመት ገደማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ የልብ ድካም ችግሮችም ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ በፍጥነት ስር ወደሰደደ የልብ እና ከልብ ጋር ተያያዥነት ወዳላቸው በሽታዎች የመቀየር ባህሪይ እንዳለው ዶክተር ቡርኬ ገልጸዋል። ለልብ ህመም አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች አንዱም ወንድ መሆን እንደሆነ መረጃው አመልክቷል።

ስትሮክ

የአሜሪካ ስትሮክ አስሲየሽን መረጃ እንደሚያመለክተው ወንዶች ለስትሮክ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከሴቶች ይልቅ በ1 ነጥብ 25 እጥፍ ብልጫ አለው። እድሜ እየገፋ ሲሄድ ሴቶችም ለስትሮክ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው እየጨመረ መሄዱ እሙን ቢሆንም፤ በለጋነት እድሜ ለችግሩ በመጋለጥ ረገድ ወንዶች የበለጠ ተጠቂዎች መሆናቸውን ነው መረጃው ያስቀመጠው። ስትሮክ በአብዛኛው ከልብ ህመም እና ከከፍተኛ የደም ግፊት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው የገለፁት ባለሞያው ወንዶች እስከ 75 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው።

ጭንቀትና ራስን ማጥፋት

የወንዶች ጤና ኔትዎርክ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ራስን በማጥፋት አደጋ ህይወታቸው የሚያልፍ ወንዶችና ሴቶች ቁጥር ሲነፃፀር የወንዶቹ በአራት እጥፍ ከሴቶቹ ይበልጣል። ለዚህ ደግሞ ዋንኛው መንስኤ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው፤ ነገር ግን ስር የሰደደ ጭንቀት ነው። በሃርቫርድ ህክምና ትምህርት ቤት ክሊኒክ ፕሮፌሰሩ ዶክተር ዊሊያም ፖላክ እንደሚገልፁት ወንዶች የሚሰማቸውን የጭንቀት እና የድብርት ስሜት በግልጽ መናገር እና ማሳየት ካለመቻላቸው የተነሳ ራሳቸውን ለማጥፋት ይገደዳሉ። ከዚህ ባህሪያቸው የተነሳ ሌሎች ሰዎች ጭንቀታቸውን በቀላሉ አይተው ስለማይረዷቸው እና ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ስለሚገቡ ራሳቸውን ማጥፋትን እንደመፍትሄ ይወስዱታል። ፕሮፌሰር ፖላክ እንደሚገልፁትም ወንዶች የድብርት እና የጭንቀት ስሜት ምልክቶችን በተለየ መንገድ ስለሚገልፁት ከሴቶች የበለጠ በጭንቀት ተጠቂ ናቸው። ወንዶች እነዚህን ስሜቶች በሀዘን መልክ ከመግለፅ ይልቅ በንዴት፣ በቁጣ፣ ነገሮችን በድፍረት በመጋፈጥ እንዲሁም ከመጠን በላይ የሆነ የአልኮል መጠጥን በመጠጣት ስለሚገልፁት እና እነዚህ ባህሪያት ደግሞ የወንድነት ባህሪይ ተደርገው በመታሰባቸው ችግራቸውን በቀላሉ መረዳት አይችሉም። ወንዶቹ ራሳቸውም ምልክቶቹ ከችግር የመነጩ ሳይሆን የወንድነታቸው መገለጫዎች ስለሚመስሏቸው እንደ ትልቅ ችግር አይተው መፍትሄ እንደማይፈልጉላቸው የገለፁት ፕሮፌሰር ፖለክ፤ ጊዜ እየጨመረ ሲሄድ ግን የሚፈጠረው ውዝግብ ራስን ለማጥፋት ቀዳሚው መንስኤ ይሆናል።

የሳንባ ካንሰር

የሳንባ ካንሰር ከጡት ካንሰር፤ ከትልቁ አንጀት ካንሰር እና ከፕሮስቴት ካንሰር ሁሉ በላይ ሞትን በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ በማድረስ ቀዳሚው የካንሰር አይነት መሆኑን የአሜሪካ ካንሰር አሶሲየሽን መረጃ ያመለክታል። ከላይ እንደጠቀሱት ህመሞች ሁሉ ይህ የሳንባ ካንሰርም ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን የበለጠ ያጠቃል። በአብዛኛው የዚህ ካንሰር መንስኤዎች ሲጋራ ማጨስ እና ትንባሆን በተለያየ መልኩ መጠቀም በመሆኑ እና ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው ስለሚገኙ በዚያው መጠን የችግሩ ተጠቂዎች መሆናቸውንም መረጃው አመልክቷል። ለሳንባ ካንሰር መንስኤ ከሆኑት ነገሮች ዘጠና በመቶው ሲጋራ ማጨስ እና የትንባሆ ተጠቃሚነት መሆኑን የገለፀው መረጃው፤ የተለያዩ ሀገራት ትንባሆ እና ሲጋራ የሚጨስባቸውን የተለያዩ ክልከላዎች በስራ ላይ ማዋላቸውን ተከትሎ የትምባሆ ተጠቃሚነቱ እየቀነሰ በመምጣቱ በሽታውም የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን አስቀምጧል።

ፕሮስቴት ካንሰር

ወንዶችን በዋናነት ከሚያጠቁ የካንሰር አይነቶች አንዱ ፕሮስቴት ካንሰር ነው። ከሳንባ ካንሰር ጀምሮም ወንዶችን በከፍተኛ ደረጃ ለሞት የሚዳርግ የካንሰር አይነት መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል። ይህ አይነቱ ካንሰር በምን ሳቢያ እንደሚመጣ እና በምን መልኩ መከላከል እንደሚቻል እስካሁን የታወቀ ነገር እንደሌለ ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት። ካንሰሩ በወንዶች የሽንት ፊኛ መግቢያ አፍ ላይ የሚገኝ ቱቦን የሚያጠቃ መሆኑ ብቻ ነው የተደረሰበት። ከዚህ ውጪ ግን ችግሩ መኖሩ በጊዜ እና ቀደም ብሎ ከታወቀ ግን ማከም እንደሚቻል ነው ዶክተር ቦንሆም የገለፁት። ይህ ችግር ከነጮች ይልቅ ጥቁሮችን፣ ከቤተሰባቸው ውስጥ መሰል ችግር የነበረበትን ሰው የማጥቃት እድል ስላለው ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ዶክተር ቦንሆም።    

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
541 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1157 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us