የዝናብ ውሃ የጤና ገፀ በረከቶች

Wednesday, 25 April 2018 12:39

ምንም እንኳን ወቅቱን ጠብቆ የሚገኝ ቢሆንም ተፈጥሮ ያለ ማንም ተቆጣጣሪነት ለሰው ልጅ ከሰጠቻቸው ነገሮች አንዱ የዝናብ ውሃ ነው። በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል እንዲሉ የዝናብ ውሃን ከሌሎች የውሃ አማራጮች እኩል የመጠቀም ሁኔታ ብዙም አይስተዋልም። በተለይ የውሃ አቅርቦቱ የተስተካከለ በሆነባቸው የከተማ አካባቢዎች የዝናብ ውሃን በችግር ጊዜ ከመጠቀም በዘለለ እንደመደበኛ ውሃ አገልግሎት ላይ ሲውል አይታይም። ነገር ግን የዝናብ ውሃ ከሌሎች በጸረ ጀርም እና በማዕድናት ከበለፀጉት የውሃ አይነቶች በበለጠ የራሱ የሆነ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በያል ዩኒቨርስቲ እና አውስትራሊያ ዩኒቨርስቲ የውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ይፋ የተደረጉ የጥናት ውጤቶች አመልክተዋል። የዝናብ ውሃ በተፈጥሮው ያለው ጤናማ የሆነ ይዘት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የጤና ጠቀሜታዎች እንዲሰጥ አድርገውታል ይላሉ ጥናቶቹ።

ከጠቀሜታው በተጓዳኝም የዝናብ ውሃን በተመለከተ ሊወሰዱ የሚገባቸው ሁለት ጥንቃቄዎች እንዳሉም ጥናቶቹ አመልክተዋል። የመጀመሪያው የዝናብ ውሃ ከአፈር ወደ ውሃ የሚገቡ እንደ ሶዲየም፣ ፖታሲየም፣ ካልሲየም እና ፍሎራይድ ማዕድናት ስለሌሉት ከዚህ ውሃ የማናገኛቸውን ጠቃሚ የማዕድን አይነቶች በሌሎች መጠጦች እና ምግቦች አማካይነት መጠቀም እና መተካት ይኖርብናል። ሁለተኛው ጥንቃቄ ደግሞ ውሃው ከላይ በሚወርድበት ወቅት እንደጀርም ላሉ በካይ ነገሮች ያለውን ተጋላጭነት በሚያስቀር መልኩ መጠራቀም ይኖርበታል። ውሃው መሬት ደርሶ አልያም በተለያዩ ቁሳቁሶች ተጠራቅሞ አገልግሎት ላይ መዋል ግዴታው ከሆነም ከእነዚህ በካይ ነገሮች ሊፀዳ በሚችልባቸው የማጣራት ወይም የማፍላት ሂደቶች ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል።

ለስርዓተ ልመት እና ሰውነት ማጥራት ያግዛል

የአልካላይን ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ የውሃ አይነት በሰውነት ውስጥ የሚከናወኑ የምግብ ስርዓተ ልመቶች የተስተካከሉ እና ጤናማ እንዲሆኑ ያግዛል። በተጨማሪም ሰውነት አላስፈላጊ እና መርዛማ የሆኑ ነገሮችን የሚያስወግድበት ስርዓት (detoxification system) የተመቻቸ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በመሆኑም የዝናብ ውሃ በደም ውስጥ ያለው (የውሃን አሲዳማነት መሳቢያው) የፒ ኤች (PH) መጠን ለሰውነት ተስማሚ በሆነ ደረጃ እንዲገኝ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በሰውነት ውስጥ የሚገኙ መርዛማ ነገሮች እና ፍሪ ራዲካልስ በደም ውስጥ ያለው የፒ ኤች መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የአሲድነት ባህሪው እንዲጎላ የማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖን የሚፈጥሩ ሲሆን፤ የዝናብ ውሃን በምንጠጣበት ጊዜ ይሄን የተዛባ ስርዓት በማስተካከል ሰውነት በተቀላጠፈ መንገድ ስራዎቹን እንዲያከናውን ያግዘዋል ይላል መረጃው። በዚህ ሳቢያ ተግባራቸው ከሚቀላጠፍ ስርዓቶች መካከልም ዋና ዋናዎቹ የምግብ ልመት ስርዓት እና መርዛማ ነገሮችን የማስወገድ ስርአት ናቸው።

የጨጓራ ህመም፣ ራስ ምታት እና የህዋሳት ጉዳትን ይከላከላል

የዝናብ ውሃ ከክሎሪን እና ከፍሎራይድ ኬሚካሎች የፀዳ ነው። የቧንቧ ውሃ አሊያም የታሸጉ የውሃ አይነቶችን ከተለያዩ ጀርሞች ለመከላከል ሲባል ክሎሪን እና ፍሎራይድ እንዲገባባቸው ይደረጋል። እነዚህ ኬሚካሎች መጠናቸው ከሚገባው በላይ ሆኖ ሲገኝም እንደ ራስ ምታት፣ የጨጓራ ህመም እንዲሁም በአንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ላይ የመጎዳት ሁኔታን ይፈጥራሉ። የዝናብ ውሃን በምንጠቀምበት ወቅት ግን ንፁህ የሆነ ውሃን ከማግኘታችንም በላይ ከእነዚህ ተያያዥ የጤና እክሎች ነፃ እንሆናለን።

ፀረ -ካንሰር ጠቀሜታ አለው

በዝናብ ውሃ ውስጥ የሚገኘው የውሃ አሲድነት ባህሪይ (ፒ ኤች) የካንሰር ሴሎችን በፍጥነት ማደግ እና መሰራጨት የመግታት ባህሪይ አለው። ይህ የዝናብ ውሃ ለእነዚህ የካንሰር ህዋሳት እንደ አንቲኦክሲደንት ስለሚሆንባቸው ህዋሳቱ እና እጢዎቹ በፍጥነት እንዳያድጉ ያደርጋቸዋል። ተፈጥረው የነበሩ የካንሰር አምጪ ህዋሳት ካሉም ስርጭታቸውን በመግታት ወደ በሽታነት የመቀየሪያ ጊዜያቸውን በማሳጠር ለህመሙ ያለውን ተጋላጭነት ይቀንሱታል።

በሆድ ውስጥ የሚከሰቱ ህመሞችን ይፈውሳል

በህንድ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ጠዋት ላይ በባዶ ሆዳቸው ከሁለት እስከ ሶስት የሻይ ማንኪያ የዝናብ ውሃ የሚጠጡ ሰዎች በሆዳቸው ውስጥ የሚሰማቸውን የህመም ስሜት በእጅጉ መቀነስ ችለዋል። በዝናብ ውሃ ውስጥ የሚገኘው ጤናማ እና የተስተካከለ የፒ ኤች መጠን በሆድ ውስጥ የሚገኘው አሲድ ተስማሚ እንዲሆን በማድረግ በአሲዱ ሳቢያ የሚከሰተውን መቆጣት ያስቀራል። በዚህ ባህሪው የተነሳም እንደ ቃር፣ የጨጓራ ህመም እና የጨጓራ ቁስለት ችግሮችን ለመቆጣጠር እና ለማስታገስ ያግዛል።

የቆዳ ጤንነትን ይጠብቃል

የዝናብ ውሃ ባህሪያት ከሆኑት አንዱ ከሳሙና ጋር ሲገናኝ በቀላሉ አረፋ መፍጠር መቻሉ ነው። በዚህም ሳቢያ በዝናብ ውሃ በምንታጠብበት ወቅት በሰውነታችን ላይ የሚያርፈው ሳሙና መጠን እንዲቀንስ እና በቀላሉ አረፋ እንድናገኝ ያግዘናል። ይኸውም ሰውነታችን (ቆዳችን) በሳሙና ውስጥ ላሉ ኬሚካሎች ያለውን ተጋላጭነት በመቀነስ ተፈጥሯዊ ይዘቱ እንዲጠበቅ ያግዛል። በተጨማሪም የዝናብ ውሃ ቀላል የሚባል የውሃ አይነት በመሆኑ ቆዳችን ተፈጥሯዊ እርጥበቱን እና የመሳሳብ ባህሪውን እንደያዘ እንዲቆይም ያግዘዋል። በመሆኑም አዘውትሮ በዝናብ ውሃ መታጠብ ቆዳችን ተፈጥሯዊ ይዘቱን የጠበቀ እና ብሩህ ቀለም ያለው እንዲሆን ያግዘዋል።

ሌላው የዝናብ ውሃ ለቆዳ የሚሰጠው ጠቀሜታ እንደ ብጉር ያሉ የቆዳ ህመሞችን ማስወገድ ነው። የዝናብ ውሃ በቀላሉ ቆዳን አጥርቶ ለመታጠብ እና ህመም ፈጣሪ የሆኑ ባክቴሪያዎችን ለማስወገድ ያግዛል። በተለይ በፊት ላይ እና በአንገት አካባቢ ብጉር እና መሰል ችግሮችን የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎችን ከቆዳ ላይ በማስወገድ እነዚህ ብጉሮች እብጠታቸው እንዲቀንስ እንዲሁም የሚፈጥሩት የህመም ስሜት እንዲቀንስ የማድረግ ጠቀሜታ አለው።

የፀጉር ጤንነት ይጠብቃል

የዝናብ ውሃ ከሌሎች የውሃ አይነቶች ይልቅ ከአፈር ከሚገኙ የተለያዩ ማዕድናት የፀዳ ነው። እነዚህ ከአፈር የሚገኙ ማዕድናት ፀጉርን በተለያየ መንገድ የመጉዳት ባህሪይ ስላላቸው በዝናብ ውሃ መታጠብ ከእነዚህ ማዕድናት ለመራቅ ያግዛል። በተጨማሪም ፀጉራችንን የምንታጠብበት ውሃ የአሲድነት ይዘት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ኬራቲን እና ፎሊክል የተባሉ ፀጉር የተሰራባቸው ንጥረ ነገሮች እየተጎዱ ይሄዳሉ። የዝናብ ውሃ ግን ያለው የአሲድነት ባህሪይ የተመጣጠነ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ያገለግላል። በተጨማሪም በዚህ ውሃ ውስጥ የሚገኘው አልካላይን ፒ ኤች ፀጉር በፍጥነት እንዲያድግ እና ስሮቹም ጠንካራ እንዲሆኑ የማድረግ ጠቀሜታ አለው።

የዝናብ ውሃ ቀላል ውሃ በመሆኑ ከከባድ ውሃ በበለጠ ፍጥት የኤሌክትሪክ ሃይል ያለው ኦቶም የመፍጠር (ionised) ባህሪይ አለው። በዚህ ባህሪውም በቀላሉ ወደ ደም በመግባት የመዋሃድ እና በሰውነት ውስጥ የሚኖረው የኦክሲጅን ዝውውር የተሳለጠ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በተጨማሪም ፍሪ ራዲካልስ የተባሉት እና ለሰውነት አላስፈላጊ የሆኑ ቁጡ የኦክሲጅን አይነቶችን ወደ ጤናማነት በመቀየር በሰውነት ህዋሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ያግዛል።

ከዚህ በተጨማሪም የዝናብ ውሃ ከሳሙና ጋር ሲገናኝ በቀላሉ አረፋ የመፍጠር ባህሪይ ስላለው ለማንኛውም አይነት እጥበት የሚያገለግል ሲሆን፤ በዚህ ባህሪውም የሚታጠቡት ነገሮች (ልብስን ጨምሮ) ተፈጥሯዊ ቀለማቸውን ይዘው ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
550 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 907 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us