በእጅ መመገብ ተመራጭ ነው

Wednesday, 02 May 2018 12:44

በእጅ መመገብ እንደ ህንድ ባሉ ሀገራት ከጥንት ጀምሮ ሲተገበር የነበረ ተግባር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራትም በአጅ የመመገብ ባህል እድሜ ጠገብ ከመሆኑም በላይ አሁንም ድረስ እየተተገበረ ያለ ድርጊት ነው። ምንም እንኳን እንደምንመገበው የምግብ አይነት የምንመገብበት መሳሪያም የተለያየ ቢሆንም፤ አሁን አሁን ግን በእጅ መመገብ የኋላ ቀርነት መገለጫ እየሆነ መምጣቱን እና ብዙዎችም እየተውት መምጣታቸውን የአሜሪካ ስነ ምግብ ሳይንስ አካዳሚ ያደረገው ጥናት ገልጿል። ከዚህ በተቃራኒው ግን እጃችንን ተጠቅመን በምንመገብበት ወቅት በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደምናገኝ ጥናቱ አመልክቷል። በመሆኑም ከማንኪያ እና ሹካ ይልቅ ተፈጥሮ የሰጠችንን እጅ ተጠቅሞ መመገብን ይመክራሉ። በእጃችን በምንመገብበት ወቅት ጣቶቻችን ምግቡን ከመሰብሰብና ለአፍ ከማቀበል ባሻገር ምግብ ወደ ደም የማስገባት አቅምም እንዳለው ጥናቱ አመልክቷል። ማንኛውንም ምግብ በእጅ ተጠቅሞ በመመገብ የሚገኙት የጤና ጠቀሜታዎችም የሚከተሉት ናቸው።

 

ጠንካራ ኃይል እንዲኖረን ያግዛል

በእጆቻችን ላይ ያሉት አምስቱም ጣቶቻችን የየራሳቸው የሆነ ባህሪይ እና ተፈጥሯዊ ውህደት አላቸው። እነዚህን የእጅ ጣቶቻችንን ተጠቅመን ምግብ በምንመገብበት ወቅት ሁሉም ጣቶቻችን የየራሳቸውን ድርሻ ስለሚያበረክቱ ሰውነታችን ጠንካራ እና የተቀናጀ ሃይል እንዲኖረው ያግዘዋል። ከእነዚህ የጣት ባህሪያት እና ተፈጥሯዊ ውህደት ውስጥ የተወሰኑት በመጉደላቸው ምክንያት ለተለያዩ የህመም አይነቶች የመጋጥ እድላችን የሚጨምር ሲሆን፤ ይሄንን ችግር በእጃችን በመመገብ ማስቀረት እንደሚቻል አካዳሚው ያደረገው ጥናት አመልክቷል። በሹካ፣ በማንኪያ አልያም በቢላዋ ተጠቅመን ከመመገብ ይልቅ ጣቶቻችንን አቀናጅተን በምንመገብበት ወቅት ከምግቡ ማግኘት የሚገባንን አስፈላጊ ንጥረ ነገር ከምግቡ እንድናገኝና ምግብ የመመገብ ሂደቱም ቋሚ ስርዓት ያለው እንዲሆን ያደርጋል።

 

የምግብ ልመትን ያሻሽላል

በእጃችን ምግብን በምንነካበት ቅጽበት አንጎላችን ለሆዳችን መልእክት ያስተላልፋል። ከድርጊቱ ድግግሞሽ የተነሳ እጅ ምግብ ላይ ሲያርፍ ልንመገብ መሆኑን የሚገልፅ መልዕክት በቅጽበት ወደ ሆዳችን ይላካል። በጣቶቻችን ላይ ያሉት የነርቭ ጫፎችም የነካነውን ምግብ የሙቀት መጠን፣ ቃናውን እና የተካተተበትን ቅመማ ቅመም እንዲሁም ቅርፁን የማጣጣም እድል ያገኛሉ። ምግቡ ለነርቭ ጫፎች ከሰጠው ስሜት በመነሳትም ሆድ አስፈላጊውን የማላሚያ ፈሳሽ እና ኢንዛይም እንዲያመርት በአእምሮ አማካይነት መልዕክት ይተላለፍለታል። ይህን ተግባር አእምሮ እና ሆድ በቅንጅት የሚያከናውኑትም ምግቡን በእጃችን ከነካንበት ጊዜ አንስቶ ወደ አፋችን እስከምናስገባ ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን መረጃው ያመለክታል። በዚህ የተቀናጀ ድርጊትም ምግቡ ወደ ሆድ ከገባ በኋላ ከትክክለኛው ፈሳሽ እና ኢንዛይም ጋር በቀጥታ ስለሚገናኝ የመላም ሂደቱ ያለ ምንም እንከን እንዲከናወን ያደርገዋል። ከዚህ በተቀራኒው የምንመገበው በተለያዩ መሳሪያዎች በመጠቀም ከሆነ ግን አእምሮና ሆድ ይህን ተግባር የሚፈፅሙበት ምግቡ አፍ ውስጥ ከገባ በኋላ በመሆኑ የመዘግየት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህም ሳቢያ ምግብ ከአስፈላጊዎቹ ኢንዛይሞችና ፈሳሾች ጋር ተገናኝቶ የሚፈጭበት ጊዜ ስለሚረዝም የልመት ሂደቱም የዘገየ ይሆናል።

 

 

ከጎጂ ባክቴሪያዎች ይከላከላል

   በእጃችን ላይም ልክ እንደሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችን ሁሉ ጎጂ ያልሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች አሉ። እነዚህ ባክቴሪያዎች ከመጉዳት ይልቅ በሽታ አምጪ ከሆኑ ተዋሲያን የመከላከል ጠቀሜታን ይሰጣሉ። እነዚህ ባክቴሪያዎች በመዳፋችን እንዲሁም በጣቶቻችን ላይ በስፋት የሚገኑ ሲሆን፤ ምንም እንኳ እጃችንን ታጥበን ብንመገብም በእጃችን ላይ የመቅረት ባህሪይ ስላላቸው ከምግቡ ጋር ወደ አፋችን የመግባት አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ምግቡ ከአፋችን አንስቶ እስከ ሆዳችን ድረስ በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ ያሉት እንደ አፍ፣ ጉሮሮ፣ የምግብ ቱቦ እና አንጀት ያሉት የሰውነት ክፍሎችን እነዚህ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ያገኙዋቸዋል። በዚህም ጊዜ ባክቴሪያዎቹ ያለፉባቸው የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ከከባቢ አየር የሚመጡ በሽታ አምጪ ተዋሲያን እንዳያጠቋቸው ይከላከሉላቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነት በመግባታቸው በሰውነታችን ውስጥ ያለው የጠቃሚ እና ጎጂ ባክቴሪያ ቁጥር የተመጣጠነ እንዲሆን እና ለጉዳት እንዳይዳረግ ያግዛል።

 

መጥኖ ለመመገብ ያግዛል

አንድ ሰው በእጁ በሚመገብበት ወቅት አጠቃላይ ትኩረቱን በምግቡ ላይ የማድረግ ሁኔታ ውስጥ ይገባል። በዚህም በምግቡ ላይ አተኩሮ በሚመገብበት ጊዜ ምን እየተመገበ እንዳለ እና ምን ያህል መጠን ያለውን ምግብ እንደተመገበ የመገንዘብ እድሉን ያገኛል። በመሆኑም መጥገብና አለመጥገቡን እያገናዘበ ስለሚመገብ የሚበቃውን ያህል ምግብ ለመመገብ እና ከመጠን በላይ ላለማለፍ ያግዘዋል። በተጨማሪም ምግቡን የምንመገብበትን ፍጥነት ለመገመት እና ለማስተካከል ያግዛል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከመጠን ያለፈ ምግብን እንዳንመገብ እንዲሁም በፍጥነት ተመግበን የተመገብነውን ምግብ መጠን መገንዘብ እንዳንቸገር ያግዙናል። እንዲህ በማድረጋችንም ከመጠን ላለፈ ውፍረት እና ለአይነት ሁለት የስኳር ህመም ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሰዋል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ከእጃቸው ይልቅ በሌሎች መሳሪያዎች ተጠቅመው የሚመገቡ ሰዎች በፍጥነት እና በብዛት የመመገብ አጋጣሚው ስላላቸው በደማቸው ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከፍ እንዲል በማድረግ በአብዛኛው ለአይነት ሁለት የስኳር ህመም የተጋጡ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም እጃችን ከምግቡ ጋር ቀጥተኛ ንክኪ ሲኖረው ቶሎ የመርካት እና የመጥገብ ስሜት ስለሚፈጥር ከመጠን በላይ እንዳንመገብ ያግዛል።

 

 

የሰውነት እንቅስቃሴ ነው

በእጃችን በምንመገብበት ውቅት በሰውነት ውስጥ የሚኖረው የደም ዝውውር ፍጥነቱ እንዲጨምር ያግዘዋል። ይሄ የሚሆነውም ምግብ ቆርሰን እስከምንጎርስ ባለው እንቅስቃሴ ውቅት አብዛኞቹ ጣቶቻችን ስለሚንቀሳቀሱ የሰውነታችን ጡንቻዎች የመንቀሳቀስ እድሉን ስለሚያገኙ ነው። ይሄ የጡንቻ እንቅስቃሴ ልክ እንደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሰውነታችን ውስጥ የሚኖረው የደም ዝውውር የተስተካከለ እና አመቺ እንዲሆን ያደርገዋል።

 

ንፅህናን ለመጠበቅ ያግዛል

ይህ ሀቅ ከተለመደው አስተሳሰብ ጋር የሚጋጭ ይመስላል። ብዙውን ጊዜ ከእጃችን ይልቅ ማንኪያ እና ሌሎች የመመገቢያ ቁሳቁሶች ንፅህናቸው የተጠበቀ ይመስለናል። ነገር ግን እውነታው ከዚህ በተቃራኒው መሆኑን መረጃዎቹ ያመለክታሉ። ምግብ ከመመገባችን በፊት አብዛኞቻችን እጃችንን የምንታጠበውን ያህል እነዚህን መሳሪያዎች የማጠብ ልምዱ ብዙም እንደሌለን የሚገልፁት መረጃዎቹ፣ በዚህም ሳቢያ በእጅ መመገብ ንጽህናው የተጠበቀ ምግብን ለመመገብ ያግዛል። ነገር ግን ምግቡን ከመመገባችን አስቀድሞ እጃችንን በአግባቡ እና በተፈለገው መጠን መታጠብ ካልቻልን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝንበት አጋጣሚ ይፈጠራል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
431 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1026 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us